መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅየሕዝብ ተቀባይነት ላይ ትኩረት ይሰጥ!

የሕዝብ ተቀባይነት ላይ ትኩረት ይሰጥ!

ሕዝብ የሚመራውን መንግሥት መርጦ እንዲያስተዳድረው እንደሚያደርገው፣ የመረጠውና አገርን እያስተዳደረ ያለው አካል የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ስለመወጣቱ አሳማኝ የሆነ መረጃን በየወቅቱ ለሕዝቡ ማድረስ ይጠበቅበታል።

ለተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ለሕዝብ በየተወሰኑ ጊዜያት በሪፖርት መልክ የሚቀርቡ መረጃዎች ቢኖሩም፣ ወቅቱን ያማከሉ አስፈላጊ መረጃዎች ለሕዝብ መቅረብ እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይ በጦርነትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅባቸው አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወረርሺኝን የመሳሰሉ አገር ዐቀፍ ትኩረትን የሚስቡ ጉዳዮች ሲከሰቱ በመደበኛነት መረጃን ለሕዝብ ማቅረብ የመንግሥት አንዱ ግዴታው ነው።

ሕዝብ በአሉባልታ እንዳይረበሽና ለፕሮፓጋንዳ ክፍት እንዳይሆን በማስረጃ የተደገፈ መረጃን በየጊዜው ሊያገኝ ይገባዋል። ከዚህ ቀደም በነበሩ ሥርዓቶች ከነበረው አኳያ ሲነፃፀር፣ አሁን ቴክኖሎጂው ለበጎ ብቻ ሳይሆን ለክፉ ዓላማ አራማጆችም መንገዱን ስላመቻቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው።

ከአገራት ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶችም ሆኑ የውስጥ ጉዳዮቻችን ለውጭም ሆኑ ለራሳችን ጠላቶች ምቹ እንዳይሆኑ በምስጢር መያዝ ያለባቸው ቢሆንም፣ በምስጢር ሥም ከሕዝብ የሚያራርቁ የተቃራኒ ወገን ወሬዎች እንዳይናፈሱ እንዲሁም የራስንም ሆነ የቡድንን ፍላጎት ብቻ ለማስፈፀም ምስጢራዊነት ጥቅም ላይ እንዳይውል ከፍተኛ የሆነ ክትትል ሊደረግ ይገባል።

ጦርነትን ከሕዝብ ደብቆ ማካሄድ እንደማይቻለው ሁሉ የደረሰውም ጥፋትና ውጤት በየጊዜው ይፋ መደረግ ይኖርበታል። ዓላማው ለፕሮፓጋንዳ የሚውል ሳይሆን ለታሪክ መማሪያና ሕዝብን ለማዘጋጃ የሚውል መሆንም ይጠበቅበታል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጦርነቶች የተደረጉ መሆኑ ቢታወቅም፣ ዓለም የሚያውቀውን የአሁኑን የጦርነት ሂደት መደበቁና በጎ በጎውን ብቻ ማሰማቱ ለየትኛውም ወገን አይበጅም። ውጊያው በዘላቂነት እንዲቋጭ የሚያደርግ መፍትሄ ለማምጣት ሙሉ መረጃ ሳይኖር መሞከሩ ስለማያዋጣ አግባብነት ያለው መረጃን ማቆየቱም ሆነ መደበቁ ጥቅም እንደማይኖረው መረዳት ይቻላል።

ከዚህ ቀደም የነበሩት ኹለት ዙር ጦርነቶችን መንግሥትም ሆኑ ሌሎች ወገኖች በአግባቡ ሲዘግቡትና በየእለቱ መረጃዎቹን ለሕዝብ ሲያቀርቡ የነበሩበት ሂደት ነበር። የስርጭት መንገዱም ሆነ የመረጃዎቹ ታማኝነት እንዳለ ሆኖ፣ ቢያንስ ሕዝቡ በቂ የሚለውን መረጃ እያገኘ እጣፋንታው ምን እንደሚሆንም ሆነ ለቀጣዩ ሁኔታ ራሱን እንዲያዘጋጅ ሲደረግ ነበር።

የጦርነቱ አዘጋገብ ሂደትም ሆነ የየእለት መረጃ ከመንግሥት ውጭ እንዳይተላለፍ ከተወሰነበት ወዲህ ግን ለውጦች መታየታቸውን አዲስ ማለዳ ትረዳለች። ይፈጠሩ የነበሩ ውዥንብሮች በተወሰነ መልኩ የቀነሱ ቢሆንም፣ አሁንም ለአሉባልታ በድጋሚ በር የሚከፍት የመረጃ ክፍተት መኖሩን መመልከት ይቻላል።

ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች ቤተሰብ ያላቸውም ሆኑ ሕይወታቸውን ለመሰዋት ቆርጠው ወደጦር ግንባር ስለዘመቱ ቤተሰቦቻቸው ዜና መስማት አጓጉቷቸው የዜና አውታሮችን ሲያስሱና ሲያጠያይቁ የሚውሉ መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል።

የጦርነቱ ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ ሕዝብ ነዋሪነቱ ቀጣይ ነውና በሕይወት መስዋዕትነት የሚገኘውን ውጤት በሙሉ ልቡ እንዲቀበለው ለማድረግ ከስር ከስር መደረግ የሚኖርባቸው ነገሮች እንደሚኖሩ ግልፅ ነው። ያልጠበቀውን ነገር በዱብ እዳ መልክ እንዲሸከም ከማድረግም ሆነ ለማመን የሚያቅተውን መልካም ዜና ዘግይቶ አቅርቦ እንዲጠራጠር ከማድረግ በየጊዜው መረጃውን የማግኘት መብቱን ማሟላት ያስፈልጋል።

የጦር ሜዳውን እያንዳንዱን ውሎ ይወቅ ማለት አስፈላጊ ባይሆንም፣ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን የትኛውም ወገን ማግኘት ይኖርበታል። በጦር ግንባር የተለያዩ ዘመናዊ መረጃ መቀባበያ ዘዴዎች እያሉ፣ ለማፈን ወይም ደብቆ አቆይቶ ጊዜ ጠብቆ ለማብሰርም ሆነ መርዶ ለመንገር የሚደረግ ሙከራ ከተጠበቀው ውጤት በተቃራኒ የሆነ ምላሽን ሊያስከትል ይችላል።

ለምሳሌ፣ ተማርከው ሲደበደቡ የነበሩ ወታደሮች ስቃይ ይፋ ከማድረግና ቤተሰብን ከማስጨነቅ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ አልያም ለሚመለከታቸው ካሳወቁ በኋላ ስለማንነታቸውም ሆነ ስለሙሉ ሁኔታቸው ዝርዝር መረጃ ማቅረብ ይጠቅማል።

የሕዝብ ተቀባይነት እንዲኖር ስለጦርነቱ ያለውን መረጃ ብቻ ሳይሆን ለጦርነቱ እልባት ለመስጠት ስለሚሞከሩ ማናቸውም ጉዳዮች ሕዝብ እንዲያውቅ መደረግ ይኖርበታል። በተለይ በተፋላሚ ወገኖች መካከል ያለውን ንግግርም ሆነ ድርድር አልያም ውይይት ሕዝቡ ሊያውቀው ይገባል።

የንግግሩ ጭብጥና አስፈላጊነትን እንዲሁም ውጤቱን ሕዝቡ አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አዲስ ማለዳ ትረዳለች። የንግግሩም ሆነ የድርድሩ ሂደትና አንኳር ጉዳዮች ከስር ከስር ለሕዝብ ይፋ የሚደረጉ ከሆኑ የትኛውም ውጤት ቢመጣ ሕዝብ ለመቀበል በተሻለ ይቻለዋል።

በምን በምን ጉዳዮች ሕዝብን ወክለው እንደሚነጋገሩ ማሳወቁ ከጉዳቱ ጥቅሙ ስለሚያመዝን ምስጢራዊ ማድረጉ ያን ያህል አስፈላጊ አይሆንም። የግንኙነቱ ሂደት በቀጥታ ይተላለፍ ብሎ የትም ያልተለመደ ሂደትን ብዙ ሰው ባለቀበት ጦርነት ይፈተሽ ማለቱ አግባብ ባይሆንም፣ በቀደመው ዘመን ከሆነውና ካስገኘው ውጤት በመመርኮዝ የተሻለ መንገድ መፈለግ ይቻላል።

ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ካለቀ በኋላ ሕዝብ ይሄ ነው ሲባል ቢያንገራግር ወደ እርምጃ ከመግባት ይልቅ፣ ከመቋጨቱ በፊት አዝማሚያውን እንዲያውቅ ቢደረግ አካሄድን ለማስተካከልም ሆነ ጫና ለመፍጠርና የሕዝብን ፍላጎት ለማስፈፀም ይጠቅማል።

- ይከተሉን -Social Media

አዲሷ የአፍሪካ አገር ደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖቿ ወደ ድርድር አምርተው የተስማሙበት ውጤት ለሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን በከፊል ይፋ በመሆኑ ሰላም ለማምጣትና ደጋፊዎቻቸውን እንደአመራሮቹ ለማቀራረብ ምን ያህል እንዳስቸገረ መመልከት ይቻላል። ተፋላሚ ወገኖችና ደጋፊዎቻቸው  ቢስማሙ እንኳን፣ አደራዳሪዎቻቸው ላይስማሙ ስለሚችሉ እንደነሱ ፍላጎታቸውን እንዳይጫኑብን መረጃውን ከስር ከስር በአግባቡ ማቅረቡ የሕዝብ ተቀባይነትን ለማምጣት ይረዳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች