ወጣቶች ለሠላም እንዲቆሙ ማድረግ

0
886

የኢትዮጵያ ሠላም ተቋም ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው። ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል።

በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ነው ። አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ ብሎም የተለያዩ ማሕበረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።

ኢትዮጵያ ካላት ጠቅላላ የህዝብ መጠን የወጣቶች ቁጥር ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ ይነገራል፡፡

ሆኖም የአገሪቱ እድገት ካላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትኩስ ኃይል አንጻር ሲታይ ያነሰ ሲሆን፣ አብዛኛው ወጣትም ሥራ አጥ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖር መሆኑ ይስተዋላል፡፡

በአብዛኛው በአገሪቱ በሚከሰቱ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደምም ወጣቱ በቀዳሚነት ተሳታፊ ሲሆን ይታያል፡፡

ለዚህ ኹሉ ችግር ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ላይ ትኩረት ባለመደረጉ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት መቆም ባለመቻሉ ነው የሚሉ አሉ፡፡

በቅርቡ (ከጥቅምት 14 እስከ 16/2015) የኢትዮጵያ ሠላም ተቋም (Ethiopian Institute of Peace) በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 የሚኖሩ የአማርኛ እና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣቶች የተሳተፉበት ሠላምና አንድነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች፣ በዚህ ወቅት ወጣቱ ትውልድ በአንድነት በመቆም አገራዊ ሰላምና ብልጽግና ከማምጣት ይልቅ፣ በስፋት በጎራ ተከፋፍሎ እርስ በእርስ ሲጠፋፋ ነው የሚታዬው የሚል ሀሳብ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ተሳታፊዎቹ ወጣቱን ወደ ግጭት የሚያመሩ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው ያሏቸውን ስድስት ነጥቦች ለይተው ያስቀመጡ ሲሆን፣ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣቶች ከእነዚህ መካከል አንደኛው የሰንደቅ ዓላማ ችግር ነው ሲሊ ተደምጠዋል፡፡

ይህንም ችግር ተገንዝቦ መንግሥት ህጋዊ መፍትሄ ባለመስጠቱ በዚህ ወቅት የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ወጣቶችን ወደ ግጭት የሚያመራ ችግር ሆኗል ነው የሚሉት፡፡

ኹለተኛው ችግር ደግሞ የማንነት/ብሔር ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን፣ የሌሎችን ማንነት በመናቅ የራስን የበላይነት በማራመድ እና በእኔ ክልል ሌላ ብሔር መኖር የለበትም በሚል የተዛባ አመለካከት ግጭቶችን በመፍጠር ዜጎች ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ እንዲሁም ሀብት ንብረታቸውን ሲያጡ እንመለከታለን ይላሉ፡፡

ሌላኛው የግጭት መንስኤ ደግሞ ኃይማኖት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ይህም ሲባል እኔ ከምከተለው ኃይማኖት ውጭ ሌላው መኖር የለበትም፣ ልክም አይደለም በሚል የአክራሪነት ስሜት ወጣቶች ላልተገባ ጥፋት እየተዳረጉ እንደሚገኝ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የተረኝነት ስሜት እንዲሁ ወጣቶች በመካከላቸው ያለው ልዩነት እንዲሰፋ የሚያደርግና ለጥፋት የሚያነሳሳ ምክንያት መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ተሳታፊ እንዳነሳችው፣ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር በብዛት ከአንድ ብሔር የተዋቀረ የሚሆን ከሆነ ወጣቶች እንዳይግባቡ ትልቅ እንከን ይሆናል ነው ያለችው፡፡

ባለንበት ወቅትም በበፊቱ ስርዓት ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች አሁንም ሳይታረሙ እየተደገሙ ያሉበት ሁኔታ ይስተዋላል፣ ችግሩ በጊዜ መስተካከል ካልቻለ ወጣቱን ወደ አንድነት ለማምጣት ትልቅ እንቅፋት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነች፡፡

የተዛባ የታሪክ አረዳድ አምስተኛው ወጣቶችን ወደ ግጭት የሚከት መንስኤ ሆኖ በተሳታፊዎች ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በፊት በተፈጠረ ክስተት፣ እሱንም መፈጠርና አለመፈጠሩ በበቂ መልኩ ባልተረጋጋጠበት ሁኔታ በአሉባልታ ብቻ ወጣቱ እርስ በእርስ ለጠብ ሲፈላለግ መኖሩን ነው ተሳታፊዎች የገለጹት፡፡

የተዛባ የታሪክ አረዳድ የሌሎች የጥላቻ መንስኤዎችም ጭምር መነሻ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ በቀደሙ ጊዜያት የተጻፉትን ሙሉ በሙሉ አምኖ መቀበል የወጣቱ ድክመት እንደሆነም ነው ያሱት፡፡

በተጨማሪም ለወጣቶች አለመግባባት ስድሰተኛ ነጥብ ተብሎ የተነሳው የሚዲያ አጠቃቀም ችግር ነው፡፡

ለሠላምና ለአንድነት መልካም ሀሳብ ያላቸው ሚዲያዎችን ከመከተል ይልቅ አሉታዊ አመለካከትን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ የወጣት ተከታይ አላቸው ያሉት ተሳታፊዎች፣ መንግሥት የመረጃ አጠቃቀምን በተመለከተ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ቢችል ብሎም ታማኝና ወቅታዊ መረጃዎችን በኃላፊነት ማድረስ ቢችል ወጣቱ የዚህ ችግር ሰለባ መሆን እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡

ከላይ ከጠቀስናቸው መንስኤዎች ውጭ ሌሎች በርከት ያሉ ነገሮችም አሉ ካሉ በኋላም፣ መንግሥት በተለይ የሰንደቅ ዓላማን ውዝግብ መፍታትን ጨምሮ የተረኝነት ስሜት በሚያንጸባርቁ አካላት ላይ ቆራጥ ውሳኔ ማሳላፍ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ከአዲስ አበባ ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር ጠቅሰውም፣ ካለው የህዝብ ቁጥር እድገትና ከኑሮው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ርዕሰ መዲና ይሰፋል እንጂ አይጠብም ይህም ጉዳይ ወጣቱን የሚከፋፍልና የሚያጣላ መሆን የለበትም፣ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ መፍትሄ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል በማለት አብራርተዋል፡፡

አሁን ያለው ወጣት እኔ ልደመጥ እንጂ የሌሎችን ላዳምጥ የሚል ባይሆንም፣ ነገሮችን በስሌት ከመመልከት ይልቅ በስሜት ብዙ ጥፋት እያደረሰ ቢሆንም፣ ወጣቱ ትልቅ አቅም አለው ብለን እናምናለን፡፡ ይህን በመቀየር የወጣቱን አቅም ለማጎልበት እንዲሁም ሠላምና አንድነት እንዲኖረው መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡

የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣቶች በበኩላቸው፣ የተለያዬ ባህል፣ ማንነትና ቋንቋ ያላቸው ወጣቶችን እርስ በእርስ ከመደጋገፍ ይልቅ የመከፋፈል ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ ነው ያሉት፡፡

ተሳታፊዎቹ ያነሷቸውን ስድስት ነጥቦች ወጣት ጆሃር ከድር እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡

በጆሃር አገላለጽ አንደኛው የወጣቶች ያለመግባባት መንስኤ የአመለካከት ችግር ነው፡፡ ስለቋንቋ፣ ስለብሄሮች፣ ስለታሪክ ወጣቶች ያላቸው ልክ ያልሆነ አመለካከት ብዙ ጊዜ ለጸብ ይጋብዛል ነው የሚለው፡፡

ለአብነትም አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮምኛ ቋንቋ ስናወራ፣ የራሳችን መገለጫ የሆኑ አልባሳትን ለብሰን ስንታይ ሌሎች የሚያንጸባርቁት ስሜት መራራቅን የሚያመጣ ነው ማለታቸውን ከእሱ ጋር የነበሩ ተሳታፊዎች እንዳነሱ ያስረዳል፡፡

ሌላኛው የወጣቶች የግጭት መንስኤ ወሰን መሆኑን ያነሳው ጆሃር፣ አዲስ አበባ በምትሰፋበት ጊዜ የእኛ ቦታ እየተወሰደ ነው በማለት ወጣቶች ለግጭት እንደሚነሳሱ ጠቁሟል፡፡

ይህን በተመለከተም ተገቢ ውሳኔ ማሳረፍ ያለበት የመንግሥት አካል በመኖሩ ወጣቶቹ በዚህ የተነሳ መጋጨት እንደሌለባቸው አመላክቷል፡፡

ሰንደቅ ዓላማም አንደኛው የግጭት መነስኤ ነው ብለን ተስማምተናል ካለ በኋላ፣ ለምሳሌ ልሙጡን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስንመለከት ከዚያ ጋር ተያይዞ እየተነገረን ያደግነው ታሪክ አለ፡፡ ያ ደግሞ የሚረብሽ ስሜት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ የተዛባ አተያይ ያመጣው መሆኑን ተገንዝበዋናል ሲል ገልጿል፡፡

በቡራዩ አካባቢ በየዓመቱ የሚከበር ኃይማኖታዊ በዓልን አንስቶም፣ ለምሳሌ በቡራዩ ወይብላ ማርያም በሚባል ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበር በዓል አለ፡፡ በዚህ ዕለት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚገልፅ ምዕመናኑ በአንገታቸው፣ በቀሚሳቸውና በነጠላቸው አድርገው ይመጣሉ፡፡ በዚህም ብዙ ጊዜ ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ በሰው ህይወትና በንብረት ላይም ጉዳት ይደርሳል፡፡ ነገሩን ከራስ ነጻነትና አመለካከት አንጻር እንደበጎ ማየት ቢቻል ግን፣ ለአንድ ቀን የሚደረግ ክስተት ይህን ያህል ጉዳት ሊያስከትል አይገባውም ነበር ባይ ነው፡፡

ቋንቋም ሌላኛው የወጣቶች ያለመግባባት መንስኤ ነው ተብሏል፡፡ ጆሃር ይህን ሲገልጽ፣ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ አማርኛ መናገር የአራዳነትና የከተሜነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ነገር ግን ኹሉም ቋንቋ ከመግባቢያነት ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ የልዩነት ምንጭ መሆን አይገባውም ይላል፡፡

ሌላኛው የወጣቱ የፀብ መንስኤ ደግሞ የተዛባ ትርክት ሲሆን፣ መልካም የሆነውን ለራስ በመውሰድ፣ መጥፎውን ለሌላ መስጠት የተለመደ ሆኗል ይላሉ በጆሃር ቡድን ያሉ ተሳታፊዎች፡፡

ትናንት የተሰራ ልክ ያልሆነ ታሪክ ሊኖር ይችላል፡፡ ሰሪዎቹ ግን የሉም፡፡ እኛ ደግሞ እንገዳደልበታለን፡፡ ስለዚህ ታሪክ የሰሩትም የጻፉትም ሰዎች የሉም፡፡ ባለፈ ታሪክ መጋጨት ይቅርና የራሳችንን ታሪክ ሰርተን እንጻፍ፡፡ ይህ ነው ግጭታችንን የሚያስቀረው በማለት ያብራራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ማንነት ጉዳይ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣት ተሳታፊዎች ዘንድ አንዱ የወጣቱ የግጭት መንስኤ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡

አዲስ አበባ የእኔ ናት የእኔ ናት በሚል እሰጣገባ ወጣቱ የጥፋቱ ሰላባ ሲሆን ተመልክተናል፣ አዲስ አበባ የእሱ መሆኗን በመግደልም ይሁን በመሞት ማረጋገጥ የሚችል አካል የለም፡፡ ይልቅስ ይህንኑ ጉዳይ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል መተው ይበጃል ነው ያሉት፡፡

ተሳታፊ ወጣቶች ችግሮችን በዚህ መልኩ ከለዩ በኋላ ይበጃሉ ያሏቸውን የመፍትሄ አማራጮችንም ሰንዝረዋል፡፡

የተነሱትን የመፍትሄ አማራጮች አስመልክቶ ወጣት ሰጤ መንግሥቱ እንደሚለው፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ከዚህ የግጭት መንስኤ እንዳይሆን ለመከላከል ኮሚቴ አዋቅረናል ይላል፡፡

ይህም ከቀጣይ ዙር የውይይት ተሳታፊዎችና ከእኛ የተውጣጡ አባላት የያዘ ትልቅ ኮሚቴ በማዋቀር፣ በዋና ዋና የአደባባይ በዓላት ቀን በቦታው ተገኝነተን ከመንግሥት አካላት ጋር በትብብር በመስራት ችግሩ የግጭት መነሻ ሳይሆን በፊት ለመከላከል ተስማምተናል ሲል አስረድቷል፡፡

የተረኝነት ስሜትን በተመለከተም ይህ ችግር የተፈጠረው በፍትህና እኩልነት በማያምኑ አካላት በመሆኑ፣ አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ለችግሩ እውቅና በመስጠት እኛ ወጣቶች ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ውሳኔ አሳልፈናል ባይ ነው፡፡

የበፊት መልካም እሴቶቻችን ላይ መለስ ብሎ መሥራት በኃይማኖት ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና አለው የሚለው ሰጤ፣ የኹሉም ኃይማኖት ተቋማት መልካምና ለትውልድ የሚበጅ ትምህርት እንዲያስተምሩ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት አቅደናልም ይላል፡፡

በመሆኑም ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ መጥፎ ተልዕኮ የሚያራምዱ አካለትን ወጣቱ መለየት እንዲችል እና ኃይማኖት የግጭት ምክንያት እንዳይሆን ከኃይማኖት ተቋማትና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በቅርበት የምንሰራ ይሆናል ነው ያለው፡፡

ልቅ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተም፣ ወጣቱ የሚሰራጩ መረጃዎችን ይዘትና የሚያሰራጨወን አካል ማንነት እንዲመረምር ብሎም ማህበራዊ ሚዲያውን ለጥላቻና ለጥፋት ሳይሆን ለበጎ ዓላማ እንዲጠቀምበት የማንቃት ሥራ ለመስራት ወስነናል ብሏል፡፡

ሰጤ በመጨረሻም፣ በውይይታቸው የተዛባ የታሪክ አረዳድን በተመለከተ ያስቀመጡትን የመፍትሄ አቅጣጫ ሲገልጽ፣ ይህን የሚያስተካክል ሚዛናዊ ትርክት ከኹሉም ማህበረሰብ የተውጣጡ ተወካይ አካላትና ምሁራን ሰርተው እስከሚያስረክቡን ድረስ ግን ችግሩን አምነን ተቀብለን እስከሚስተካከል በትዕግስት ለመጠበቅ ተስማምተናል ሲል አስረድቷል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች ከዚህ ውይይት በፊትና በኋላ የነበራቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡

ውይይቱ ከምንም በፊት ሰውን እንድናከብር እና አንድን ነገር ከማድረጋችን በፊት ለምን ብለን እንድንጠይቅ አግዞናል፡፡

ከገደልነው፣ አካሉን ካጎደልነውና ካፈናቀልነው እንዲሁም ካቃጠልነው ንብረት ያተረፍነው የለም፡፡ ዛሬ አንዱ ተነስቶ ውጡ ተነሱ ቢለን አንወጣም፡፡ ለማን እንደምንሞትና ሰውን እንደምንጎዳ፣ ለማን ጥቅም ስንል አካል እንደምናጎድልና አካላችን እንደሚጎድል ተገንዝበናል ነው ያሉት፡፡

በውይይቱ ግንዛቤ ያገኙ ወጣቶችም በቀጣይ ሌሎች ወጣቶች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ብሎም ለተቸገሩ ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ የበኩላቸውን ለማበርከት እንቅስቃሴ ለማድረግ አስበናል ነው ያሉት፡፡

ይህ ውይይት ቢሰፋና በዬቦታው መዳረስ ቢችልም ወጣቶች ራሳቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ማህበረሰቡ ላይ በጎ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ የራሳቸውን ታሪክ ተናግረው የሌላውን ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ብዙ ቁምነገር ሸምተውም ለሠላምና ለልማትም ይተጋሉ በማለት አመላክተዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here