እ.ኤ.አ በ2002 ኤችአይቪ ኤድስ ላይ መሠረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን በመያዝ ሥራ የጀመረው አምረፍ ኸልዝ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጥቅምት 15/2015 በሂልተን ሆቴል ሥራ የጀመረበትን 20ኛ ዓመት አክብሯል።
የአምረፍ ኸልዝ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ምሥራቅ መኮንን፣ በጤና መስክ ላይ አተኩሮ ሥራ የጀመረው አምረፍ በአሁኑ ሰዓት የመጠጥ ወኃን በማቅረብና ወጣቶችን በማብቃትም የአገልግሎት ዘርፉን በማሳደግ እየተሳተፈ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኮቪድ 19 ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ በነበረበት ጊዜም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ የሠራ ሲሆን፣ ከ14 ሺሕ በላይ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ አስፈላጊውን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል።
አምረፍ ከዩኤስኤድ (USAID) ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ ከ2021 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሚዘልቅና በ18 የኢትዮጵያ ከተሞች ኹለት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ “ከፍታ” የሚሰኝ ፕሮጀክት ጀምሯል።
በዚህ ፕሮጀክትም ወጣቶች በአገራቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሲቪክ ዘርፎች ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሁም የለውጥ ኃይል እንዲሆኑ እየተሠራ እንደሚገኝ ምሥራቅ ገልጸዋል።
የአምረፍ ኸልዝ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጊቲንጂ ጊታሂ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አምረፍ ከተመሠረተ 65 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተመዝግቦ ሥራ የጀመረበትን 20ኛ ዓመት ስናከብር በዓመት እስከ 18 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እያደረገ ሥራዎቹን እየሠራ ይገኛል›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
ለራስ ችግሮች በራስ መፍትሔ ማግኘት እንደሚገባ አምረፍ ያምናል ያሉት ጊቲንጂ፣ በዚህም ወጣቶችን በማብቃት ጥሩ ወጤት ማግኘት ይቻላል ብለዋል። የድርጀታቸው የኢትዮጵያ ቅርንጫፍም በኢትዮጵያዊያን እየተመራ ጥሩ ውጤት በማምጣት ላይ እንደሚገኝ ተናግረው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ አምረፍ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ውስጥ መልካም ሥራዎችን እንደሠራ አውስተው፣ በቀጣይም ውጤታማ ሥራዎቹን እንዲሠራ የመንግሥታቸው ቀና ትብብር እንደማይለየው አረጋግጠዋል።
አምረፍ ኸልዝ አፍሪካ መሠረቱን በአፍሪካ ያደረገ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር በአፍሪካ አገራት ግብረ ሰናይ ሥራውን በመሥራት ላይ ይገኛል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015