11ኛው የዶሮ ኤክስፖና 7ኛው የእንስሳት ሀብት አውደ ርዕይ እና ጉባኤ ባሳለፍነው ሐሙስ ጥር 17/2015 በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል።
በአውደ-ርዕዩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉን መሪዎችና ቁልፍ የአገር ውስጥ የውጪ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ወንድሙ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹አገራችን በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘች እንደመሆኗ፤ አውደ ርዕይ እና ጉባኤው ይህንን ሀብት በተደራጀና ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ በመታገዝ የእንስሳት ተዋጽኦ በአግባቡ ለማቀነባበር እንዲሁም የእንስሳት መኖ፣ የእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ጥሩ ልምድ የሚገኝበት ይሆናል›› ሲሉ ገልጸዋል።
በመድረኩም ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ከእንስሳት እና ከእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት በምትችልበት ወቅት ላይ መሆኗ ተመላክቷል።
ለተከታታይ ሦስት ቀናት በቆየው አውደ ርዕይ እና ጉባኤ ላይ፤ በእንስሳት መኖ፣ እንስሳት ጤና፣ ዶሮ፣ ስጋ እንዲሁም የወተት እሴት ሰንሰለት ላይ የተሰማሩ ከ10 አገራት የተውጣጡና ከ70 በላይ የሚሆኑ ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች፣ አገር በቀል ድርጅቶች እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለድርሻ አካላት በአውደ ርዕዩ ላይ ተሳታፊ ሆነውበታል።
እነዚህ ተሳታፊዎችም ከጠቅላላው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ሰፊውን የሚወክሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከመላው ኢትዮጵያና ከጎረቤት አገራት ከሚመጡ ከአራት ሺሕ በላይ የዘርፉ የንግድ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ጋር የንግድ ግንኙነት መፍጠራቸውም ተገልጿል።
ይህን ዓለም ዐቀፍ አውደ ርዕይ እና ጉባኤ በኢትዮጵያ የተለያዩ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ፕራና ኤቨንትና መቀመጫውን ሱዳን ያደረገው “ኤክስፖ ቲም“ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015