ስንዱ አምሃ (የአባት ሥም የተቀየረ) ዐስር ዓመት ገደማ በቤሩት ነው የኖረችው። ወደ አገሯ የመጣችው ከአምስት ዓመት በኋላ ሲሆን፣ ወላጅ አባቷ በድንገተኛ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በመጣችበት ወቅት ነበር ከአዲስ ማለዳ ጋር የተገናኙት።
ስንዱ በቤሩት የሰው ቤት ተቀጥራ ትሠራ ነበር። ወደቤሩት ለመሄድና በዛም ሰው ቤት ለመቀጠር ያለፈችበትን መንገድ መለስ ብላ ማስታወስ አትፈልግም። ግን ለሥራ የገባችበት ቤትና ያገኘቻቸው ሰዎች ከሞላ ጎደል ጉዞዋን ረስታ የወደፊት ኑሮዋን ለማሸነፍ እንድትታገል በሚያስችል መጠን ጥሩ እንደነበሩ ጠቅሳለች።
‹‹በልጅነቴ ብዙ ልሆነው የምፈልገውና ልደርስበት የምመኘው ሕልም ነበረኝ። ብዙ ነገሬን አጥቻለሁ። ግን ያለፉት 10 ዓመታት እንዴት ነበሩ ተብዬ ብጠየቅ ‹እኔ እድለኛ ነኝ፤ ጥሩ የሥራ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት› ብዬ ነው የምናገረው።›› ትላለች።
‹‹አምላኬ በብዙ መልኩ ጠብቆኛል›› ብላ ፈጣሪዋን የምታመሰግነው ስንዱ፣ ትሠራበት የነበረበት ቤት ያሉ ቤተሰቦች ሰው አክባሪና ሥርዓት ያላቸው መሆናቸውና እርሷም ሥራዋን በአግባቡ የምትሠራ መሆኑ በደኅና እንዳቆያት ትጠቅሳለች።
በአንጻሩ በአካልም በመንፈስም ከባድ ጉዳት የሚደርስባቸው፣ ጾታዊ ጥቃት የሚገጥማቸውና ሊገምቱት የማይችሉት ፈተና ውስጥ የሚገኙ በሰው ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ ሴቶችን እንደምታውቅ ትናገራለች። ‹‹አቤት የማይባልበት፣ ብትጮኺ የማትሰሚበት አገር መኖር ከባድ ነው። የሰው አገር የሰው ነው፤ የሰው ቤት የሰው ነው።›› ስንዱ ከንፈሯን እየመጠጠች የተናገረችው ነው።
በርካታ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ሴቶች አገራቸውን ጥለው የተሻለ ገቢን ፍለጋ፣ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውንም ሕይወት ለማሻሻል በተለያዩ የአረብ አገራት ሰው ቤት ተቀጥረው ይሠራሉ። በዚህም አግኝተው ለቤተሰባቸው ከሚልኩትና ለራሳቸውም ከሚቆጥቡት ገንዘብ ባለፈ የሚደርስባቸው የተለያየ አካላዊ፣ ጾታዊና ሥነልቦናዊ ጥቃት በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል።
ይህን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ይህ ነው የተባለ የተቀመጠ መፍትሔ ባይኖርም፣ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች ወይም ኤምባሲዎችና የመንግሥታት ግንኙነት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አያጠራጥርም። በዛ መሠረት የታወቀና የተለየ አካሄድ ካልተዘረጋ በቀርም እነዚህን ችግሮች መፍታት ከባድና አስቸጋሪ መሆኑ አያጠራጥርም።
አንዳንድ አገራት ሴቶች ዜጎቻቸው የቤት ሠራተኛ ለመሆን ወደ የትኛውም አገር እንዳይሄዱ እስከመከልከል ደርሰዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ እሱን በሕግ ለማጽናትና ለማሳመን እስኪችሉ ድረስ የተለያዩ እግዶችን ሲያደርጉ ይስተዋላል። በቅርቡ በዛምቢያ በተደጋጋሚ ይህ ጉዳይ ሲነሳ እንደነበር ሲደመጥ ቆይቷል።
ዌባንቱ (Mwebantu) የተባለ አንድ የዛምቢያ ዜና አውታር በድረገጹ እንዳስነበበው፣ እድሜያቸው በ20ዎቹ መጨረሻ ያሉ ወጣት ሴቶች ወደ ኦማን ጉዞ እንዳያደርጉ ከአየር መንገዱ እንዲመለሱ ሲደረግና እንዳይወጡ ሲከለከሉ ነበር። ወደ ቱርክ እና ፓኪስታን ጭምር እነዚህ ወጣት ሴቶች እንዳይሄዱና ከአየር መንገድ እንዲመለሱ መደረጉንም ነው ድረ ገጹ ያስነበበው።
ጉዳዩ የሚመለከተው የአገሩ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ያደረገው ዜጎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከሄዱ በኋላ፣ የጠሯቸውና የወሰዷቸው ሰዎች ለከፋ ጥፋትና ጥቃት አሳልፈው እየሰጧቸው ነው በሚል እምነት እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል።
እንደ ኢንዶኔዥያ ያሉ አገራት ደግሞ ቀደም ባሉ ዓመታት ባወጧቸው ሕግጋት፣ ሴት ዜጎቻቸው ለቤት ሠራተኝነት ባህር አቋርጠው እንዲሄዱ እንደማይፈቅዱ አስታውቀው ነበር። ከሆነና ሴቶቹ ለሥራ የሚወጡ ከሆነም፣ እንደ ማንኛውም ቅጥር መብታቸው ሊከበር፣ በሳምንት የአንድ ቀን እረፍት እንዲያገኙ፣ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና መደበኛ የሆነ የአሠሪና ሠራተኛ ውል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። ‹የሰው አገርም ሆነ የሰው ቤት፤ ሕግና ሥርዓት ግን ያስፈልጋል› ሲሉም ለዜጎቻቸው ጥበቃ ለመሆን ሲተጉ ታይተዋል።
ይህን ጉዳይ ለምን አነሳነው?
አዲስ ማለዳ ይህን ጉዳይ አሁን እንድታነሳ ምክንያት የሆናት በቅርቡ የደረሳት አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው። ጥናቱ በሊባኖስ በስደት ላይ ካሉት የሰው ቤት ሠራተኞች መካከል 68 ከመቶ ለጾታዊ ትንኮሳ ተዳርገዋል ሲል አስታውቋል።
ጥናቱን ያደረገው ‹እኛለኛ በስደት› የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። እኛለኛ በስደት የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2017 በቤይሩት ሊባኖስ የተመሠረተ ነው። ድርጅቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት በሊባኖስ የሚገኙ የሰው ቤት ሠራተኛ ሴቶችን ሲያገለግል ቆይቷል።
ድርጅቱ በሰው ቤት ሠራተኞች የተቋቋመ እና አሁንም በሰው ቤት ሠራተኞች የሆኑት እና የነበሩትን የሚመራ ነው። ላለፉት አምስት ዓመታትም ቁጥራቸው ከ15 ሺሕ ለበለጡ የሰው ቤት ሠራተኞች የምግብ፣ የሕክምና አገልግሎት ሲያቀርብ ነበር።
ይኸው ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ጥናት በሊባኖስ ያሉት የሰው ቤት ሠራተኞች ቁጥራቸው ከ300 ሺሕ በላይ ናቸው ብሏል። አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጠቅሶም ከእነዚህ 300 ሺሕዎች መካከል አብዛኛዎቹ ማለትም 80 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መሆናቸውን ያነሳል።
ታድያ ጾታዊ ትንኮሳ የሚደርስባቸው የተባሉ ሴቶች ከመቶዎቹ 68 መሆናቸው ይጠቀስ እንጂ ቁጥራቸው ከዛም ሊበልጥ እንደሚችል የጥናቱ ውጤት ያስረዳል። እንዴት ነው ቁጥራቸው የሚጨምረው ከተባለ፣ ‹‹በጾታዊ ትንኮሳ በሚቀሰቀሰው ወይም በሚፈጠረው ሀፍረት ምክንያት በርካታ ሴቶች የገጠማቸውን ላለማንሳት ወይ ለመርሳት እንደሚጥሩ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ለጾታዊ ትንኮሳ የተዳረጉት እህቶች ቁጥር ከ68 በመቶ በላይ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ግምት አለን።›› ሲል ድርጅቱ በጥናቱ ላይ ጠቅሷል።
ድርጅቱ በሊባኖስ ያሉት የሰው ቤት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳን በተመለከተ ያደረገውን ይህን ጥናት ላለፉት 10 ወራት ሲያዘጋጅ መቆየቱንም አስታውቋል። ጥናቱም የተዘጋጀው ሊባኖስ ከሚገኘው የሊባኖስ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ መምህር ከሆኑት ዶክተር ጃስሚን ዲያብ ጋር በጋራ መሆኑን ለመገናኛ ብዙኀን በተላከው መረጃ ተጠቅሷል።
የእኛለኛ በስደት ድርጅት ጥናቱን ለማዘጋጀት ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ የሰው ቤት ሠራተኞችን አነጋግሬ መረጃ ሰብስቤ ነበር ይላል። ያነጋገራቸው እህቶች አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ከፊሊፒንስ፣ ከካሜሮን፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ስሪ ላንካ፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ የመጡ መሆናቸውንም ይጠቅሳል።
በሴቶች ላይ በዚህ ቁጥር መጠን በደልና ጥቃት ሲደርስ የአገሩ መንግሥት ወደየት ቢገባ ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የሊባኖስ መንግሥት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ እንደ ወንጀል እንዲቆጠር ሕግ አጽድቋል። ‹Law 205› ተብሎ በሚጠቀሰው በዚህ ሕግ ጥቃት ሲፈጽም የተገኘ ሰው የአራት ዓመታት እስር እንዲሁም ከፍ ያለ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል። ከዛም በላይ ለተጠቂም ሆነ ምስክር ሆኖ ለሚቆም ሰው ከለላ ያደርጋል።
ይህ ሕግ ጥሩ መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን በስደት ላይ ያሉትን ወይም ከተለያየ አገር ወጥተው በሊባኖስ እየሠሩ ያሉትን ያካተተ አይደለም። እነዚህ በስደት ላይ ያሉ ሰዎች በዚህ ሕግ አለመካተታቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም እስያ የመጡ ስደተኛ ሴቶችን ለአደጋ ያጋለጣቸው መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው።
በተጨማሪም፣ በጥናቱ ሊባኖስ ሠርተው ወደ አገራቸው የሚመለሱ የሰው ቤት ሠራተኞች ለጭንቀት እና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳታቸው የሕክምና አገልግሎት ማመቻቸት ላይ በርትቶ መሥራት እንደሚገባም ተመክሯል።
ስንዱ ይህን በሚመለከት ሐሳብ ስትሰጥ ‹በዓለም ዐቀፍ ሕግ ወይም መሰል በሆኑ ስምምነቶች ብዙ ሊያስጠይቁ የሚገቡ ጉዳዮች በእህቶቻችን ላይ በሰው አገር ይፈጸማሉ። ሕጉ ግን ለዋናው ዜጋ እንጂ እንደ እኛ ላለው ስደተኛ የሚያገለግል አይመስልም። የሰው ቤት የሰው ነው የሚባለው ለዚህ ይመስለኛል፤ የራስ አይደለምና ምን ማድረግ ይቻላል!›› ስትል ትዝብት ባዘለ ድምጸት ትጠይቃለች።
ብሂሉ ሊገልጽ የፈለገው የታወቀ ቢሆንም፣ እንደወረደ ስንረዳው ‹የሰው ቤት የሰው› ከሆነ፣ ማንኛውም ሰው እንደ ሰውነቱ ሊስተናገድ ይገባልና በስደት አገር ያሉ ሴቶች እንደ ሰው መብታቸው ከተከበረ፣ ከጥቃት የሚጠብቀው ሕግ ለእነርሱም ባገለገለ ነበር። ግን አይደለም።
በሊባኖስ ያለው ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃትን የተመለከተው ሕግ ስደተኛ ሴቶችን የሚመለከት አለመሆኑና ለእነዚህ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ማግለሉ፣ ሴቶቹን ይበልጥ ለጥቃት የሚያጋልጣቸው ጉዳይ ነው ሲል የእኛለኛ በስደት ድርጅት አጽንዖት ሰጥቶ ስጋቱን ገልጿል። ይህም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው።
ድርጅቱ ‹‹በሊባኖስ ያሉት ስደተኛ እህቶቻችን የሚገጥማቸው እንግልትና ስቃይ እጅግ በጣም አስከፊ እንደመሆኑ ተቋማችን ችግሩን ለመቅረፍና በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሊባኖስ ባለው ሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ላይ ይሰማራል።›› ሲልም በቀጣይ በዘህ ጉዳይ ላይ አጠንክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል።
በተያያዘ ከ2020 ጀምሮም ችግር ላይ ወድቀው የነበሩ ከ700 በላይ ኢትዮጵያዊያን የትኬት ወጪ በመሸፈንና ከሊባኖስ ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማድረግ በኩል ማገዙን አስታውሷል። ከዓለም ዐቀፉ የዓለም ሥራ ድርጅት ጋር በመተባበርም በሕጋዊ ክስ ምክንያት ወደ አገራቸው መመለስ ያልቻሉ 200 ስደተኞችን ጠበቃ በማቆም ክሳቸው እንዲነሳ አስችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015