“ወደ ፈተና አታግባን” እያለ የዘወትር ጸሎቱን የሚያቀርብ በርካታ ማኅበረሰብ ባለባት አገር አንድ ተማሪ የተሰጠውን ትምህርት ስለማወቁ ለማስመስከር ፈተና መፈተኑ አዲስ ነገር አይደለም። የፈተናው ዓላማ ተማሪውን ለመጣል፣ አልያም ማንነቱን እንዲገመግምበትና ስለራሱ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው አይደለም።
አንድ ተማሪ ፈተና ተፈትኖ እንዲያልፍ የሚጠበቀው የወቅቱን ትምህርት በአግባቡ አውቆ ወደቀጣይ ክፍል ወይም ወደሥራው ዓለም እንዲቀላቀል ነው። ይህ ማለት ውጤቱም ሆነ ፈተናው እሱነቱን የሚገመግም ሳይሆን፣ በተነጻጻሪነት በወቅቱ የቱ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያውቅበት ነው። በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችም እጣ ፋንታውን የሚወስንበት የኑሮ መስፈርቱ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
የግል ዩኒቨርስቲዎች በሌሉበት በቀደመው ዘመን የማትሪክ ፈተናን እስከ 7 ጊዜ በኋላም ሦስት ጊዜ ደጋግሞ መውሰድ ይፈቀድ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ኅብረተሰቡ ፈተናውን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ያም የሆነበት ምክንያት አንድ ተማሪ ካልተሳካለት ሕይወቱ አልባሌ ሆኖ እንደሚቀር ስለሚታመን ነበር።
በዛን ዘመን የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ውስን ስለነበሩ፣ እንዳሁኑ ያሉት ቦታዎች ተሰልተው የተወሰኑት እንዲያልፉ ይደረግ ነበር እንጂ፣ አላለፉም የሚባሉት ለትምህርት ብቁ አይደላችሁም ማለት አልነበረም።
ይህን እውነታ በርካታ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆቻቸው ባለማወቃቸው ውጤት ያልመጣላቸው በማኀበረሰቡ ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ ቤተሰብም እንዲያፍርባቸው ሲደረግ ቆይቷል። የፈተናው ጫናም ቀድሞ ስለሚጀምር ዘንድሮ ተፈታኝ ነህ እየተባለ ተማሪውም ለከፍተኛ ጭንቀት እንዲዳረግ ይደረግ ነበር።
ማኅበረሰቡ የችግሩን ስፋት ሳይረዳ ልጆቹን ለከፍተኛ ጭንቀት በመዳረጉ ብዙዎች በፈተና ወቅት እስኪያልባቸው እንዲርበተበቱና ጥለው እንዲወጡ ያደርጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጎበዝ የሚባሉም ውጤታቸው እንዲበላሽ ከማድረጉ ባሻገር፣ ሕይወቴ ተበላሸ ብለው በርካቶች ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርሱበት ጊዜም ነበር።
በፊት የነበረው ጭንቀትም ሆነ ውጥረት፣ ዘመኑ ባመጣው ሰፊ እድል ሳቢያ ሊቀር ሲገባው አሁንም ድረስ በባለሥልጣናቱም ሆነ በቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም በራሳቸው በተፈታኞቹ ዘንድ የተዛባ አመለካከት እንዳለ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።
በግንብ ተደብቆ አጥፊን የመቅጣት ዓላማን ብቻ እንዳነገበ ትራፊክ ፖሊስ፣ ፈታኞች ተማሪዎችን ለምን እንዴትና በምን መንገድ መፈተን እንዳለባቸው ማወቅና ሁሉንም ማስገንዘብ አለባቸው።
ተማሪ የሚወድቅበትን መንገድ ብቻ ለይቶ ለመጣል ሲባል መፈተን ተገቢ ላለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ላያስፈልግ ይችላል። ጎበዝ አስተማሪ ለመባል ከባድ ፈተናን የሚያወጡ እንዳሉ ኹሉ፣ ጥሩ አስተምሯቸዋል ለመባልም ሲሉ ቀላል ጥያቄዎች አውጥተው በቀጣይ ያሉ ተፈታኞችን ተስፋ የሚያደበዝዙም ሆነ የሚያዘናጉ መምህሮች አይጠፋም።
በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚሰጥ ፈተና ግን፣ ግራ ቀኙን ዐይቶ አማካይ የሆነ ኹሉንም አኩል ለማወዳደር የሚረዳን መስፈርት አውጥቶ ይፈትናል። ተማሪውም ከቀደሙት ዓመታት ልምድ ወስዶ ስለሚመጣ ለውጥ ሲደረግ አስቀድሞ እንዲያውቀው ይደረጋል።
የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና በብዙ ፈተናዎች የተወጠረ እንደነበር አዲስ ማለዳ ትረዳለች። ተማሪን ለመፈተን ብሎ ፈተና ውስጥ የገባው መንግሥት፣ የተለመደ ስርቆትንና ኩረጃን ለማስቀረት ሲል በከፍተኛ ወጪ አዲስ ዓይነት የአፈታተን ዘይቤን የጀመረበት ዘመን ነበር።
ዓላማውንም ሆነ መንገዱን ብዙዎች ያደነቁት ቢሆንም፣ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ግን በጎ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እምብዛም አልታየም። ይህ ለምን ሆነ ብሎ የመጠየቁ ፋንታ የመንግሥትም ቢሆን፣ ዋናው ከተማሪዎች ዝግጅት አንጻር እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም። መንግሥት አስቀድሞ እንደተዘጋጀበት ሁሉ፣ ተፈታኞችም እንደ አዲስ አጥንተው ራሳቸውን ችለው ለመፈተን የሚዘጋጁበት እድል ሊመቻችላቸው በተገባ ነበር።
ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የተማረውን የሚፈተንበት እንደመሆኑ፣ ለአራት ዓመታት ያህል እንደቀደሙት ታላላቆቹ እኮርጃላሁ ብሎ በወጉ ሳይማርና ሳይዘጋጅ የከረመውን ድንገት ተነስቶ ባልጠበቀው ሁኔታ ማለፊያ መንገዱ ሲጠብቅበት ተስፋ እንደሚቆርጥ መገመት አይከብድም።
ይህ ቢሆንም ግን፣ የተዘጋጁም ተማሪዎች እንደመኖራቸው ማን ምን ያህል ዝግጁ ነበር የሚለውን በመለየት፣ እንደወታደር መቼም ቢሆን ዝግጁ የነበረውን ተማሪ ቀዳሚ ፍላጎቱን በምደባም ሆነ በትምህርት ዓይነት ምርጫ እንዲያገኝ ማድረጉ ይበጃል።
እንደአዲስ ማለዳ እምነት በሺዎች የሚቆጠሩ ለዓመታት የተለፋባቸው ተማሪዎች ይቅርና አንድም እስረኛ ቢሆን የመፈተን እድሉን ሊነፈግ አይገባም። የወጣትነት እድሜ ገፋፍቷቸውም ይሁን በተለያየ ምክንያት ተቀስቅሰው፣ ላለመፈተን የወሰኑት ተማሪዎች ላይ ዘላቂ ውሳኔ ማስተላለፉ ተገቢ አይሆንም።
ኪሳራው የእነሱ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም እንደመሆኑ ውሳኔው ተደጋግሞ ሊጤን ያስፈልጋል። ከቤተሰቦቹ ተለይቶ መዋዕለ ሕፃናት አልገባም ያለን ታዳጊ ኹለተኛ ትምህርት ቤት የሚባል አትሄድም ብሎ መከልከል ወንጀል እንደመሆኑ፣ ግራ ቀኙን አስማምቶ መንግሥት በሆደ ሰፊነት የተማሪዎቹን ሁኔታ ሊያስብበት ይገባል።
አንፈተንም ያሉበት ምክንያት ተገቢ ነው አይደለም ብሎ ከመገምገም ይልቅ፣ ማንኛቸውም ምክንያት በትምህርት ሂደት ላይ ጣልቃ መግባት እንዳልነበረበት በመረዳት፣ እርምቱ ከራሱ ከመንግሥት አሰራር መጀመር እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ለዓመታት የካድሬ ምልመላን የሚያካሂዱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ የሆኑ የትምህርት ተቋማትም ተማሪዎቻቸውን ገለልተኛ ለማድረግ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አምኖ፣ ከዘንድሮው ፈተና ውጤት ብቻ ሳይሆን ከሂደቱ ትምህርትን መውሰድ የመንግሥት ቀዳሚው ተግባር መሆን ይጠበቅበታል።
ተማሪዎቹን ለመዝለፍም ሆነ ለማሸማቀቅ ከመሞከርና የግል አስተያየትን ከመስጠት ይልቅ የእኔ ልጅ ቢሆንስ እንዲህ ያደረገው ብለን፣ የግል ድርጅታችንን ለማውረስ ቢሆን ብለን ከልጆቻችን የምጠብቀውንም በማሰብ ምክረ ሐሳብ ማመንጨት ግድ ይላል።
ተማሪዎቹ ስላልተፈተኑ ሕይወታቸው ይመሳቀላል ብሎ ማሰቡም ተገቢ አይሆንም። የዘመናችን የዓለም ቀዳሚ ቱጃሮች አብዛኞቹ አለመማራቸው ቢታወቅም፣ ሁሉንም መቀስቀሻና የትምህርትን አስፈላጊነት ማራከሻ እንዳይሆን እየታሰበበት፣ ፈተናውን ያቋረጡት በማኅበረሰቡ እንዳይገለሉም ሆነ እንዳይከበሩ መደረግ ይኖርበታል።
እልኸኝነት ለመንግሥት ይቅርና ለተማሪም ስለማይገባ ፈተናው የማለፊያ እንጂ የማሸነፊያ እንዳይሆን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015