መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብበትውልድ መቀያየር ያልከሰመ ርዕይ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

በትውልድ መቀያየር ያልከሰመ ርዕይ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

በዛሬው ዘመን አካደሚ ማለት የቋንቋም የሌላም እውቀት ያላቸው ፕሮፌሰሮች (ሊቃውንት) እየተሰበሰቡ አዲስ እቃ ሲሠራ ወይም ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ አንድ ቃል ሲገኝ እንደዚህ ብለን እንሰይመው ብለው የሚማከሩበት፣ ስለ ትምህርትም ደንቡና ሥርዓቱ እንደዚህ ቢሆን ይሻላል እያሉ የሚወስኑበት፣ ስለ አገርም ፖለቲካና ችግር እንደዚህ ቢሆን ይሻላል እያሉ ሐሳባቸውን የሚያመዛዝኑበት፣ ይህንንም የመሰለውን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚሆን ነገር ሁሉ እየተማከሩ በትምህርትም በጽሕፈትም ለሕዝብ እንዲታወቅ የሚያደርጉበት ቤት ነው።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴበእድሜ መሰንበት፤ ሁሉን ለማየት (1926)

በ1926 በተጻፈው ‹በእድሜ መሰንበት ሁሉን ለማየት› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሳይንስ አካዳሚን ጥቅምና አስፈላጊነት በጉልህ ገልጸዋል። በጉዞ ማስታወሻዎቻቸው፣ በታሪካዊ መጻሕፎቻቸው፣ በግብረ-ገብ ማስተማሪያ ጽሑፎቻቸው፣ በንቁ ዲፕሎማትነታቸው፣ በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው የሚታወቁት ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፤ በእድሜ ሰንብተው ባያዩም የመኖሪያ እልፍኛቸው አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲሁም የሥነጥበባት ማዕከል ለመሆን በቅቷል።

ባሳለፍው መስከረም 14 ቀን 2015 እለተ ቅዳሜ፣ ቤታቸውን ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ባዋለው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት፣ የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መታሰቢያ የፎቶ ዓውደ-ርዕይና በሥራዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

የታሪክ ምሁሩ ባህሩ ዘውዴ (ኤምሬተስ ፕሮፌሰር) ስለ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ሥራዎችና ሕይወታቸው ሲገልጹ ‹‹ኅሩይ የባህላዊና ዘመናዊ ሕይወት ኅብር ናቸው። መሠረታቸው ባህላዊ ሆኖ ዘመናዊ እውቀትን ለመቅሰም ወደ ኋላ የማይሉ፣ ቀስመውም እውቀታቸውን ለሌሎች ማካፈል የቻሉ ሰው ናቸው።›› አሉ።

‹ቋንቋ እውቀት አይደለም› ሲባል ይሰማል። በዚህም ላይ በአንድ ፈርጅ የሚስማሙ፣ በሌላ ፈርጅ ደግሞ አንስማም ብለው የራሳቸውን አመክንዩ በማንሳት ቋንቋ እውቀት መሆኑን ለማሳየት የሚጥሩ አሉ። ኹለቱም ፈርጀኞች የሚስማሙበት እውነት ግን፣ ቋንቋ እውቀትን የማግኛ መንገድ መሆኑ ላይ ነው። በዚህ ልክም የብላቴን የቋንቋ ችሎታና ቋንቋዎችን ለማወቅ የነበራቸው ፍላጎት የእውቀት መሻት ደረጃቸውን የሚያሳይ ነው።

ባህሩ እንደሚሉት ኅሩይ የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን በራሳቸው ጥረት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተማሩ ሲሆን፣ አረብኛ ቋንቋ ለመማር ሞክረው ነበር።

‹ምናልባትም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ካልበለጧቸው በቀር በዘመናቸው በውጪ አገራት ጉብኝት ቀዳሚው ኢትዮጵያዊ ናቸው።› የተባለላቸው ኅሩይ፤ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውም በ1903 በንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሥርዓተ ንግሥ ላይ ለመታደም ከደጃች ካሳ ጋር ወደ እንግሊዝ ያደረጉት ጉዞ ነው። በወቅቱም በእንግሊዝ አገር ያደረጉትን የአምስት ወራት ቆይታቸውን በቀን ማስታዎሻቸው ላይ መዝግበው አስቀምጠዋል። ይህ ማስታወሻም ከመቶ ዓመታት በኋላ በባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ (1903 ዓ.ም)›› በሚል ርዕስ በ302 ገጾች ተዋቅሮ ለንባብ በቅቷል።

በባህሩ ገለጻ ኅሩይ ከሄዱባቸው አገራት መካከል ቁንጮውን ጉዞ ያደረጉት ወደ ጃፓን ሲሆን፣ ከተጓዙባቸው ዘጠኝ ታላላቅ ጉዞዎች መካከል በአምስቱ ዙሪያ መጻሕፍት መጻፋቸው ጉዞዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማካፈል እንዲችሉ አድርጓቸዋል። በፎቶግራፎች የበለጸገው ማኅደረ ብርሃን /ሀገረ ጃፓን/ የሚለው መጽሐፋቸው፣ በጃፓን የነበራቸውን ጉብኝት ያስቃኙበትና በባህሩ ዕይታም ከተጻፉት የጉዞ ማስታዎሻዎች የቁንጮውን ደረጃ የሚይዝ ነው።

በእነዚሁ መጻሕፎቻቸውም የውጪውን ዓለም ኑሮ ተመልክተው ምን ትምህርት መውሰድ ይቻላል የሚለውን ጥያቄ መልሰዋል። ለጉዞ ምን ያስፈልጋል የሚለውንም በዝርዝር ቃኝተው በጉዞዎች ወቅት ‹‹ምን ያህል መሀረብ ያስፈልጋል?›› የሚለውን እስከ መግለጽ ድረስ ጽፈዋል።

ከጉዞ ማስታወሻዎችም ባሻገር በታሪክም ሆነ በልብወለድ ዘርፍ በርካታ መጻሕፍትን የጻፉት ኅሩይ፣ አጠቃላይ መጽሐፎቻቸው ከኻያ እንደሚበልጡ ይነገራል። የሕይወት ታሪክ /በኋላ ዘመን ለሚነሱ ልጆች ማስታወሻ/ የሚለው መጻሕፋቸውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ‹የሕይወት ታሪክ መዝገብ› (Biographical Dictionary) ነው።

ከአሽከርነት በተነሳው የመንግሥት አገልግሎታቸውም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከዛም ዋና ከንቲባ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል። ለከተማ አስተዳደሩም ‹ማዘጋጃ ቤት› የሚለውን ሥያሜ እንዳወጡለት ይነገራል።

በሐበሾች እና በነጮች መሀል የሚደረጉ ክርክሮችን ለመዳኘት በተቋቋመው ‹ልዩ ፍርድ ቤት› ውስጥም በብላታ ማዕረግ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ሠርተዋል። ለዚህ ኃላፊነትም ዘመናዊ ትምህርት መማራቸው እጩ እንዳደረጋቸው ይነገራል።

ከሚያዚያ 19/1924 ጀምሮ የኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን እስኪወር ድረስም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን፣ በወረራው ወቅት ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጋር ወደ እንግሊዝ አገር ተሰደዋል። ኅሩይ በንጉሡ ዙሪያ ካሉት ሹማምንት መሀል እጅጉን ለንጉሡ ቅርብ እንደነበሩ የጠቀሱት ባህሩ፣ ለዚህም በንጉሡና በኅሩይ መካከል ተመሳሳይ ዝንባሌ መኖሩ ምክንያት ነው ብለዋል። ለዘመናዊነት የነበራቸው ፍላጎት እንዲሁም የተለሳለሰ ለውጥ ለማምጣት ያላቸው አቋም የንጉሡ የቅርብ ሰው እንዲሆኑ ካስቻሏቸው ምክንያቶች መሀል የሚጠቀሱ ናቸው።

ኅሩይ ባላቸው የቋንቋ ችሎታ መሠረት ተመርጠው በስደት ወቅት ለንደን ውስጥ በሚገኘው ያኔ በነበረ ሥያሜ ‹‹ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም›› በኋለኛ ሥያሜው ደግሞ ‹‹የኦሪየንታልና የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት›› በተባለው ተቋም ውስጥ የግዕዝና የአማርኛ ቋንቋ መምህር በመሆን ሠርተዋል። በዚህ ተቋምም ከእርሳቸው በኋላ አራት ኢትዮጵያዊ የታሪክ ምሁራን የዶክትሬት (PhD) ዲግሪያቸውን የሠሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ምሁራን መካከልም ባህሩ ተጠቃሽ ናቸው።

ኅሩይ ከእርሳቸው ባለፈም ኹለት ልጆቻቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባለውለታ የሆኑ ሲሆን፣ ፈቃደሥላሴ ኅሩይ፣ በራስ እምሩ ይመራ የነበረው ‹ጥቁር አምበሳ› ጦር እንዲመሠረት ከፍተኛ ሚና የነበራቸውና የጣሊያን ወረራ ለመመከት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ፤ በመጨረሻም በጣሊያኑ የጦር መሪ ግራዚያኒ የተረሸኑ ናቸው። ሌላው ልጃቸው ሲራክ ኅሩይ ደግሞ ‹ራሴላስ› የሚለውን በጠጣር እንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ወደ አማርኛ በመተርጎም ይታወቃሉ።

ማስረሻ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) ደግሞ፣ ኅሩይ ዘመንኛ ጥያቄዎችን በማንሳት ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን ጠቅሰው ለአብነትም ‹‹የልብ አሳብ /የብርሃኔና የጽዮን ሞገሳ ጋብቻ/›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የሴቶችን የመብት ጥያቄ ያነሱበት አግባብ ዘመነኛነታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ማስረሻ እንደሚሉት ኅሩይ ዘመናዊ አኗኗርን ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱም አዲስ አበባ ውስጥ በሹካና ማንኪያ ይበላበት የነበረ የሐበሻ ቤት የሳቸው ብቻ እንደነበረ ገልጸዋል። የውጭ አገር ዲፕሎማቶችንም በቤታቸው ይጋብዙ እንደነበረ አውስተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ኅሩይ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከንጉሡ ጋር በእንግሊዝ አገር ውስጥ በስደት በመኖር ላይ እያሉ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ መስከረም 10/1931 በባዝ ከተማ ሉግዘምበርግ በተባለው ቦታ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈጽሟል። በዚሁ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ወቅትም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤

‹‹ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። ይህ የአዳም ልጆችን ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በሀገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ፣ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሀቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ ችሏል። በጊዜውም የጻፋቸው መጻሕፍት ከፍተኛ ባህርዩን የሚገልጹ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በአጭሩ ከጸባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፣ ከራስህ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፣ እውነትን ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።››

‹‹ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህ፣ መንፈስህ የሚሰፉበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ስፍራ በሰላም እረፍ።›› ሲሉም ከነጻነት በኋላ አጥንታቸው ፈልሶ በአገራቸው እንደሚያርፍ ቃል ገብተዋል። ከድል በኋላም አጥንታቸው መስከረም 11/1940 አዲስ አበባ ገብቶ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እኔ ብለው ካወሩባቸው ኹለት አጋጣሚዎች መሀል የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥርዓተ ቀብር ላይ ያደረጉት ይህ ንግግር አንዱ ሲሆን፣ ይህን ማድረጋቸውም ለኅሩይ ያላቸውን ክብር የሚያሳይ እንደሆነ ባህሩ ዘውዴ ተናግረዋል። ሌላው ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እኔ ብለው ንግግር ያደረጉበት አጋጣሚ ደግሞ በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ምሥረታ ጊዜ ነው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ስምንት ወራትን ብቻ የኖሩበት በአዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ዘመናዊ መኖሪያ ቤታቸው ከዓመታት በኋላ ዓላማቸው የሚሳካበት፣ ሥራዎቻቸውም ህያው የሚሆኑበት የሳይንስ አካዳሚ መሆን ችሏል።

ትውልድም ሥራዎቻቸውን ያይ፣ ታሪካቸውንም ያውቅ ዘንድ ለአንድ ወር የሚዘልቅ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይን አካዳሚው አዘጋጅቷል። ለዕይታ የቀረቡት አርባ የሚደርሱ ፎቶዎቻቸውም በውጪ አገራት ያደረጓቸውን ጉብኝቶች የሚያስቃኙ፣ በቤታቸው እንዲሁም በተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎች ያሳለፏቸውን ታሪካዊ ሁነቶች የሚያስመለክቱ ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች