ተወርዋሪ ኮከቦች!

በለጋ እድሜ ታይተው የጠፉ፣ በውስን ዓመት ውስጥ ብዙ ቁምነገር ሠርተው፣ ወደፊት ምን ሊሠሩ ነው ተብሎ የበለጠው ሲጠበቅ ሞት የወሰዳቸው የጥበብ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ዮሐንስ አድማሱ ‹እስኪ ተጠየቁ› የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፉ ላይ፣ እንደራሱ ሁሉ ‹ተወርዋሪ ኮከብ› ሆነው ያለፉትንና የሚያልፉትን እንዲህ ሲል በስንኞች ገልጿቸዋል።

‹‹ተወርዋሪ ኮከብ የደረሰው ቦታ የጨለመ ምድር፤

አይታይም ነበር።
ጨለማ አካል ገዝቶ፣
ይዳስስ ነበረ በየቦታው ገብቶ።
ብሩህ ነጸብራቁ፣
ውበቱና ድምጹ አንድነት ተሰምተው አንድነት ቢበርቁ፤
የሚያውቅለት ጠፍቶ፣
ምሥጢሩን አካቶ፤
ተወርዋሪ ኮከብ…
በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ፣
ተወርዋሪ ኮከብ…
በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ።

እንዲህ ባለ መልክ ከዚህ ዓለም የተለዩን አንጋፎች በርካቶች ናቸው። ሚካያ በኃይሉ፣ ኢዮብ መኮንን፣ ታምራት ደስታ፣ ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ ደረጄ ዱባለ፣ ኤርሚያስ አስፋው፣ ኤልያስ መልካ፣ ዳዊት ነጋ እንደተለዩን በየቅጽበት የምናስታውሳቸው የሙዚቃ ሰዎች ናቸው። ድንገተኛው ሞት አሁን ደግሞ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅን ወስዷል።

‹ያለፈን ላይቀይር በከንቱ ይለፋል፣

መቼም ሰው ደፋር ነው ፈጣሪን ይጋፋል።›

ልደትና እድገት

ማዲንጎ በጎንደር አዘዞ ነው የተወለደው። ገና የሦስት ወር ጨቅላ ሳለ ነው እድገቱን ወዳሳለፈባት ወደ ደቡብ ጎንደሯ ደብረታቦር ከተማ የሄደው። የሕይወት ታሪኩ እንደሚያስረዳው፣ የታወቀበት እና አብሮት የኖረው ሥም ማዲንጎ ይሁን እንጂ ወላጆቹ ያወጡለት ሥም ‹ተገኔ› ነበር።

ማዲንጎ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት በልጅነቱ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በሰጣቸው ቃለመጠይቆች ተናግሯል። በኋላ የሰባተኛ ክፍለ ጦር ካምፕ የ603 ኮር የሙዚቃ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ ተመለከተ። ይሄኔ ነው ‹ድምጻዊ መሆን እችላለሁ!› ብሎ በማመን እድል እንዲሰጡት ጠየቀ። እድል አልተነፈገም። ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ ማጉያውን ጨብጦ የድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩን ‹ና ተላክ ልቤ…› የተሰኘውን ሙዚቃ ተጫውተ። ከዛም መድረክ መረማመጃ የሚሆን የሚያበረታ አድናቆትን አገኘ።

ያገኘው አድናቆት ብቻ ሳይሆን ተቀባይነትንም ነበር። እናም በዛው በወታደር ቤት ሙዚቃውን ቀጠለ። ማዲንጎ የሚለው ሥምም የወጣለት በዛው በወታደር ቤት ነው።

ተዋናይና የኪነጥበብ ሰው በምናቡ ከበደ ‹ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ሥራውን ሲጀምር› በሚል ባስነበበው ጽሑፍ የራሱንም ትዝታ አብሮ አንስቷል። ቃል በቃል እንዲህ ይላል፤

‹‹ጊዜው 1982 ነው። የ4ኛ ሜካናይዝድ የኪነት ቡድን ጎንደር አዘዞ ከተማ ሎዛ ማርያም ላይ ነበር። እኔ የኪነቱ የትያትር ባለሙያና ኪቦርድ ተጫዋች ነበርኩ። ያኔ ማዲ የ14 ዓመት ልጅ እያለ ዘፋኝ መሆን እፈልጋለሁ አስገቡኝ ብሎ ይዘውት መጡ። ድምጹን ሞከርነው። ተኬ፣ ‹ይህ ልጅ የፊልም ተዋናዩን ማዲንጎን ይመስላል› አለ። እኔም ‹ሳክስፎን ተጫዋቹን ዲንጎ ማዲንጎን ይመስላል› አልኩ።

ማዲንጎ የተፈተነበት ዘፈን፤ የፍቅራዲስን ነቃጥበብ እና የፀሐዬ ዮሐንስ ‹ትዝ ትዝ አለኝ ጎራው..ማን እንደናት ማን እንደ ሀገር› የሚለው ዘፈን ነበር። ወደድነው። ተቀላቀለን። የሚደንቀው ነገር፤ የፀሐዬን ዘፈን ማጀቢያ ሙዚቃዎችን መግቢያና መሸጋገሪያዎችን ሁሉ፣ ምቱን ሳይቀር እሱ ነበር ያስጠናን። ወደ ባህርዳር “መኮድ” 1983 ስንመጣ አብሮን ነበር።

…የ603 ኮር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ቤት ምሽት እንግዶች ሲመጡ ማዲንጎ እና አፀደ በድምፅ፣ እኔ ኪቦርድ ተጫዋች ሆኜ ግርማ ቤዝ ጊታር፣ መቶ አለቃ ደሳለኝ ሊድ ጊታር …ምሽቱን በሙዚቃ አስደስተን ማዲንጎ ብዙ ብር ይሸለም ስለነበር ያገኘውን ያካፍለን ነበር። ማዲንጎ አባ መስጠትነቱንና ቸርነቱን ያኔ ጀምሮ ነበር የማውቀው። ማዲንጎ ለሀገሩና ለሠራዊቱ የነበረው ፍቅር ያኔም እጅግ ጥልቅ ነበር።›› ብሏል።

ማዲንጎ በወታደር ቤት ብዙ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ድምጻዊ የመሆን ሕልሙን የማሳካት እርምጃዎችን ወሰደ። በቅድሚያ ያደረገው ኑሮውን በባህርዳር ከተማ ማድረግ ነበር። አደረገው።

ከዛ በኋላ ነው ወደ አዲስ አበባ ያመራው። በአዲስ አበባም የተለያዩ የሙዚቃ ቡድኖችን በመቀላቀል እጅግ የሚያደንቃቸውን የታዋቂ ድምጻውያን ሙዚቃዎችን ማቀንቀን ጀመረ። የኤፍሬም ታምሩ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ፀጋዬ  እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ይሁኔ በላይ፣ ኤልያስ ተባባልን ሙዚቃዎች አዘውትሮ ይጫወት ነበር። በኋላም የራሱን ሥራዎች ወደመሥራቱ ተሻገረ።

- ይከተሉን -Social Media

በ1987 የመጀመሪያ የሆነ ‹ሥያሜ አጣሁላት› የተሰኘውን አልበም ለአድማጮች አደረሰ። ተቀባይነትን ለማግኘት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። በዛ ብርታትም ‹አይደረግም› የተሰኘ ኹለተኛ አልበሙን ለሕዝብ አደረሰ። ሙዚቃዎቹ የያዙት መልዕክት ጥንካሬና ውበት ከራሱ መረዋ ድምጽ ጋር ተዳምረው፣ ሥራዎቹ ዘመን የሚሻገሩ ስለመሆናቸው ያሳብቃሉ።

ከ‹አይደረግም› አልበሙ በኋላ ስምንት ዓመታትን አሳልፎ ‹ስወድላት› የተሰኘውን ሦስተኛ አልበሙን ለአድማጮች አደረሰ። ይህም አልበሙ በእጅጉ የተወደደለት አልበም ነበር።

ማዲንጎ በሙዚቃ ሥራዎቹ ያላነሳው ጉዳይ የለም። ስለአገርና ስለፍቅር በይበልጥ ዘምሯል። ስለኢትዮጵያም ደጋግሞ አቀንቅኗል፤ ጀግኖቿን በአድናቆት አመስግኗል፣ ታሪኳንም ዘክሯል።

 ምስክርነት

ብዙውን ጊዜ ለሰዎች ምስክርነትን ለመስጠት ምክንያት እናስሳለን። ድግስ ወይም የሽልማት መሰናዶ አልያም ሌላ አንዳች ኹነትን እንጠብቃለን። በተገኘው አጋጣሚ ሰዎችን የማመስገንና እውቅና የመስጠት ልምድ የለንም። ሞት በቀጠሮ የሚመጣ አይደለምና እርስ በእርስም ሆነ አብዝተን የምናደንቃቸውን ሰዎች በአካለ ስጋ እያሉና እያለን፣ ተገቢውን ክብርና እውቅና መሰጣጠት ተገቢ ነው።

ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ከሙዚቃ ሥራው በተጓዳኝ እንደ ሰው ከቤተሰብ፣ ከወዳጅና ከጓደኞቹ ጋር ያለው ወዳጅነት ብሎም መልካም ሰው ስለመሆኑ አሁን ብዙዎች እየመሰከሩ ይገኛሉ።

‹‹ሕወሓት ኢሕአዴግ አስሮኝ እያለ ማንም ሊጠይቀኝ ይፈራ ነበር። የራሴ የቅርብ ዘመዶቼ ለቤተሰቤ ስልክ መደወል ይፈሩ ነበር። ማዲንጎ አፈወርቅ ግን በድፍረት መጥቶ ጠየቀኝ። አሞኝ በወታደር ተከብቤ ስታከም በድፍረት መጥቶ የጠየቀኝ ማዲንጎ ነው። የ5 ዓመት ልጄ እንዳይርባት እጁን የዘረጋላት ማዲንጎ ነበር። በዓላማ አብረን የነበሩ ብዙዎች አሁን የሉም። ማዲንጎ ግን እስከ እለተ ሞቱ ለሀቅ እንደቆሞ አልፏል።››

ሀብታሙ አያሌው

- ይከተሉን -Social Media

‹‹ከአምስት ዓመት በፊት በአንድ ማለዳ ለአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ስልክ ደወልንለትና ‹ለባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ብቸኛ እናቶቻችን አስቤዛ ለመግዛትና ለበዓል እንዲሆን ጫማ መጥረግ ፕሮግራም አለንና እባክህ ተገኝ› አልነው። ‹‹ኮንሰርት አለኝ። ዛሬ ወደ አሜሪካ እበራለሁ። ይህ በረከት ከሚያልፈኝ ለምን አሁን መጥቼ እኔ ጫማ አልጠርግም!።›› አለን። እንዳለውም ጓደኛችን አብርሽ ያለበት ቦታ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ደርሶ ዝቅ ብሎ ጫማ በመጥረግ ሌሎች የምንወዳቸው ደጋጎች እንዲሳተፉ መነሳሳትን ፈጥሮልናል። ማዲ እናመሰግናለን።››

ሔኖክ ፍቃዱ (ባይሽ ኮልፌ)

ይህን እንደማሳያ አነሳን። በርካቶችም ቀና ልብ ያለው ድምጻዊ እንደነበር እየመሰከሩ፣ በኅልፈቱ የተሰማቸውን ሐዘንም እየገለጹ ቆይተዋል። ከዚህም በተጓዳኝ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ሐዘናቸውን ሲገልጹና ማዲንጎ ለአገሩ በሙያው ያበረከተውን አስተዋጽኦ በማድነቅ ሲመሰክሩ ተስተውሏል።

‹‹አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ለአገሩና ለትውልድ ጥበብንና ባህልን አውርሶ ያለፈ እውቅ ከያኒ ነው። የሚችለውን ኹሉ ለሚወዳት አገሩ ተቀኝቷል። በችግር ውስጥ ሆኖም ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር ሲል ከጠላት ጋር የሚዋደቀውን ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊታችንን እና የጸጥታ ኃይላችንን ግንባር ድረስ ዘልቆ አበረታትቷል። ስለኢትዮጵያ ቀደምት ሥልጣኔና ታሪክ፣ ሰላምና አንድነት፣ ነጻነትና ክብር በርካታ የጥበብ ሥራዎችን ሠርቷል። ለቤተሰቦቹ፣ ለአድናቂዎቹ እና ለሙያ አጋሮቹ መጽናናትን እመኛለሁ።››

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

‹‹ማዲንጎ የተዋጣለት ከያኒ ብቻ ሳይሆን ልበ ቀና እና አገር ወዳድ ነበር። የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው። ማዲንጎ እንደሰው ሰከን ያለ ስብዕና የተላበሰ ሰው ነበር።››

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ

‹‹የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ድንገተኛ ህልፈት መስማት በእጅጉ ያስደነግጣል። ማዲንጎ በሙያው ለአገሩ ሰፊ አበርክቶ ያለው፣ ኹሌም ለአገሩ ጥሪ ቀድሞ የሚደርስ ትሁትና የተዋጣለት ባለሙያ ነበር። ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጆቹ መጽናናትን እመኛለሁ።››

- ይከተሉን -Social Media

ስለሺ በቀለ (ዶክተር ኢንጂነር)
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር

‹‹አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በማረፉ የተሰማኝ ሀዘን ከባድ ነው። ለአገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ ነው፤ አገር በተደፈረች ጊዜ ሕመሙን እየቻለ ግንባር ተገኝቶ ሠራዊቱን አጀግኗል፣ ሠልጣኞችን አበረታቷል። ነፍሱ በሰላም ትረፍ!››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ማዲንጎ አፈወርቅ ባሳለፍነው ማክሰኞ መስከረም 17 ቀን 2015፣ በመስቀል በዓል እለት ነበር ዜና እረፍቱ የተሰማው። ሐሙስ መስከረም 19/2015 እለትም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡

አዲስ ማለዳ ለድምጻዊው ቤተሰቦች፣ አድናቂዎች፣ ወዳጆችና የሥራ ባልደረቦች፣ ሐዘንም ለተሰማቸው ሁሉ መጽናናትን ትመኛለች። ተወርዋሪ ኮከብ ሆኖ ያለፈው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅም የነፍስ እረፍት እንዲያገኝ ትመኛለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች