ከ773 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው 97 ኪሎግራም ኮኬይን በቁጥጥር ሥር ዋለ

0
759

ዕረቡ መስከረም 18 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከ773 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለውና 97 ኪሎግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ በአዲስ አበባ ኤርፖርት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

መነሻዋን ከናይሮቢ ኬንያ መዳረሻዋን አዲስ አበባ ያደረገች ግለሰብ 97 ነጥብ 48 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን በያዘቻቸው ኹለት ሻንጣዎች ይዛ ለማሳለፍ ስትሞክር በጉምሩክ ኮሚሽን ኤርፖርት ቅርንጫፍ በቁጥጥር ሥር ውላለች፡፡ተጠርጣሪዋ የትራንዚት መንገደኞች እና ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበትን እቃ ያልያዙ መንገደኞች የሚወጡበትን በዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ወይም አረንጓዴ የጉምሩክ ማለፊያ መስመር (Green Line) በመጠቀም እያንዳንዳቸው 48 ነጥብ 62 እና 48 ነጥብ 86 ኪሎግራም ክብደት ያላቸውን ኹለት ሻንጣዎችን ለመሳለፍ ስትሞክር ተይዛለች ተብሏል፡፡

ግለሰቧ በያዘቻቸው ሻንጣዎች ውስጥ የሚገኙት እቃዎች በመፈተሻ መሳሪያ /x-ray/ እንዳይለዩ ለማደረግ መጽሐፍ በማስመሰል እና በአልሙኒዬም ፎይል በመጥቅለል ለመደበቅ የሞከረች ቢሆንም፤ በተደረገው ጥብቅ ፍተሻ እና ክትትል በሻንጣዎቹ ውስጥ ያለው ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ መሆኑ ሊረጋገጥ ችሏል፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽን “አደንዛዥ እፁ ፍተሻውን አልፎ ቢገባ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ከማስከተሉ በተጨማሪ ለሽብርተኞች ቢተላለፍ የዜጎችን ደህንነት የማናጋት አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ይገነዘባል” ሲል አስታውቋል፡፡ኮሚሽኑ የግለሰቧን እንቅስቃሴ በንቃት ሲከታተሉ ለነበሩ በጉምሩክ ኮሚሽን ኤርፖርት ቅርንጫፍ ሰራተኞችና አመራሮች፣ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ለተሳተፉ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ሰራተኞች ፣ በኤርፖርት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን እና ለፀረ- አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ሀይል ከፍተኛ የሆነ ምስጋናን አቅርቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here