የትኛው ተቃዋሚ፣ የትኛው መንግሥት ነው የሚለው የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል

0
1425

ፖለቲከኛ ነበረች፤ ፍሬዘር ነጋሽ። የፖለቲካውን ዓለም የተቀላቀለችው በለጋ እድሜ ነው። እንደውም ወደ መአድ ቢሮ ስታመራ እድሜዋ ለፖለቲካ ፓርቲ አባልነት አይፈቅድም ነበር። እናም በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ ተሳትፋ የሚሆነውን ታይ፣ የሚባለውንም ታዳምጥ ነበር። በዛም እንደ አስራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር)፣ ኃይሉ ሻወል (ዶ/ር) እና አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር) ካሉ ሰዎች የቀሰመችው ብዙ ነው።

በዚህ መልክ የተጀመረ የፖለቲካ ተሳትፎዋ በኋላ ኢዴፓ ፓርቲን በመመሥረት ውስጥ ቀጥሏል። የፖለቲካ እንቅስቃሴዋ እንዲሁም በኋላ ላይ በሕትመት ሚድያው ላይ የነበራት ተሳትፎ ለእስር ዳርጓታል። ይህም ነፍሰጡር የነበረችበት ወቅት በመሆኑ ሁኔታውን ፈታኝና ከባድ አድርጎባት ነበር።

የአገር ፍቅርን፣ ለሕዝብ መብት መቆምና መታገልን ከቤተሰቧ ወርሳለች። ይህም ነው መጀመሪያ ፖለቲካ ውስጥ ከዛም ወደ ጋዜጠኝነት የወሰዳት። የጋዜጠኛነት ሙያንም ከ1996 ወዲህ በኢትዮጵያን ሪቪው ኦንላይን ሚድያ በመሥራት ጀመረች። በኋላም መረጃ ቲቪ አገር ውስጥ እንዲመሠረት በማድረግና በሥራ አስኪያጅነት፣ መንጎል ሚድያ በመሥራችነትና በመሪነት እንዲሁም አንድ አፍታ በጋዜጠኝነት ሠርታለች።

ቀጥሎም ከ2013 ምርጫ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት ሚድያ ዳሰሳ (Media Monitoring) ላይ እያለች ነው ሐመር ሚድያ እና ኮምዩኒኬሸንን በማቋቋም ሀርመኒ ዩትዩብን እና የራድዮ ፕሮግራምን የጀመረችው። ከዚህም ባሻገር በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥም በከፈተችው ስፕሪንግ የህትመትና የማስታወቂያ ድርጅት የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ኦንላይን ሚድያ ማኅበር ፕሬዝዳንት ናት የሆነችው ፍሬዘር፣ በ2014 ማብቂያ ላይ ወዳጆቿ፣ አጋሮቿ እና በአምባሳደርነት የምታገለግልበት ምስካበ የአረጋዊያንና ሕጻናት መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ ሆቴል ልዩ ዝግጅት በማድረግ ሸልመው አመስግነዋታል። ፍሬዘር ነጋሽ ይህንን እና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም የኦንላይን ሚድያን ነባራዊ ሁኔታ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ፖለቲከኛ ነበርሽ፤ በጋዜጠኝነት አገልግለሻል አሁንም እያገለገልሽ ነው። እንዲሁም ደግሞ የንግድ ሥራ ውስጥም አለሽ። የትኛውን ታስበልጪያለሽ?

በጣም ደስ የሚለኝ፣ የምወደውና ቢሳካልኝ ብዬ የማስበው ሚድያ ላይ መሥራትን ነው። ምክንያቱም የሚድያ ተደራሽነትና ኃይል ገንዘብ ካለው አቅም በላይ ነው። በተለይ ትውልድን ለማነጽ፣ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃን ለማኅበረሰቡ ለማድረስ፣ በአገር ግንባታና ሰላም ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማደረግ የሚያስችል አንዱ ሚድያ ነው።

በአገራችን በአባይ ጉዳይም ሆነ በሰሜኑ ጦርነቱ ላይ የሚድያ ተጽእኖ በበጎም በመጥፎም ዐይተነዋል። ምን ያህል ሐሰተኛ መረጃ ዲፕሎማሲን ‘አሸንፎ’ እንደጎዳን ታዝበናል። ልክ እንደዛው ሁሉ በመልካምም ተጽእኖ መፍጠር ይቻላል፤ ከተጠቀምንበት።

ሚድያ ላይ ብዙ ነገር መሥራት ይቻላል። እናም በዚህ ላይ ብሠራ መረጃ ከማስተላለፍም፣ ከማስተማርም አንጻር ብዙ መሥራት እችላለሁ ብዬ ስለማምን ሚድያ ላይ መሥራትን ነው የምወደው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ብሎም የግለሰቦች ተሳትፎ በፊት የነበረውና አሁን ያለውን ለማነጻጸር የሚያስችል ሁኔታ ገጥሞሽ ያውቅ ከሆነ፣ እንዴት ታዘብሽው?

ፖለቲካ በእኛ ጊዜ ቀረ ልበል? (ሳቅ) እኔ በነበርኩበት እድሜና ከዛም በኋላ በተሳተፍኩበት ትግል ውስጥ እንደ አሁኑ መያዣ መጨበጫ ያጣ የትግል ሕይወት ወይም የፖለቲካ አካሄድ አልነበረም። አሁን ድብልቅልቅ ብሏል። የትኛው ተቃዋሚ፣ የትኛው መንግሥት ነው የሚለው የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ያኔ ግን ማን ነው ተቃዋሚና ደጋፊ የሚለው በግልጽ የሚታይበት ነው። ዓላማና ግብሽ የታወቀ ነው። አሁን ግን ፓርቲዎች ይመሠረታሉ፣ ሀምሳ እና መቶ ከዛም በላይ ፓርቲ አለ ይባላል። ግን አንዳቸውም ለአገር ጥቅም ቆመው በየጊዜው መግለጫ ሲያወጡ ወይም ሲቃወሙ አይታይም።

በፊት በተለያየ ጊዜ በአገሪቱ የሚፈጠሩ ክስተቶች ላይ መግለጫዎች ይወጣሉ፤ ሰላማዊ ሰልፎች ይካሄዳሉ። የማኅበረሰብና የተማሪዎችም እንደዛው። በዚህ ደረጃ ትግሉ በጣም ግልጽ የሆነበት የትግል ስልት፣ የፖለቲካ ትግል ወይም አካሄድ ነው የነበረው።

አሁን ግን የአንዱ አባል ልሁን ቢባል እንኳ አባል ለመሆን የሚቻልበት ግልጽ የሆነ አቋም ያለው ፓርቲ አይታይም። ኢዜማን ጨምሮ ከብልጽግና ጋር ምን ይለያቸዋል ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ኢዜማ ምን ታገለ? ምን ያህል ምክረ ሐሳብ ሰጠ? ከሕዝብ እና ከአገር ጎን ምን ያህል ቆመ? ስንል፣ ትንሽ ጥያቄ ያስነሳል። ግን እሱም አንድ የትግል ስልት ሊሆን ይችላል። በጥቅሉ በእኛ ጊዜ በግልጽ ለአገር ጥቅምና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ ፓርቲዎች በብዛት ነበሩ።

አሁን በፖለቲካው ያለሽበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

በጣም ቆይቻለሁ ከወጣሁ። ግን የሚገርምሽ ፖለቲካ ደም ውስጥ ከገባ አይለቅም። በነገራችን ላይ ሰው ፖለቲካን ለምን እንደሚጠላ አይገባኝም፤ እኔ እወዳለሁ። ስወደው ግን የሴራና የጥላቻው ፖለቲካን ሳይሆን በትክክል ከአገር ጉዳይ፣ ከማኅበረሰብ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከመሳሰለው ጋር የተገናኘውን ነው። ለሕዝብ ድምጽ መሆን፣ ከአገር ጉዳት ጎን መቆም ቀላል አይደለም። ለእኔ ይሄ ፖለቲካ ከተባለም እድሜ ልኬን ፖለቲከኛ ሆኜ መኖር እፈልጋለሁ።

የፖለቲካ አባልነት የተውኩትና ያቆምኩት ከ1995 ጀምሮ ነው። በ1996 መጨረሻ ደግሞ ወደ ጋዜጠኝቱ ሕይወት ገባሁ። ስጀምርም በኦንላይን ሚድያ ነው።

ፖለቲካ ውስጥ ቆይቶ ወደ ጋዜጠኝነት መምጣት ሚዛንን አያስትም፣ አይቀላቀልም? ከፖለቲካ ወደ ሚድያ ስትገቢስ አልተቀላቀለብሽም?

በጣም አስቸግሮኛል። ያስቸገረኝ ለምሳሌ ቃለመጠይቅ ላይ አንዳንዴ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ሲነካ ያስቆጣኛል። እና አንዳንድ ጊዜ ከእንግዳዬ ጋር ልከራከር እችላለሁ። ግን ለብሔር ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ ወግኜ አይደለም። ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ግን የምቆጣበትና የምከራከርበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ አጋጣሚ ይቀላቀልብኛል።

ግን ጋዜጠኛ የተባለውን ሁሉ እሺ ብሎ ነው ወይ የሚቀበለው የሚለው ነገር ጥያቄ ይፈጥርብኛል። ገለልተኛ ይሁን ሲባል፣ አንዳንድ ጊዜ የአገር ጥቅም፣ የማኅበረሰብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይም ኮስተር ማለት ያበለት ይመስለኛል። እነዚህ ዓለማቀፍ ስምምነቶችም ስለሆኑ በፍጹም ልናልፋቸው አይገባም።

ግን እንዳልሽው ይቀላቀላል። በተለይ በሶሻል ሚድያው ላይ በምጽፍ ጊዜ ይቀላቀልብኛል። ጋዜጠኝነት የሚለው ሌላ ነው፤ እኔ ደግሞ ለሕዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክቲቪስት ሆኜ ታገኚኛለሽ። ያ ትክክል አይደለም። አሁን በእርግጥ ተቆጥቤአለሁ፣ ቢሆንም ግን ውስጤ በጣም ይታፈናል።

ሙያውን ስለምወደው ያንን ማቆም እንዳለብኝ አውቄ አቁሜአለሁ። ግን አክቲቪስት አይደለሁም። እጽፋለሁ፣ ሕዝብ አነቃለሁ። እንጂ ወግኜ የምጽፈው ነገር የለም።

ኦንላይን ሚድያ ነጻ ስለሆነ እኛም እንደ አገር ዘግይተን የተቀላቀልነው በመሆኑ፣ በዛ ምክንያት በሌሎች አክቲቪስቶች እጅ ወደቀ። ስለዚህ ኦንላይን ሚድያ የሚሠራ አክቲቪስት ነው ነው የሚባለው። አክቲቪስቱ ደግሞ እንዳለ ግልብጥ ብሎ እዛ ውስጥ ገባ። ዩ ትዩብ፣ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም ይከፍታል። በዛም የፈለገውን ኢንተርቪው ያደርጋል። ግን ይህን መቆጣጠር አያስፈልግም ወይ ነው?

እንደውም አሁን ወደ ቢዝነስም እየገባ ነው፤ አገር ጉዳይ። አክቲቪስት ሆኖ ቢዝነስ ሲሠራ እንዴት እንደሆነ አላውቅም። አክቲቪስት ለእኔ ለአንድ ማኅበረሰብ ወይም ለአንድ ጉዳይ ወግኖ ለዛ ድርጅት ወይ ማኅበረሰብ መሥራት ነው። እንጂ በዛ ማኅበረሰብ ተጠቅሞ ሀብት ማካበት አይደለም።

ይህ ግን የሚስተካከል ነው። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ ሲነቃ የሚያዳምጠውንና የማያዳምጠውን ለይቶ እየጣለ ሲሄድ፣ እየጠራ የሚመጣ ጉዳይ ነው።

የኦንላይን ሚድያ ማኅበር አለ። በዛም ፕሬዝዳንት ሆነሽ እያገለገልሽ ነው። ስለማኅበሩና ይህን ችግር ከመፍታት አንጻር የታሰበ ነገር ካለ ብናውቅ?

የኢትዮጰያ የኦንላይን ሚድያ (የበይነ መረብ ሚድያ) ማኅበር ነው። ሙሉ ለሙሉ ተቋቁሞ አላለቀም፤ መደራጀት ይቀረዋል። በሂደት ላይ ነው። ተመዝግበው፣ ለመዘገብ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩና ፈቃድ ሳያወጡ የሚሠሩ አሉ። ፈቃድ ሳያወጡም ጥሩ ነገር የሚሠሩ አሉ፤ ቢዝነስ አድርገዉት እየሠሩ ያሉም አሉ።

ግን ለአገር ጥቅምና ግንባታ እንዲውል ሰብሰብ ማለት ያስፈልጋል። ገቢውም ሆነ የሚሰራጨው መረጃ ቀላል አይደለም። ወደ ሕጋዊ መንገድ መጥቶ፣ ሰብሰብ ብሎ መደራጀትና መሥራት ቢቻል ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ ነው ያለን። እና ሌሎችም ወደእኛ እንዲመጡ ነው የምንፈልገው፤ ፈቃድ ያወጡትም ሆነ ያላወጡት።

ዋናው ግን እኛ ልንሠራ ያሰብነው፣ አንዱ ሥልጠና ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛው ጋዜጠኛ ኦንላይን ሚድያን በሩቁ ነው የሚሸሸው። ምክንያቱም ባለሞያ ባልሆኑ ሰዎች እጅ ወደቀና የማይሆን ነገር ይለቀቃል። ስለዚህ ኦንላይን ሚድያ ላይ ስትሠሪ በባለሞያዎች ጥሩ ምስል አይሰጥሽም።

ብዙ ጊዜ በተለያዩ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞችን አምጥቼ ለማሠራት ሞክሬአለሁ። ግን ከኦንላይን ሚድያ ጋር ብዙም አይተዋወቁም፤ አንዱ የሚያሸሻቸውም እሱ ይመስለኛል። ወደፊት ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ጋር በደንብ ተዋህዳ የኦንላይን ሚድያ ቲቪ በደንብ የሚሰራጭበትና መደበኛው ሚድያ የማይፈለግበት ጊዜ ይመጣል። ስለዚህ ከወዲሁ ሥልጠናዎችን በመስጠት ጋዜጠኞችን ማብቃትና ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

ሌላው እንደሚታወቀው በመንግሥት ደረጃም ስለ ኦንላይን ሚድያ ያለው አመለካከት ደካማ ነው። ያንን ማስተካከል አለብን ብለናል። ምክንያቱም ኦንላይን ሚድያ ሲባል ባለሥልጣናት መረጃ መስጠት ይፈራሉ። ለምን ቢባል ንግግር ተሰንጥቆ፣ ተቆራርጦ ይወጣል የሚል ነው አንዱ። ያንንም ማጥራት አለብን።

አንድ ባለሥልጣን ኢንተርቪው ላድርግ ብዬ ብሄድ ስንት ተከታይ አለሽ ነው የሚለኝ። ባለሥልጣኑም የሚገፋሽ የውሸት ነገር ተናግረሽ፣ ተከታይ ወደማፍራት ነው። ለምን? ኹለት እና ሦስት መቶ ሰው እያየሽ እንዴት አንቺ ጋር እመጣለሁ ይልሻል። ስለዚህ ከዛ በላይ ተመልካች ለማግኘት ሰበር ዜና፣ ጉድ ፈላ ማለት አለብሽ። እንዲያ ዓይነት ነገሮች መቅረት አለባቸው። ዋናው እውነታ እና ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ ማሰራጨት ስለሆን፣ ኹለትም ይሁን ሦስት መቶ ሰው አየ፣ ይህን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።

የማኅበሩ አባላትም የኦንላይን ሚድያ ባለሞያዎች ናቸው። ከዛም አልፎ ፈቃድ አውጥተው፣ ቢሮ ከፍተውና ስቱድዮ ገንብተው እየሠሩ ያሉ ናቸው። አሁን ከ15 በላይ የሚሆኑ አባላት አሉን።

አሁን ላይ የእኛን አዲስ ማለዳ ጨምሮ በርካታ ‘ሜይን ስትሪም’ የሚባለው መደበኛ ሚድያ ወደ ዲጂታሉ እየቀረበ ነው። ማኅበራችሁ ከመደበኛ ሚድያዎች ጋር ያለው ቅርበት ምን ይመስላል?

ካሉን 15 አባላት መካከል ኹለቱ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን የሆኑ ቲቪ እና ሬድዮ ያላቸው ናቸው። የህትመት ሚድያዎችም አሉ፣ ኦንላይን የሚጠቀሙ።

ኦንላይን ሚድያ ሲባል ዩ ትዩብ ብቻ አይደለም። የአዲስ ማለዳ ዓይነት ጋዜጦች ዌብሳይት ላይ አሉ። እኔ ጋዜጣ ግዢ ከምትይኝ አዲስ ማለዳን ኦንላይን የየእለቱን ዜና በፍጥነት ዐያለሁ። ጋዜጣ ሄዶ ከመግዛትም ጊዜን ይቆጠባል። መረጃንም መርጠሽ ለማየት እድል ይፈጥራል።

ይሄ የማይቀር ነው። የዋጋ ንረት ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብና ሠራተኞችም ከጊዜ አንጻር፣ ፍላጎትም ጭምር ወደ ቴክኖሎጂ መግባታችን የማይቀር ነው። ቲቪ ሰዓት ጠብቆ ስንት ሰው ሊያይ ይችላል ከዚህ በኋላ? ሁሉም በእጅ ሞባይል እና በላፕቶፕ ነው የሚጠቀመው። እና ኦንላይን ሚድያ ማኅበራዊ ሚድያዎችንም ያጠቃልላል።

አሁን ከመደበኛው ይልቅ ሞባይላችን መረጃን ፈጥኖ ያቀብለናል። ይህም በማን ነው ካልን፣ በኦንላይን ሚድያ ነው። ለዛ ነው ብዙ ጊዜ በተለይ መደበኛዎቹ ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ግዴላችሁም የኦንላይን ሚድያ ሥራን ተለማመዱት የምለው።

ሌላው ዐይተሽ ከሆነ መደበኛ ሚድያዎች ዩ ትዩብ አይጠቀሙም ነበር፤ አሁን ይጠቀሙበታል። ለመረጃ ፍጥነት ብቻ አይደለም። ከአቅምም አንጻር በቲቪ ከሚመጡ ማስታወቂያዎች በብዙ እጥፍ ዩትዩብ የሚከፍለው እየበዛ ነው። ስለዚህ ለራሳቸው በጀት፣ ለኢኮኖሚ ሲባል ወደዛ መምጣቱ የተሻለ ነው። አገርም ከዛ የምታገኘው ገንዘብ አለ፤ ያ ገቢ ቀላል አይደለም። እናም መንግሥት ጭራውን ይዞ ከሚያንፈራግጠው ዋናውን ጭንቅላት መያዝ ይችል ነበር።

መንግሥት ማሰብ ያለበት፣ ጤናማ የሆነውም ያልሆነውም እንዴት ተስተካክሎ ገቢው ለአገር ገቢ ይሆናል የሚለውን ነው። ፍቃድ አውጥተው፣ በሥርዓት ከገቢዎች እና ከመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ጋር መሥራት እንደሚቻል መንግሥት ቢያስብበት ነው የሚሻለው፤ እንጂ መጋጨት የለበትም።

አንድ የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር (ሥም መጥቀስ ባልፈልግም) ከኦንላይን ሚድያ ጋር የመሥራት ፍላጎት የለኝም ብለውኛል። የኮምዩኒኬሽን ሰው በዚህ ጊዜና በዚህ ዘመን፣ ቴክኖሎጂ በረቀቀበት ሰዓት እንደዛ ሲሉ፣ በጣም ነው ያዘንኩት። እኛ’ኮ ኢንቨስት አድርገን ነው ብዬ ተናግሬ ለማሳመን ሞክሬአለሁ። እንደዛ ያሉኝ ሰው ዛሬ ምንም ነገር ቢናገሩ ከእውቀት አንጻር ነው የሚናገሩት ብዬ ልናገር አልችልም፤ የተሰጣቸውን ወረቀት እያነበቡ ብቻ ነው የሚመስለኝ። ምክንያቱም በአሁን ሰዓት ከኦንላይን ሚድያ ጋር ካልሠሩ ከማን ጋር ሊሠሩ ነው?

ስለአባይ ግድብ ሲጮኽ የነበረው ማነው? ትዊተር ላይ ድምጽ ሲያሰማ የነበረው መደበኛ ሚድያው ነው? የሰሜኑ ጦርነት ላይ በዓለም አደባባይ ያሳጣን ኦንላይን ሚድያ ነው። እነ ቢቢሲ ወዴት ነው እየሄዱ ያሉት? ኦንላይን ሚድያ ነው።

እና ከመደበኛው ይልቅ ኦንላይን ሚድያ ኃይል አለው። ጋዜጠኝነት ኃይል አለው፤ አራተኛ መንግሥት ነው ብለናል። ያንን ከሆነ ይህኛው (ኦንላይን መሆኑ) የበለጠ ያጠናክረዋል ብዬ አምናለሁ። እና አሁን ላይ በወረቀት ተሸጦ አይሆንም፤ የህትመት ዋጋ እየናረ ነው። ጋዜጣ አዙሮም አይሆንም። ሁሉም ወደዚህ እንዲመጣ ነው ጥሪ የማስተላልፈውም። እና ቀስ በቀስ በተለይ የህትመት ሚድያዎች ወደዚህ መምጣትን መለማመድ አላባቸው።

ከባድም አይደለም። በእርግጥ የሚሰጡ ርዕሶች ጥሩ ነገር የለውም ብለን እንድናስብ ያደርጋል። ግን አንቺ እንደ ባለሞያ ኦንላይን ሚድያ ውስጥ ገብተሸ ብትሠሪ፣ ርዕስ ልትሰጪም ልትሠሪም የምትችው ከጋዜጠኝነትን ደንብና ሥርዓት አንጻር ነው። የእኛም ዩትዩብ (ሀርመኒ) ሠራተኞች ባለሞያዎች ናቸው። ገብተሽ ብታይው የተጋነነ ነገር የለውም። ባለሞያ በተቀጠረ ቁጥር የጋዜጠኝነት ሙያን ሥርዓት ይጠበቃል። ግን ማውራት የቻለን፣ አክቲቪስት ሁሉ ከቀጠርሽ፣ ካልጮኸ ተመልካች አያገኝም ብሎ መሥራት የጋዜጠኝነት ውበትን ይጠፋል።

በኦንላይን ሚድያ ላይ ሰዉ የሚፈልገውና የሚቀርብለት ይጣጣማል ትያለሽ? የሚቀርበው ሐሰት እና ግነት የበዛበትንስ ሰዉ ፈልጎ ነው የሚቀርብለት?

አገራችንም ሆነ ዓለማችን ባሉበት ሁኔታ አዳዲስ መረጃዎችን የማግኘት ፍላጎት አለ። ሰው ምንአልባት በተፈጥሮ መጥፎ ነገር ላይ ቶሎ ትኩረት ይሰጥ ይሆን? አላውቅም። ግን ይህ በሂደት ይቀረፋል፤ በማስተማር። ዋጋ ግን ያስከፍላል። ዓመት አልፎኛል፣ ግን ያለው ተከታይ (ሀርመኒ) ትንሽ ነው፤ እስከ አሁን ብዙ ገንዘብም ማመንጨት አልጀመረም።

እኔ ዩ ትዩበርና ኦንላይን ሚድያ ባለሞያ ነኝ። ከዐስር ዓመት በላይ በዚህ ቆይቻለሁ። አንድ ነገር ፈጥሬ ወይም የተገላቢጦሽ ሠርቼ በማጮኽ አንድ ሚሊዮን ተመልካች እንደማገኝ በደንብ አድርጌ አውቃለሁ። ሙያዬ ነው። አቅሙ፣ የቁሳቁስ ግብዓቱም ሠራተኛውም አለኝ። ግን ሕሊናም አለ፣ ሙያውን አከብራለሁ።

ማኅበረሰቡ በብዛት የሚያየው የሚጮኸውን ነው፤ ገንዘቡን ከፍሎ። ገንዘቡን ከፍሎ እርስ በእርስ የሚያጋጨውን፣ የራሱን አእምሮ የሚያቆሽሸውን፣ ሥነልቦናውን የሚሰብረውን ነገር እያዳመጠ ነው ያለው። ተስፋ የሚሰጡ ዩ ትዩብ ገጾች ተመልካች የላቸውም። በጣም ይጨንቃል። እኔ ሙያው ውስጥ ሆኜ ራሱ አንድ ዩ ትዩብ ስከፍት፣ ሕጻናትና እናቶች ተደፈሩ፣ መነኮሳት እንዲህ ሆኑ፣ ቤተእምነቶች እንዲያ ናቸው… ይሄ ብቻ ነው የሞላው። መረጃው መውጣቱ ጥሩ ነውኮ፣ ግን በዛ። እናት ልጇን እንዲህ አደረገች፣ አባት ልጁ ላይ እንዲያ አደረገ እየተባለ እንዴት ብለን ነው የቤተሰብን አንድነት የምንጠብቀው፤ በጣም በዛ።

እኔ ለመሥራት የተዘጋጀሁት ከዚህ በተቃራኒ ነው። ልጁን የሚደፍር አባት ካለ፤ ልጁን ለብቻው አሳድጎ፣ ለወግ ማዕረግ ያበቃ አባት አለ። የልጅ ነፍስ የምታጠፋ ሠራተኛ ዛሬ አለች አይደለ? ይህ ከስንት አንድ ነው የሆነ ነው። ግን ታማኝ ሆና እድሜ ልኳን ሰው ቤት እያገለገለች የኖረች አለች። ዩትዩብ ላይ መጥፎው ነው ጎልቶ የሚታየው። ይህ የማኅበረሰብ፣ የሥነልቦና ጤንነት ይፈጥራል ወይ?

ቁሳቁስና ገንዘብ ስላለ ብቻ እየተሠራ ነው። ይህን ሃይ የሚል መንግሥት ያስፈልጋል። ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲሠራ ያስፈልጋል። መረጃ አይውጣ ሳይሆን በዛ ነው። ሲበዛ ማስቆም ሳይሆን ጥሩ የሚሠሩትን በአንጻሩ ማበረታታት ነው።

ከዛ ውጪ ግን ሕዝብ መርጦ ነው የሚያየው፤ ተገዶ አይደለም። መደበኛ ሚድያ ላይ ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት ድረስ ዜና አቀርባለሁ ካለ፣ መጠበቅ እንጂ አማራጭ የለም። እዚህ (ኦንላይን) ላይ ግን መርጠሽ ጤናማውን ነገር እያየሽ መያዝ ይቻላል።

አንድ ዩ ትዩብ በሚሊዮን የሚቆጠር ተመልካች አለኝ የሚለው ስለታየ ነው። አቀረበ፣ ተመረጠ። አስገድዶ አይደለም። ስለዚህ ማኅበረሰቡ መርጦ እንዲያዳምጥ መሠራት አለበት። ሶሻል ሚድያው ጦርነትና ዘረኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል። ይህ ሁሉ ጥላቻ በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የተነሳ ነው። እንጂ ማርገብ ይቻል ነበር የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ማኅበረሰቡን ማስተማር፣ ማስገንዘብ አለብን።

ሌላው ትልቅ ክፍተት የሚፈጥረው መንግሥት ራሱ ነው። መረጃ ይደብቃል፣ በትክክል አይሰጥም። በተለይ ለኦንላይን ሚድያ። እንደውም ማኅበሩ አንዱ ዓላማው መንግሥት ለኦንላይን ሚድያ ባለሞያዎች መረጃ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ሄደን እኔ ከዩትዩብ ነው የመጣሁት ብል እና አንቺ ከአዲስ ማለዳ ነው የመጣሁት ብትይ፣ ለአንቺ መረጃ ይሰጣል፤ ለእኔ ግን አይሆንም።

አንደኛ ይፈራሉ። ይጋነን፣ ምንም ይበል መረጃ መሰጠት አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ጊዜ መረጃ የማይሰጥ ኃላፊ ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን ካለ ይጠየቃል ብለው ነበር። ግን እርሳቸውስ ይሰጣሉ ወይ? ከኦንላይን ሚድያ ጋር መሥራት አልፈልግም ያለ የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር እንዴት ነው መረጃስ የሚሰጠን?

ስንት የኦንላይን ሚድያ ነው ፓርላማ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወይም የመንግሥት መግለጫ ላይ እንዲካፈልና እንዲዘግብ የሚጠራው። እኛ ራሳችን ጎትጉተን በጉልበት የምንሄድባቸው ቦታዎች አሉ። ይህ የመረጃ አሰጣጥ ክፍተቱ በራሱ ለሐሰተኛ መረጃ መጮኽ ሚና አለው።

ማኅበረሰቡ መደበኛውን ሚድያ ያምነዋል? አያምንም። የሆነ ቦታ ልማት አለ ብሎ መደበኛው የዘገበው ላይ አንዱ ዩትዩበር እዛው ቦታ እርሻ ተቃጠለ ቢል፣ ሰው የሚያየው የሚያምነውም ተቃጠለ የተባለውን ነው። ግን ለመደበኛው ሚድያ የተሰጠው መረጃ ለኦንላይን ሚድያ ቢሰጥና በጋራ ቢሠሩ ምን ችግር አለ?

ጭራሽኮ መደበኛው ሚድያ ላይ የተሠራ ዜናን እኛ ወስደን ብንሠራ ለዩትዩብ ይከሱናል፤ ወሰዱብን ብለው። የመረጃ ምንጭ መሆን ሲገባቸው ጭራሽ እኛን ያሳግዱብናል። ታድያ ባለሥልጣኑ ካልሰጠን፣ መግለጫ ላይ ተገኝተን መረጃ ካልወሰድን መረጃ ከየት ይገኛል? ይህን መንግሥት ማስተካከል አለበት።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here