መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበጉራጌ የታሰሩ ሰዎች የጤና ክትትል ለማድረግ መከልከላቸው ተነገረ

በጉራጌ የታሰሩ ሰዎች የጤና ክትትል ለማድረግ መከልከላቸው ተነገረ

በጉራጌ ዞን በመንግሥት ኃይሎች የታሰሩ ወጣቶችና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የጤና ክትትል ለማድረግ መከልከላቸውን የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በመንግሥት ኃይሎች የታሰሩት የዞኑ ወጣቶችና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ‹‹ለ30 ዓመት ገደማ ሲያነሱት የቆየውን የክልል እንሁን ጥያቄን በተመለከተ›› መንግሥት ‹በክላስተር ተደራጁ› ያለውን መመሪያ ‹ተቃውማችኋል› ተብለው መሆኑ ተሰምቷል።

ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ አንድ የታሳሪ ቤተሰብ ወጣት ልጃቸው ሐምሌ 14/2014 እንደታሰረ ገልጸው፤ ‹‹ስለሚያመው የሕክምና ክትትል ያስፈልገዋል። ነገር ግን ለመታከም እንኳ ከእስር ቤት መውጣት ተከልክሏል። በእስር ቤቱም የጤና ክትትል የለም። ገብቼ ለማየትም ልዩ ኃይሎችና ሌሎች ጥበቃዎች እየከለከሉን ነው። ነፍስ ያጠፋ ሰው እንኳ ይህን ያህል ግፍ አይደረግበትም።›› ብለዋል።

ሌላኛው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ታሳሪዎች የምግብ አቅርቦት እንደማይደረግላቸው ጠቁመው፤ ከታሰሩት መካከል ሕክምና የሚከታተሉ ሰዎች ስለመኖራቸውም መስክረዋል። መረጃ አቀባዩ በወልቂጤ ከተማ ያሉ ታሳሪዎች ከሕክምና ክልከላ በተጨማሪ፤ ምግብ በማግኘት ረገድም ሳይከለከሉ እንዳልቀሩ ጠቁመዋል።

ነዋሪው እንደገለጹት፣ የሕክምና ክትትል ማድረግ የነበረባቸው እስረኛ እናቶችም ልጆቻቸውን እንዳይጠይቁ እየተከለከሉ ነው። ወላጆችም ከምግብና ሕክምና ክልከላው ጋር በተያያዘ መስከረም 5/2015 ለጉራጌ ዞን ምክር ቤት ቅሬታቸውን ለማቅረብ መሞከራቸው ተገልጿል። ይሁን እንጂ፣ በልዩ ኃይል ወከባና ክልከላ እየተፈጸመባቸው በመሆኑ አቤቱታቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ ፈቃድ የጠየቁ ጠበቃ በበኩላቸው፣ በጉራጌ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት፤ አዋጁ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ መሆኑን ነው።

‹‹እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ጉራጌ ዞን ላይ ያወጀውም ሆነ በደቡብ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 121/1/ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም›› ብለዋል።

በመሆኑም፣ የወረደው አዋጅ የታሰሩትን ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ወጣቶች መብት የሚጥስ ነው ብለዋል። ጠበቃው አክለውም፣ ‹‹ኮማንድ ፖስቱ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን የሰብዓዊ መብቶች የሚደፈጥጥ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ኮማንድ ፖስት ነው።›› ሲሉ ተችተዋል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 እንዲሁም በአንቀጽ 19 ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተያዘ ሰው የቀረበበት ክስ በዝርዝር ወዲያው መንገር ይገባል የሚለው ሕግ በመጣሱም የታሰሩ ሰዎች መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ተብሏል።

የሕግ ጠበቃው ወልቂጤ ከተማ ላይ የታሰሩት ወጣቶች መንግሥት ‹‹ስለአካባቢያችን ሰላም እንወያይ›› ብሎ የጠራቸው መሆናቸውን አስታውሰው፣ ለሰላም የተጠራን ወጣት እንደ ወንጀለኛ ማሰርም የሰዎችን መብት አስገድዶ መጣስ ነው ብለዋል።

መንግሥት ያቀረበው ‹በክላስተር ተደራጁ› የሚል መመሪያ ያልተዋጠላቸው የጉራጌ ማኅበረሰብ ክፍሎች የክልል እንሁን ጥያቄያቸውን ይዘው እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ መግለጻቸውን፣ እንዲሁም በክላስተር አንደራጅም በማለታቸው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ወጣቶች በመንግሥት አካላት እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆናቸውንም አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች