መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየሰሜን ወሎ መታወቂያ የያዙ ተፈናቃዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን ገለጹ

የሰሜን ወሎ መታወቂያ የያዙ ተፈናቃዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን ገለጹ

የሰሜን ወሎ መታወቂያ የያዙ ተፈናቃዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን አዲስ ማለዳ ከተፈናቃዮቹ አንደበት አረጋግጣለች።

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕውሓት ቡድን ባሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 በሰሜኑ በኩል ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት መቀስቀሱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በጦርነት ቀጠና ያሉ የሰሜን ወሎ ነዋሪዎች ሰላም ወዳለባቸው አጎራባች ከተሞች ተፈናቅለዋል።

ይሁን እንጂ ተፈናቃዩቹ የሰሜን ወሎን መታወቂያ በመያዛቸው ምክንያት ወደ መጡበት ቦታ እንዲመለሱ እየተደረጉ ከመሆኑም በላይ የእስር እና ድብደባ እንግልት እየተደረገባቸው በመሆኑ ቅሬታ አድሮባቸዋል።

አዲስ ማለዳ በኮምቦልቻ እና ደሴ ከተማ የሚገኙ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ድረስ የተጓዙ ተፈናቃዮችን ስታነጋግር፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሰሜን ወሎ መታወቂያ የያዙ ተፈናቃዮችን በማደን እያሰሩ ነው ብለዋል።

በኮምቦልቻ እና ደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች እንደገለጹት ከሆነ፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ‹‹የሰሜን ወሎን መታወቂያ ይዛችኋል›› ተብለው ለእስር ተዳርገው ነበር።

የኮምቦልቻ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ተፈጠረ የተባለውን ድርጊት ሐሰተኛና መሠረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል። የቆቦ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ድርጊቱ እውነት መሆኑን ገልጾ ይህን የሚፈጽሙ አካላት መታቀብ እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

‹‹እስርና ድብደባ እየተፈጸመብን ነው›› የሚሉት የሰሜን ወሎ ነዋሪዎች፤ ካሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 ጀምሮ መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ የምግብ ዋጋ ከተለመደው በላይ እንደናረና የመንግሥት ባለሥልጣናትም ወደ ቤታችሁ ተመለሱ እያሏቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ተፈናቃዮቹ በወልድያ፤ ሀራ፤ መርሳ፤ ኮምቦልቻ እንዲሁም በደሴ ከተማ ተበታትነው የሚገኙ ሲሆን፤ የሰሜን ወሎን መታወቂያ ይዘው እንደሆነ በማደን የመንግሥት ባለሥልጣናት እያሰሯቸው በመሆኑ ቅሬታውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ፤ ‹‹ከመጀመሪያው ጀምሮ በምንጓዝበት ወቅት የመከላከያ ሠራዊትም ጭምር በየመንገዱ ተመለሱ በማለት እያገደን ነበር።›› ሲሉ አስታውሰዋል።

ለአብነትም ‹‹በሃራ መገንጠያ መከላከያ ተፈናቃዮችን ወዴት ነው የምትሄዱት፣ እዛው ሆናችሁ ተዋጉ። ማን እንዲዋጋላችሁ ፈልጋችሁ ነው›› ብሎ አግዷቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

በደሴ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሰሜን ወሎ መታወቂያ ያለውን እያደኑ በመሆኑ በመደበቅ ተሳቀው ቀናትን እየገፉ መሆኑን በመጥቀስ ያሉበትን ኹኔታ አብራርተዋል። በተያያዘም ደብረ ብርሀን የደረሱ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ወደ ሰሜን ወሎ እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በኮምቦልቻ፤ ደሴ እንዲሁም በደብረ ብርሃን የሚገኙ የተፈናቃዮች ቤተሰቦችም ከባለሥልጣናቱ ጋር ክርክር ውስጥ ሳይገቡ እንዳልቀሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

 ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው፣ ለምን በመታወቂያችን ምክንያት እንታሰራለን ብለው ሲጠይቁ ‹‹ከእናንተ ጋር ተመሳስሎ የሕወሓት ሰላይ እየገባ ነው›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

‹‹የባለሥልጣናቱ ምላሽ ሙሉ ለሙሉም ባይሆን እውነት የመሆን ዕድል ይኖረዋል። ይሁን እንጂ የሰሜን ወሎን መታወቂያ የያዘ ኹሉ ግን ሰላይ ነው ብሎ ለማሰርና ማንገላታት የሚያደርስ መሆን የለበትም›› ባይ ናቸው።

በመሆኑም ሰላዮችን በተለያዩ ዘዴዎች መለየት እንጂ በሰበብ አስባቡ በተደጋጋሚ መፈናቀል የገጠመውን የማኅበረሰብ ክፍል ቢቻል ማገዝ እንጂ ማሳደድ እንዲቆም መንግሥት መሥራት አለበት ብለዋል ተፈናቃዮቹ።

ከራያ ቆቦ እንዲሁም ከኮምቦልቻ ከተማ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ለተነሳው ቅሬታ ምላሻቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ የተደረገው ሳይሳካ ቀርቷል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች