መነሻ ገጽዜናወቅታዊየአካባቢ ምርጫ እና የምርጫ ቦርድ ዝግጅት

የአካባቢ ምርጫ እና የምርጫ ቦርድ ዝግጅት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ደረጃዎች ያሏቸው ምርጫዎችን የማካሄድ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ከሚያካሂዳቸው ምርጫዎች መካከል አጠቃላይ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ሕዝብ ውሳኔ እና ማሟያ ምርጫ ተጠቃሽ ናቸው።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የአካባቢ ምርጫ ማለት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሚካሄድ የብሔረሰብ ዞን፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ መሆኑ ተደንግጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በኹለት ዙር አካሂዶ ማጠናቀቅ ባይችልም፣ አምስተኛውን ዙር አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው። ቦርዱ ለአካባቢ ምርጫ የሚያደርገው ዝግጅት ስለ አካባቢያዊ ምርጫ ጥናት አስጠንቶ ከባለድርሻ አካላትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማካሄድ ጀምሯል።

ቦርዱ የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ኹለት ጊዜ ውይይት ያካሄደ ሲሆን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

በውይይት መድረኮቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢ ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፉና በቂ ግንዛቤ ማግኘት እንዲችሉ ቦርዱ ያመቻቸው የምክክር መድረክ ላይ የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ አስካሁን የተደረጉ የአካባቢ ምርጫዎች ለይስሙላ እንጂ ትክክለኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የታየበት ምርጫ አንዳልነበር ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስተኛውን አካባቢያዊ ምርጫ ትርጉም ያለው ምርጫ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት እና ለአካባቢ ምርጫ ጉልህ ሚና ካላቸው የክልል መንግሥታት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ እንደሚሉት፣ በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ ባለድርሻ አካላት ያላቸው ግንዛቤና ፍላጎት የጎለበተ ነው ማለት ባይቻልም፣ የክልል መንግሥታት የሕግ ማዕቀፎቻቸውን አሻሽለውና በቂ ዝግጀት አድርገው የተሳካ አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ እንዲቻል ለክልሎች ጥያቄ ማስተላለፉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍና አፈጻጸም ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ  አካላት ጋር ባካሄደው ምክክር ላይ፣ ቀደም ብለው የተደረጉ ምርጫዎች የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ወይም ኢሕአዴግ የበላይነት የተስተዋለባቸው እንደነበሩ በጥናቱ ተመላክቷል። የአካባቢ ምርጫዎችን ለማካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ክልሎች ቢሮዎችን እንዲከፍትና ከክልል አስተዳደሮች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።

የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ በአካባቢ ምርጫ ላይ ያለው የግንዛቤ እጥረትና የአካባቢ ምርጫ መመሪያ አለመኖሩ እንደተግዳሮት ያስቀመጠው ቦርዱ፤ ያስጠናው ጥናት አካባቢያዊ ምርጫን ለማስፈጽም አመቺ መመሪያ ከቦርዱ እስከ ክልል መንግሥታት ማዘጋጀት እንደሚገባ ይጠቁማል።

የቀረበውን ጥናት መሠረት በማድረግ የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መውጣት ያለባቸው ሕጎች እንዲወጡ ቦርዱ እንደሚያደርግ፣ በቦርዱ የወጡ መመሪያዎችንም ለዚሁ እንዲረዳ እንደሚሻሻሉና ራሱን የቻለ መመሪያ በቦርዱ እንደሚዘጋጅ ብርቱካን ተናግረዋል። የፓርቲዎች አንዱ ትኩረት ምርጫ ማካሄድ እንዲቻል ምን በጎ አስተዋጽዖ እናበርክት በሚለው ላይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከቦርዱ ጋር በመተባበር በአምስተኛው አካባቢ ምርጫ ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሳተፉ እየሠራ መሆኑ ተሰምቷል። ምክር ቤቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢ ምርጫ ለመሳተፍ እንዲችሉ ከፓርቲዎች ጋር እየሠራ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ቦርዱ አምስተኛውን የአካባቢ ምርጫ በተያዘው ወይም በ2015 ለማካሄድ እቅድ እንዳለው ተናግረዋል። ቦርዱ ትክክለኛ ቀኑን ባይወስንም በዚህ የበጀት ዓመት ውስጥ በአብዛኞቹ ክልሎች የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ ማቀዱንና ስለሚካሄድበት ጊዜ ዝርዝር እቅድ እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም፣ እያንዳንዱ ክልልና አካባቢ የተለያየ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛት፣ የተለያየ የመንግሥት አወቃቀር ስላለው ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለስኬቱ ሲባል በሁሉም ቦታዎች የአካባቢ ምርጫን በተመሳሳይ ቀን የማድረግ እቅድ እንዳልያዘ ጠቁመዋል።

ስድስተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ገና ከውጥኑ ጀምሮ የተለያዩ እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደ አጠቃላይ ምርጫነቱ ሳይሆን፣ በተለያየ ጊዜ በዙር የሚደረግ ምርጫ ሆኗል። ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በኮቪድ 19 መካሄድ ባለበት ጊዜ አለመካሄዱን ተከትሎ፣ ለአንድ ዓመት ተራዝሞ ከሰኔ 14/2013 ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ እና መስከረም 20/2014 ከተካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ የቀጠለ ሦስተኛ ዙር ምርጫ ቢቀርም እስካሁን አልተካሄደም።

የአካባቢ ምርጫ ማካሄድ ሐሳብ ከምርጫ ቦርድ የመነጨው ገና አገራዊ ምርጫ ሳይጠናቀ ቢሆንም፣ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ከተቻለ ኹለቱንም ምርጫ በአንድ ላይ ካልተቻለ ለየብቻው ሊያደርግ እንደሚችል ሰብሳቢዋ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ምርጫውን ለማካሄድ የሕግ ማዕቀፎችና አስቻይ ሁኔታዎች በጥናት መለየታቸው አስፈላጊ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል። የአካባቢ ምርጫ ለረዥም ጊዜ ባለመካሄዱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ተሳታፊዎቹ በአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በአካባቢ ምርጫ ዜጎች በተለያየ ሁኔታ በአግባቡ መወከል የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቦርዱ የማስፈጸም አቅሙን እስከታች በማጠናከር እንደሚሠራም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የአገራዊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከምክክሩ ጎን ለጎን ምርጫ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል አራት የአካባቢ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ የመጨረሻው ከተካሄደ ከዘጠኝ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በዚህ ዓመት እንደሚደረግ ከሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ አስቀድሞ ጠቅላላ ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች ያልተደረጉ ምርጫዎች እንዲደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአካባቢ ምርጫው ከመደረጉ በፊት የሕዝብ እና ቤት ቆጠራው መካሄድ እንዳለበት አቋም መያዙንም ከዚህ በፊት አሳውቆ ነበር። 44 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይሳተፍበታል የሚል ግምት የተሰጠውን የአካባቢ ምርጫ ሥራ ለማስፈጸም ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት ጠይቆ፣ 212 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደተመደበለት የገለጸው ምርጫ ቦርድ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫ አናደርግም ብሏል።

ምርጫ ቦርድ ያስጠናው ጥናት እንደሚያስረዳው አካባቢ ምርጫ ለዴሞክራሲ መሠረት መሆኑንና በዋናነት ከልማትና ከአገልግሎት ቅልጥፍና ጋር የተያያዘ የአካባቢያዊ አስተዳደር ነው። ይሁን እንጂ አካባቢ ምርጫ ከአጠቃላይ ምርጫ ሰፊ እና ውስብስብ መሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል። የአካባቢ ምርጫ የክልል መንግሥታት የሥልጣን ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ሲሆን፣ በአንድ በኩል የዜጎችን የመወከል እድል የሚያሰፋ በሌላ ጎኑ ደግሞ ውድድርን የሚያመጣ የዴሞክራሲ ልምምድ ነው ተብሏል።

ይሁንና በእድገት ረገድ ወደ ኋላ የተጎተቱ እና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብሔርተኝነት በተካረረባቸው አገሮች ውስጥ ፓርቲዎች ከብሔራዊ አጀንዳዎች ይልቅ ጎሳን፣ ግለሰቦችንና ሌሎች መስፈርቶችን ወደፊት ይዘው የሚቀርቡ በመሆኑ የአካባቢ ምርጫ ለውድድር ሳቢነት የማይኖረውና ውጤቱም መሠረታዊ የሚባል የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጣ ነው ማለት እንደማይቻል ለውይይት በቀረበው ጥናት ተመላክቷል።

የብሔራዊ ምርጫ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ፤ የአካባቢ ምርጫ ከአጠቃላይ ምርጫ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ እስካሁን ከዚህ አንጻር የተሳካልን ሂደት አድርገናል ማለት አይቻልም ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች እና በክልል ምክር ቤቶች ሕዝብን ወክለው የሚገቡ ተመራጭ ሰዎች ከአብዛኛው ሕዝብ የእለት ተእለት የሥራ እና የግንኙነት መስመር የራቁ ሲሆኑ፣ በአካባቢ ምርጫ የሚመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ግን ከይዘትም ሆነ በዓይነት በወካይና ተወካዩ መካከል ያለውን ርቀት የሚያጠብ፣  አገልግሎትን በተሻለ ቅርበት ለማግኘትና ቁጥጥርም ለማድረግ የተሻለ ምቹነት የሚፈጥር ሥርዓት ነው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች አከናውኖ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ምርጫ ባልተካሄደበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ 17 ምርጫ ክልሎች (በአብዛኛው የክልል ምክር ቤት) ምርጫ አልተካሄደም። ቦርዱ በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ባለው የጸጥታ ችግር ምርጫ ማካሄድ አለመቻሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ለታኅሳስ 21/2014 እቅድ ይዞ ሳይሳካለት ቀርቷል።

በመጀመሪያው ዙር እና በኹለተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ፣ ለሦስተኛውም ዙር ምርጫ የተሸጋገሩ አካባቢዎች እስካሁን ምርጫ ሳይደረግባቸው አጠቃላይ ምርጫ ከተካሄደ አንድ ዓመት አልፎታል። በሦስተኛ ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ክልሎች ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአማራ ክልል 10፣ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ሲሆኑ፣ በክልል ደረጃ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን በኦሮሚያ ክልል ሰባት እና አማራ ክልል ዘጠኝ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት በመጀመሪያውም ይሁን በኹለተኛው ዙር ምርጫ ያልተደረገባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ማጀቴ (ማኮይ) የምርጫ ክልል፣ አርጎባ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ሸዋሮቢት የምርጫ ክልል፣ ኤፌሶን የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ አርማጭሆ የምርጫ ክልል እና ድል ይብዛ የምርጫ ክልል ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰሜን ሸዋ ዞን ችግር የተከሰተባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ባለመካሄዱ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አሁንም በሦስተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ አካባቢዎች አሉ። እነዚህም ቤጊ የምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ አያና የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ ገሊላ የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ አሊቦ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ)፣ ጊዳም የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች