መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብየተጓዥ ማስታወሻየሳምንት ቆይታ በኤምሬቷ ወርቅ ከተማ - ዱባይ

የሳምንት ቆይታ በኤምሬቷ ወርቅ ከተማ – ዱባይ

በውበቷ ብዙዎች የሚማልሉላት ከተማ ናት፤ ዱባይ። በንግድ ሥራ ውስጥ የሚገኙ በርካቶችም እንደ ጓዳቸው ሄድ መለስ እያሉ ለሽያጭ የሚያቀርቧቸውን እቃዎች ይሸምቱባታል። የገንዘብ አቅም ያላቸው ሆነው ለመዝናናትና እረፍት ለማድረግ የሚመርጧትም ጥቂት አይደሉም። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ወደዚህች ከተማ አቅንቶ ነበር። በቆይታው የታዘበውንም እንደሚከተለው አጋርቷል።

መንደርደሪያ

የግማሽ ክፍለ ዘመን ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረችውና በመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ (ፐርሺያ) ባህረ ሰላጤን ታክካ የምትገኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬት 83 ሺሕ 600 ሜትር ስኩየር የቆዳ ስፋት አላት። በያዝነው የፈረንጆች ዓመትም የሕዝብ ቁጥሯ 10.08 ሚሊዮን እንደደረሰ ተገምቷል። የኤምሬትን የቆዳ ስፋት ትንሽነት ከኢትዮጵያ አንጻር ለማስቀመጥ አፋር ክልል ያለው የቆዳ ይዞታ ላይ 10 ሺሕ ሜትር ስኩየር መጨመር ብቻ ይበቃል። ይሁንና እያስመዘገበች በምትገኘው ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ምክንያት ‹‹የባህረ ሰላጤው ነብር›› የሚል ቅጽል ሥም ወጥቶላታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት እንደ ጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር በታኅሣሥ 2 ቀን 1971 በስድስት ኤምሬቶች ማለትም አቡ ዳቢ፣ ዱባይ፣ ሻርጃህ፣ አጅማን፣ ኡም አል ቁሚን እና ፉጃኤርህ በፌዴሬሽን መልክ የተመሠረተች ናት። ከኹለት ወራት በኋላም ራስ አል ኬኢማህ ስድስቱን በመቀላቀል የፌዴሬሽኑ ሰባተኛ አካል ሆኗል።

የመጀመሪያው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በመሆን ያገለገሉትና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ፌዴሬሽንን በመመሥረት ቁልፍ ሚና የተጫወቱት፣ ብሎም የአገሪቱ መሥራች አባት በመባል የሚታወቁት ሼኽ ዚያድ ቢን ሱልጣን አል ነሀያን ናቸው። በወቅቱ የአቡ ዳቢ ገዢ የነበሩት ሼክ ዚያድ* ሰባቱን ኤምሬቶች በማሰባሰብ አንድ አገር ሆነው በጋራ እንዲቆሙ ከማድረግም ባሻገር እስከ ኅልፈተ ሕይወታቸው 2004 ድረስ የአገሪቱም ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።

ሼኽ ዚያድን ተክተው እስካሁን ርዕሰ ብሔርና የአቡ ዳቢ ገዢ የሆኑት ሼኽ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሀያን ሲሆኑ፣ ምክትላቸው ሼኽ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም በተደራቢነት ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የዱባይ ገዢ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በዱባይ ከተማ ሕንጻዎችና የአደባባይ ማስታወቂያዎች ላይ የገዢውን ትልልቅ ምስሎች አለመመልከት አይቻልም፤ በከተማው ላይ በብዛት ይታያሉና።

ዱባይ – የወርቅ ከተማ

ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ የአየር ማረፊያ የፍተሻ መስፈርቱን አልፌ የአገራችን የምንጊዜም ኩራት በሆነውና ሰንደቋን በሰማይ ላይ ከፍ አድርጎ በሚያውለበልበው አየር መንገዳችን ET-612 አውሮፕላን ላይ የተሳፈርኩት ከበረራው በግምት ሠላሳ ደቂቃ በፊት ነው። ምሽት 4፡50 ላይ የዱባዩ በረራ ተጀመረ። በወሬ እንዲሁም በተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች የማውቃትን ዱባይ በአካል፣ በዐይኔ በብረቱ ለማየት ጓጉቻለሁ። በእርግጥም ጉጉቴ ሌሎች የሰሜን አሜሪካ ወይም የአውሮፓ ከተሞችን ከማየት ጉጉት ያልተናነሰ ምናልባት የበለጠ ይሆናል።

በመነሻዬ እና በመዳረሻዬ መካከል ያለውን የ6 ሺሕ 178.2 ኪሎ ሜትር ርቀት አራት ሰዓት ከ15 ደቂቃ በፈጀ የቀጥታ በረራ በማገባደድ በዓለማችን ትልቁ፣ ዘመናዊው እና ፋታ አልባው የዱባይ ዓለማቀፍ የአየር ማረፊያ (DXB) ደረስኩ።

የአየር ማረፊያውን ስፋት አንዱ ማሳያ ከአውሮፕላን እንደወረድን ዕቃችንን ለመቀበልና ተፈላጊውን የበረራ መስፈርት ማሟላታችንን ለማረጋገጥና ወደ ወርቋ ከተማ ለመግባት የሚያስችለንን የይለፍ ፈቃድ ለማግኘት ምናልባትም በኪሎ ሜትር የሚሰላ ርዝመት ያለው ርቀት በሰው አልባ ሜትሮ መጓዛችን ነው። የተጓዝኩት ወደ አየር ማረፊያው አንድ አካል መሆኑን ልብ ይሏል። ብዙም ሳልጉላላ የይለፍ ፈቃድ አገኘሁ። እቃዬን ሸክፌ ጉዞዬን ወደ ተናፋቂዋ ከተማ አደረኩ።

ከአየር ማረፊያው ገና ከመውጣቴ የሙቀት ወላፈን መላ ሰውነቴን ገረፈው። ለካስ እስከሁን ድረስ የነበርኩበትና የተላለፍኩት ሙሉ ለሙሉ የአየር ማቀዝቀዣ በተገጠመላቸው አዳራሾችና ኮሪደሮች ውስጥ መሆኑን ተገነዘብኩ። በኋላም በቆይታዬ እንደተረዳሁት መኪናዎችና ሜትሮዎች፣ የሆቴል ክፍሎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ መደብሮች፣ ፌርማታዎች ምን አለፋችሁ ሁሉም ማቀዝቀዣ ተገጥሞላቸዋል። በዚህም አየር ማቀዝቀዣዎቹ የዱባይ እስትንፋስ መሆናቸውን ተረድቻለሁ።

በዱባይ ከተማ የደረስኩት ሌሊት ላይ ቢሆንም በመብራት የተንቆጠቆጡት መንገዶችና ሕንጻዎች ቀን ይሁን ሌሊት ቢያምታቱ አይደንቅም። በቀናት ቆይታዬ ምሽት ላይ ዱባይ የብርሃን ከተማ መሆኗን ጭምር ተመልክቻለሁ። በዱባይ የሚገኙት በሥነ ሕንጻ ውበታቸው፣ በአደራደራቸው እንዲሁም በማይረብሽ ውብ ኅብረ ቀለማቸው በብዛትና ጥራት ችምችም ያሉት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች በቀን ውበታቸው የደበዘዙ ቢመስሉ እንኳን አምረው፣ ደምቀውና ተብረቅርቀው በምሽት ይታያሉ፤ ልብም ያማልላሉ።

ዱባይ ለቅንጣት የጊዜ ልኬት እንኳን መብራት ጠፍቶባት እንደማያውቅ ያናገርኳቸው ሰዎች አጫውተውኛል። የመብራት ጉዳይ ከተነሳ ዘንድ* በአዲስ አበባችን መብራት በቀን መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን ለቀናት ላይመጣ ይችላል። ይህ የዕለት ተዕለት የሕይወታችን አንዱ ልምምድ ስለሆነ ብዙዎቻችንን አይገርመንም። ይልቅስ ለቀናት መብራት ካልተቆራረጠ እንዴት ይሄን ያክል ጊዜ ሳይጠፋ ቀረ የሚል ግርምት አዘል ጥያቄ ሰርክ ማንሳታችን የተለመደ ነው።

መብራት ጠፍቶ ሲመጣ የሚሰማው የድል አድራጊነት ጩኸት፣ ፉጨትና ጭብጨባ የተለመደ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕግ የተቀበልነው ሆኗል። ምናልባት ተስፋ የምናደርገው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት በሚጀምርበት ጊዜ (መቼ የሚለው ጥያቄዬ ተይዞልኝ) የአሁኑን የኃይል መቆራረጥ እንደ ተረት ተረት የምናወራበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል ብሎ ተስፋ ማድረግ የሚከፋ አይመስለኝም።

በቆይታዬ ወቅት በአማካይ የዱባይ የአየር ሙቀት 99 ዲግሪ ፋራናይት ወይም 37.22 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሲሆን፣ ለንጽጽር ይረዳን ዘንድ በተመሳሳይ ቀናት አዲስ አበባ 61 ዲግሪ ፋራናይት ወይም 16.11 ዲግሪ ሴሊሺየስ የአየር ሙቀት ነበራት። ልዩነቱ ግልጽ ስለሆነ ማብራሪያ የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም።

እጅግ ካስገረሙኝ የዱባይ የቀን ተቀን እንቅስቃሴዎች መካከል የከተማ ጽዳት አንዱ ሲሆን መቼ እና እንዴት ቢያጸዱት ነው እንዲህ ሊሆን የቻለው ያስብላል። ምንም ዓይነት ቆሻሻ መሬት ላይ ተጥሎ አይታይም። እልም ባለው በረሃ ላይ የተገነባችው ዱባይ ከተፈጥሮ ጋርም ግብ ግብ የያዘችም ትመስላለች።

- ይከተሉን -Social Media

በየመንገዱ ዳር በሕንጻዎች መካከል ብቻ ማንኛውንም አካባቢ አረንጓዴ ለማድረግ ሳር፣ ቁጥቋጦዎች እና ዛፍ ተተክለዋል። ተክሎቹ የዝናብ ውሃ ቢናፍቃቸውም መሬት ለመሬት በተዘረጋ ጥቁር ጎማ አማካኝነት ውሃ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዲደርሳቸው ይደረጋል።

የሰፋፊዎቹ የዱባይ አውራ ጎዳናዎች ላይ ቅንጡ የሆኑትን ሮልስ ሮይስ ፋንቶም፣ ላምበርጊኒ፣ አውዲ፣ ፌራሪ፣ ቢኤምደብሊው፣ ፖርሽ፣ ኤስዩቪ፣ ሬንጅ ሮቨር፣ ሜርቼዲስ ቤንዝ፣ ወዘተ መኪናዎች መመልከት ብርቅ አይደለም። በዱባይ ጎዳናዎች ላይ አዲስ አበባን ያጨናነቋትን አሮጌ እና አሮጌ ስሪት መኪናዎችን ለማየት ይናፍቅዎታል። አሮጌ መኪና አላየሁምና!

በከተማው ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ብዙ አማራጮች ያሉ ሲሆን በዓይነት፣ በጥራትና በዋጋ የተለያዩ ናቸው። ሜትር ታክሲዎች፣ አውቶብሶች እና በየሦስት ደቂቃ ልዩነት የሚመጣው ሜትሮ ፈጣን ባቡር ዋናዎቹ መጓጓዣዎች ሲሆኑ፣ ከከተማ አውቶብስ በስተቀር ሌሎቹን አማራጮች ተጠቅሜያለው፤ ተመችተውኛል!

ሌላው የገረመኝ በመንገድ ላይ የመኪና እንቅስቃሴ ወቅት አንድም የትራፊክ ወይም ጸጥታ አስከባሪ ፖሊስ አለማየቴ ነው። በወቅቱ ጠይቄ እንደተረዳሁትና በኋላም ላይ በተለያዩ ዘገባዎች እንዳረጋገጥኩት ‘ፖሊስ የሌለበት ፖሊስ’ (Police without policemen) የሚባለውን ፕሮጀከት የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በመንገዶችና በየመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያና አጥሮች ላይ የካሜራ መረብን ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የሚያገናኝ ቋት በመፍጠር ተግባራዊ ከተደረገ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይህ ማለት ማንኛውንም የጎዳና ላይ የመኪና ሆነ በየመንደሩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለኻያ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። አንድ ተሽከርካሪ ጥፋተኛ ቢሆን በቴክኖሎጂ እገዛ ቅጣቱ ወዲያውኑ በእጁ ሞባይል ላይ ይደርሰዋል። በመንገድ ላይ የመኪና አደጋ ቢደርስ ለፖሊስ በስልክ ማሳወቅና ተጎጂዎችን ለመርዳት ወደ አንቡላስ መደወል ግዴታ መሆኑንም ተረድቻለሁ። በእርግጥ በዱባይ የትራፊክ አደጋ ለሞት ከሚዳርጉ ቀዳሚ ምክንያቶች መካከል የሚመደብ መሆኑ አንዳንድ የቁጥር መረጃዎች ያመላክታሉ።

ከወንጀል ጋር በተያያዘ ከሌሎች አቻ የዓለማችን ኢንዱስትሪ ከተሞች ጋር ስትነጻጸር ዱባይ ዝቅተኛ ወንጀል የሚፈጸምባት ከተማ ነች። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለዱባይ መንገደኞች ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ በአጠቃላይ ወንጀል በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ችግር እንዳልሆነ ጠቅሷል።

በዱባይ 23 ዓመታትን የኖረውና ዱባይን የእጅ መዳፌን ያህል አውቃታለሁ የሚለው ግብጻዊው አስጎብኚ በዱባይ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ቢጠፋ 90 በመቶ እንደሚገኝ ከገጠመኞቹ በመነሳት አስረድቶናል። ዱባይ ከቀማኞች፣ ከማጅራት መቺዎችና ከኪስ አውላቂዎች የጸዳች ከተማ ነች ሲል በልበ ሙሉነት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ዱባይ ውስጥ ከሚኖሩት የውጪ አገር ዜጎች መካከል ወደ 67 በመቶ የሚጠጉት የዘር ሐረጋቸው ከደቡብ እስያ ይመዘዛል። ከሕዝቡ 25 በመቶ የኢራን ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ 8 በመቶ ደግሞ ምዕራባውያን መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

- ይከተሉን -Social Media

ዱባይ ተግዳሮቷን ወደ መልካም አጋጣሚ የለወጠች ውብ ከተማ ስትሆን ለመኖር መሥራት ግድ ይላል። አንዳንዶች ዱባይ የሚለው ቃል ከኹለት የእንግሊዘኛ ቃላት ጋር በማጣመር ማንነቷን ይገልጻል ይላሉ፤ ቃላቶቹም ዱ (do) እና ባይ (buy) ሲሆኑ ካልሠሩባትና ካልገዙባት ዱባይ ከባድ የኑሮ ዳገት ናት የሚል አንድምታ ይሰጣል።

የዱባይ ከተማን የወፍ በረር ቅኝት እንደዚህ ካስቃኘሁ በተከታይ ጽሑፌ ደግሞ ዱባይ ስለምትታወቅበት የቱሪዝም መስህብ፣ ስለትላልቅ የንግድ ሕንጻዎች፣ ስለወርቅ ሱቆች፣ ሻርጃህ ስለሚገኘው በአሸዋ ተራራ ላይ ስለሚደረገው የበረሃ ላይ የመኪና አስደናቂ ‹ግልቢያ›፣ ስለፓልም ጁሜራህ ሰው ሠራሽ ደሴት፣ ኢትዮጵያውያን በብዛት ስለሚገኙበት ዊንፒ ስለተባለው የገበያ ስፍራና የአኗኗር ዘያቸው እንዲሁም አንዲት ስኬታማ ስለሆነች ኢትዮጵያዊት ሴት በአጭሩ የማቀርብ ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች