መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብነብይ መኮንን በአገሩ ሲከበር

ነብይ መኮንን በአገሩ ሲከበር

እንዲህ ሆነ፣ እስር ቤት ውስጥ ነው። በዚህ እስር ቤት ውስጥ ለወትሮው ከወረቀት እና ከመጻፊያ ብዕር ተለይቶ የማያውቅ ሰው ገብቷል። መቼ ከአካል እስር እወጣለሁ ሳይሆን መች እጽፋለሁ፣ መች በሐሳቤ የሚመላለሰውን በብዕር ወደ ወረቀት አጋባለሁ የሚለው ጭነቁ ሳይሆን አልቀረም!

መላ ፈለገ። የሐሳቡን ጥያቄ ለመመለስ ምንም ነገር ላይ ከመጻፍ ወደኋላ የሚል ዓይነት አይደለም። አወጣ አወረደ። እናም በቅርቡ የታየውና ያገኘው የሲጋራ ወረቀት ነው። ብቸኛው አማራጭም ብዕሩን በዛ ላይ ማሳረፍ ነበር። አደረገው።

እናም በሐሳቡ የሚመላለሰውን ከማስፈር ባሻገር በጊዜው በእጁ የነበረውን ‹Gone with the Wind› የተሰኘውን መጽሐፍ ይተረጉም ጀመር። እነዛ ቁርጥራጭ የሲጋራ ወረቀቶችም የመጻፍ መሻቱን ያስታገሱ ዘንድ ባለውለታው ሆኑ። ውለታ የዋሉት ለእርሱ ብቻ አይደለም። በኋላ ሁሉም አልፎ ‹ነገም ሌላ ቀን ነው› የሚለው መጽሐፍ ለአንባቢዎችም እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል።

የዚህ ታሪክ ባለቤትና 10 ዓመታትን በእስር ላይ ሆኖ ይህን የትርጉም መጽሐፍ ለንባብ ያቀረበው ደራሲ፣ ተርጓሚና አርታኢ እንዲሁም ጋዜጠኛው ነብይ መኮንን ነው።

በነገራችን ላይ ‹Gone with the Wind› የተሰኘው መጽሐፍ በፈረንጆቹ 1936 ማርጋሬት ሚሼል በተባለች አሜሪካዊት ጋዜጠኛ የተጻፈ ነው። ጋዜጠኛዋ በአንድ አጋጣሚ እግሯ ላይ ሕመም ገጥሟት አልጋ ላይ ውላ ነበር። በዚህን ሰሞን ነበር በአገሯ አሜሪካ ይለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ በገጸ ባህርያት መልክ ውስጥ ስላ መጻፍ የጀመረችው። በመጽሐፏም የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ምን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዳደቀቀው ጠቅሳና ተያያዥ ነጥቦችን አንስታ የጦርነትን አስከፊ ገፅታ አሳይታለች።

ይህን መጽሐፍ ማዘጋጀት ዐስር ዓመታት የወሰደ ሲሆን፣ ለንባብ ከቀረበ በኋላ በወራት ውስጥ በሚሊዮን ቀጂዎች ተሸጧል። በርካታ ታላላቅ ሽልማትን ለደራሲዋ ያስገኘም ሲሆን፣ ወደ 27 ቋንቋዎች ተተርጉሟል።  ቆይቶም ርዕሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ፊልም ተሠርቶበታል።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፣ ነብይ መኮንን በእስር ቤት ሳለ በዛ መልክ ተርጉሞ ያዘጋጀው ይኸው መጽሐፍ በ1980ዎቹ ለንባብ ቀረበ። የጊዜው ሳንሱር ታድያ ርህራሄ ያለው አልነበረም። የተርጓሚውን ድካም ከመጤፍ ሳይቆጥር ቆራርጦ አቀረበው። ከዛ ባይብስም ቀጥሎ ደግሞ መጽሐፉ <ከነበረው ስርዓት ጋር የሚስማማ ስላይደለ> ተብሎ ዳግም እንዳይታተም፣ በመጀመሪያ እትም ብቻ እንዲቆይ ተደረገ።

ይህ ከሆነ አሁን 32 ዓመታት ገደማ አልፈዋል። ዛሬም ሌላ ቀን ሆኗል። ‹ነገም ሌላ ቀን ነው› የተሰኘው መጽሐፍም ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ለኹለተኛ ጊዜ ታትሞ ባሳለፍነው ነሐሴ 30/2014 በድጋሚ ለንባብ በቅቷል።

ስለ ነብይ መኮንን

ነብይ መኮንን በያዛቸው ሙያዎች ሁሉ ስኬታማ መሆኑን ከሥራዎቹ በተጓዳኝ ያለማንገራገር ብዙዎች የሚመሰክሩለት ምስጉን ሰው ነው። ታድያ እንዳልነው ባሳለፍነው ነሐሴ 30/2014 በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዘጋጅነት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ሦስት የትርጉም ሥራው የሆኑ መጻሕፍት (የመጨረሻው ንግግር፣ ነገም ሌላ ቀን ነው እና የእኛ ሰው በአሜሪካ) ተመርቀዋል። በመድረኩም አንጋፋ እንዲሁም ወጣት ገጣሚዎች፣ ደራሲዎች፣ ጋዜጠኞችና የነብይ መኮንን ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎቹ ታድመው ነበር።

ከእነርሱም መካከል የተወሰኑት ከራሳቸው እንዲሁም ከነብይ መጻሕፍት የተቀነጨቡ ሥራዎችን አቅርበዋል። እንዲሁም ከነብይ ጋር ስላላቸው ትውውቅና ቀረቤት ብሎም በጓደኝነትና ወዳጅነት ስላለው መልካምነትና በሙያውም ስላካበተው ብቃት ምስክርነት የሰጡ ነበሩ። ከእነዚህም መካከል ተፈሪ ዓለሙ፣ በኃይሉ ገ/መድኅን፣ ጌትነት እንየው፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ተስፋሁን (ፍራሽ አዳሽ) እና ምልዕቲ ኪሮስ ይገኙበታል።

ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ ስለ ነብይ ሲናግር <<ድንቅ መምህር ነው።>> በማለት ጀመረ። ጋሽ ነብይ አባቶቻችን በሕይወት ለሌሉ እንደአባት የሚሆንና የሆነን መካሪያችን ነው ሲልም ገለጸው።

አያይዞም ነብይ ብቃቱና እውቀቱ ሳይገድበው ከትውልዱ ዝቅ ብሎ በማስተማር፣ ምክር በመስጠት፣ በማክበር ውስጥ ብዙዎችን በብዙ ያስተማረ መምህርና ወዳጅ ነው ሲልም ተናገረ። <<እንድናነብና እንድንጽፍ የሚያተጋን ሰው ነው። ጋሽ ነብይን በወዳጅነት ማግኘት ትልቅ እድል ነው።>> በማለትም ስሜቱን አጋርቷል።

በተመሳሳይ ገጣሚዎቹ ሰሎሞን ሳህለ እና ምልዕቲ ኪሮስም ነብይ ወግ አዋቂና ጨዋታው የማይጠገብ፣ ወጣት የሥነጽሑፍ ሰዎችን በማገዝ በኩል ቀዳሚ ተጠቃሸ የሆነ ሰው ነው ሲሉ ፍቅር፣ አክብሮትና አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በኃይሉ ገብረመድኅንም ገጠመኞችን መነሻ አድርጎ ከነብይ ጋር ስላላቸው ትውውቅና ወዳጅነት፣ ሳቅና ጨዋታን አክሎ ለታዳምያኑ አውስቷል።

በተለይም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሚወጣውን ርዕሰ አንቀጽ በማውሳት፣ ተረቶችን፣ ትረኮችን፣ ሀይማኖታዊ ታሪኮችና ምክሮችን መነሻ አድርጎ ለዘመናት የማይሰለቹ ጽሑፎችን ሲያቀርብ መቆየቱን አንስቷል። በዚህም ለነብይ ያለውን አድናቆት ገልጿል።

ነብይ መኮንን ለአገር የሚሳሳና አብዝቶ የሚጨነቅ መሆኑን ማሳያም በርካታ ሥራዎች አሉት። ይህንንም በሚመለከት ሐያሲ እና ፀሐፊ አብደላ ዕዝራ (ነፍስ ኄር) ‹የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበው ስዉር-ስፌት› በሚል በጻፈው ሐተታ ላይ ‹በጥሞና ስለ አራት ግጥሞች› ሲል ባሰፈረው አንድ ጽሑፍ ያነሳል። በዚህም ላይ አያሌ ገጣምያን ስለ አገር በተለያየ መንገድ የጻፉ መሆናቸውን አውስቶ፣ ነቢይ መኮንን ከአማርኛ ገጣሚያን የሚለየው አንድ ወይም ሁለት ሳይሆን፣ በአገር ጉዳይ ከሃያ ግጥሞች በላይ መቀኘቱ ነዉ›› ይላል።

- ይከተሉን -Social Media

ወደ መጽሐፍ ምርቃቱ ስንመለስ፣ የመሰናዶው አዘጋጅ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ በዝግጅቱ ላይ ከነብይ ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን፣ አጠር ያለ ንግግርም አድርገዋል። በዚህም <<ጋሽ ነብይ ከጸሐፊ በላይ የቤተ መጻሕፍቱ አጋር ነው።>> ያሉት ይኩኖአምላክ፣ እሱ ብቻውን በዋና አዘጋጅነት የተሳተፈባቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች የቤተ መጻሕፍቱን ሰፊ ክፍል የሚይዙ መሆኑን ጠቅሰዋል። ድርጅቱም የመጽሐፍ ምርቃቱ ላይ የተሳተፈው በዚህ የተነሳ መሆኑን አንስተው፣ ለነብይ አክብሮትና ምስጋናን ቸረዋል።

በዛው መድረክም ነብይ በበኩሉ ስጦታ ያበረከተ ሲሆን፣ ይህም በአንድ ኢጣሊያዊ ሰዓሊ በልዩ መልክ ተቀርጾ የተሠራ እና ልክ እንደ <ብሬል> ጽሑፍ በእጅ ሲዳሰስ ፊደሎቹ የሚነበቡ “ዋ” የተሰኘ የግጥም ስብስብ ያረፈበት ነው። ይህን አንድም የእጅ ጥበብ ውጤት የሆነን ሥራ ለሌሎች ሁለት ተቋማትም የሰጠ መሆኑን የጠቀሰው ነብይ፣ <<ይህ (የግጥም ስብስቡ) በወመዘክር/በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሲቀመጥ እኔ እዛ እንዳለሁ እቆጥረዋለሁ። እንዲሁም አሁን ምንነቱና ዋጋው ለሚገባው እንደሰጠሁት አምናለሁ> ሲል ስጦታውን ለአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ለይኩኖአምላክ መዝገቡ በስጦታ መልክ አስረክቧል።

ነብይ መኮንን በእርግጥም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ፣ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በኩራትና በክብር የሚቀመጡ ድንቅ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን ማበርከት የቻለ ሰው ነው። መለስ ብለን ሥራዎቹን ስናወሳ፣ የግጥም ስብስብ መጻሕፍቱን እናገኛለን። እነዚህም ስውር ስፌት (ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት) እንዲሁም ነፍሰ ጡር ግጥሞች የተሰኙትን መጥቀስ ይቻላል።

<ነገም ሌላ ቀን ነው> ከተሰኘው የትርጉም ሥራው ባሻገር በ1994 ለንባብ የበቃው <የእኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘው የጉዞ ማስታወሻ እንዲሁም በ2014 መጀመሪያ አካባቢ ለንባብ የቀረበው <የመጨረሻው ንግግር> (The Last Lecture) የተሰኘ የትርጉም ሥራ የሆነ መጽሐፍም አለው። በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ግን እነዚህ መጽሐፍት እስክ አሁን ድረስ ከአንድ ጊዜ በላይ ሳይታተሙ የቆዩ ናቸው።

ከዚህም ባሻገር ነብይ የቴአትር የጽሑፍ ሥራዎች አሉት። ከእነዚህም ጁሊየስ ቄሳር፣ ናትናኤል ጠቢቡ እና ማደጎ የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው። በዚህ አያበቃም፣ ነብይ የሙዚቃ ግጥም ሥራዎችም አሉት።

አንጋፋው የሥነ ጽሑፍ ሰው ነብይ መኮንን፣ <ነብይ በአገሩ ተከበረ> ተብሎ መጽሐፉን ከመመረቅ ጎን ለጎን የቀደመውም ሆነ አሁን ያለው የሥነ ጽሑፍ ቤተሰብ ለነብይ ያለው አክብሮትና ፍቅር የተገልጸበት ነበር። በዝግጅቱም የነብይ ሁሉም ሥራዎች በሚባል ደርጃ ለአንባብያን የቀረቡ ሲሆን፣ ሦስቱ የተመረቁት መጻሕፍትም በአንድ ላይ ተዳብለው ቀርበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች