መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየመንግሥት ቀሪ የቤት ሥራዎች

የመንግሥት ቀሪ የቤት ሥራዎች

ኢትዮጵያ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የቆየችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ጨርሶ ሳይቀረፍ ነው አዲሱ ዓመት 2015 የገባው። ይህ ዓመት በአዲስ መልክ ሊጀመሩ ከሚችሉ ሥራዎች ባሻገር ያደሩና የከረሙ ቀሪ የቤት ሥራዎች በብዛት የቆየለት ነው። ይልቁንም ከሕግ እና ፖለቲካ አንጻር እንዲሁም የምጣኔ ሀብትን የተመለከቱ አገራዊ ጉዳዮች መፍትሄ ፍለጋ ሲንከባለሉ ቆይተው አዲሱን ዓመት ተቀላቅለዋል።

እነዚህም ሁሉ የየራሳቸው ባለድርሻ ያላቸው መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ከምንም እና ከማንም በላይ ግን የመንግሥትን ውሳኔ፣ አካሄድና ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸው አያጠራጥርም። የየዘርፉ ባለሞያዎችም መንግሥት ከቀደመ አካሄዱና ከነባር ስህተቱ ታርሞ አሁን ላይ ሊኖረው የሚገባው አካሄድ ላይ ምክረ ሐሳብ እየሰጡ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው ኢዮብ ትኩዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ቀደሙ ክስተቶችን በማውሳትና ባለሞያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ

መንግሥት ሁሌም ከሕዝብ ጋር በማበር በርካታ ተግባራትን የማከናወን የቤት ሥራ እንዳለበት ይታወቃል። ይልቁንም አሮጌው ተሸኝቶ አዲስ ዓመት በተተካ ቁጥር ያለፈውን መሰናክል ስር እንዳይሰድ በማድረግ የደፈረሰው ሰላም እንዲጠራ፤ ሕግ እንዲከበር በማድረግ፤ ለዕድገት አደግድጎ መነሳት እንደሚገባ መንግሥትም ራሱ  ያምንበታል።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። ጦርነትና ድርቅ ሲከሰት ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች እንደሚበረቱ ያለፉት ዘመን ክስተቶችን መመልከት ይቻላል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው ጦርነት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጦርነት አይደለም። ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሆነ ውጪአዊ ጦርነቶችን እንዳስተናገደችና በዚህም ዘርፈ ብዙ ወጣውረዶች እንደገጠሟት ታሪክ ይዘክራል።

ክስተቱ ከዘመናቱ ጋር አብሮ ቢጓዝ እንጂ ያቆመበት ኹኔታ የለም። በተለይም 2013 እና 2014 ኢትዮጵያዊያን በጦርነት የታመሱበት፤ በድርቅ እና ርሃብ የተቆሉበት አስከፊ ዘመን እንደነበር አይዘነጋም። አስከፊ ክስተቶቹ አሁንም ቢሆን እንደቀጠሉ መሆናቸውን ለመረዳት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በአራቱም ማዕዘን ያሉበትን ኹኔታ ማጤንን ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ አሁንም ለአንድ ዓመት ከ11 ወር ገደማ በሰሜኑ በኩል በተፈጠረው ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል የተፈጠረው ጦርነት ጥቅምት 24/2013 መነሻውን ትግራይ ክልል መቀሌ አድርጎ ነበር። ከተኩስ አቁም ስምምነት ጀምሮ በድርድር ይፈታል የሚል ተስፋ ተሰንቆበትም ነበር። ሆኖም ግን የድርድር ሂደቱ ከሽፎ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ለሦስተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።

በዚህም የንጹሐን ሞት፤ መፈናቀል፤ የድጋፍ እጥረት፤ የንብረት ዘረፋ፤ የተለያዩ ተቋማት ውድመት እና ሌሎች መሰል ክስተቶች ከአምና እስከ ዘንድሮ እንደቀጠሉ ናቸው።

ይህም ብቻ ሳይሆን ሽብርተኛ የተባሉ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጠቃሽ ሌላኛው ትኩሳት ነው። በኦሮሚያ ክልል (ወለጋ የተለያዩ ዞኖች) ከአራት ዓመት ለማያንስ ጊዜ ኦነግ ሸኔ በንጹሓን ላይ የሚያደርሰው ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሌላኛው መፍትሄ የተጠማ ችግር መሆኑ አይካድም። እየሆነ ያለው ችግር ከዚህ በላይ ከቆየ ዘርፈ ብዙ መዘዝ ያስከትላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ታዲያ በአጠቃላይ የዋጋ ንረት፤ የሕግ ጥሰት፤ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተደጋጋሚ መራዘም እና ሌሎች በርካታ ተደራራቢ ችግሮች በ2015 አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የመንግሥት የቤት ሥራ መሆን እንዳለባቸው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን እየጠቆሙ አቅጣጫ በመስጠት ላይ ናቸው። ምሁራን ካስቀመጧቸው አጣዳፊ መፍትሄ ከሚስፈልጋቸው ችግሮች መካከል ዋናዎቹ በየመስካቸው ተከፋፍለው በሚከተለው መልኩ ተቀምጠዋል።

ሕግና ፖለቲካ

በአንድም በሌላም መንገድ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለፖለቲካዊ ጉዳይ ሲባል በብዙ መንገድ ሲጣስ የተስተዋለበት ጊዜ 2014 ነበር። በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የመከበራቸው ጉዳይ አጠያያቂ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎችም ቢሆኑ ደጋግመው ሲያነሱ ተደምጠዋል።

የሆነው ሆነና በ2014 የተፈጠሩ ዐይን ያወጡ ስህተቶችና መተላለፎች ወደ 2015ም እንዳይዘልቁ መንግሥት የቤት ሥራ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም የሕግና የፖለቲካ ምሁራን ከወዲሁ ምክረ ሐሳብ እየሰጡ ነው።

የሕግ ጥሰት ለዘመናት የቆየ ችግር መሆኑ ይነገራል። በለውጡ መንግሥት ጅማሮ ግን እልባት ያገኛል የሚል ብሩህ ተስፋ በሕዝቡ ዘንድ አጭሮ ነበር። በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን እየተስተዋለ ያለው ነገር ግን ተቃራኒው በመሆኑ ሕዝባዊ ቅሬታዎች ይነሳሉ። በጉዳዩ የሕግ ባለሙዎችም ይስማሙበታል።

ሕግና ፖለቲካ እየተጣረሱ በመሆናው ሕገ መንግሥቱ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ ሰዎች ተገዶ እየተጣሰ ነው የሚሉት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ያየህይራድ ተመስገን ናቸው።

ጠበቃው ከፖለቲካ ጋር የተንሻፈፉ የሕግ ጥሰቶች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አንስተው፣ መንግሥት ሕጉን አስገድዶ እየጣሰ በመሆኑ በ2015 ላለመድገም የቤት ሥራ ወስዶ ማስተካከል አለበት ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ያየህይራድ በመጀመሪያ ደረጃ ያነሱት፣ ሕግ የጣሱ አካላት ትክክለኛ ፍርድ ሳይበየንባቸው ይቅርታ ማድረግ ጥፋት የሚያከናውኑ ሰዎችን እሰየው የሚያሰኝ የሚመስል የተሳሳተ አካሄድ መሆኑን ነው። ከዚህ በፊት በነበራቸው የሥልጣን ዘመንም ሆነ በሰሜኑ ጦርነት ዘርፈ ብዙ በደል በማድረሳቸው መንግሥትን ጨምሮ በሕዝብ በኩል ቅሬታ ሲነሳባቸው የነበሩ የቀድሞ የሕወሓት አመራሮች ከእስር መፈታታቸውም ለዚህ አንድ ምሳሌ ነው ብለዋል።

ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች በ2014 ታህሳስ ወር መገባደጃ መንግሥት በይቅርታ እንደፈታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የሕግ አማካሪው ይህንኑ ድርጊትም ‹‹ሕጉን እንዲላላ የፈቀደ ዘፈቀዳዊ ፖለቲካ›› ሲሉ ተችተዉታል። በመሆኑም መሰል ድርጊት እንዳይደገም መንግሥት ሊያስብበት ይገባል ይላሉ።

ሌላው መንግሥት ሊያጤነው ይገባል የተባለው፤ የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በእኩል ዐይን ማስተናገድ እንደሚገባ ነው። የሕግ አማካሪው አንድም መገንጠል የሚያበረታታውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ማሻሻል ወይም ኹሉንም በእኩል ዐይን ማስተናገድ የመንግሥት ድርሻ መሆኑ መታወቅ አለበት ባይ ናቸው።

በተለይም በጉራጌ ዞን በኩል የክልልነት ጥያቄ በሚያነሱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ‹‹ክላስተርን ተቃውማችኋል›› በሚል ሰበብ የሚያደርገው እስር እና እንግልት ከዚህ በኋላ ሊነሱ በሚችሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዳይደገም ማድረግ ይገባል ብለዋል።

‹‹ሕግን የፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እያመሰው በመሆኑ፣ በተለይም ከባንዲራ ጋር በተያያዘ  ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ነው›› ያሉት የሕግ ባለሞያው፤ ይህ መስተካከል ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑም ጠቅሰዋል።

ከባንዲራ ጋር በተያያዘ በተለይም በበዓላት ወቅት በርካታ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች የሚገደሉበት አጋጣሚ ጥቂት እንዳልሆነ አውስተዋል። የሕግ አማካሪው ‹‹ባንዲራውን የሚቀያይሩት ባለሥልጣናት ናቸው። የሕዝብ ባንዲራ አንድ ነው። እርሱም አረንጓዴ፤ ቢጫ እና ቀይ። ሌላውን ዓርማ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በሕዝብ ላይ ቃታ እስከመሳብ ድረስ የሚስተዋሉ የሕግ ጥሰት በዚሁ በቃ ሊባል ይገባል። ይህም ለዘመናት መፍትሄ የተጠማ ችግርና መንግሥት እንደ ቤት ሥራ ሊወስደው የሚገባ ጉዳይ ነው።›› ብለዋል።

የፖለቲካ ተንታኙ ይድነቃቸው ሱራፌል በበኩላቸው፣ በባንዲራ ምክንያት የሰውን ልጅ መግደል እንዲቆም መንግሥት የቤት ሥራውን መሥራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል። በተያያዘም፣ ችግሩ ሲደጋገም የኖረና መፍትሄ ያልተሰጠው ነው ብለው፤ በበዓላት ጊዜ ባንዲራ በሚይዙ ሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያካሂዱ የመንግሥት ኃይሎችም በሕግ ተጠይቀው አስፈላጊው ቅጣት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ።

ባንዲራን በተመለከተ ሞት እንዲቆም መንግሥት ወጥና ቋሚ የባንዲራ ሥርዓትን የማጠናከር ግዴታ አለበትም ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ይድነቃቸው በተጨማሪም፣ ‹‹መንግሥት ኦነግ ሸኔን ለመመከት ኃይል አጥሮት ሳይሆን፤ ሌላ ፖለቲካ እያካሄደ ስለሆነ ነው። በተለይም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተለያዩ ዞኖች ንጹሐን ሰዎች በማንነታቸው እየተጨፈጨፉ ነው ያሉት።›› ሲሉ ወቅሰዋል።

ይህ ወደ 2015 መዝለቅ የለበትም ብለው፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድንም እጅ ሲሰጥ በሕጉ ተጠያቂ ማድረግ ሌላኛው የመንግሥት የቤት ሥራ ነው ሲሉ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።

የፖለቲካ ተንታኙ አክለውም፣ ጋዜጠኞች ከቤታቸው እየታፈኑ የሚወሰዱበት እና የሚሰወሩበት የሕግ ጥሰት እንዲሁም የሰሜኑን ጦርነት መንዛዛት በተመለከተም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተደጋገመ ቁጥር ሰብዓዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስን እያስከተለ ያለው የሰሜኑ ጦርነት፣ እልባት እንዲቸረው ማድረግ ትልቁና ዋነኛው የመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አለበት ነው ያሉት።

የጋዜጠኞችን እስር በተመለከተም ‹‹ማንኛውም ሰው ሕገ ወጥ ከሆነ በሕጉ መሠረት ሊዳኝ ግድ ይለዋል። ሆኖም ግን ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ከሕግ አግባብነት ውጭ እንዲሁ እየታፈሱ የሚወሰዱበትና ከተወሰዱ በኋላም ያሉበት ቦታ የማይታወቅበት ሁኔታ እንዲስተካከል ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው›› ብለዋል።

ከሕግና ፖለቲካዊ ይዘት በተጨማሪ መንግሥት ሊያከናውነው ይገባል የተባለው የቤት ሥራ በተለይም ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው ኢኮኖሚያዊ ጦስ ነው።

ኢኮኖሚያዊ የቤት ሥራ

አገራት አንዴ ወደ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ወደነበረው የቀደመ የዕድገት ደረጃ ለመመለስ ቢያንስ 10 ቢበዛ ደግሞ 20 ዓመታት ሊወስድባቻው እንደሚችል የአፍሪካ ልማት ባንክ በ2013 ያወጣው ጥናታዊ መረጃ ያሳያል። የምጣኔ ሀብት አማካሪዎች በበኩላቸው፣ ጦርነት ከጅማሮ እስከ ፍጻሜው ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከተቋጨ በኋላም የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ቀላል እንደማይሆን ይገልጻሉ።

ጦርነት በተለይም በአገር ውስጥ (እርስ በእርስ) የሚካሄድ ከሆነ የአገርን ኢኮኖሚ መጉዳቱ ስለማቀር ከስር ከስር መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ የገለጹት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምጣኔ ሀብት አማካሪው ያሬድ ኃይለመስቀል ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

አማካሪው ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጦስ በተመለከተ ዋና ዋና ናቸው ያሏቸው አራት ነጥቦችን አንስተዋል።

በዚህም በአርሶ አደሮች ላይ የሚከሰት ሞት እና የእርሻ ሥራ መስተጓጎል ወይም መቋረጥ አንደኛውና የመጀመሪያው ጉዳት ነው። በዚሁ አውድ በተለይም የክተት አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት አምራቹ ክፍል በጦርነቱ መሳተፉ እንዲሁም አርሶ አደሩ ከግብርናው ዘርፍ ለመውጣት መገደዱ ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑ ተብራርቷል።

ጦርነት በተለይም በአገር ውስጥ የሚካሄድ ከሆነ፤ የተካሄደበትን አገር ኢኮኖሚ የሚጎዳ መሆኑ የምጣኔ ሀብት አማካሪው በኹለተኛ ደረጃ ያነሱት ነጥብ ነው።

በሦስተኛ ደረጃ የተነሳው ሐሳብ የሚተኮሰውን ጥይትም ሆነ መተኮሻውን ለመግዛት የሚወጣው ዋጋ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ነው። በጦርነት ጊዜ ተቃራኒ ኃይልን ድል ለማድረግ የሚተኮሰው የመሣሪያ ዓይነት ኹሉ የሚገዛበት ውድ ዋጋ የኢኮኖሚ ኪሳራን እንደሚያስከትል ያሬድ በአጽንኦት ይገልጻሉ። ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ግብዓትን ለማሟላት የሚያገለግልን ገንዘብ ለጦር መሣሪያ መግዣ ማዋል የአገርን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ኪሳራ ውስጥ መክተቱ እንደማይቀርም ለአብነት አንስተዋል። ይህም በጥልቀት መታሰብ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ከሰው ልጅ ሞት በተጨማሪ መሠረተ ልማት፤ የተቋማት እንዲሁም የንብረት ውድመት እየተከሰተ መሆኑ በተደጋጋሚ እየተነገረ ቆይቷል። ለሦስተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰው በዚሁ ጦርነትም መሰል ክስተቶች እየተፈጸሙ መሆኑ እየተሰማ ነው። ታዲያ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመተካት የገንዘብ እጥረት ፈታኝ ሆኖ ይስተዋላል። የምጣኔ ሀብት አማካሪውም በአራተኛ ደረጃ ያነሱት ይህንኑ ጉዳይ ነው።

በጦርነት ጊዜ የሚከሰት የመሠረተ ልማት ውድመትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የገንዘብ አቅርቦት ማጠር ሌላኛውና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ወደኋላ የሚጎትተው ችግር ነው ብለዋል።

በመሆኑም፣ ከላይ የተጠቀሱት አራት ነጥቦች ጦርነት በተስፋፋ ቁጥር ጎን በጎን የሚንሰራፉ ችግሮች በመሆናቸው በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከባድ የቤት ሥራ ከፊቱ ተደቅኖ እየጠበቀው እንደሚገኝ አቅጣጫ ተሰጥቷል።

ጦርነት የኢኮኖሚን እድገት እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ምክንያቶች መካከል አንደኛውና ዋነኛው ነው ሲባል የሚሰማ ሲሆን፤ ባለንበት ዘመንም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። አለማየሁ ገዳ (ፕ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ናቸው።

‹‹የጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ጫናና የወጪ አሸፋፈኑ ተግዳሮቶች ከአንዳንድ አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ በ2013 ባጠናቀሩት ጥናት የሚከተለውን ሐሳብ አስቀምጠዋል።

‹‹ጦርነት ለኢትዮጵያ የልማት ኋላ ቀርነት ዋነኛው መንስኤ ነው። ከ100 ዓመታት በፊት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፤ ጦርነትና ከአውሮፓ ጋር ያለው የተዛባ የንግድ ልውውጥ ለኢትዮጵያ የልማት ኋላ ቀርነት ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን በአንክሮ ነግረውን ነበር። ዛሬም ይኸው ነው የኾነው።›› ይላሉ።

እንደተባለውም፣ በሰሜኑ በኩል ለአንድ ዓመት ከ11 ወር በዘለቀው ጦርነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያሽቆለቆለበት ወቅት መሆኑ እርግጥ ነው። በመሆኑም፣ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመቆም የኢኮኖሚ ቀውሱን ችግር ካልፈታ ጉዳቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይመጣ በማሳስብ ላይ ናቸው።

ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ ጦርነቱ በተለይም በ4 ማክሮ (ዐቢይ) ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል በጥናታቸው ቀድመው አስጠንቅቀው ነበር።

አራት ማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ብለው ካስቀመጧቸው መካከል የዋጋ ንረት፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ የፈራረሱ የሕዝብ እና መንግሥት ተቋማትን ለማቋቋም የሚገጥም የገንዘብ እጥረት እንዲሁም ለጦርነቱ የከተተውን ሠራዊት ወደ ሰላም መንገድ የማምጣትና ወደ ሥራ ዘርፍ የማስገባት ተግዳሮቶች ናቸው። የፖለቲካ ተንታኙ ይድነቃቸው በበኩላቸው፣ ይህንኑ ሐሳብ በመጋራት መንግሥት በ2015 በግንባር ቀደም የሚሠራቸው የቤት ሥራዎች መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የዋጋ ንረት ማኅበረሰቡን ከፍተኛ ምሬት ውስጥ የከተተ ችግር ሆኖ ተስተውሏል። ዓለማየሁ በጥናታቸው 70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት ተሰቅዞ የተያዘ መሆኑን አስፍረው፤ የዋጋ መናር ደግሞ የሚጎዳው በድህነት ስር ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል መሆኑን በአንክሮ ገልጸዋል።

ፀሐፊው የዋጋ ንረቱን በተመለከተ የመፍትሄ አቅጣጫ ሲሰጡ፣ መንግሥት በነጻ ገበያው ላይ የዋጋ ተመን ማድረግ እንዳለበት ነው። ‹‹እንኳን  በጦርነት  ጊዜ  በመደበኛውም  ጊዜ ቢሆን የምግብ አቅርቦታችን ከምግብ ፍላጎታችን በ30 በመቶ ገደማ በየዓመቱ ጉድለት የሚያሳይ ነው›› ሲሉ በተለይም በጦርነት ወቅት ሊጨምር እንደሚችል በጥናታቸው አስቀምጠዋል።

የፖለቲካ ተንታኙ ይድነቃቸው በበኩላቸው፣ ሕዝቡን ላማረረው የዋጋ ንረት መፍትሔ ማግኘት፣ መንግሥት በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ።

ሕዝብና ቤት ቆጠራ

ሕዝብና ቤት ቆጠራ በየ10 ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 11 በአንቀጽ 103 ተደንግጓል። ይሁን እንጂ፣ ቆጠራው በድንጋጌው እና በጊዜ ሰሌዳው መሠረት እየተካሄደ አይደለም። በኢትዮጵያ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በ1976 ሲሆን፤ ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው ደግሞ ከ1999 እስከ 2000 እንደነበር ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ለ4ኛ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ቆጠራው፣ ከ2010 ጀምሮ ለአራተኛ ጊዜ እየተራዘመ ቆይቶ፤ በ2014ም በተመሳሳይ ለ5ኛ ጊዜ መራዘሙን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ተቋም መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በግምታዊ ቁጥር እንደተቀመጠ ይታወቃል።

ታዲያ ይህ ግምታዊ የሕዝብ ቁጥር መንግሥት የሚያከናውነውን የበጀት ክፍፍል ፍትሐዊ አያደርገውም የሚል ቅሬታን ሲያስነሳ ተስተውሏል። የሕዝብና ቤት ቆጠራ ዋነኛ አስፈላጊነቱ፣ መንግሥት በአንድ ስፍራ በሚኖረው የሕዝብ ብዛት ተመርኩዞ አስፈላጊውን በጀት ፍትሐዊ በሆነ ሂደት እንዲያከፋፍልና ማኅበረሰቡ በሚያስፈልገው አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን መሆኑ ይታመናል።

በመሆኑም፣ ለ5ኛ ጊዜ የተራዘው 4ኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራም ሌላኛው መንግሥት ሊወስደው እና በአፋጣኝ ሊያከናውነው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ ይድነቃቸው ሱራፌል በዚሁ ርዕሰ ጉዳይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይድነቃቸው በተያያያም፤ ጦርነቱ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ረገድ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ተጠንቶ፤ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተካሂዶ የመንግሥት የ10 ዓመት ዕቅድም በምልሰት መታየት አለበት ብለዋል።

ዓለማየሁ ገዳ በበኩላቸው፣ በ2013 ባጠናቀሩት ጥናት የመንግሥት የ10 ዓመት ዕቅድ በድጋሚ መታየት እንዳለበት አስቀድመው በማስጠንቀቅ ጽፈዋል።

በመሆኑም የሕግ ባለሙያዎች፤ የፖለቲካ ተንታኞች እንዲሁም የምጣኔ ሀብት አማካሪዎች መንግሥት በ2015 ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች የመቅረፍ የቤት ሥራ አለበት ሲሉ መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች