መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየጄሪካንና የውሃ መሳቢያው ንጽጽር

የጄሪካንና የውሃ መሳቢያው ንጽጽር

ባሳለፍነው ሳምንት መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ኹለት በምስሎች የተደገፉ ታሪኮች የብዙዎችን ትኩረት የሳቡ ነበሩ።  አንደኛው በጎጃም ግዛት በአንዲት ከተማ የውስጥ ለውስጥ ኮብል ስቶን መንገድ ላይ የተደረደሩ ጀሪካኖች የታዩበት ነው። ሌላው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ለአርሶ አደሮች ይታደላል የተባለ ለመስኖ የሚያገለግል የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ክምችት ነው።

ኹለቱን ምስሎችና ታሪኮች የሚያገናኛቸው ምንድን ነው ሳትሉ አትቀሩም። ለማሽኖቹ የሚያስፈልግ ነዳጅ የሚቀዳባቸው ጀሪካኖች አይደሉም ሰልፍ የያዙት። ቁጥራቸው በውል ባይጠቀስም፣ ጀሪካኖቹ 25 ሊትር የሚይዙ ትልልቆቹ መሆናቸውን ከሰማያዊ ቀለማቸውና ከመጠናቸው መገመት ይቻላል። ቁጥራቸውን ለመገመት ቢያስቸግርም በመቶዎች የሚቆጠሩ ለመሆናቸው አደራደራቸው ያስረዳል።

እነዚህ ጀሪካኖች የተደረደሩት አረቄ ሊገዛባቸው እንደሆነ ያሳወቁት የመረጃ ምንጮቹ፣ ሁኔታው በየእለቱ የሚታይ ወይም በብዙ ጊዜ አንዴ የሚከሰት እንደሆነ ባያብራሩም፣ ለትዕይንተ ሕዝብ አውራ ጎዳና ላይ የተኮሎኮሉ ስለሚመስሉ ብዙዎችን ጉድ አስብለው ነበር። በዚያን ያህል መጠን አረቄ ገበያ ካለው ለምን ከውጭ የምናስገባውን ነዳጅ በጎጆ ኢንዱስትሪ ለመተካት ጥረት አናደርግም እያሉ ስለነገሩ ያሾፉም ነበሩ።

አንዳንዶች የጀሪካኖቹ ሰልፍ እውነት የአረቄ ከሆነ ምን ያህል የአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኹኔታ እንደከፋ የሚያሳይ ነው ብለዋል። ጠርሙስ ቢራና እሽግ ውሃ ዋጋቸው ተወዶ በመሸጫቸው መቀራረባቸው በሚያስቀልድበት በዚህ ዘመን፣ ኅብረተሰቡ ራሱን ዘና የሚያደርገው በቀላሉ አስካሪ በሆኑ አረቄን በመሳሰሉ መጠጦች እንደሆነ አመላካች ነው ያሉም አሉ።

በተለያዩ ከተሞች የጠጅ ቤቶች መስፋፋት ጋር የችግሩን አሳሳቢነት በማገናኘት የጀሪካኖቹን ሰልፍ በማነጻጸር ለማስገንዘብ የጣሩም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ጠላ በየመኖሪያ ቤቱ ስለማይጠመቅ ውጭም ስለሚወደድ ያለው አማራጭ አረቄ ነው ብለው የሚናገሩ ቢኖሩም፣ ካቲካላው ራሱ ዋጋው ጨምሯል ብለው ስሞታ የሚያቀርቡም አልጠፉም። የአረቄ ምርት ሕግና ስርዓት ሳይኖረው ብዙ ተጠቃሚዎችን እንዳፈራና ተወዳጅነቱ እንደጨመረ የሚመለከቱ እኩያን ከገቢው ለመጠቀም በማሰብ ክፉ እንዳይሠሩበት ያሳሰቡም ነበሩ።

ሕንድ አገር በየቤት ውስጥ የሚጠመቅን አልኮል ይዘት ያለው መጠጥ፤ አገኘን ብለው ጠጥተው በየጊዜው ይህን ያህል ሰዎች ሞቱ የሚባለው ዓይነት ዜና አገራችን እንዳንሰማ ይታሰብበት ያሉ ጥራቱ ያሳሰባቸውም ነበሩ። ያን ያህል አረቄ ለማምረት ምን ያህል እህል ፈጅቶ ይሆን እያሉ በተደረደረው ጀሪካን ብዛት ላይ ተመርኩዘው ብዙ የጠየቁም ነበሩ።

በሌላ በኩል፣ ወሬው ይፋ በሆነበት ወቅት ከኦሮሚያ ክልል ባላሥልጣናት በኩል የተሰማው የውሃ መሳቢያ ማሽን እደላ ብዙ አስብሏል። የታደለ ሕዝብ ከ10 ሺሕ በላይ ፓምፕ ልትታደል ነው ተብሎ ተከምሮለት ያያል፤ ያልታደለው ደግሞ ፍላጎትህን የሚያሟላልህን አረቄ ለማግኘት ወረፋውን ተመልከት እየተባለ ነው እያሉ የክልሎቹን አመራሮችም ሆነ ተጠቃሚዎቹን እያነጻጸሩ በጉዳዩ ለማስተማር የጣሩ ነበሩ።

ሕዝቡ ወሰን ሳይለየው በጋራ አድርጎ መሬቱን በመስኖ እያለማ በትርፍ ጊዜው አረቄውን እየጠጣ እርሻውን ቢጠብቅ መልካም ነበር ያሉም አሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች