የ2014 ኪነ-ጥበባዊ በረከቶች

0
1384

አገርን አገር በማድረጉ ሂደት ውስጥ ኪነ-ጥበብ የራሱን የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚወጣ አያጠራጥርም። ታሪክን ሰንዶ ከማስቀመጥ ባለፈ በኪነ-ጥበብ ታሪክ ይSራል። ጊዜ ጊዜን ሲወልድ፤ ቀን ቀንን፣ ወር ወርን፣ ዓመትም አስከታዩን ወልዶ ቦታቸውን አስረክበው ይሄዳሉ። ተረኛው 2014ም ዘንድሮነቱን ለቆ አምና መባሉ አይቀርም።አዲስ ማለዳም ዓመቱ በኪነ-ጥበብ መስክ ምን አበረከተልን የሚለውን ለመዳሰስ ወዳለች። ኪነ-ጥበብ ሰፊ የሆኑ ዘርፎች ቢኖሩትም፣ መረጃ ማግኘትን እንዲሁም ተደራሽነትን መሠረት አድርጋ ሥነ-ጽሑፍ፣ ቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ፊልም እንዲሁም የቴሌቭዥን ድራማዎችን በመዳሰስ የተወሰኑትን እንደሚከተለው ታስታውሳለች።

ሥነ-ጽሑፍ

ሥነ-ጽሑፍ በጽሑፍ መልክ የሚቀርብ፣ ሕይወትን ውብ በሆነ መልክ የሚያንፀባርቅ የፈጠራ ሥራ ነው። በውስጡ ልብወለድን የሚያቅፈው ሥነ-ጽሑፍ በራሱም ሆነ እንደ ሙዚቃና ቴአትር ባሉት የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ላይ በሚያሳርፈው አሻራ ተደራሽነቱ ከፍ ያለ ነው።

ማእከላዊ የሆነ የመረጃ ቋት ኖሮ አሳሳች ያልሆኑ ቁጥራዊ መረጃዎች ባይገኙም፣ በርካታ የሆኑ መጽሐፍት ለንባብ የበቁበት ዓመት እንደሆነ መጽሐፍት ቤቶችንና መጽሐፍ አዟሪዎችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል። እንደ አገር የንባብ ባህላችን ያልዳበረ መሆኑ የማይካድ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተዳምሮ የወረቀትና የህትመት ወጪ ከፍ በማለቱ በርካታ የተጻፉ ነገር ግን ያልታተሙ መጽሐፍት እንደሚኖሩ ይገመታል።

የህትመቱን ዓለም ተግዳሮቶች ተወጥተው በ2014 ለህትመት የበቁ በርካታ መጻሕፍት ቢኖሩም ዓመቱን ለማስታወስ አንዱን እንዲህ እናስታውሳለን።

ሚያዚያ ወር ላይ ለንባብ የበቃው የደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “የተጠላው እንዳልተጠላ” መጽሐፍ የአዲስ ማለዳ አይረሴ ምርጫ ነው። የደራሲው አስራ ኹለተኛ መጽሐፍ የሆነው ይህ መጽሐፍ ብዙዎችን አነጋግሯል። ለየት ያለ የአጻጻፍ ዘዴን ተከተሎ መጻፉና ይዞ የተነሳው ሐሳብ ያልተለመደ መሆኑ የአንባቢዎችን ቀልብ እንዲገዛ አድርጎታል።

እንደ ማኅበረሰብ ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ ምክንያቱን ማግኘትና በገጸ-ባህሪዎቹ አማካኝነት እንደምክንያትነት የሚቀርብ ጉዳይን ይዞ ውጣ ውረድ በተሞላበት መንገድ ሌሎቹን ማሳወቅና ማንቃት ላይ ያተኩራል።

የመጽሐፉን ጭብጥ በመደገፍም በመቃወምም በርካታ አስተያየቶች በአንባቢዎ የተነሱ ሲሆን፣ ደራሲውም እነዚህን አስተያየቶች ይዞ በመነሳት ሌሎች ደራሲዎች መጽሐፍትን እንዲጽፉ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ቴአትር

ቴአትር በመድረክ የሚተወን ጥበብ ሲሆን የአፈጻጸም፣ የሙዚቃ፣ የድምፅ እና የመዝናኛ ቦታዎችን (መድረክ) የሚያጣምር የአፈጻጸም ጥበባት ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። በአገራችን ከመቶ የዘለሉ ዓመታትን ያስቆጠረው ቴአትር በጣት በሚቆጠሩ ቴአትር ቤቶች ይከወናል። ከእነዚህ ቴአትር ቤቶች መካከልም ብሔራዊ ቴአትር ዋናው ነው።

በዚሁ ቴአትር ቤት ሰባት ቴአትሮች መድረክ ላይ ያሉ ሲሆን “ላጤው ባለትዳር” ቴአትር ደግሞ ባገባደድነው 2014 ለመድረክ የበቃ ቴአትር ነው። በዳንኤል ሙሉነህ ተደርሶ በሔኖክ ብርሀኑ የተዘጋጀው ይህ ቴአትር፣ ስድስት ተዋንያንን የሚያሳትፍ ነው። ከሰኔ 28 ጀምሮም ለዕይታ በቅቷል።

ቴአትሩ የፍቅር ኮሜዲ ዘውግ ያለው ሲሆን፣ ፊልም ሲተውኑ የምናውቃቸውን ተዋንያን ወደ መድረክ ያመጣ ነው። ዘለግ ያለ ዝግጅትና ኪነ-ጥበባዊ አቅም በሚጠይቀው የቴአትር ሥራ አዲስ ቴአትር መድረክ ላይ መመልከት የሚያስደስት እንደሆነ የተመልካቾች አስተያየት ያስረዳል። በዚህ ረገድም “ላጤው ባለትዳር” በወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መዘጋጀቱ የቴአትርን ብሩህ ተስፋ ያሳያል።

ሙዚቃ

ሙዚቃ የሰው ድምጽን፣ የመሣሪያ ድምጽን ወይም ኹለቱንም በማጣመር ስርዓት ያለውን ውበት፣ ኅብርና ስሜትን የሚገልፅ ረቂቅ ጥበብ ነው። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በሸክላ ከተቀረፁት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሥራዎቸ በኋላ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎች ተቀርፀው ለአድማጭ ደርሰዋል።

አድማጭም የየራሱ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን ቢኖረውም፣ እያንዳንዱ ዘመን የየራሱን አሻራ በሙዚቃው ላይ አስቀምጧል። ይህኛውም ዘመን የራሱን አሻራ በማስቀመጥ ላይ ይገኛል።

ቀደም ካሉ ዓመታት በተለየ መልኩ የዓለም ሉላዊነት (Globalization) ሙዚቃው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። በዚህም ነጠላ ዜማዎች እንደበዙ ማየታችን አንዱ ማሳያ ነው። በምስል ተቀናብረው የሚለቀቁ ሙዚቃዎች እንደመበርከታቸው ለምስላቸው መጨነቅም በዚህኛው የሙዚቃ ትውልድ የምናስተውለው ነው።

ባገባደድነው ዓመትም በርካታ የሙዚቃ ሥራዎች ለአድማጭ የደረሱ ሲሆን፣ “ስድስት” የተሰኘው የሮፍናን ኑሪ ኹለተኛ አልበም ደግሞ አይረሴ ነው።

ሮፍናን “ነፀብራቅ” በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ ለአድማጮች ከተዋወቀ በኋላ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባለ ግዙፍ ሥም ሙዚቀኛ ሆኗል። “ስድስት” የሚሰኘው ኹለተኛ አልበሙም በበርካቶች የተወደደለት ሲሆን ሥያሜውን ጨምሮ በውስጡ የያዘው መልዕክት ለብዙዎች አነጋጋሪ ነበር። ሙዚቀኛው ስለ አልበሙ ሥያሜ ሲጠየቅ፣ ‹ሁሉም የራሴ ብሎ የያዘው እውነት ባለበት በዚህ ሰዓት› የስድስት ዓመት ልጅ ለዓለም ያለውን ዕይታ ተምሳሌት ለማድረግ አልበሙን “ስድስት” ብሎ እንደሰየመው ተናገሯል።

አስራ ሰባት ሙዚቃዎችን የያዘው አልበሙ አገራዊ የሆኑ የሙዚቃ ስልቶችን በዘመናዊ መንገድ ለአድማጮች ከማድረስ ባለፈም ትልልቅ ሐሳቦችን በውስጡ ይዟል። የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃን በሰፊው ለአድማጭ ያደረሰው ሮፍናን ኢትዮጵያዊ ምቶችን በመጠቀም ይታወቃል።

ፊልም እና የቴሌቪዥን ድራማ

በ1957 “ሂሩት አባቷ ማን ነው?” በሚለው ፊልም እንደተጀመረ የሚነገረው የኢትዮጵያ ፊልም እድገቱ ቢያጠያይቅም ተደራሽነቱ እያደገ መምጣቱ የሚታይ እውነት ነው። በዩትዩብ (Youtube) ተደራሽ የሚሆኑ የአገራችን ፊልሞች በርከት ያሉ ሲሆን፣ የታሪክና የትወና ጥራታቸው በብዙ ተመልካቾች ዘንድ ጥያቄ ይቀርብበታል።

በተቃራኒው ደግሞ ብዙ የተለፋባቸው ከከተማ ውጪ የሚቀረፁ ፊልሞችንም ተመልክተናል። በዚህ ረገድ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች በተመሳሳይ መንገድ ላይ ሲሆኑ፣ የቴሌቪዥን ድራማዎች ረዥም ከመሆናቸው አንፃር ከባድ ያደርጋቸዋል።

ባገባደድነው ዓመት የተጠናቀቀውና በአርትስ ቴሌቪዥን ሲታይ የነበረው “እረኛዬ” ድራማ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ነበር። በሦስቱ እንስት ደራሲያት ማለትም በቅድስት ይልማ፣ አዜብ ወርቁ እንዲሁም ቤዛ ኃይሉ ተደርሶ ከደራሲዎች በአንዷ ቅድስት ይልማ የተዘጋጀው ድራማ፣ በአራት ምዕራፎች እና 48 ክፍሎች ተከፋፍሎ ለዕይታ ቀርቧል።

በታሪክ አወቃቀርና በትወናው ጥራት የብዙዎችን ቀልብ መያዝ ችሎ የነበረው ድራማው ካለቀ በኋላም መነጋገሪያ መሆኑ እንደቀጠለ ነው። መቼቱ ታሪኩን መሸከም የሚችልና የአገሪቱን ባህልና ወግ በአግባቡ የሚያሳይ መሆኑ በብዙዎች እንዲወደድ ካደረጉት ምክንያቶች መሀል የሚጠቀሱ ናቸው። የአገራችንን አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ያሳተፈው ድራማው አገራዊ ጠንካራ ጭብጥን የያዘና መፍትሄም የሚጠቁም ነው።

ኪነ-ጥበባዊ መድረኮች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደማቅ ኪነ-ጥበባዊ መድረኮችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል። በእነዚህ መድረኮች የሚቀርቡ ሥራዎችም ኪነ-ጥበባዊ ይዘታቸው ከፍ ከማለት ባለፈ የአገራቸንን ነባራዊ ሁኔታ በተለያየ መንገድ መግለጽ፣ መሄስ እንዲሁም መገሰጽን ያካተቱ ናቸው። ያልተሰሙ አዳዲስ ሐሳቦች የሚሰሙባቸው መድረኮች ሆነው፣ በከያኒነት የማይታወቁ ግለሰቦችን ወደ መድረክ በማምጣት ሐሳባቸውን እንዲገልፁ አስችለዋል።

በዚህ ረገድ ጦቢያ ግጥምን በጃዝ ተጠቃሽ ነው። ወርሃዊ የሆነው ይህ መድረክ ብዝኀ ሐሳቦችን በመያዝ የሚታወቅ ነው። ግጥም፣ ሙዚቃ፣ ግለ-ተውኔት፣ ተውኔት፣ ዲስኩር እንዲሁም ሌሎች ይዘቶችን ይዞ ለመድረክ የሚበቃው ጦቢያ በመድረኩ ታድመው ከሚከታተሉት ታዳሚያን በተጨማሪ በቴሌቪዥን እና ዩትዩብ (Youtube) ብዙ ተመልካቾችን አግኝቷል። የኪነ-ጥበብ መድረኮች ከተዝናኖት ባለፈ የሐሳብ ገበያ እንደሆኑም ማሳያ ሆኗል።

የመጽሐፍት ውይይቶች   

ደራሲዎች ከመጽሐፎቻቸው ባለፈ ሐሳባቸውን ከአንባቢያን ጋር ፊትለፊት የሚነጋገሩባቸው መድረኮች ያገባደድነው ዓመት አይረሴዎች ናቸው። በዚህ ረገድ ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ እና ዋልያ መጽሐፍት የሚያዘጋጁት መጽሐፍ የማስፈረም፣ ከደራሲያን ጋር የመተዋወቅና የመጨዋወት ልዩ ሥነ ስርዓት ግንባር ቀደሙ ነው።

ሳምንታዊ በሆነው በዚሁ መሰናዶ ደራሲዎችና አንባቢዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው ሐሳብ የሚለዋወጡ ሲሆን፣ በአንባቢያን ልቦና የሚመላለሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ያደርጋል። ለደራሲያን አበረታች ከመሆን ባለፈም ወደ ድርሰቱ ዓለም መቀላቀልን ላሰቡ መልካም መነሳሻ ነው።

ኪነ-ጥበብ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት የበለጠ ጠቃሚ ይሆን ዘንድ በረከቶቹን ማስቀጠል ሌሎች በረከቶችንም መፍጠር እንደሚገባ የአዲስ ማለዳ ማጠቃለያ ሲሆን፣ ‹የጎመን ድስት ውጣ የገንፎ ድስት ግባ› ብለን ቀጣዩን ዓመት እንቀበል ዘንድ ምኞቷ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here