መነሻ ገጽዜናትንታኔበዓልና ትራንስፖርት

በዓልና ትራንስፖርት

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚያስነሱና እምብዛም ትኩረት ከማይሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የበዓላት ወቅት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እጥረት እና አለመኖር ተጠቃሽ ነው።

በዓልን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተሽከርካሪ አካላት መኪና የለም ከማለት ባሻገር፣ በደላላ ጭምር ትኬት የመሸጥ እና ከመደበኛ ዋጋ እጥፍ እንዲሁም እጅግ አስወድደው ሲያስከፍሉ ይታያል።

ይህ በበዓላት ወቅት ያለው የትራንስፖርት እጥረት ከክልል መዲናዎች በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡ ላይ የተሽከርካሪ እጥረቱ እንዳለ ይታያል።

ከዚህ ጎን ለጎን በርካታ ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ወደተለያዩ ቦታዎች በዓልን ለማክበር ወደ ቤተሰብ ጋር በሚያቀኑበት ወቅት በትራንስፖርት ዘርፍ በሚታይ ብልሹ አሠራር እና በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮች ምክንያት ሰዎች መጉላላታቸውን እና ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን የሚገልጹም አሉ።

የበዓል ሰሞን በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ለሚታዩ ችግሮች እና ብልሹ አሠራሮች በምክንያነት ከሚጠቀሱት መካከል፣ በስምሪት ላይ የሚሠሩ አካላት ቸልተኝነት፣ አንድ አንድ ሥነምግባር የጎደላቸው ደላሎች እና አሽከርካሪዎች እንዲሁም የትራፊክ ፖሊሶች የቁጥጥር ማነስ ተጠቃሽ እንደሆኑ ሲነገር ይሰማል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እና የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ብዙዎች ይናገራሉ።

አሁንም አዲስ ዓመት መሆኑን ተከትሎ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደሚያጋጥም ይታወቃል። በአዲስ አበባ ከሚኖሩት መካከል 42 በመቶ ያህሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ታዲያ እነዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወደየትውልድ ቀያቸው ጎራ በማለት ከቤተሰብ ጋር ማሳለፋቸው የተለመደ ነው። ነገር ግን፣ በዚህ በዓልን ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ በሚደረገው ጉዞ የትራንስፖርት ችግር አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ቀጥሏል።

በተለይም በአዲስ ዓመት የተጓዦች ቁጥር ስለሚጨምር ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እጥረት እና መጨናነቅ እንደሚያጋጥም ይታወቃል።

ከዚያም አልፎ መኪና ሲገኝ ከተለመደው መደበኛ ታሪፍ በላይ ለመክፈል እንደሚገደዱ ተጓዦች ይናገራሉ። የትራንስፖርት መጨናነቅ፣ የታሪፍ ጭማሪ እንዲሁም በአሰቡበት ጊዜ እና ሰዓት ለመሄድ አለመቻል ከበዓሉ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

ሳምራዊት ዓለሙ በዓልን ከቤተሰቦቿ ጋር ለማሳለፍ በማሰብ የጉዞ ትኬት ለመቁረጥ ወደ አውቶብስ ትኬት መቁረጫ ጎራ ማለቷን ትገልጻለች።

ሳምራዊት ወደ ሐዋሳ የሚያደርሳትን የአውቶብስ ትኬት ለማግኘት ብዙ እንደተቸገረች ተናግራለች። በየበዓሉ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ቤተሰብ እንደምትሄድ በመጥቀስ እና በዓልን ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ ትራንስፖርት የምታገኝበት መንገድ ግን አሰልቺ መሆኑን አውስታለች።

በተለይ በትኬት መቁረጫው አካባቢ የኮሚሽን ሥራ የሚሠሩ ደላሎች ትኬቱን ቀድመው በመግዛት ከ300 ብር በላይ አትርፈው እንደሚሸጡትም ተናግራለች። ይህ እንዳይሆን ትኬቱን በዓሉ ከመቃረቡ ቀደም ብሎ መቁረጥ እንዳለባት ብታነሳም፣ አስቀድማ ብትሞክርም እንዳልቻለች እና የትራንስፖርት እጥረት እና መጉላላቱ እንዳልቀረላት ሳትናገር አላለፈችም።

 የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታጠቅ ነጋሽ በበኩላቸው፣ በዓልን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊው የኅብረተሰብ ቁጥር እንደሚጨምር በመረዳት ዝግጅት ተደርጎል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ2015 የዘመን መለወጫ ወይም ለእንቁጣጣሽ በዓል እንዲሁም ለቀጣይ የመስቀል በዓል ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ክልሎች እንዲሁም ከክልል ከተሞች ወደ መዲናዋ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር በመገንዘብ በአዲስ አበባ በሚገኙ በስድስት መናኽሪያዎች ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

በዚህ መሠረትም በመናኽሪያዎች ውስጥ ኅብረተሰቡ ተሽከርካሪዎችን ሳይጉላላ እንዲያገኝ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በተጨማሪ በመናኽሪያዎች ውስጥ የሚገኙ የስምሪት ባለሙያዎች የቁጥጥር ዝግጅት አድርገው ተሽከርካሪዎችን ወደ መስመር የማስገባት ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው።

- ይከተሉን -Social Media

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶችም በከተማዋ ከሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተጠበቀ ሳለ፣ በከተማ ዙሪያ ባሉ ከተሞችም አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሕወሓት ሦስተኛውን ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ከበዓሉ ጎን ለጎን መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ግዳጁን ለሚቀላቀሉ እና ስንቅ ለሚያቀብሉም ጭምር የትራንስፖርት አገልግሎት እየተመቻቸ ያለበት ሁኔታ እንዳለም ተነግሯል።

ዳይሬክተሩ አክለውም መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ተንተርሶ ወደ ሁሉም ክልል ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ታሪፍ አውጥቷል ብለዋል።

ይህን መንግሥት ያወጣውን ታሪፍ እንዳይስቱ በተደጋጋሚ እንደተነገራቸው ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ያወጣውን ታሪፍ የሚጥሱ እንዲሁም በሕገ ወጥ መልክ ከመናኽሪያ ውጪ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች እና ደላሎች እንዳሉ ጥቆማ ደርሶናል ብለዋል።

ይህንንም ኅብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ እና ከስምሪት ባለሙያዎች በተጨማሪ በጸጥታ አካላት ጭምር በመቆጣጠር እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ ተብሏል።

በቅርቡም ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የዚህን ዓይነት ተያያዥ ወንጀል የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ላይ ተከታትሎ እርምጃ ለመውሰድ እና ድርጊቱን ለማስቀረት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ተብሏል።

ከስምምነቱ ውስጥ የነዳጅ ድጎማ ላይ ከተቀመጠው የታሪፍ ምጣኔ በላይ የሚያስከፍሉ ተሽከርካሪዎች እና ረዳቶችን መለየት እና እርምጃ መውሰድ አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በመናኽሪያዎች ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የተመቻቸ መሆኑን በመረዳት ከመናኽሪያዎች ውጪ እንዳይሳፈሩ ብለዋል። በተጨማሪ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች እና ደላሎችን በመጠቆም ኅብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ከመጪው የአዲስ ዓመት በዓል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች በመኖራቸው፣ እንዲሁም የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ከመጠን በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች በመኖራቸው ቁጥጥር አደርጋለሁ ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ነው።

በአዲስ ዓመትና በቀጣይ ከሚከተሉ በዓላት ጋር ተያይዞ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ከወትሮው በተለየ መንገድ የሚንቀሳቀስበት ወቅት በመሆኑ የትራፊክ ፍሰት ችግሮች እንዳያጋጥሙ እና ተያያዥ አደጋዎች እንዳይኖሩ የትራፊክ ፖሊሶች የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ብርሃኑ ኩማ ተናግረዋል።

ይህ የቁጥጥር ሂደት ከጳጉሜ 1/2014 ጀምሮ እስከ መስከረም 20/2015 ድረስ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። የመጀመሪያው ሂደት ለትራፊክ ደንብ አስከባሪዎች ግንዛቤ ላይ የተደገፈ ሥራ ተሠርቶ እሱን ለባለአሽከርካሪዎች እና ለእግረኞች የግንዛቤ ትምህርት እንዲያስተምሩ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በኹለተኛነት ደግሞ ለአሽከርካሪዎች በ2015 ሕግን የጣሰ ጥፋት እንዳያጠፉ የትራፊክ ደንብ ተቆጣጣሪዎች እና የትራፊክ ፖሊሶች የሚያግዝ ሥራ አከናውነዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪ በአዲስ ዓመት እና በቀጣይ በዓላት ወቅት ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ፣ ቀበቶ ሳያስሩ የሚያሽከረክሩ እና ሌሎች ተያያዥ ጥፋት የሚያጠፉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

እንደ ዛሬው ኢትዮጵያ ችግር ላይ ባልነበረችበት እና የኑሮ ውድነቱ ጣራ ባልነካበት ጊዜ በዓላትን ተከትሎ የሚመጣው የትራንስፖርት ችግር እምብዛም ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም ነበር። መንገደኛውም ቢሆን ምሬቱን እና ችግሩን በሆዱ አምቆ በመያዝ ካሰበው ቦታ ለመድረስ እና ከቤተሰብ ጋር በዓልን ለመዋል ያለውን ተስፋ ሙሉ ለማድረግ የቻለውን ያደርጋል እንጂ “የመንግሥት ያለህ” ብሎ ሲጮኽ አይሰማም።

በዓላትን ምክንያት በማድረግ ሁልጊዜም የትራንስፖርት መጨናነቅ፣ እጥረት እና የዋጋ መናር ቢኖርም ይህ ችግር የመንገደኞችን ከቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ጋር ሰብሰብ ብሎ በዓልን የማሳለፍ ሐሳብ አለማስቀየሩ ኹነቱ የበዓሉ አንደኛው ድምቀት እና መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑም ይወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች