መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳብዙ ሥራ የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ተስፋ

ብዙ ሥራ የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ተስፋ

የዘመን መለወጫ ተስፋን የሚፈነጥቅባቸው በርካቶች ናቸው። የታመመ ሌቱ ረዝሞበት የንጋትን ብስራት ይናፍቃል። ሲነጋ ደኅና አድርጎ የሚያስነሳው አንዳች ተአምር ኖሮ ሳይሆን በንጋቱ የመዳንን ተስፋ ስለሚያገኝ ነው። የዘመን ለውጥንም እንደዛ የሚናፍቁና የሚቀበሉ ጥቂት አይደሉም። በብዙ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ለምትገኘው ለኢትዮጵያ መልካሙን መመኘት፤ ጥሩው እንደሚሆንላት ተስፋ ማድረግና ያንን በእምነት መጠበቅ ትልቅ ኃይል ያላቸው መሆኑ እሙን ነው። ሆኖም፤ ሁሉም እውን እንዲሆኑ ግን ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ አያጠራጥርም። የአዲስ ማለዳው ኢዮብ ትኩዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት፤ የተለያዩ ባለሞያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የዘመን መለወጫ ተስፋን የሚፈነጥቅባቸው በርካቶች ናቸው። ለታመመ ሌቱ ረዝሞበት የንጋትን ብስራት እንደሚናፍቅና ሲነጋ አድኖ የሚያስነሳው አንዳች ተአምር ኖሮ ሳይሆን ንጋቱ የመዳንን ተስፋ እንዲያገኝ፤ የዘመን ለውጥን እንደዛ የሚናፍቁና የሚቀበሉ ጥቂት አይደሉም።

እምነትና ተስፋ ለሰው ልጆች የልቦና ውቅር መሠረት መሆናቸው ይነገራል። እነዚህ ምንም እንኳ ከተጨባጩ እውነት ጋር የማይስማሙ ቢመስሉ እንኳ መሻገሪያ ድልድይ ናቸው። ሆኖም ግን ሥራን መፈለጋቸው እንደማይቀር የማኅበራዊ ዘርፍ ባለሞያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

‹‹ከእንቁሽ ጋር ዝለቂ››

ዓለሙ አያሌው በመሰናዶ ትምህርት ቤት እንዲሁም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለ18 ዓመታት የታሪክ መምህር ሆነው አገልግለዋል።

እኚህ መምህር ከአራት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ስለተፈጠረው ችግር ሲያስቡ እንደ መምህር ተጨንቀዋል፤ እጅጉን ያሳስባቸውማል።

ሆኖም የመጣውን አዲስ ዓመት በምናባቸው ከወዲሁ ሲያሰላስሉ፤ ልባቸው በብሩህ ተስፋ እንደተመላ ይናገራሉ።

የታሪክ መምህሩ ‹‹ከእንቁሽ ጋር ዝለቂ›› በማለት የኢትዮጵያን መጪ ጊዜ እየተጣሩ ያለፈውን ክስተት  አንስተው፤ መውጫ መንገዱ በእምነት እና ተስፋ መሆኑንም ይገልፃሉ።

‹‹ዓለም የደስታና የሀዘን ቅልቅል ስለመሆኗ የሰው ልጅ በየቀኑ የሚገፋው የሕይወት ዑደት ይመሰክራል። ጥሩ ዜና ይሰማል። መጥፎም እንዲሁ። በዓለም ውስጥ ሀዘን እና ደስታ ዝብርቅርቅ እያሉ ቀጥለዋል።›› ሲሉ የዓለምን ባህሪ ጠቅለል አድርገው አስቀመጡ።

ኢትዮጵያም በጦርነት የሞቱ፤ ገና በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ፤ በድርቅ የተራቡ መኖራቸውም አይዘነጋም። ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ የደፈረሰ ሰላሟ ጥርት ብሎ በሰላም  እንድትመጣ በተስፋ እንጥራት ይላሉ።

‹‹ኢትዮጵያ በ2015 አዲስ ዓመት አዲስ ሆና እንድትመጣ በተግባር የሚገለጽ ምኞት፤ በእምነት የተቀረጸ ተስፋ በኢትዮጵያዊያን ሕሊና ሰፊ ቦታ ሊሰጠው ይገባል›› የሚሉት መምህሩ፤ ‹‹ከእንቁሽ ጋር ዝለቂ››ን በግጥም እንዲህ ገለጡት፤

  የመርዶው ቀን ይለቅ፤  የሞት ጀንበር ይጥለቅ

በአዲስ ቀን በአዲስ ልብስ፤  በኅብረት እንድመቅ።

ተስፋችን ይለምልም፤  በእምነት ታርቆ

ምኞታችን ይስመር፤  ጦርነት ርቆ።

አንቺ ውድ ኢትዮጵያ፤  በእንቁሽ አሸብርቂ

- ይከተሉን -Social Media

መልካም ዘመን ይዘሽ፤ ከእንቁሽ ጋር ዝለቂ።

መምህሩም ኢትዮጵያ እንደ አደይ አበባ ፈክታ እንድትመጣ እና ሕዝቦቿ ሀዘናቸውን እንዲረሱ ያላቸውን ምኞት በግጥም አንስተዋል። ‹‹የመርዶው ቀን ይለቅ፤ የሞት ጀንበር ይጥለቅ›› ይሉና በ2014 በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን የተከሰተውን ሰብዓዊ፤ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ቀጣዩ ዓመት ሳይሸጋገር በዚሁ እንዲቆም በተስፋቸውን ይገልጻሉ።

የታሪክ መምህሩ፣ ‹‹አዲስ ዘመንም ሆነ በሌላኛው ወቅት ምኞት፤ እምነት እና ተስፋ በሰው ልጅ ደም ተዋህደው የሚኖሩ የሕይወቱ ክፍል ናቸው። በተግባር ሲገለጹ በሀዘን ፈንታ ደስታን  ያጎናጽፋሉ›› ሲሉም ይናገራሉ።

እምነት፣ ተስፋ እና ምኞት

አሮጌው ዓመት አልቆ ቦታውን ለአዲሱ ዓመት ሲያስረክብ በተለይም ምኞት፤ እምነት እንዲሁም ተስፋ በሰዎች አንደበት ተደጋግመው ሲነገሩ ይደመጣል። እነዚህ ሦስቱ በማንኛውም ወቅት በሰው ልጅ ሕይወት አንዱ ክፍል ስለመሆናቸው የሥነ ልቦና ምሁራን ይናገራሉ።

አዲስ ዓመት ሆነም አልሆነም የሰው ልጅ ጤናማ እና የተሻለ ሕይወትን እንዲኖር ሦስቱ ነገሮች ማለትም ምኞት፤ እምነት እንዲሁም ተስፋ ያስፈልጉታል ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያ፤ በዕርቅ ማዕድ እና በኮሜዩኒኬሽን የምክር አገልግሎት ሰጪ ቴዎድሮስ ድልነሳው ናቸው።

ቴዎድሮስ ምኞት፤ እምነትና ተስፋ ተመጋጋቢ መሆናቸውን በዝርዝር ገልጸው፣ በተለይም በአዲስ ዓመት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ቢገለጹ ለኑሮ መሻሻል ለውጥ አለው ብለዋል።

‹‹ተስፋ ማለት መልካሟን ነገ መጠበቅና መልካም እንድትሆን መጣር ነው። ተስፋ ያለው ነገ አለው። ለነገ ተስፋ የሌለው ደግሞ ለሌላው ይቅርና ለራሱም አይጠነቀቅም። ለራሱ የማይጠነቀቅ ደግሞ ለሌሎች ክፉ መመኘቱ አይቀሬ ነው።›› ይላሉ ባለሙያው።

- ይከተሉን -Social Media

ተስፋ እና ምኞት ደግሞ በእምነት የሚገለጹ ናቸው ብለዋል። ቴዎድሮስ የተለያዩ የእምነት አይነቶችን አንስተዋል። አንዱ እና መጀመሪያው ሰው በፈጣሪው ያለው እምነት ነው። ይህም አንድ ሰው የሚመኘው ጉዳይ ከአቅሙ በላይ ከሆነ፤ እንዲያሳካለት ለፈጣሪው በተስፋ አሳልፎ የሚሰጥበት  ሂደት ነው።

ቀሪዎቹ የእምነት አይነቶች ደግሞ በራስ መተማመን እና ሌሎችን ማመን መሆናቸውን ቴዎድሮስ ይናገራሉ። በራስ መተማመን ሲኖር ምኞት ከተስፋ ጋር ይስማማል። ምንም ሳይሠሩ የተመኙትን አገኛለሁ ማለት ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ይቆጠራል። ታዲያ በራሱ የሚተማመን ሰው የተመኘውንና ተስፋ ያደረገውን ነገር ከቃል ባለፈ ከግብ ለማድረስ በእቅድና በስልት ይመራል ይላሉ የሥነ ልቦና ባለሙያው። እንዲህ ሲሆን ምኞቱን በተግባር ይገለጻልና ነው።

በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ማንኛውም ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ በተደጋጋሚ ይሰበካል። ማንም ቢሆን እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴ፤ ስንዴ ዘርቶ ደግሞ እንክርዳድን ያጭድ ዘንድ እንደማችል በእምነት ተቋማት በኩል በተደጋጋሚ ይነገራል።

ታዲያ በፈጣሪም ሆነ በራስ እንዲሁም በሌሎች በኩል እምነት ማድረግ ለምኞትና ተስፋ መሳካት ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው የተባለው። ለዚህም ነው በየዓውደ ዓመቱ አንዱ ለሌላው መልካም ምኞቱን የሚገልጸው።

ተስፋ እና እውነት

ተስፋና እና አውነት በሚለው አውድም የታሪክ መምህሩ ዓለሙ አያሌው ሐሳባቸውን አካፍለዋል። በአንድም በሌላም መንገድ ተስፋ እና እውነት የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽዎች ናቸው ይላሉ መምህሩ።

‹‹በዓለም ታሪክ መውጫ ቀዳዳ የሌላቸው የሚመስሉ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። ተከስተው ግን አልቀሩም እንዲያውም ያ አልፎ ሌላ የተሻለ የመጣበት አጋጣሚ አለ። ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንዳስስ የሰው ልጅ በጥንት እና በአሁኑ ዘመን ብርሃን የሚያገኝበት መንገድ የሰማይና የምድር ያክል ልዩነት አለው።

በመጀመሪያ እሳት የሚያገኘው ኹለት ድንጋዮችን በማጋጨት ከሚፈጠረው ብልጭታ ነበር። አሁን ግን የኤሌክትሪክ ብርሃን ተጠቃሚ ሆኗል። ከጨለማ ወደ ብርሃን ከብረሃን ደግሞ ወደ ተሻለ ብርሃን ተሸጋግሯል። ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ በጨለማ ብቻ እንደሆነ እንደማይቀር ነው። የተፈጠሩ መሰናክሎች ቀኑ ይረዝማል እንጂ ለለውጥ በር ከፋች ናቸው። ምክንያቱም ችግር ብልሃትን ይፈጥራል።›› ሲሉ መጥፎ ክስተት እንደተከሰተ እንደማይቀር ጠቅለል አድርገው ያስረዳሉ።

- ይከተሉን -Social Media

አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያም አሁን ካለችበት ዘመን የደረሰችው ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ብዙ የጦርነት ሜዳዎችን፤ ድርቅ፤ ርሃብ እና ሌሎች ክስተቶችን ድል በመንሳት እንጂ፣ እንዲሁ አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ አይደለም›› በማለት ያስታውሳሉ።

በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግፉ የበረታ ይመስላል። ዳሩ ግፍ ሲበረታ ጥንካሬም ተከትሎ ይመጣል ይላሉ። ‹‹እርግጥ ነው በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ የተራበ እና በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚኖርም አለ። ይሁን እንጂ ተስፋ ካለ ኹሉም መስተካከሉ፤ መቀየሩ አይቀርም።›› ይላሉ።

ይማም አብዱላዚዝ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ናቸው። በበኩላቸው በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሰው ልጅ የሚሞተው ተስፋ የቆረጠ እለት ነው ሲሉ ተስፋ በመቁረጥ የሚመጣውን ከባድ ችግር ያስረዳሉ።

በተያያዘም፤ እስከዛሬ የተከሰተውን ክፉ ገጠመኝ ማሰባችን ለመተከዝ ሳይሆን፤ የመፍትሔ፤ የመውጫ መንገድ ለመፈለግ መሆን አለበት ብለዋል። ‹‹2015 ገመገም ላይ ቆሞ 2014ን እያሰቡ መቆዘም ተስፋ ቢስነትን ያሳያል። ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ እንደሚባለው፣ ተስፋ በማድረግ ነገን የምንጠብቅ ከሆነና ባቀድነው ልክ ከሠራን፤ አላህም ስለሚያግዘን ነገ የተሻለ ይሆናል።›› በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።

ብዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ እውነታ ያሳስባቸውና ‹‹በቃ ተስፋ ቆርጫለሁ›› ሲሉ ይደመጣሉ። በተጓዳኝ ደግሞ በተለይም አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ተስፋ በመሰነቅ ሰላም በሰፈነባት አገር አዲስ ሕይወት ለመኖር ያቅዳሉ።

‹‹አንድን ነገር ጉድለቱን ብቻ በመገንጠል ስለ አሉታዊ ነገር ብቻ ማሰብ የኹኔታውን ሙሉ ግንዛቤ እንዳይኖረን ይዳርጋል>> ብለዋል ቴዎድሮስ። በተያያዘም፤ የሰው ልጅ ከጦርነት ርቆ አያውቅም። ብዙ ቦታዎች ችግሮች መኖራቸው አይካድም። ነገር ግን አስተውለን ካየን ከዚህ በፊት የተከሰቱ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮችም እንዳሉም ማስታወስ ይገባል ነው ያሉት ባለሙያው።

እናም ነገሮችን በሰፊው በማየት እና ከጨለምተኝነት በመውጣት አዲሱን ዘመን በደስታ ተቀብለን ተስፋ እና ምኞታችንን እውን ማድረግ እንችላለን›› ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ተስፋ የማደረግ ጥቅም

ተስፋ ለሰው ልጅ ትልቅ ቁልፍ ነው የሚሉት የሥነልቦና መምህርቷ ትዝታ ወርቁ ናቸው። ትዝታ፣ ሃይማኖትም የሚያስተምረን እምነት፤ ተስፋ እና ፍቅር ለስጋም ሆነ ለነፍስ ስለሚያስፈልጉ ነው ይላሉ።

አስከትለውም ‹‹በመሆኑም ተስፋ ትልቁ የሕይወት መሪ ነው። የሰው ልጅ ተስፋ ከሌለው ተኝቶ ለመነሳትም አይፈልግም፤ ተስፋ ከሌለው አያስብም። ዓላማ አይኖረውም። ዓላማ ከሌለው የሕይወት ትርጉም አይገባውም። በጥቅሉ ተስፋ የሌለው ሰው ከባህር እንደወጣ አሳ ነው›› ሲሉ አጠር አድርገው ገልፀዋል።

ተስፋ በሚያደርግና በማያደርግ ሰው መካከል ያለው ልዩነትም በሕይወት የመኖርና ያለመኖርን ያክል ነው ይላሉ። እንደ ገለጻቸው ከሆነ፤ የሰው ልጅ እየኖረ ነው የሚባለው ለነገ እቅድና ዓላማ ሲኖረው ነው። እቅድና ዓላማ ደግሞ መሠረታቸው ተስፋ ማድረግ ነው ይላሉ።

የሥነ ልቦና አማካሪው ቴዎድሮስ በበኩላቸው፣ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይም ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ሕይወትን ከነ ሙሉ ውጥንቅጧ ዐይተን በተወሰነ መልኩ ከተስፋ ጋር መቆም አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።

ተስፋ ያለው ወጣት ትምህርቱን መጨረስ እንዳለበት፤ ትዳር መሥርቶ እንደሚወልድ፤ ሲወልድ ልጁን ማስተማር እንዳለበት ወ.ዘ.ተ… በማቀድ ነገውን ዛሬ ላይ ሆኖ ያመቻቻል። ይህም ተስፋ ማድረግ ነው ይላሉ።

ተስፋ ብቻውን?

ተስፋ ማድረግ ብቻ ግን ለውጥ ይሆናል? ተስፋ ብቻ ለውጥ ከሆነማ ሰው ተስፋ ያደረገበት ጊዜ መች ትንሽ ነበር የሚሉም አሉ። አንዱ ዓመት ተገባዶ ሌላኛው ሲተካ በአዲስ ምዕራፍ የተሰነቁ አዳዲስ ተስፋዎች በሰው ልጆች ልብ ይመላሉ። ይህ በየዓመቱ ሰንሰለቱን ጠብቆ የሚከናወን የሰው ልጆች የዘመን ሀቅ ነው።

ይሁን እንጂ ተስፋ ብቻ ለውጥ አይሆንም የሚሉም አሉ። ተስፋ ብቻ ለውጥ አይሆንም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ ሱራፌል አያሌው ናቸው። በርግጥ ተስፋ ከሌለ እውነት የለም ማለት ነው ብለው፤ እውነት ደግሞ መሠረቱ ተግባር መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

‹‹ለምሳሌ መንግሥትም በ2015 ጦርነት፤ መፈናቀል፤ ርሃብ እንዳይደገም ሊመኝንና ተስፋ ሊያደርግ ይችላል። ግን ያ ብቻ አይበቃም። ሕዝብም መንግሥትም የድርሻውን መወጣት ግድ ይላቸዋል።›› ነው ያሉት።

ተስፋ እውን ሆኖ 2015 መልካም ዘመን የሚሆነው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ወይም አንድ ሌላ ማንኛውም ግለሰብ የእንኳን አደረሳችሁ ምኞታቸውን ስላስተላለፉ ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ያ ግለሰብ ምኞትና ተስፋውን በተግባር ሲገልፁ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

‹‹በ2014 እንደተደረገው ሰው እየተነቀለ ችግኝ የሚተከል ከሆነ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፤ የመፈቃቀር፤ የመተሳሰብ ይሁንልን፤ ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ የሚለው የተስፋ ቃል ብቻ ለውጥ እንደማይሆን መገንዘብ ይገባል››  ሲሉ ያሳስባሉ።

የሰው ልጅ ሕይወት በጦርነት እያለፈ፣ መንግሥት ግን ከአንዱ እስከ ሌላኛው የክረምት ወቅት ሲያሳስበው የነበረው የችግኝ ተከላ እንደነበር ያስታወሱት ሱራፌል፤ በ2015 ተመሳሳይ የጦርነት አውድማ እንዳይፈጠር አንገብጋቢ መፍትሄ የሚያስፈልገውን ችግር ቅድሚያ መፍታት ይገባል ብለዋል።

መንግሥት በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር የማስቆም ሙሉ ኃይል እንዳለው የሕግ አማካሪው ተመስገን ፈንታው በበኩላቸው ይናገራሉ። ይህን ለማረጋገጥም ሕወሓት የአማራ ክልልን አብዛኛውን ቦታ፤ የአፋር ክልል በኩል በከፊል መቆጣጠር ችሎ መንግሥት ሲነሳ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ነበረበት እንዲመለስ መሆኑ በቂ ነው ይላሉ።

የሕግ አማካሪው የሕወሓት ቡድን ካወደማቸው ስፍራዎች ሳይደርስ መንግሥት ማስቆም ይችል ነበር ሲሉ ነው።

በሌላ በኩል ብሔር ተኮር ተግባር ሲከናወን ይስተዋላል ያሉት አማካሪው፤ ድርጊቱ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ያላካተተ በመሆኑ ሌላኛው ትኩሳት ነውና አዲሱ ዓመት ሰላም የፍቅር እንዲሆን ሌሎች መሰል አካሄዶችን መንግሥት ማስተካከል አለበት ሲሉ መክራሉ።

አገር ከጫፍ እስከ ጫፍ በምትታመስበት ወቅት ስለሌላ ነገር ማሰብ እዚሁ 2014 ላይ መቅረት እንዳለበትም ያምናሉ።

የሰብል ክምር ተቃጠለ ሲባል ችግር ከመቅረፍ ታቅቦ ሌላ ብቋያ መጎብኘት፤ ሕዝብ እየተገደለ ስለወሰን ማካለል መቃተት፤ ሰዎች እየሞቱ ለቤተ መንግሥት ግንባታ 2.2 ቢሊዮን ብር ማውጣትና የመሳሰለው በቀጣዩ ዓመትም የሚደገም ከሆነ ተስፋ ብቻውን ለውጥ ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው።

ቴዎድሮስ በበኩላቸው፣ ስለ ጦርነቱም አንስተው ‹‹ጥናቶች የሚያሳዩት ዝቅተኛ ጦርነት ያለው በዚህ ዘመን እንደሆነ ነው ብለው፣ ኹሉም ነገር በሂደት እንደሚለወጥ ተስፋ ማድረግ ይገባል ብለዋል። አክለውም፤ ሕይወትም ትርጉም የሚኖረው በተስፋ ተጠንስሶ በተግባር ሲገለጽ ነው፣ ሀዘን ከሌለ ተስፋ የለም። ተስፋ የምናደርጋቸውንና የምንመኛቸውን ነገር ግን መለየት ይገባል ብለዋል።

በዚህ ጽሑፍ ምክራቸውን የለገሱን የታሪክ መምህሩ፤ የሥነ ልቦና ባለሙያዎቹ፤ ሕግ አማካሪው  እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኙ ለመላሙ ኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን ገልጸዋል። አዲሱ ዓመት የሠላም፤ የመፈቃቀር እንዲሆን ተመኝተዋል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች