መነሻ ገጽዜናወቅታዊየ2014 ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች

የ2014 ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች

አምና ተብሎ ሊጠራ ሰዓታት ብቻ የቀረው 2014 በዜጎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ በርካታ እንግዳ መሰል ክስተቶች የተከሰቱበት ዓመት ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

በዚህ ምድር ላይ 69 ዓመት ኖሪያለሁ የሚሉ አባዎራ ‹‹በጭራሽ ይህ ዓመት መደገም የሌለበት ነው። በሕይወቴ በኖርኩበትም ሆነ ስለጥንት ከሰማሁትም እንደዘንድሮው ያለ ክፉ ዓመት አገራችንን አላጋጠማትም።

ሰው ድሮም አሁንም ይገዳደላል፣ ኢትዮጵያዊ ሆነን ግን በዘር ይህን ያህል ስንቧደንና ስንገዳደል የመጀመሪያችን ነው። ኑሮ ተወዶ ጥቃቅን ነገር ሳይቀር ከሰማይ የራቀንም በዚህ ዓመት ነው። ደግሞ ይኽ ዓመት ምን ያላሳየን አለ?›› ባይ ናቸው።

ወጣት እፀገነት በላይ (የአባቷ ሥም የተቀየረ) ደግሞ ‹‹2014ን መጥፎ ወይም መልካም የሚያስብል ምንም የተለየ ነገር የለም። እንደ አገር ካየነው አምናም በፊትም ዘንድሮም ድሆች ነን። ብዙ ነገራችን መሠረታዊ ለውጥ አልታየበትም። ሰዎች ይህን ዓመት የተለየ መጥፎ አድርገው ሲያወሩ እሰማለሁ፣ እኔ ግን በዚህ አልስማማም። ምናልባት ክፉ ነገር ስላልደረሰብኝ ከሆነ ተሳስቻለሁ›› ነው የምትለው።

ፖለቲካ

አሁን ያለው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመተንተንና ለማስረዳት የሚከብድ መሆኑን ብዙዎች ሲሉት የነበረ ነው። በ2014 በፖለቲካው ዘርፍ ጎልተው ከታዩ ነገሮች ቀዳሚው የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሳይሆን አይቀርም።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት መስከረም 24/2014 በመመሥረቱ፣ ከዚያ በመለስ ያለውን ጊዜ አዲስ ምዕራፍ በሚል መጠሪያ ሰጥቶታል።

ለብዙዎች ግልጽ እንደሆነው ብዙ የተባለለት አዲስ ምዕራፍ ሲባል በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው፣ በኹሉም ዘርፎች በጎ በጎ የሆኑ ለውጦች የሚስተናገዱበትና አገርም የተሻለ ቁመና ላይ መገኘት የምትችልበት ማለት ነው።

ይሁን እንጂ፣ ከአዲስ ምዕራፍ በኋላ የተከሰቱ ዐበይት ክስተቶችን ዋቢ አድርገው የሚናገሩ ሰዎች አዲስ ምዕራፍ ‹በሕዝብ ላይ የተነዛ ፌዝ› ነው ማለታቸው አልቀረም።

ከሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም ከቀደመው የኢሕአዴግ አገዛዝ ጋር በተገናኘ በሕዝብና መንግሥት ዘንድ ሰፊ ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩ የሕወሓት ቀንደኛ አመራሮች፣ የፖለቲካ ሥነ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በይቅርታ ሰበብ መፈታት ለሕዝብ ዐይንና ጆሮ ድንገተኛ ነበር።

ይህ የሆነው በጥር ወር መባቻ ሲሆን፣ በአሻባሪነት በተፈረጀው የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የክስ መዝገብ ስር የተካተቱት እነ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የቀድሞ የሕወሓት አመራሮች ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል።

ይህ ድርጊት ሕግን የጣሰ ነው ከመባሉ ባለፈ በፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ተማክሬ አላውቅም የሚል ቅሬታውን ያጎላ እንደነበር በሰፊው ተወርቷል።

እንዲሁም፣ ብዙ መጣረሶችና ልዩነቶችን በአግባቡ በመፍታት አገራዊ መግባባትን ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በይፋ ሥራውን የጀመረው በ2014 መጋቢት ወር እኩሌታ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።

የፖለቲካ ሥነምህዳሩ ሰፍቷል በሚባልበት ሁኔታ በተቃራኒው በርካታ ጋዜጠኞች የታሰሩበት፣ ሰዎች ከቤታቸው ታፍነው የሚወሰዱበትና ለቀናት የት እንዳሉ የማይታወቁበት ዓመትም ነበር።

በ49 ቢሊዮን ብር አዲስ ቤተመንግሥት ሊገነባ መሆኑ የተጠቆመውም በዚሁ በ2014 ነው። ከዛም ባሻገር ትልቅ ትኩረት የሳበው ሕዝብ ያልተሳተፈበትና የገዥው ፓርቲ የተናጠል ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነ በማንሳት ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ የሚነገርለት የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወሰን የተካለለበትም ዓመት ይኸው 2014 ሆኗል።

የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የዘረጋውን ከቀረጥ ነጻ ዕድል ለኹለት ዐስርት ዓመታት የተለያዩ ምርቶችን በመላክ ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ከዚህ ዕድል መታገዷም የዚህ ዓመት ክስተት ሆኖ አልፏል።

- ይከተሉን -Social Media

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት እንዲሁ በኢትዮጵያ ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።

‹‹የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሕግ›› በሚል የቀረበው ይህ ረቂቅ ተፈጻሚ ቢሆን የጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ አስገዳጅ ሕግ የሚጥል ነው በማለት አዎንታዊ ድጋፍ ከሰጡት ሌላ፣ ተራው ዜጋ ሠርቶ እንዳይኖር ያደርጋል በሚል ሰፊ ተቃውሞ የቀረበበትም ነበር። “ኖ ሞር” ወይም “በቃ” በሚል ምዕራባውያንም ላይ የተቃውሞ ዘመቻ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የተካሄደበት ዓመትም ነበር።

ሆኖም በ2014 ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው ዓለም ዐቀፍ ጫናዎች በጉልህ ሊጠቀስ የሚችለው ‹‹HR 6600›› ረቂቅ የፕሬዝዳንቱ ፊርማ ሳያርፍበት በመቅረቱ እውን ሳይሆን ቀርቷል።

ሌላው ከዲፕሎማሲ ጋር የተገናኘው የዓመቱ ክስተት ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት ግንኙነታቸውን ያደሱት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ነበር።

ብዙ ጊዜ የኹለት አገራት ግንኙነት በኹለት ነጠላ መሪዎች ሲወሰን ይታያል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትንም ከዚህ ጎራ በመመደብ፣ ግንኙነቱ ተቋማዊ ይሁን በማለት ብዙዎች ሲጠይቁ ነበር። የኹለቱ አገራት ግንኙነት ምን መመስል እንዳለበት ሕዝብ ያልተወያየበት ጉዳይ መሆኑም ግልጽ ነው።

ይሁን እንጂ፣ የታሰበው ተቋማዊና ሕዝባዊ ትስስር እስኪፈጠር ባለበት ቢቀጥል መልካም የነበረ ቢሆንም፣ የኹለቱ መሪዎች ግንኙነት ጫጉላውን ጨርሶ ወደ ማብቂያው ደርሷል ሲባልም ይሰማል።

በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር ላይም ለዚሁ አሉባልታ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ፣ ኤርትራ ለሦስት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን በዲፕሎማት የሚመራ ግንኙነት ደረጃውን ዝቅ አድርጋ ጉዳይ አስፈጻሚዋን ወክላለች።

ዓመቱ በአንድ ዓመት ኹለት ጊዜ ጦርነት የተካሄደበት ጊዜም መሆኑ ይጠቀሳል። በሽብርተኛነት የተፈረጀው ሕወሓት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የጀመረውን ጥቃት ገፍቶ በአፋርና አማራ ክልሎች በርካታ ጥፋቶችን ያደረሰበት ዓመት ከመሆኑም ባሻገር፣ ሕወሓት በአገር ህልውና ላይ የደቀነው አደጋ ተቀልብሷል የተባለበትና የመጀመሪያው ምዕራፍ በተባለ የዘመቻ ኦፕሬሽን ቡድኑ ደብረ ሲና ደርሶ ዳግም ወደ መቀሌ ተመልሶ የመሸገበት ወቅት ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

እንደገናም የደረሰው ጥፋት ባላገገመበት ሁኔታ ከአምስት ወራት በኋላ፣ በነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንታት አዲስ ጥቃት ከፍቶ ጦርነቱ ለሦስተኛ ዙር ማገርሸቱ የማይዘነጋ ነው።

እንዲሁም፣ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቃ በመግባት ሰፊ መሬት የያዘችበት፣ አልሸባብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት ውጊያ የከፈተበት ዓመትም ነበር። የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ልትውል የነበረበት ጥቃት የካሄደበትም ዓመትም ነው፤ 2014።

ቀደም ብሎ የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ሊደራደሩ ይችሉ ይሆን የሚል ከፍተኛ የሕዝብ ጥርጣሬ የነበረ ሲሆን፣ በኋላም መንግሥት ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ በሚል ከቡድኑ ጋር ለመደራደር በይፋ በመናገር የድርድር ሂደቶችን ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል።

በዓመቱ የክልልነት ጥያቄ በስፋት የተነሳ ሲሆን፣ በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ካሉ ብሔሮች በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ ከርመዋል።

12ኛ ክልል እንዲቋቋም በመንግሥት ውሳኔ ከመሰጠቱም ሌላ፣ የመንግሥትን የክላስተሪንግ አደረጃጀት በመቃወም ራሴን በራሴ አስተዳድራለሁ በማለት ሲሟገት የከረመው የጉራጌ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር የነበረው መካረርም በ2014 መጨረሻ አካባቢ ጎልቶ የታየ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው።

ኢኮኖሚ

በ2014 ዓመት ኢኮኖሚው ዘርፍም በርከት ያሉ አበረታች የሚባሉ እንዲሁም በአሉታዊ መልኩ የሚገለጹ ክስተቶች ተስተናግደዋል።

በተለይ ግን ብዙ ያስባለውና ከዚህ በፊት ባሉት ዓመታት ያልታየው የኑሮ ውድነት በዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከባድ ጫና አድርሷል። በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋቸው ከኹለትና ሦስት እጥፍ በላይ ነው ያደገው። በዚሁ ዓመት የተከሰተው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት የኑሮ ውድነቱን ከእስካሁኑ እንዳባባሰው ይታመናል።

- ይከተሉን -Social Media

ሲሚንቶ በዚያኛው ዓመት 600 ብር ገደማ ድረስ ይሸጥ ከነበረበት በዚህ ዓመት እስከ 1 ሺሕ 800 ብር ደርሷል።

ዘይትም እንዲሁ በሊትር ከእጥፍ በላይ የጨመረው በዚሁ ዓመት ነው። ነዳጅ እስካሁን ሲሸጥ ከነበረበት የድጎማ ስርዓት ተላቆ አንድ ሊትር ከኻያ ብር በላይ ጭማሪ የተደረገበትም በተገባደደው ዓመት ነው።

የአገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ ለሆነው የግብርና ዘርፍ ግብዓት የሆነው የአፈር ማዳበሪያም ዋጋው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኩንታል ሦስት እጥፍ መጨመሩ የሚታወቅ ነው።

በአንጻሩ የኢትዮጵያ የወጭ ገቢ ንግድ ገቢ በዚሁ በጀት ዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ መግባቱ እንደ በጎ ተወስቷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ፣ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ሂደት 88 ከመቶ መድረሱ እንዲሁም የኹለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ሌሎች የዓመቱ በጎ ውጤቶች እንደነበሩም የሚዘነጋ አይደለም።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ተግባር ላይ የዋሉበት፣ የመጀመሪያውና ብቸኛው ነጻ የንግድ ቀጠና የተቋቋመበት እንዲሁም ለባንክ እድገትና ተደራሽነት ሚና ያላቸው ተጨማሪ አዳዲስ ባንኮች ሥራ የጀመሩበት ብሎም የባንክ ዘርፉ ለውጭ ገበያ ክፍት እንደሚሆን ውሳኔ የተሰጠበት ዓመት ሆኖ አልፏል።

በርካታ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ በሚል በየቦታው የመሠረት ድንጋይ ተጥሎላቸው የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው የሚነገር ቢሆንም፣ በዚሁ ዓመትም ጉልህ ፋይዳ ላላቸው ትላልቅ የመሠረት ልማት ግንባታዎች ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ታይቷል።

በማኅበራዊ ሕይወት ረገድም ዓመቱ ብዙ ምስቅልቅሎች የታዩበት እንደሆነ ብዙ ተብሏል። በየቦታው በሚከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም በመንግሥትና ግለሰቦች ደረጃ በሕግና ስርዓት የመመራት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ እንደ ማኅበረሰብ ብዙ መልካም እሴቶች የተሸረሸሩበት ጊዜ እንደነበር ብዙዎች ሲጠቅሱ ይሰማል።

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስህተት እንደሆኑ የተነገረላቸው ክስተቶችም እንዲሁ የብዙዎችን ማኅበራዊ ሕይወት አናግተው ማለፋቸው ሳይጠቀስ አይታለፍም። በተለይ ብዙ ወላጆችንና ተማሪዎችን ያስከፋው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት፣ እንዲሁም ብዙ ሌብነት የተፈጸመበት የ14ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ይገኙበታል።

በውጭ አገር የስደት ኑሮ ሲሰቃዩ የነበሩ እጅግ በርካታ ዜጎች ዓመቱን ሙሉ በተለይ ከሳውዲ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተመልሰዋል።

በጥቅሉ ዓመቱ በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የተስተናገዱበት ነው። ማኅበረሰቡ እንደሚመሰክረውና መንግሥትም እንደሚለው ሌብነት (ሙስና) ከእስካሁን ብሶ የታየበት፣ በአገሪቱ በርካታ ቦታዎች ዜጎች በሰላም ወጥተው የማይመለሱባቸው ሆነው መክረማቸው በብዙዎች አይዘነጋም። ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ አትገቡም ተብለው ለወራት ዜጎች የተቸገሩበትና በመንግሥት ውሳኔም የተማረሩበት ወቅት ነበር።

በርካቶች ይህ ዓመት (2014) ለሬሳ ሳጥን ሻጭ እንጂ ለሌላው ሕዝብ ክፉ ዓመት ነበር በሚያስብል መልኩ እንዲህ ዓይነት ዓመት መልሶ አይምጣብን ሲሉ ይደመጣሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች