መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየሰላሙ ዘንግ ብረት

የሰላሙ ዘንግ ብረት

ኢትዮጵያ ሰላም ከራቃት ዓመታት ቢቆጠሩም አብዛኛው በተቻለው ሰላሟን ለመመለስ ሲጥር ይታያል። የተወሰነው ደግሞ ያለውና የቀረው ሰላምም እንዲደፈርስና መልሶ እንዳይመጣ ሌት ተቀን ሲማስን ይኖራል። ይህ በተቃራኒ የቆመ ፍላጎት እያለ መንግሥትም ይሁን ተቋማትና ግለሰቦች የጠፋው ሰላም እንዲመለስ አሁንም ሲወተውቱ ይሰማል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ሰላም እንዲመጣ ብሎ በከፍተኛ ወጪ የሰላም ሚኒስቴር የሚባል ግዙፍ ተቋማትን የጠቀለለ መሥሪያ ቤትን አቋቁሞ ነበር። ይህ ተቋም የምሥረታው ሰሞን ደፋ ቀና ሲል በሚዲያዎችም አይጠፋም ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የሰላም መደፍረሱ ሲብስበትና ጦርነትም ወቅታዊ መሆኑ ቀርቶ ዘላቂ ሲሆን ቀስ በቀስ ደብዛው እየጠፋ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

የሰላምን አስፈላጊነት የተጠየቀ ሁሉ የሚናገረው ነገር እንዳለ ሆኖ፣ በተቃራኒው ደግሞ ያለ ጦርነት ዘላቂ ሰላም አይመጣም የሚሉም በርካቶች ናቸው። ድምጻዊት ማሪቱ ለገሠ በአንድ ሥራዋ ‹የሽንፈት ሰላም ሰላም እንዳልሆነና እንደማይሻል› የተናገረችበት ስንኝንም የሚቀበሉ አሉ።

ያም ተባለ ይህ፣ ሰላምን ለማምጣት ጦር ማዝመትና የፀጥታ ኃይልን ማሰማራት የሚጠበቅበት መንግሥት ሌሎች አማራጮችንም ሲያማትር እየተመለከትን እንገኛለን። ጳጉሜ ሦስት የሰላም ቀን ተብሎ ተሰይሟል። ‹‹ይህም ተመስገን ነው፣ ጳጉሜ ስድስት ሆኖ በየአራት ዓመቱ ብቻ በሰላም እንዳያውሉን›› ብለው የተሳለቁ ነበሩ።

የሰላም ቀን ተብሎ መዘከሪያም ይሁን ማክበሪያ እለት መመደቡ በሐሳብ ደረጃ ችግር የለውም ያሉ፣ አከባበሩ ወይም ታስቦ የሚውልበትን መንገድ ሲተቹ ታይተዋል። ጥንት ሰላም በነበረበት ዘመን የነበሩ ትውስታዎችን እያስታወሱ፣ ኢትዮጵያዊ የፈለገበት ሲጓዝና የመረጠበት ሰፍሮ ሲኖር እያሳዩ ቢያስተክዙን ይሻል ነበር ያሉ አሉ።

የጎዳና ላይ ሰልፍም ይሁን “ወክ” ለሰላም ምን ጥቅም አለው ያሉ፤ በከፍተኛ ወጪ በርካታ መኪኖችን ተከራይቶና መንገድ ዘግቶ የኅብረተሰቡን ሰላም መንሳት እንዳይሆን እያሉ የቀለዱ አልጠፉም። እንዲሁም በየጎዳናው ክላክስ እያደረጉና በስፒከር እያጮኹ አንጻራዊ ሰላም ያለባት ዋናዋ መዲና ውስጥ መለፈፉ ምን ጥቅም አለው ያሉ አሉ።

ምነው ሰላም ወደራቃቸው አካባቢዎች ተጉዘው ሰላምን ሌት ተቀን ለሚመኙና ለነፈጓቸው ቢሰብኩ ያሉም ነበሩ። የሰላም መንገድ ተብሎ አንድ ጎዳና መሰየሙም የሌላው መንገድ ሰላማዊነት ለእንግዶቻችን አጠያያቂ እንዳያደርገው ያሉም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ከሁሉም አስተያየቶች የተለየው የመጀመሪያው “የሰላም ፖል” ተብሎ አንድ ባንዲራ መስቀያ የብረት ዘንግ መቆሙ በብሥራት መልክ መነገሩ ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ ያለችውን ርግብ ሐውልት ይሠሩላታል ብለው የጠበቁ እንዳሰቡት ሳይሆን፣ ለምታርፍበት ይሁን ለምትመለከተው የሚሆን ቋሚ ብረት ተተክሎላታል።

አንዳንዶች ስለብረት ዘንጉ ከሰጡት አስተያየት መካከል፣ አንዳንዶች ሠላም ስናጣ ሮጠን ታቅፈን የሰላም ያለህ የምንልበት ይሆን ብለውም ቀልደዋል። እንዳይርቀን በየአካባቢው ቢተከልልን ያሉም ነበሩ።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች