ከ1 ሺሕ 400 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የውጭ ትምህርት እድል እንደተመቻቸላቸው ሚኒስቴሩ አስታወቀ

0
2779

በ2014 በጀት ዓመት ከ1 ሺሕ 400 በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የውጭ ትምህርት እድል እንደተመቻቸላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የውጭ ትምህርት እድል ክፍል ኃላፊ ኤርዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ ሚኒስቴሩ በየዓመቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የውጭ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ከተለያዩ አገር መንግሥታት ጋር አብሮ ይሠራል።

በዚህ መሠረት በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 1 ሺሕ 450 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የውጭ አገር የትምህርት እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት መቻሉን ኃላፊው ጠቁመዋል።

እነዚህ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ50 በላይ ከሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች እድሉን ያገኙ ናቸው።

ቻይና፣ ሀንጋሪ፣ ፖላንድ፣ ራሺያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ የትምህርት እድሉን የሰጡ ናቸው ተብሏል።

አብዛኛውን አሃዝ የሚሸፍነው በኢትዮጽያ የማይሰጡ እና የማይኖሩ የትምህርት ዘርፎች ሲሆኑ በኒኩለር፣ ስፔስ ሳይንስና በሌሎች የምህንድስና ትምህርት ዓይነቶች፣ በኢኮኖሚክስ እና ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ውስጥ የሚገኙ የዶክትሬት የትምህርት ዘርፎች መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

የውጭ የትምህርት እድሉን ያገኙ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ያላቸው እና በኢትዮጵያ በሚገኙ የተማሩበት ትምርት ቤት መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ መሆናቸውም ተነግሯል።

ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን የአውሮኘላን የበረራ ትኬት እንደሸፈነ እና ሌላው የትምህርት ወጪ በየአገራቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሸፍኑ ተነግሯል።

ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ የመንግሥት እንዲሁም ለግል ትምህርት ተቋማት እድል እንዲያገኙ ከተለያዩ አገራት ጋር በየዓመቱ በጥምረት ይሠራል ተብሏል።

በተያያዘ ኢትዮጵያም በየዓመቱ ለሌሎች ጎረቤት አገራት ነጻ የትምህርት እድል የምትሰጥበት ሂደት እንዳለም ኃላፊው አስረድተዋል።

ከዚህ ውስጥ ለሶማሊያ፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለኬኒያ እና ሌሎች አገራት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኹለተኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል እንደሚሰጥ እና ይህም በመንግሥታት የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲሁም ውይይት የሚያልቅ ነው።

ይህ የነጻ ትምህርት እድል በየዓመቱ እንደሚሰጥ እና እስካሁን ባለው ለሶማሊያ ብቻ ከ400 ላላነሱ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድሉ የተሰጠ ሲሆን፣ የሌሎች አገራት ቁጥራዊ መረጃ ለጊዜው በማስረጃ ላይ ተደግፎ ለመግለፅ እንደማይቻል ኃላፊው ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በባለፈው ዓመት እንዲሁ ራሳ ከተሰኘ የግል ኩባንያ ጋር በሕንድ አገር ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙ አይዘነጋም።

እነዚህ ነጻ የትምህርት እድሎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ እና ኩባንያው ከዚህ በፊት ከአንድ ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በሕንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች እና መስኮች ነጻ የትምህርት እድል ሲሰጥ መቆየቱም ተወስቶ ነበር።

በቀጣይ ከአምስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል እንደሚሰጥም መጠቆሙ ይታወቃል። ነጻ የትምህርት እድሎቹ ሕንድ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ ሲሆኑ፣ አጫጭር ሥልጠና፣ የዲግሪ፣ የማስተርስ እና የፒ.ኤች.ዲ. ፕሮግራሞችን ያካተተ እንደነበርም ተወስቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here