መነሻ ገጽዜናትንታኔየሐሰተኛ የትምህርት መረጃ መበራከት

የሐሰተኛ የትምህርት መረጃ መበራከት

በ15 ሺሕ ብር ዲግሪ ገዝተው የባንክ ቤት ሥራ እንደጀመሩ አልደበቁም። ከዚህ በፊት ሲሠሩ የነበረው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ነው። ዮሐንስ አስራት (ለዚህ ዘገባ ሥማቸው የተቀየረ) ከአንድ የግል ኮሌጅ የማኔጅመንት ዲግሪ ገዝተው ቀድሞ የነበሩበትን የሥራ ዘርፍ ከሳምንት በፊት ለቀው ሌላ ሥራ እንደጀመሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እውነታውን ተናግረዋል።

በርካታ ሰዎች እኮ ከዲግሪም አልፎ ማስተርስ ይገዛሉ ሲሉ ገለጻቸውን ጀመሩ። ግለሰቡ በርካታ የሥራ ባልደረቦቻቸው ከዲግሪም አልፈው ማስተርሳቸውን ጭምር በብር መግዛታቸውንና አሁን ከበፊቱ የተሻለ ደመወዝ እየተከፈላቸው መሆኑን እንደሚያውቁ በመግለጽ ንግግራቸውን ቀጠሉ። አሁን ላይ ከሌላው ተቋም በተለየ መልኩ የተሻለ ክፍያ ያለው በባንክ የሥራ ዘርፍ ነው ሲሉ ዲግሪ የገዙት የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት መሆኑን አብራሩ።

እንደ ግለሰቡ ገለጻ ከሆነ፤ ዲግሪ የገዙት ተበድረው ነው። ተበድረው እስከመግዛት ያደረሳቸው አንገብጋቢው ችግር ደግሞ በአነስተኛ ደመወዝ ቤተሰብ ማስተዳደር ከኑሮ ውድነቱ ጋር ስላልታረቀላቸው ነው።

‹‹በሦስት ሺሕ ብር ደመወዝ የቤት ኪራይ ከፍዬ፣ ሦስት የቤተሰብ አባሎቼን ማስተዳደር አቀበት ስለሆነብኝ ሥራ ለማግኘት ዲግሪ ገዛሁ።›› ያሉት ባለታሪኩ፤ በገዙት ዲግሪ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ግን ሕሊናቸው ‹‹አንተ አጭበርባሪ›› እያለ በየሰከንዱ እንደሚወቅሳቸው በመጸጸት ያወሳሉ።

ግለሰቡ ዲግሪ ለመግዛት በተለይ የገፋፏቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው ሲሆኑ፤ ‹‹አንተ ብቻ ታማኝ ሆነህ የሕዝብን ችግር አትፈታ። ይልቅ ለምን በችግር ትቆራመዳለህ›› የሚል ምክራቸው በተለይም የባለታሪኩን ልብ ዘልቆ ገባ።

‹‹እውነታቸውን እኮ’ነው። አሁንስ ቢሆን እኔ ብቻ የሕዝብን ችግር እፈታለሁ እንዴ!›› በማለት የተቸራቸውን ምክር ሳያቅማሙ እንደተስማሙበት ያስታውሳሉ።

ቀጥለውም ‹‹ዲግሪውን ልግዛ የሥራውን አሠራር ግን ከጓደኞቼ ልማር›› በሚል እሳቤ ሐሳባቸውን እውን አደረጉት። ታዲያ በቅርቡ የነበሩበትን የሥራ ዘርፍ ለቀው አዲሱን የሥራ ዘርፍ ይቀላቀሉ እንጂ፣ ጉዳዩን የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች ባንክ ቤት ሲያገኟቸው ሰውነታቸው ሽምቅቅ እንደሚልም አልደበቁም።

አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ግን ‹‹ከእውነት ጋር ተጣልቼ፤ የሐሰት እንጀራ እየበላሁ መሆኔ ሰላሜን ነስቶኛል። ልጆቼ ከኔ ምን እንደሚማሩ ሳስብ ጨንቆኛል›› ይላሉ። ከሚከፈላቸው የተሻለ ደመወዝ ይልቅ በሕሊናቸው የሚመላለሰው ‹‹አጭበርባሪ›› የሚለው ወቀሳ ሚዛን እየደፋ ስለመምጣቱ በመጸጸት ይናገራሉ። ‹‹ሕሊናዬን ሸጬ የተሻለ ደመወዝ ከሚከፈለኝ ከመንግሥትም ሆነ ከግል ተቋም ወጥቼ የግል ሥራዬን ብሠራ የተሻለ ገቢ ከማግኘቴም ባሻገር ያጣሁትን ሰላሜንም በእጄ አደርጋለሁ›› ከሚለው ውሳኔ ደርሻለሁ ብለዋል።

ከላይ የተጠቀሱት ባለታሪክ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ አካላት በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ወደ ሥራው ዓለም እንደሚቀላቀሉ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የሚያወጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ተቋሙ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እንደገለጸው ከሆነ፤ የሐሰተኛ የትምህርት መረጃ መበራከትን ተከትሎ የትምህርት ተቋማትም ተማሪዎችን በትኑ እስከመባል ደርሰዋል።

ታዲያ በ2014 በጀት ዓመት የተለያዩ የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ከተባሉ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል 222 ያህሉ ተማሪዎቻቸውንም እንዲበትኑ ውሳኔ መተላለፉን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን አስታውቋል።

የሐሰተኛ መረጃ መበራከት

አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች በሥማቸው የሐሰተኛ የትምህርት መረጃ እንደወጣ እየጠቆሙ ነው። ለአብነትም አርባምንጭ ትምህርት ኮሌጅ በሥሙ የተዘጋጁ ከ100 በላይ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መሰራጨታቸውን ጠቁሞ፤ ቅጥር የሚያወጣ ተቋም ሁሉ ቅድሚያ ከኮሌጁ ጋር ትክክለኛ መረጃ ሊለዋወጥ እንደሚገባ ባሳለፍነው ነሐሴ 11/2014 ማሳሰቡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየተበራከተ ስለመምጣቱ የትምህርት ሥልጠና ባለሥልጣን የሚያወጣቸው ቁጥራዊ ማስረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ። በ2014 በጀት ዓመት የሥነ ስርዓት ጥሰት በፈጸሙ ከ350 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ተገልጿል።

ከዚህ በተጓዳኝ ጥናት በተደረገባቸው የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከ10 ሺሕ በላይ ማስረጃዎች መካከል 505ቱ ትክክለኛ ስላለመሆናቸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መግለጹ ይታወቃል። እነዚህ የሐሰተኛ ማስረጃዎች ተገኙ የተባለው ኹሉም ተቋማት ሳይዳሰሱ ነው። ለአብነትም በዚህ ጥናት የጉምሩክ ኮሚሽንና የጤና ሚኒስቴር ተቋማት እንዳልተዳሰሱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በይፋ አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ129 ከተሞች ከ2 ሺሕ 500 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ከ3 ሺሕ 315 በላይ የሚሆኑ የትምህርት መርሐ ግብሮችን ዘርግተው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት ይፋ አድርጓል።

- ይከተሉን -Social Media

ታዲያ ያልተዳሰሱ ቀሪ ተቋማት አለመዳሰሳቸው ቀላል የማይባል ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከወዲሁ እየተገለጸ ነው። በሌላ በኩል፣ እውቅና በሌለው የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገንዘባቸውን ከፍለው ውጤት ባሠሩ አካላት ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ዳሰሳ የትምህርት ማስረጃ ሐሰተኛ የሆነባቸው በርካታ ዜጎች ችግር ላይ ስለመውደቃቸውም ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ድንገተኛ ፍተሻ ያደረገባቸው 355 የግልና የከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት የመዘጋት እርምጃ እንደተወሰደባቸው መገለጹ አይዘነጋም። ታዲያ የቁጥሩ ከፍና ዝቅ ማለት እንጂ ቁጥራዊ መረጃው የሚያመላክተው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየተበራከተ መሆኑን ነው።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ የተገኙ አካላት በየወቅቱ እየተመነጠሩ የሚወጡበት አጋጣሚ እንዳለም ይነገራል። ባሳለፍነው ሰኔ ወር 2014 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ በማይገባቸው የደረጃ እድገት ላይ ተቀምጠዋል ተብለው ከተጠረጠሩ 70 የመንግሥት ሠራተኞች መካካል 49 የሚሆኑት ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው በወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።

ከ1955 እስከ 2014 ድረስ በተደረገ የተመራቂ ተማሪዎች መረጃ ዳሰሳ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ከሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች መካካል ከ100 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ማስረጃቸው ሐሰተኛ መሆኑን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ፒኤችዲ) ባሳለፍነው ሚያዚያ 2014 መግለጻቸው አይዘነጋም።

ከአራት ዓመት በፊት በኦሮምያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በተደረገ የማጣራት ሥራም በክልሉ ከ6 ሺሕ 400 በላይ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው የተቀጠሩ ሠራተኞች መገኘታቸውና፤ ሌሎች 8 ሺሕ 300 የመንግሥት ሠራተኞች ደግሞ የትምህርት ማስረጃቸው ሐሰተኛ እንደሆነ ተጠቁሞባቸው እየተጣራ መሆኑም ተገልጾ እንደነበር የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዋል። በኋላም የተወሰኑት በይቅርታ ወደሥራቸው እንደተመለሱ ተነግሯል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው ሲሠሩ በተገኙ 500 በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል።

የሚያስከትለው ጦስ

የሐሰተኛ መረጃ መበራከት ከማኅበረሰቡም አልፎ በትምህርት ላይ ባሉ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል የሥነ ልቦና ምሁራን ይገልጻሉ።

- ይከተሉን -Social Media

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ተመርኩዞ ወደ ሥራው ዓለም መቀላቀል በተለይም በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ስንፍናን ያስተምራል የሚሉት የሥነ ልቦና ምሁር ትዕግስት አክሊሉ ናቸው።

የሰዎች አእምሮ ከሚያደክም ነገር ይልቅ ቀለል ያለና አቋራጭ ነገርን ለመወሰን ቅርብ ነው ያሉት ትዕግስት፤ ደመወዝ ላይ ከማተኮር ባሻገር ራሳቸውን በእውቀት ገንብተው፤ ሳይማር ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ ለማገልገል ዛሬ ከመጻሕፍት ጋር ተጣብቀው የሚውሉ ተማሪዎች ይህን ሲያስተውሉ አእምሯቸው ‹‹እኔ ብቻዬን ግዴታ አለብኝ!›› የሚል እሳቤን ማጫሩ እንደማይቀር ተናግረዋል።

የሥነ ልቦና መምህርቷ እንዳሉትም ሁሉ፤ በተባለው የተሳሳተ አስተሳሰብ የተነደፉ ተማሪዎች ስለመኖራቸው አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ተማሪዎች መረዳት ችላለች።

በርካታ ተማሪዎችም ‹ለግሬድህ ብር ይጨነቅበት! አንተ ዘና በል!› በሚል ንግግር እንደቀልድ አስመስለው እውነታውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ። በተለይም በግል ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎች ሲመረቁ ይዘውት የሚወጡት ውጤት ጀርባ ያለው ምንጭ ጠንክሮ ማጥናት ሳይሆን ጠንክሮ ብር ማዘጋጀት ስለመሆኑ ራሳቸው ይመሰክራሉ።

ሥሜ በፍጹም እንዳይጠቀስ ያሉ አንድ የኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ የግል ኮሌጅ ምሩቅ ‹‹ለውጤት ብር ይጨነቅበት፤ እንደድሮ ተማሪዎች መቸከል እኮ አጉል ድካም ሆኖ ቀርቷል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሥነ ልቦና መምህርቷ፣ ‹‹ለውጤቴ ብር ይጨነቅበት›› ያሉ ተማሪዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደተጠናወታቸው አንስተው የሚከተለውን ምክር እንካችሁ ብለዋል።

‹‹‘ለውጤቴ ብር ይጨነቅበት’ በሚለው አስተሳሰብ ከእውቀት ነጻ የመሆን እድል እየተንሰራፋ ይመጣል። ብር ያለው ሥራ እያገኘ ሊሆን ይችላል። እውቀት ግን እንደሌለው ማሰብ አይከብድም›› ሲሉ ልዩነቱን አብራርተዋል። እውቀት ከሌለ ደግሞ አእምሮንም ማቆሸሽ፤ ሕዝብንም ለበደል ሲሳይ ማድረግ ጤነኛ ተግባር አይደለም ሲሉ መክረዋል።

ሌላኛዋ ሥሜ ከመጠቀስ ይቆይ ያሉ ምንጭ፤ ውጤት ከሚገዛውና ሌት እና ቀን አጥንቶ ከሚመረቀው ይልቅ በፍጥነት ሥራ የማግኘት እድል ያለው ውጤት የገዛው ነው ይላሉ። እንዲሁ ዓይነት እድል የገጠማቸው ሰዎችንም አውቃለሁ በማለትም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አክለውም፣ ‹‹መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራተኞችን ደመወዝ ቢያሻሽል ይህ ሁሉ ችግር አይመጣም ነበር›› የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።

ሐሰተኛ የትምህርት መረጃ የሚያበራክቱት በሕገ ወጥ ሥራ ተሰማርተው ዝቅተኛ ውጤትን ከፍ አድረገው የሚሠሩ አካላት ስለመሆናቸው ፖሊስ በተለያየ ወቅት ሲገልጽ ይስተዋላል። በመርካቶ፤ አራት ኪሎ፤ ቦሌ አካባቢዎችም ውጤት በማስተካከል ሕገ ወጥ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች ስለመኖራቸው አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በጠየቀችበት ወቅት ለመረዳት ችላለች።

ምን ተሻለ?

ለሐሰተኛ ትምህርት መረጃ መበራከት ዋና ዋና ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል ሳይማሩ ውጤት መግዛት፤ ዝቅ ያለ ውጤትን ብር ከፍሎ አቀነባብሮ ከፍተኛ ውጤት ይዞ ለሥራ ቅጥር መቅረብ ተጠቃሽ ናቸው። በመንግሥት ተቋም የተመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ ውጤታቸውን በማቀነባባር ለሥራ እንደሚወዳደሩ ከታወቀ ዋል አደር ማለቱ ይታወቃል።

ምንም እንኳ ሁሉም ተደራሽ ባይደረጉም የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ሐሰተኛ ውጤት ገዝተው በሕገወጥ መንገድ ሥራ ላይ በተቀመጡ አካላት ላይ እርምጃ ሲወስድ ይስተዋላል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየስፍራው ተሰግስገው ዝቅተኛ የሆነን ውጤት ከፍ አድርገው የሚያቀነባብሩ፤ በእውቀት ያልተገነባ መንጃ ፍቃድ የሚሰጡ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግን እምብዛም ሆኖ ይስተዋላል።

የሕግ አማካሪዎች በበኩላቸው እርምጃቸው የላላ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ብርሀኑ ይርዳው የተባሉ በማንኛውም ፍርድ ቤት የሕግ አማካሪና ጠበቃ በበኩላቸው፣ ሕገ መንግሥቱ ሐሰተኛ ማስረጃ ማቅረብን እንደሚያወግዝ ገልጸው የሚመለከተው አካል በጥብቅ ሊያተኩርበት ይገባል ብለዋል።

የሐሰተኛ መረጃ መበራከቱን መንግሥት ራሱ ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም ያሉት ጠበቃው፤ በዚሁ የሕግ ጥሰት ውስጥ የተገኙ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ለማወቅ ለትምህርት ሥልጠና ባለሥልጣን የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

የስርዓት ትምህርት ተንታኙ መስፍን ተክለማርያም በበኩላቸው፣ ሐሰተኛ የትምህርት መረጃ ፍሰትን በተመለከተ መፍትሔ ያሏቸውን አራት ፍሬ ሐሳቦች በሚከተለው መልኩ አጠር አድርገው አስቀምጠዋል።

‹‹በመጀመሪያ ደረጃ በየከተማው ተሰማርተው ውጤት የሚያቀነባብሩ አገር አውዳሚዎችን አድኖ መያዝና ዳግም ወደ ድርጊቱ እንዳይመለሱ የማያዳግም እርምጃ መውሰድና የቅጣት መመሪያ ማውጣት ይገባል። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የሚገኙ ባለሥልጣናትን በደንብ መፈተሽ፤ ሕገ ወጥ ሆነው የተገኙተን ዳግም ወደ ሥራው እንዳይመለሱ ማድረግና የቅጣት መመሪያ ማውረድ ጉዳዩን ሊገታው ይችላል።›› ብለዋል።

አክለውም ሥልጣን ላይ ያሉ ሕገ ወጥ ሰዎችን ከማረም ጎን በጎን፣ ተቋማት ተመራቂዎችን ለቅጥር በሚጠሩበት ወቅት መረጃቸውን በደንብ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምሩቃን ድርጊቱን እንዲጸየፉ ትምህርት መዘርጋት በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት የመፍትሔ ሐሳብ ነው። ዋነኛውና የመጨረሻው ደግሞ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጋለጥ ያስችላል በተባለው ቴክኖሎጂ ሁሉንም ተቋም ማሰስ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች