መነሻ ገጽዜናወቅታዊ200 ተከታታይ እትሞች

200 ተከታታይ እትሞች

ልጓም በማይያዝለት ነገር ግን በሥራ ብቻ በሚያሸንፉት የሚሮጥ ጊዜ መካከል፣ አዲስ ማለዳ ጉዞዋን ከጀመረችበት እለት አንስቶ ያለማቋረጥ ለ200 ሳምንታት ወደ አንባቢዎቿ ስትደርስ ቆይታለች። መልኳን ሳትለቅና ሳትቀይር፣ ብዝኀ ሐሳቦችን እያስተናገደች፣ ሙያዊ ሥነምግባርን ጠብቃና አክብራ ለዛሬ ደርሳለች። ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ረጅም ነውና፣ መንገዷ ይቀጥላል።

ባለፉት 200 እትሞች በርካታ አዳዲስና ያልተሰሙ ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን ስታደርሳችሁም ነው የቆየችው። ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ሽፋን አግኝተዋል። የጥበብ ዘርፍን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ዕይታዎችም በአውደ ሐሳብ እና ማኅበረ ፖለቲካ አምዶች ተስተናግደዋል።

እስከ ነሐሴ 28/2014 በሚቆጠረው በዚህ ወቅት፣ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በርካታ አለመረጋጋቶች፣ 6ኛው አገራዊ ምርጫ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በርካታ ክስተቶች አልፈዋል። እነዚህንም ጉዳዮች በሚመለከት ጥንቅሮችን አቅርባለች። በቀጣይም በተመሳሳይ ይልቁንም ከፍ ባለ ደረጃ ለአንባብያን መረጃዎችን ማድረሷን ትቀጥላለች።

ለአሁን ግን መለስ ብለን 100ኛ እትሟን ካከበረችበት ሳምንት ጀምሮ እስከ 200ኛው እትም ካሉ፣ በልዩነት ከምትሠራቸው የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳዮችን መካከል መለስ ብለን ልናስቃኛችሁ ወደናል።

ትጥቅን የማስፈታት እና ሕግን የማስከበር ዕቅድ

ለረጅም ዓመታት በፖለቲካ ልዩነታቸው በውጭ እና በጎረቤት አገራት ተጠልለው የትጥቅ ትግል ሲያካሒዱ የነበሩ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ውጣ ውረዶችም በዚሁ ጋር ተያይዞ ተከስቷል።

ወደ አገር ውስጥ ከገባው እና በትጥቅ ትግል ውስጥ ነበር ከሚባለው አንደኛው የሆነው ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ)ነበር። በርካታ ታጣቂ የነበሩት ፖለቲካ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አስመራ አቅንቶ የነበረው በለማ መገርሳ እና በወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ድርድር ተደርጎ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ግን በትጥቅ መፍታት እና ብረት ማውረድ ዙሪያ ከባድ የሆነ ውዝግብ ተከስቶ እንደነበርም ወቅቱ መወያያ ርዕስ ሆኖ አልፏል።

ትውልድን ያረከሰ ሌላ ትኩሳት

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ በትግራይ ክልላዊ ምርጫ መደረጉ በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሕወሓት መካከል ያለውን ልዩነቱን ወደ ጡዘት ጎዳና አድርሶቶታል።

ሕገ ወጥ በተባለው ምርጫ ላይ መስከረም 25/2013 የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊ የሥልጣን ዕድሜ አልቋል በሚል ሰበብ የትግራይ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት የሚመጣን ማንኛውንም ትእዛዝ አንቀበልም ሲሉ የፌዴራሉ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ሕጋዊ ያልሆነ መንግሥት ስለሆነ ያለው የክልሉን በጀት በወረዳዎች በኩል የምንሰጥበትን አሰራር እከተላለሁ በማለት አሳውቋል።

ቤንሻንጉል ጉምዝ -የመንግሥት ቸልተኝነት ጥግ

በኢትዮጵያ ላለፉት ኹለት ዓመታት ሰላም ከራቃቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን አንዱ ነው። መተከል ከወትሮውም ችግር የማያጣው አካባቢ እንደነበር ይነገርለታል። ታዲያ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሉትን ሆነና ነገሩ እየተባባሰ በየቀኑ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት የሚቀጠፍበት ቦታ መሆን ከጀመረ ሰነባበተ።

መተከል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ስር የሚተዳደር ዞን ይሁን እንጂ፤ በዞኑ ከጉምዝ ውጪ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሺናሻና አገው ብሔሮች ተሰባጥረው የሚኖሩበት አካባቢ ነው። በዞኑ በየጊዜው ለሚያልፈው የንጹሐን ዜጎች ሕይወት ማቆሚያ አልተገኘለትም። መንግሥት ችግሩን ለማስቆም ቁርጠኛ አይደለም የሚሉ ትችቶች በብዛት ይሰማሉ።

የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳዎቻችን ምን ይሁኑ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም መሠረት 6ተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ ለፌዴራል እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንዲሁም ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ግንቦት 28 እና ሰኔ 05/2013  ምርጫ እንደሚካሄድ አሳውቆ እየሠራ ይገኛል።

በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከተጠቀሱት ተግባራት መካከል አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት መረጣም  በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት  የምርጫ ምልክት ማስገቢያ እና ውሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

የአንድን አገራዊ ምርጫን ውጤት ከሚወስኑ ዐቢይ ሂደቶች መካከል የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት አንዱ ጉዳይ  ነው። ለምን ቢባል ፓርቲዎቹ የሕዝብን ድምጽ ለመግዛት ፖሊሲዎቻቸውን በይፋ የሚያስተዋውቁበት እና በቃላቸው መሰረት ሊጠየቁ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱበት ብሎም ቃል የሚገቡበት በቃላቸውም መነሻነት በጊዜ ሂደት የሚዳኙበት መድረክ በመሆኑ ነው።

ከሰበብ ባለፈ ትኩረት የሚያሻው የእሳት አደጋ ጉዳይ

አሁን ላይ በየወሩ በሚባል ደረጃ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች  የሚነሱ የእሳት አደጋዎች ቁጥራቸው እየተበራከቱ ነው።  የእሳት አደጋዎቹ በዚህ ዓይነት መጠን መከሰት የተለመደ ባለመሆኑ ዘወትር ከምናስባቸው  ምክንያቶች  ዞር አድርጎ ማሰብ የግድ ይላል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት 110 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል። በእነዚህ አደጋዎች የአምስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ለደረሱት አደጋዎች የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአግባቡ አለመዘርጋት እና/ ወይም የኤሌክትሪክ ኃይልን በጥንቃቄ አለመጠቀም የአንበሳውን ድርሻ ሲይዝ፣ በቀላሉ በእሳት ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችንና ተቀጣጣይ ነገሮችን እሳት በቀላሉ በሚያገኛቸው ቦታዎች ማስቀመጥ፣ የቡታጋዝ እንዲሁም የሲሊንደር ፍንዳታዎች ሌሎች የቃጠሎው መንስኤ መሆናቸውን በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢኮኖሚያችን ነገር

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል። በኢኮኖሚያዊ መስኮች ከብድር ጫና እስከ ወጪ ንግድ፣ ከገቢ አሰባሰብ እስከ ዋጋ ግሽበት ያሉትን እና ሌሎች ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ዓመታት የወጪ ንግድ ትልቅ ችግር ውስጥ እንደነበር እና ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሻሻል እንዳሳየ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ኮቪድ፣ አንበጣ፣ ጎርፍና ከሁሉ በላይ ደግሞ ግጭት ማጋጠሙ የውጪ ንግዱን ለማሻሻል ተጨማሪ ጋሬጣ እንደሆነ አንስተው፤ በተለይ  እንደ አገርም በግጭት ምክንያት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት  እንደባከነ ገልጸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የኮቪድ ከትባት ግንዛቤን በጨረፍታ

በአፍሪካ ደረጃ፣ በኮቪድ 19 ስርጭት ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት የተቀመጠች አገር ስትሆን እስካሁን ድረስ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በበሽታው ተይዘዋል። ቁጥራቸው ከ50 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿም በዚሁ ወረርሽኝ ሞተውባታል። እንደ ሲዲሲ አፍሪካ ዘገባ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ከፍተኛ የተጠቂዎችን ቁጥር በመያዝ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።

ከአኅጉሩ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ከተመዘገቡ ቀዳሚ አምስት አገራት አንዷ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ፣  ‹አስትራዜኔካ› የተሰኘውን የኮቪድ ክትባት ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብልቃጥ አግኝታለች።

የክትባቱ አገራችን መግባቱን ተከትሎ፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች የሚለቀቁትን እና በከተማችን ስለክትባቱ የሚናፈሱትን ወሬዎች ይዘን አሁን በአገር ውስጥ እየተሰጠ ያለውን የኮቪድ 19 ክትባት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያላቸውን ግንዛቤ አዲስ ማለዳ ለመቃኘት ሞክራለች።

በእውነታ ላይ ያልተመሠረተው የአሜሪካ ማዕቀብ

ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ዘመናት ሁሉ ፍላጎቶቻቸውን እና ጥቅሞቻቸውን ለመጫን የፈለጉ የውጭ ኃይሎች ሲፈትኗት እንደቆዩ ይታወቃል። የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሞከሩ ኃይሎችን ሕዝቦቿ የበዙ ጫናዎችን ተቋቁመው አሳፍረው በመመለስ እና ክብሯን በመጠበቃቸው ሁሌም ሥሟ የሚነሳ አገር ሆናለች።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በዘመናዊ ቅኝ ግዛት እሳቤ በተቃኙ የውጭ ኃይሎች አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ትግል ተከትሎ ፈተናው እጅጉን እያየለባት መጥቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ከወደ አሜሪካ የተሰማው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ በሚል ሽፋን እና ለትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላትን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል የቪዛ ገደብ ወይንም ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ መሬት ሽሚያ

- ይከተሉን -Social Media

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄዱ የመሬት ሽሚያዎች በግልጽ እየተስተዋሉ መጥተዋል። በተለይ ደግሞ አሁን አሁን አዲስ አበባ ላይ  በልማት ሥም በከተማ አስተዳደር ደረጃ መሬቶች እና የተገነቡ ሕንጻዎችን በስፋት መሻማት የተለመደ ተግባር ሆኖ ይገኛል። በቀደሙት ኹለት ዓመታት ውስጥ ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ሲነገር ቆይቷል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ልዩ ዞኖች እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ የፖለቲካ ፍላጎትንና ትንተናን ተንተርሶ የሚካሄድ እንደሆነም በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ነበር። ሕገ-ወጥ ግንባታዎችም የሚያካሄዱት ዝቅተኛ ኑሮ ከሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጀምሮ ሀብት ባላቸውና የፖለቲካ ዓላማ ባነገቡ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ እገዛ ጭምር እንደነበር ይታወቃል።

የክተት አዋጅ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ

የአማራ ክልል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝንት የተፈረጀው ሕወሓት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት የክተት አዋጅ ጥሪ አድርጓል። በትግራይ ክልል ጥቅምት 24/2013 በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ሕወሓት ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በማግስቱ የተጀመረው የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥት ፍልሚያ ከስንምንት ወራት ቆይታ በኋላ የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ለ15 ቀን ያክል የተረጋጋ ቢመስልም ዳግመኛ አገርሽቷል።

…የአማራ ክልል መንግሥት የክተት አዋጅ ጥሪ ያስተላለፈው ይህንኑ በሽብርተኝንት የተፈረጀውን የሕወሓትን ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፣ ጥቃቱን ለመመከት የተደራጀ ኃይል እንደሚያስፈልግ በማመኑ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። የክተት አዋጅ ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር ሲሆኑ፣ በክተት አዋጅ ጥሪያቸው ላይ ‹በክልሉ ውስጥ ማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሳሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ይክተት› በማለት ነው።

 አዲስ ዓመት – አዲስ ተስፋ

አሮጌው የ2013 ዓመት የተለያዩ መልካምና አስከፊ ክስተቶችን አስተናግዶ በማለፍ ተራውን ለተከታዩ አዲስ ዓመት አስረክቧል። የ2014 ዓመትን ‹ሀ› ብለን ልንጀምር ዛሬ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የዕንቁጣጣሽ በዓልን ቀን ላይ እንገኛለን። በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መልክና ይዘት ይዞ እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን ቤት ያፈራውን አዘጋጅቶ በማቅረብ በደስታና በፍቅር ዐውደ ዓመቱን በማሳለፍ ላይ ነው።

የአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ወቅታዊው የአገራችን የሠላም ማጣት ኹኔታ ሥጋት የፈጠረና የበዓል አከባበሩ ላይ መቀዛቀዝን ያስከተለ ሆኗል። በወረርሽኙ ላይ በሚታየው መዘናጋትና በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በተነሳው ጦርነት ምክንያት የቤተሰብ አባላቸውን አጥተው በዓሉን በሐዘን እና በከፍተኛ ድብርት ውስጥ የሚያሳልፉትም ጥቂቶች እንዳልሆኑ ይታወቃል።

የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎች

ኢትዮጵያ ድርብርብ ችግሮች በተደቀኑባት በዚህ ወቅት በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ የፊታችን ሰኞ መስከረም 24/2014 አዲስ መንግሥት ይመሠርታል። ይህም አዲስ መንግሥት ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊቱ ተደቅነው እየጠበቁት ነው።

ኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ ውጥረት ውስጥ ገብታለች። ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላ አንድ ወር በቀረውና በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአውሮፓውያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና አለ። ወዲህ ደግሞ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ ከጎረቤት አገሮች ከግብጽና ሱዳን ጋር ያልተቋጨ ውዝግብ ላይ ትገኛለች። ከሰሜኑ ጦርነት እና ተያያዥ ችግሮች በተጨማሪ ከሱዳን ጋር ያላት የድንበር ውዝግብና የ‹ኢትዮጵያ ገፋችን› ክስ የቀጠለና እልባት ያላገኘ ጉዳይ ነው።

የጦርነቱ ፍጻሜ ወደ ድርድር ያመራ ይሆን?

ሕወሓት በትግራይ ክልል መቀመጫውን ባደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24/2013 በወሰደው ጥቃት የተነሳ “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሚል ጦርነቱ በአጭር እንዲቋጭ እና ከሕወሓት አመራሮችም የተወሰኑት እጅ እንዲሰጡ፣ የቀሩትም እንዲገደሉና እና ሌሎች ደግሞ እንዲታደኑ ተደርጓል። በሂደቱም በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ክልሉን የማረጋጋትና የማስተዳደር ሥራ እየሠራ ስለነበር፣ ብዙዎች ጦርነቱ በፍጥነት የሚጠናቀቅ እና ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ወደ ነበረበት ሠላም የሚመለስ መስሏቸው ነበር።

…ቀድሞውንም በብዙ አገሮች ተኩስ አቁም እንዲደረግና ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ሲጠየቅ መክረሙ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት በሰጠው ማብራሪያ ላይ፣ “ከሕወሓት ጋር ለመደራደር ቢያንስ ንጹሐንን ከሚያሰቃይበት የአፋርና አማራ ክልል መውጣት አለበት” ማለቱን ተከትሎ በበርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚነሳው መሠረታዊ ሐሳብ፣ “አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ከሚንቀሳቀስ ቡድን ጋር በእውነቱ ቁጭ ብሎ መደራደር ይቻላል ወይ?” የሚለው ነው።

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እና የዋጋ ግሽበት

የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን የማቅረብ እና የመሸጫ ዋጋ የመተመን ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ በዚህም የነዳጅ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋን በየወሩ ይከልሳል። የነዳጅ ዋጋ በየወሩ እንደየሁኔታው የሚከለስ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ወራት ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጭ ያሉት የነዳጅ ምርቶች ባሉበት ዋጋ ረግተው እንዲቆዩ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

አዲስ በተደረገው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ማሻሻያ መሠረት፣ ቤንዚን ላይ በተደረገ የዋጋ ማስተካከያ ባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሊትር 31 ብር ከ74 ሣንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

የመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት ከከፍታ ወደ ዝቅታ

ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነቱ እና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እልባት አለማግኘታቸውን ተከትሎ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መምጣቱን ብዙዎች እየገለጹ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ግልጽ እና አሳማኝ መረጃ አለማቅረቡ ሲሆን፣ በተለይ ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች የሕዝብን ፍላጎት ያላማከሉ እና የሕዝብን ይሁንታ ያላገኙ ናቸው የሚል ትችት በመንግሥት ላይ በርትቷል።

መንግሥት በቂ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብና የሕዝብን ፍላጎት ያማከለ ግልጽ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት የሚሉ ሐሳቦች በማኅበረሠቡና ምሁራኑ በብዛት ቢንሸራሸርም፣ እስካሁን የሚፈለገውን ያክል አሳማኝ መረጃ እና ግልጽነት ከመንግሥት እንዳልመጣ እየተነገረ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሐሳብ የሠጡ ምሁራን በሕዝብ በኩል ለሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጋጣሚ በሚገኙባቸው መድረኮች ላይ የሚሰጧቸው ሐሳቦች አሳማኝና በቂ አለመሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ግልጽ ያልሆኑ አካሄዶችን ለሕዝብ ማብራራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና የመንግሥት ፍጥጫ

በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚፈጠሩ ችግሮች ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተቃውሞ በር ሲከፍቱ ይስተዋላል። እስከ አሁን የተሰሙ የተማሪ ተቋውሞዎች በብዛት የተሰሙት በመንግሥት ላይ ሲሆን፣ በየጊዜው ችግሮች ሲፈጠሩ ተማሪዎች መንግሥትንና የድርጊቱን ፈጻሚ የሚያወግዙበትና የሚቃወሙበት ድምጽ ያሰማሉ።

ሰኔ 11/2014 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ በመቃወም የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ተቃውሞ እንደ ማንኛውም ሰላማዊ ተቃውሞ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ መሞከራቸው፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለኃይል እርምጃና እስር ተዳርገዋል።

ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲያቸው ድርጊቱን በመቃወም ባሰሙት የተቃውሞ ሰልፍ፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ድብደባና እስር  ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተማሪዎችን ሰላማዊ ሰልፍና የተቃውሞ ደምጽ ለማፈን በሚመስል መልኩ ተማሪዎችን በኃይል ለመበተን ሲሞክሩም ታይተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች