ዘግናኝ ግፍ

ከሠሞኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ ነው ብሎ ለማመን የሚያዳግት የግፍ ግፍ በጨቅላ ሕጻናት ላይ መፈጸሙ ብዙዎችን በሀዘን የዋጠና መነጋገሪያ የሆነ ነበር።

ወንድምና እህት ሕጻናትን በአንድ ጊዜ አንቃና አርዳ የገደለችው ወንበዴ ወይም በሽተኛ የሆነችና የማታውቃቸው ሴት አይደለችም። እንድትንከባከባቸው ኃላፊነት የተሰጣት የቤት ሠራተኛ መሆኗ ብዙዎችን ጉድ ያሰኘ ክስተት ነበር። ለማመን የሚከብደው አሰቃቂ ግፍ የተፈፀመባቸው ወላጆች ‹ኑ!› ተብለው ከሥራቸው ወደቤታቸው ሲመለሱ በዘግናኝ ሁኔታ የተገደሉ ጨቅላ ሕጻናት ልጆቻቸውን አግኝተዋል።

አረመኔያዊ ተግባሩን የፈፀመችው ሴት እጇን ለፖሊስ የሰጠች መሆኑ ቢነገርም፣ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ከመናገር የተቆጠቡ ነበሩ። እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ድርጊትን እንድንላመደው ማስተዋወቅ ይሆናል በሚል ቅጣት ሲፈፀምባት መናገሩ ይሻል ነበር በማለት ድርጊቱ ይፋ መደረጉን የተቃወሙም ነበሩ።

ሌላውም ሰው ልጁን ለማን አሳልፎ እንደሚሰጥ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያስተምራል በሚል ድርጊቱ መነገሩ ተገቢ ነው በሚል የሞገቱም ነበሩ። መነገር አለመነገሩ ቢያወዛግብም፣ የቤት ሠራተኛዋን ድርጊት ግን እየዘገነነውም ቢሆን የኮነነው ብዙ ነው።

ድርጊቱን ስለፈፀመችው ሴት የጤና ሁኔታ ምንም የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በጨቅላ ሕጻናት ላይ እንዲህ የጨከነችው ‹የአእምሮ በሽተኛ› ሳትሆን አትቀርም የሚለው የብዙዎች አስተያየት ነው። ድርጊቷን ከእርኩስ መንፈስ ጋር አገናኝተው የሰፈረባት ነገር ቢኖር እንጂ ያለምክንያት እንዲህ አታደርግም በማለትም ግምታቸውን ያስቀመጡ ነበሩ።

ስለገዳይዋ የጤናም ሆነ የአስተሳሰብ ሁኔታ መላምታቸውን በሀዘኔታ ካስቀመጡት ባሻገር፣ ስለወላጆቻቸው ሁኔታም ያሳሰባቸው በርካቶች ናቸው። እንዴት ሊፅናኑ ይችላሉ፣ የማይረሳ ግፍ ተፈጽሞባቸው ምንስ ተብሎ ማፅናናት ይቻላል የሚል እጅግ ብዙ አስተያየት ተሰንዝሯል። ፈጣሪ እንዲያበረታቸውና እንዲፅናኑ ያልተመኘ የለም ማለት እስኪቻል ድረስ የተፈፀመውን ግፍ የሰማ ሀዘኔታውን ገልጿል።

እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊቶች እየተበራከቱ የመጡት ቆፍጠን ያለ ሕጋዊ ቅጣት ስለሌለ ነው በሚል የዚህች ነፍስ አጥፊ ላይ የሚወሰነውን ፍርድ ለመስማት እንደሚጓጉም ያሳወቁ አሉ። ቅጣት አስተማሪ ብቻ ሳይሆን አስፈራሪም መሆን ስላልቻለ ጥፋተኞችም ቅጣት የሚባለውን ስለማይፈሩት ነው ግፍ የተባባሰው የሚል አስተያየት የሰጡ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ጠንከር ያለ ውሳኔ እንዲተላለፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

ከብዙ አስተያየት ሰጪዎች መረዳት የሚቻለው የቤት ሠራተኛዋ ድርጊት ምን ያህል አሰቃቂ ግፍ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የፈጸመችው ወንጀል ብዙዎች ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን የሚል አስተሳሰብን እንዲያንጸባርቁ አድርጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች