መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅከታሪክ እንማር!

ከታሪክ እንማር!

ታሪክ ለኹላችንም መማሪያ ተብሎ የሚጻፍና ለትውልድ የሚተላለፍ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህን አስተማሪ የቀደሙ ትውልዶች ድርጊትን ባለማወቅ አልያም በመዘንጋት ጥፋት ሲደጋገም፣ ሽንፈትም ባህል ሲሆን ይታያል።

የዓለማችን ታሪክ በአብዛኛው የሚያወራው ስለጦርነት መሆኑ ግልፅ ነው። የእለት ተእለት የነገሥታትንም ሆነ የተራው ግለሰብ የውሎ ሂደትን ለመጻፍም ሆነ ለማስተላለፍ ካለመቻሉ አንፃር፣ ዋና ዋና የትውልዱን አቅጣጫ መስመር ያስያዙና አዲስ ጎዳና ያስጀመሩ የውጊያና የለውጥ ድርጊቶች በአብዛኛው ይመዘገባሉ።

የመጀመሪያ ታሪክ ተብሎ የተመዘገበው የሰው ልጆች መስተጋብር ጦርነት እንደሆነ የሚናገሩ የታሪክ ባለሙያዎች አሉ። በሜሶፖታሚያ ማለትም በአሁኗ ኢራንና ኢራቅ አካባቢ የነበሩ ሱመራውያን የተባሉ የመጀመሪያውን ሥርወ መንግሥትና ጽሑፍ እንደመሠረቱ የሚነገርላቸው የሥልጣኔ ጀማሪዎች ተብለው በምዕራባውያን የሚታወቁ የሱመር ጎሳዎች ከግብፃውያን አስቀድመው ያካሄዱትና ከ4 ሺሕ 700 ዓመታት በፊት ከኢላሞች ጋር የተዋጉበት ጦርነት በድንጋይ ላይ ተጽፎ ተገኝቶ የመጀመሪያው ውጊያ ተብሎ ማስተማሪያ ሆኗል።

ሌላው በዝርዝር ስለጦርነት የተጻፈበት ታሪክ የግብፁ ራምሲስ ኹለተኛ ሂታይቶች ይባሉ ከነበሩት በአሁኗ ቱርክ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ሶሪያ ምድር ውስጥ በቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ1 ሺሕ 275 ያካሄደውና በርካታ እልቂት የተፈፀመበት ታሪክ እንደሆነ ይታወቃል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስንነሳም የሦስቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች አባት በሚባለው በአብርሃም ዘመን 4 ነገሥታት ከ5 ነገሥታት ጋር ያደረጉት ጦርነት እንዲሁም አብርሃም ወንድሙንና ንብረቱን ለማዳን ያደረገው ድንገተኛ ጥቃት ተመዝግቦ ይገኛል። የግሪኩ አሌክሳንደር የጦርነት ስልት፣ የሮሙ ጁሊየስ ቄሳር አነሳስና የጦርነት ዘዴ፣ የሳላዲን ብቃት እንዲሁም የቅርቡን የፈረንሳዩን የናፖሊዮንን የጦርነት ስትራቴጂ ጭምር ምዕራባውያን ራሳቸውን አስተምረዉበት ለመበልፀጊያ ተጠቅመዉበታል።

የአገራችንን ካነሳን የነ አፄ ካሌብና አፄ አምደጽዮን ጀግንነት፣ እንዲሁም የቅርቦቹ የነአፄ ቴዎድሮስና የነአፄ ምኒልክንም ሆነ የመኳንንቶቻቸውን የጀብድ ታሪክ ማየት ይቻላል። የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለው አረዳድ የተለያየ ቢሆንም፣ በጦርነት ብቃታችን አንዱ አካባቢ ከሌላው የተለየ ብቃት አለው ሊያስብል እንደማይችል የእርስ በእርስ ጦርነቶቻችን ያስከተሉት እልቂትና የቆዩባቸው ጊዜያት ብዙ ሊያስተምሩን ይገባ እንደነበር አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በቀደሙት ዘመናት ንጉሠ ነገሥቶች የበላይ ሆነው የበታች ንጉሦችም ሆኑ መኳንንቶቻቸው እርስ በእርስ ተጣልተው ሕዝብ እንዳያስተላልቁ ዳኛ ሆነው በመጠበቅ ያጠፋን ይቀጡም ነበር። በፍትሐ ነገሥትም ሆነ በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደምናየው፤ ሕዝብ እንዳያልቅ አስቀድሞ የሚደረጉ የማሸማገል ድርጊቶችም ነበሩ። የውጪ ጠላት ላይ የሚኖር አንድነት የውስጥ ችግር ሲከሰት ስለማይኖር፣ አንዱ ከሌላው ጋር ሲሻኮት የተለየ ጥንቃቄ ይደረግ እንደነበር ይነገራል።

በተለይ በዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ እልቂቱ በተከሰተበት ወቅት ካህናቱም ሆኑ የአገር ሽማግሌዎች የብዙኀኑን እልቂት ለማስቀረት ትልቅ ሚና ነበራቸው። ወገን ይዘው የሚያባብሱ አሁንም እንዳሉት በቀደመው ዘመንም የነበሩ ቢሆንም፣ ዋና ዓላማቸው ሕዝብ እንዳያልቅ የሚሠሩ ይበዙ እንደነበር ይነገራል። ይህን ዓላማቸውን ለማሳካትም ድርድር እና እርቅን በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቀሙበት እንደነበር ግልፅ ነው።

በመንፈሳዊነት ከሚታወቁ ጥቂት ነገሥታት ውጪ ኢትዮጵያ ያለጦርነት ቆይታ የምታውቅበት ጊዜ እንደሌለ ይነገራል። በየ11 ዓመቱ ወይ ጦርነት አልያም ድርቅ ወይም አንድ የሆነ የተፈጥሮ ክስተት ተከስቶ ብዙዎች እንደሚያልቁ የሚያምኑ አሉ። በአንጻሩ በየ40 ዓመቱ እልቂት አይቀርልንም ብለው ማስረጃ የሚያቀርቡም አሉ። በ2008 እና 2009 ከነበረው ክስተት 40 ዓመታትን ወደኋላ እየቀነሱ የሱማሌን ወረራ 1969፣ የጣሊያንን ኹለተኛ ሙከራ1929፣ የአድዋን 1988 እንዲሁም በ1948 የአፄ ቴዎድሮስን የውስጥ ጦርነት እንዲሁም እስከ አፄ ልብነድንግል ድረስ የነበሩትንና ከእሳቸውም በፊት የነበሩ የእርስ በርስ ጦርነቶቻችንን ከባዕዳን ጥቃት ጋር እያነፃፀሩ ሲናገሩ ይደመጣል።

ያም ተባለ ይህ፣ ኢትዮጵያ ጦርነት አንዱ መገለጫዋ እስኪመስል ድረስ አሁንም ከአዙሪቱ እንዳልወጣች እየተመለከትን እንገኛለን። ከዚህ አስከፊ ታሪኳ መማር ያልቻሉ መሪዎቿ ድሃውን ኅብረተሰብ እየማገዱ ለመሞቅና አብስለው ሆዳቸውን ለመሙላት ሲጥሩም ማየት ይቻላል። በምን እንደሚጣሉም ሆነ በምን እንደሚደራደሩ እውነቱ የማይነገረው ሕዝብ፣ ለእልቂት ሲሆን “ና ለአገርህ ድረስ” እየተባለ እርስ በእርሱ እንዲባላ ያደርጉታል።

አገራዊ የሩጫም ሆነ እግር ኳስ ውድድርን በቀጥታ በውድ ወጪ ከመመልከት ይልቅ እጣ ፈንታውን የሚወስንበትን ሕይወቱን ሊቀጥፍበት የሚችለውን የባለሥልጣናቱን ግንኙነት በግልፅ ሊያውቅ ሲገባ፣ ጨለማ ውስጥ አቆይተው እሳት ሲፈጠር ወስደው ይማግዱታል። ይህ ዓይነት ማሞኘትና ወደ እልቂት መውሰድ በየትኛውም ወገን የሚፈፀም ቢሆንም፣ ሊቆም የሚገባው አፀያፊ ድርጊት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሠሞኑን እንደአዲስ የተጀመረው የዋናው ጦርነት አካል የሆነው የሦስተኛው ዙር ውጊያ የተለመደውን መንገድ ተከትሎ ተመሳሳይ እልቂት ሊያስከትል ቀንን መቁጠር ጀምሯል። ባለፉት ውጊያዎች የደረሰው እልቂት ያቆሰለው ገና ጠባሳ ሳይሆን ቁስሉ እያመረቀዘ፣ የወደመው ሀብትም ሳይተካ በነበረው ችግር ላይ የሚጨመር ሌላን ሰቆቃ ይዞ ሲመጣ ተመሳሳይ ዲስኩር ማሰማት ከማንም የማይጠበቅ ተግባር ነው።

በቀደሙት ዘመናት የተፈፀመውን ታሪክ ለመቀበል የሚያንገራግሩም ቢሆኑ፣ አሁን በዘመናቸው ከተፈፀመው ተመሳሳይ ኹነት ሳይማሩ አንድ ዓይነት ጥፋት ለመድገም እየተሽቀዳደሙ ይገኛሉ። ኹለቱም ወገኖች መጀመሪያ ውጊያ ውስጥ ከገቡበት የባሰ ኹኔታ ውስጥ ኾነው አሁንም ሌላ አማራጭ አጥተው ወደጦርነቱ መመለሳቸው ሊያሳዝን በተገባ ነበር።

ከራሳቸው ጠባሳ መማር ሳይችሉ ሌላን በአረር የሚያስጠብሱ በበዙበት በዚህ ዘመን ሕዝቡ ዝም ብሎ ከመነዳት ቆም ብሎ ሊያስብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ትመክራለች። በአንድ ቀን ጦርነት እየተተኮሰ የሚባክነው አገር ውስጥ የማይሠራ ሀብት ብቻ ሳይሆን ሊያሳስበን የሚገባው፣ በዛ አረር ስንት ዓመትና ቀናትን በሕይወት እንዲቆይ የተለፋለትን ሰው መግደል መቻሉ ሊያንገበግበን ይገባል። አሁንም ጊዜው አበቃ የሚባልበት ስላልሆነ ኹሉም ወገን ወደቀልቡ ተመልሶ ሊተሳሰብ ግድ ይላል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች