መነሻ ገጽአንደበት“ማንም እንደፈለገው ባለጊዜ ነኝ ብሎ አዲስ አበባን እንደፈለገ ሊጫናትና የአዲስ አበባን ሕዝብ...

“ማንም እንደፈለገው ባለጊዜ ነኝ ብሎ አዲስ አበባን እንደፈለገ ሊጫናትና የአዲስ አበባን ሕዝብ ሊጫወትበት አይገባም”

ኢትዮጵያ ካሏት አንጋፋ የፌዴራሊዝምና ሰብዓዊ መብቶች ምሁራንና ተመራማሪዎች መከካል አንዱ ናቸው። በሙያቸው ከማስተማርና ምርምሮችን ከመሥራት ባሻገር ሙያዊ ሐሳቦችን ወደ መድረክ በማምጣትና በመሞገት ይታወቃሉ፤ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በፌዴራሊዝምና መልካም አስተዳደር ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል። እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ሕግ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና ሰብዓዊ መብቶች መምህርና ተመራማሪ በመሆን እያለገሉ ይገኛሉ።

ከመምህርነታቸው በተጓዳኝ የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ እና የመንግሥታት ምላሽ፣ በሴራ የተፈተነች ሕይወትና የኢሕአዴግ ሸፍጦች የተሰኙ ሦስት መጽሐፍትን ለሕትመት አብቅተዋል። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በብልጽግና ፓርቲ ጥላ ስር ተወዳድረው፣ የምክር ቤት አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። የምክር ቤት አባሉ እና የሕግ ምሁሩ ሲሳይ መንግሥቴ፣ ጠንካራ ሐሳቦችንና ትችቶችን በማንሳት ይታወቃሉ። በአዲስ አበባ እና አጠቃላይ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል ወሰን ማካለል ሕገ መንግሥታዊ መሠረት አለው ማለት ይቻላል? የምክር ቤት ውሳኔስ አይፈልግም?

የአዲስ አበባ ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ አማራጮች ለማመላከት እሞክር ነበር። አዲስ አበባ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውክልና የላትም። ይሄን ያክል ትልቅ ሕዝብና ከተማ ያለ ውክልና ያለበት ሁኔታ አለ። አዲስ አበባ ላይ በተለይ ምርጫ 1997ን ተከትሎት የአዲስ አበባ የነበሩ ተቋማት ወደ ፌዴራል መንግሥት ተጠሪ ሆነው እንዲሄዱ መደረጉ፣ በተለይ ቅንጅት በማሸነፉ ምክንያት የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ የመጣበት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ውልና ማስረጃ ኤጀንሲ ይባል የነበረው፣ የትራንስፖርት ቢሮ፣ የገቢዎች ቢሮ ወደ ፌዴራል እንዲሄዱ የተደረገበት ሁኔታ አለ።

አሁንም ድረስ ሌሎች ተመልሰው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና በአሁኑ ሥያሜው የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አሁንም ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት ሆነው የቀጠሉበት ሁኔታ አለ። በፓርላማም ቢሆን አዲስ አበባ በቂ የውክልና ወንበር አላገኘችም።

ከኦሮሚያ ጋር ያለው የወሰን ይገባኛል ወይም ተለይቶ ያለመቀመጡ ጉዳይ ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጠ እንደነበር ይታወቃል። ችግሩ ለአላስፈላጊ ግጭት በር እየከፈተ ስለሆነ በምክር  ቤት ይሄን ጥያቄ አንስተነው ነበር። የወሰን ማካለሉ ለምክር ቤት ውሳኔ አልቀረበም።

ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ መሠረት አዲስ አበባና የኦሮሚያ ግንኙነት ምን እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን የሚያስተዳደር ነው። ከኦሮሚያ ጋር የሚያገናኘው የልዩ ጥቅም ጉዳይ ነው። አዲስ አበባ በተጠቀመችው ልክ ለኦሮሚያ የሚገባውን ጥቅም ልትሰጥ ትችላለች።

ከዚያ ባሻገር አዲስ አበባ የተቋቋመችበት ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 ላይ የኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስተዳደር ወሰናቸውን በስምምነት ይወስናሉ ይላል። ኹለቱ የማይስማሙ ከሆነ የፌዴራል መንግሥት እንደሚወስን ሥልጣን ሰጥቷል። በዚያ መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ነው። አሁን አዋሳኙ ለኹለቱም ጥቅም በሚሆን መልኩ ተለይቷል አልተለየም? የሚለው ሌላ ጥናት ሊያስፈልገው ይችላል።

በወሰን ማካለሉ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ የተካለሉና ከኦሮሚያም ወደ አዲስ አበባ የተካለሉ አካባቢዎች አሉ።

ወሰን ማካለሉ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑንና ጤነኛ የፖለቲካ ውሳኔ እንዳልሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ምሁራን እያነሱ ነው። እርስዎ ምን ይላሉ?

እንግዲህ ሁሉም የየራሱን ግንዛቤና ያለውን መረጃ መነሻ አድርጎ ነው ሐሳብ የሚሰጠው። ዋናው ነገር ከተማ አስተዳደሩ እና የኦሮሚያ ክልል ስለ ውሳኔው መግለጫ ሲሰጡ ሕዝብ ሰብስበን አወያይተናል ብለው ነው ሪፖርት ያደረጉት። እኔ እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ስህተት ብዬ የማስበውና ትክክል ያልሆነው አዲስ አበባ ምክር ቤት በወሰን ማካለሉ ጉዳይ ላይ በግልጽ አልተወያየም።

ምናልባት ተወያየን የሚሉት የተወሰንን የምክር ቤት አባላትን ስብሰባ ጠርተውን መረጃ ሰጥተውናል። ከመረጃ መስጠት ያለፈ ይሄ ትክክል ነው፣ ይሄ ትክክል አይደለም ብለውን የውሳኔ ሐሳብ እንድናቀርብ የሚያስችል ውይይት አላካሄድንም። ስለዚህ ልክ ምክር ቤቱ ተወያይቶ እንደወሰነ ተደርጎ የሚተላለፈው መልዕክት ትክክል አይደለም።

ከአዋሳኝ አካባቢ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደተደረገ ነው የተገለጸልን። እኛ ጥያቄውን አንስተናል፣ እነዚህ ሰዎች ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቆጥበው በአዲስ አበባ ነዋሪነታቸው እጣ የደረሳቸው ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነን እያሉ ከመሀል ከተማ ጭምር እዚያ ሄደው የሰፈሩ ሰዎች፣ በአንድ ጊዜ ከአዲስ አበቤነት ወደ ኦሮሞነት ሲቀየር የሥነ ልቦና ተጽእኖው ቀላል አይሆንም።

ከዚያም አልፎ በቀጣይ የአስተዳደርና አገልግሎት ጉዳይ ሲነሳ፣ በኦሮሚኛ ነው አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው። የኦሮሚያ ክልል ኦሮሚኛን በሥራ ቋንቋነት ስለሚጠቀም ማለት ነው። ምናልባት ከትምህርት ጋር የተያያዘውን ችግር የለውም በአማርኛ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ። አጠቃላይ የባህል፣ የቋንቋና የሥነ ልቦና ጉዳይ ከታየ ‘ኦሮማይዝድ’ የመሆን እድል አለው። ስለዚህ በዚህ ምክንያት የሚደርስባቸው ጫና ወይም ሳይፈልጉ በግድ በድንገት ወደ ኦሮሚያ ሲካለሉ ቅሬታ ቢያድርባቸው ትክክል ነው።

እነዚህ ሰዎች ተወያይተው፣ አማራጭ ቀርቦላቸው ውሳኔ ሰጥተውበት ነው ወይ ይሄ ውሳኔ የተወሰነው? ከተባለ አይመስለኝም። ውይይትም የተካሄደው የይድረስ ይድረስ ስለሆነ፣ የራሱ ውስንነቶች ይኖሩታል። ግን ደግሞ መወሰን ነበረበት፣ ሁልጊዜ ኦሮሚያዎችን አዲስ አበባ የኛ ናት እያሉ፣ አዲስ አበባም እንዲሁ እየተስፋፋች ያለ ስምምነት የሚኬድበት ሁኔታ የለም።

- ይከተሉን -Social Media

በአዲስ አበባ መስፋት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች፣ መሀል አዲስ አበባ ላይ ባዶ ቦታ እያዩ ለምን ማስፋት አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ኹለተኛ አዲስ አበባ ስትሰፋ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ይፈናቀላሉ። በአዲስ አበባ መስፋት የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የአማራና የጉራጌ ማንነት ያላቸው አርሶ አድሮች ጭምር ናቸው። ስለዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚፈናቀሉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች ብቻ አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም።

ዞሮ ዞሮ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ወሰን ተካሎ አዲስ አበባም የአዲስ አበባን ማልማት አለበት፣ የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያም እንደዚሁ የራሱን ወሰን አውቆ የሚሠራውን ሥራ መሥራት አለበት። አንዳንድ ጊዜ አዋሳኝ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ከመሠረተ ልማት አገልገሎት ይገለሉ ነበር። ምክንያቱም የአዲስ አበባም ወደ ኦሮሚያ ሊሄዱ ይችላሉ ብሎ ይሰጋል፣ አሮሚያም ወደ አዲስ አበባ ሊሄዱ ይችላሉ ብሎ ይታሰባል።

ስለዚህ በአዋሳኝ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በብዙ መልኩ እየተቸገሩ እንደሆነ ሪፖርቶች ያመላክታሉ። ውሳኔው ያንን ችግር ለመቅረፍና በዘላቂነት የሚኖራቸውን ግንኙነት ሕግና ውሳኔን መሠረት ያደረገ እንዲሆን እምነት አለኝ።

ሌላው በአዲስ አበባ ጉዳይ አወዛጋቢ የሆነው የኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ መደረጉ ነው። እርስዎም በምክር ቤት ይሄን ጉዳይ አንስተው ነበር። ሕጋዊነቱ ላይ መሠረት አለው? ጤነኛስ እሳቤ ነው ማለት ይቻላል?

ይሄ ሕጋዊ መሠረት የለውም። ከጤነኛ እሳቤም የሚመጣ ነው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ጤነኛ እሳቤ ቢሆን፣ ሕጋዊ መሠረት እንዲከተል ይደረግ ነበር። ሕጉንና ስርዓቱን ተከትሎ መዘመርና መውለብለብ እንኳን ካለበት በየደረጃው ውይይት ተካሂዶበት፣ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ተደርጎ፣ ከተማ አስተዳደሩም በየደረጃው ያሉ አካላት ተነጋግረው መወሰን አለባቸው። አሁን እየሆነ ያለው ግን ትምህርት ቢሮም እንደ ቢሮ አስቦበት ግልጽ የሆነ ደብዳቤ አስተላልፎ አይመስለኝም ይሄ ነገር የሆነው።

እየሆነ ያለው በየትምህርት ቤቱ ያሉ የኦሮሞ መምህራንና ተማሪዎች ይሄን እናደርጋለን የሚል ዓይነት ስሜታዊነትና የባለጊዜነት ስሜት የሚንጸባረቅበት ነው። ተዉ ሲባሉም የማንአለብኝነት ሁኔታ የሚታይበት ነው። በየደረጃው ያሉ አካላትም ይሄን ከማረም ይልቅ፣ ምን ችግር አለው ያሉበት ሁኔታ አለ። የሚያሳዝነው ነገር ይሄ ጉዳይ በየመድረኩ ሲነሳ ከንቲባዋም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሚሰጡት ማብራሪያ የበለጠ ጤናማ እንዳልነበረ፣ ግልጽ የሆነ ባለጊዜነት የተንጸባረቀበት መሆኑን ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ፓርላማ የማይነጻጸርና ውሸት የሆነ ነገር አቅርበዋል። በአዲስ አበባ የሚገኙ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች፣ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ይስቀሉ እንጂ መዝሙር አያዘምሩም። ቢያዘምሩ እንኳን ፈቅደው እንጂ ተገደው አይደለም።

የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ኦሮሚኛ ተናጋሪ ብቻ የሚማርባቸው ትምህርት  ቤቶች አይደሉም። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሳያገናዝቡ እንዲሁ በስሜት ለምን ተቃወሙን፣ ለምን እኛ የፈለግነውን ስናደርግ ዝም አይሉም የሚል ቁጭት ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ መሪ የማይጠበቅ ኦሮሞ ጠልነት ነው ብለው ሕዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ ንግግር አድርገዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በማግስቱ ወለጋ ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ የተከሰተበትን ሁኔታ እናስታውሳለን። አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ሰከን ብሎ ማሰብ ይጠይቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገር ነው እንጂ የሚመሩት አንድ ፓርቲ ወይም የኦሮሞን ፍላጎት ብቻ ይዘው አይደለም ወንበር ላይ የተቀመጡት።

የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ለኦሮሞ ሕዝብ እንጂ ለሌላው ሊሆን አይችልም። ሰንደቅ ዓላማውም በክልል ብቻ እንዲውለበለብ የተገደበ ነው። ከክልሉ ወጥቶ አዲስ አበባ ላይ እንዲውለበለብ የሚፈቅድ ሕግም አሠራርም የለም። በማንአለብኝነት ሥልጣኑን ስለያዝነው ጊዜው የእኛ ስለሆነ፣ የፈለግነውን ብናደርግ ማንም ሊያስቆመን አይችልም የሚል መታበይ የተንጸባረቀበት እንደሆነ ነው እኔ የማየው።

ለወደፊቱ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚነሱ ውዝግቦችን ለማስቀረት እንደ ምክር ቤት አባልነትዎና እንደ ፌዴራሊዝም ባለሙያነትዎ ምን ይመክራሉ?

እኔ ምክር ቤትም ላይ ያነሳሁት ነገር አለ። የመጀመሪያው ነገር አዲስ አበባ ላይ ሕግና ስርዓት መከበር አለበት። ማንም እንደፈለገው ባለጊዜ ነኝ ብሎ አዲስ አበባን እንደፈለገ ሊጫናትና የአዲስ አበባን ሕዝብ ሊጫወትበት አይገባም። ይሄን ለማስቀረት አንደኛ ሕገ መንግሥቱ መከለስ አለበት፣ በብሔራዊ ምክከሩ አንዱ አጀንዳ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ሕገ መንግሥቱ ሲከለስ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል ሆና እንድትወጣ የአዲስ አበባ ሕዝብ መሥራት አለበት።

የአዲስ አበባ ሕዝብ ችግሩ አንድ ሆኖ አይታገልም። ፖለቲከኞች በብሔር ከፋፍለው ሊያስከትሉት ይፈልጋሉ። ኦሮሞን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሊያስከትሉት ይፈልጋሉ፣ አማራን የአማራ ፖለቲከኞች፣ ትግሬን የትግሬ ፖለቲከኞች፣ ጉራጌን የጉራጌ ፖለቲከኞች ሊያስከትሉት ይፈልጋሉ። ሁሉም በየፊናው አንድ እንዳይሆን ሊከፋፍለው ይሞክራል። አዲስ አበባን የሚመጥን አደረጃጀት መፈጠር አለበት።

ኹለተኛው ሕገ መንግሥቱ እስከሚሻሻል ያለውን ሕግ ማክበር ነው። ለአዲስ አበባ ኃላፊነት የተሰየሙ ሰዎች ለአዲስ አበባ ጥቅም የሚቆሙ መሆን አለባቸው። የአዲስ አበባ  ጉዳይ የሚያሳስባቸው እንጂ ለመጡበት ክልል ጥቅም የሚሠሩ ከሆነ የአዲስ አበባ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህ እዚህ አካባቢ ኅብረተሰቡም ፍላጎቱን በግልጽ ማሳየት አለበት። ሕዝቡ የተዛባ፣ ያልተገባና ትክክል ያልሆነ ነገር ሲኖር መቃወምና ሐሳቡን መግለጽ ይኖርበታል።

በታቻለ መጠን የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን መሪ መምረጥና መቆጣጠር መቻል አለበት። ያ ሲሆን ነው በትክክል የአዲስ አበባ ሕዝብ መብትና ጥቅም ሊከበር የሚችለው። አዲስ አበባ ላይ የሚታዩ ጫናዎችን ማስቀረት የሚቻለው ሕዝቡ በትክክል ራሱን በራሱ ማስተዳደር ሲችል ነው።

ከአዲስ አበባ ጉዳይ ወጣ ስንል፣ ኢትዮጵያ የገጠማትን የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ እስካሁን ተጨባጭ ለውጥ አልታየም። ይህ ከምን የመነጨ ነው ማለት ይቻላል?

- ይከተሉን -Social Media

እውነት ነው ተጨባጭ ለውጥ አልታየም። በአማጺውና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው ጦርነት መቆም አለበት። የትግራይ ሕዝብም ኢትዮጵያዊ ነው። ሕዝቡ ከባድ ስቃይ ላይ ነው ያለው። ጦርነቱ እንዲቆም በተለያዩ አካላት ድርድር ተሞክሮ እስካሁን ውጤታማ አልሆነም።

ለምንድን ነው ውጤታማ ያልሆነው? ትሕነግ በባህሪው ለድርድር የሚመች ድርጅት አይደለም። ለራሱ የሚጠቅመውን ብቻ ነው ለማስተናገድ የሚሞክረው። አገኘዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ድርድሩ የሚያሳጣው ከመሰለው ወደ ኃይል የመሄድ ልምድ ነው ያለው። በድርድር የማይሳካልኝና ጥቅሜ የማይከበርልኝ ከሆነ በኃይል አሸንፌ የምፈልገውን አራምዳለሁ ብሎ የሚያስብ ቡድን ስለሆነ፣ ትክክለኛ የድርድር መርህ ወይም በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመገዛት ፍላጎት የለውም። ምክንያቱም ኑሮው በራሱ የተመሠረተው በጦርነት ላይ ነው።

ከዚያ ባሻገር ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ የራሱ የሆነ ውስንነቶች የሉም ማለት ላይሆን ይችላል። የፌዴራል መንግሥቱ አካሄድና አያያዝ የራሱ ውስንነቶች ይኖራሉ። ግን በአብዛኛው መሠረታዊ ችግር ያለው ትሕነግ ላይ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።

የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት እንደ ትልቅ እንቅፋት የሆነው የራያ አላማጣ እና ወልቃይት የማንነት ጥያቄ ነው። በተለይ ለአማራ እና ለትግራይ ክልል ውዝግበ እንዴት ማስተናገድና እልባት መስጠት ይቻላል?

እውነት ነው እንዳልከው በዚህ የድርድር ሂደት ውስጥ አንዱ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሊነሳ የሚችለው የወልቃይት ጠገዴና የራያ አካባቢ ወደ ትግራይ መሆን አለበት፣ የለም ወደ አማራ መሆን አለበት የሚል ክርክር ነው። እንግዲህ የኹለቱም ወገን ፖለቲከኞች እነዚህን አካባቢዎች ይፈልጓቸዋል። ከሁሉ በላይ መፍትሔው ያለው ከሕዝቡ  እጅ ነው።

መፍትሔው ሊሆን የሚችለው ወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ድሮም አማራ ነኝ ብሎ የሚያምን ጎንደሬ ነው። ስለዚህ ይሄን ሕዝብ እንዲወስን እድል መፍቀድ ነው። የራያንም አካባቢ እንዲሁ በጉልበት ሥልጣን በተቆጣጠሩበት ወቅት ያካተቱበት ሁኔታ አለ። ያ ሲሆን ተቃውሞዎች ተነስተው ነበር። እኛ ወደ ትግራይ አንካለልም ያሉትን የተወሰኑትን አፍነው ገድለው፣ የደረሱበት ሁሉ የማይታወቅ አለ። ስለዚህ በሕጋዊ የመብት ጥያቄ ሲነሱ የነበሩ ሰዎችን ሲያፍኑ ነበር የቆዩት፣ አሁንም እሱን ነው እያደረጉ ያሉት።

ከወልቃይት ባለፉት 40 ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መፈናቀሉን አቶ ብናልፍ በአንድ ወቅት ሲናገሩ አስታውሳለሁ። ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች የደረሱበት የማይታወቅ የዘር ማጥፋት ወንጀልም ተፈጽሟል። ራያም ላይ አርሶ አደሮች የተገደሉበት ሁኔታ ነበር፣ አሁንም ይሄ ቀጥሏል።

ስለዚህ ይሄ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው፣ ለእነዚህ ሕዝቦች ከማንም ጫና ነጻ ሆነው ሐሳባቸውን በሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሄን ኃላፊነት መወጣት አለበት። የፌዴራል መንግሥትም ይሁን ኹለቱ ክልሎች ሕዝብ በሚወስነው እንዲስማሙ የሚያደርግ ነገር መኖር አለበት። የትግራይ ፖለቲከኞችም እንዲህ ነው ስላሉ፣ የአማራ ፖለቲከኞችም የለም እንዲህ ነው ስላሉ እልባት ያገኛል ብዬ አላምንም።

በየአካባቢው ምክንያታዊ የሆኑ እና ያልሆኑ የክልልነት ጥያቄዎች እየተበራከቱ የመምጣታቸው መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?

የፌዴራል ስርዓት አንዱ ለየት ያለ ባህሪ እንዲኖረው የሚያደርገው አደረጃጀቶች በአንድ ጊዜ ብቻ ተሠርተው የሚያበቁ አይደሉም። በሂደት እየሰፋም ወይም እየተዋሃደ የሚሄድበት አደረጃጀት ሊኖር ይችላል።

ለምሳሌ ናይጄሪያን ብንወስድ በሦስት ክልል ጀምራ፣ ከሦስት ወደ ስድስት፣ እያለ አሁን ሠላሳ ስድስት ክልሎች አሏት። ስለዚህ የክልሎች መብዛት ጉዳይ አይደለም፣ ክልሎች በትክክለኛው አደረጃጀት ቢዋቀሩ እንኳን በሂደት የሚዋሃዱ ይኖራሉ፣ እንደገና ተከፋፍለው አዳዲስ ክልሎች ሊወጡ ይችላሉ። ፌዴራሊዝም ላይ የሚያጠኑ ሰዎች ፌዴራሊዝም ያልተጠናቀቀ ፕሮጀክት ነው፣ በሂደት እየተሟላ የሚሄድ፣ በሂደት መፍትሔ እየሰጠ የሚሄድ ነው ይሉታል።

ከዚያም አልፎ በአሃዳዊ አስተዳደር ስርዓትም እኮ ይሠራል። የኢትዮጵያን አሃዳዊ አስተዳደር ስርዓት ታሪክ የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብናይ 1930ቹ 30 እና ከዚያ በላይ አውራጃዎች ናቸው የነበሩት። ከዚያ በኋላ በ1940ቹ መጀመሪያ ላይ እነዚህን አውራጃዎች በአንድ ላይ ጠቅለል አድርጎ ማደራጀት የግድ ይል ስለነበር፣ እነዚህ አውራጃዎች ሰብሰብ ተደርገው በ12 ጠቅላይ ግዛቶች ተደራጁ።

ከዚያ ባሌ እና ሐረርጌ አንድ ላይ ስለነበሩ፣ እሱ ሰፊ ግዛት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ እንደገና ተጠንቶ ከሦስት ዓመታት በኋላ ባሌ እና ሐረርጌ ለኹለት ተከፍለው ራሳቸውን የቻሉ ሲሆኑ 13 ጠቅላይ ግዛቶች ሆኑ።

በ1945 ደግሞ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ስትዋሃድ፣ 14 ጠቅላይ ግዛት ተባሉ። ለረዥም ጊዜ 14 ጠቅላይ ግዛት ሆኖ ቆየ። በደርግ ጊዜ ደግሞ በመጨረሻ ሥማቸው ቀይሮ ክፍለ አገር አላቸው እንጂ 14ቱ ቀጠሉ። አዲስ አበባም እንደዚሁ የራሷ አስተዳደር ነበራት።

ይሄ ግምት ውስጥ ገብቶ መጨረሻ ላይ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ደርግ በመጨረሻ የሥልጣን እድሜው አካባቢ፣ 1980 አዲስ ሕገ መንግሥት ሲያዋቅር  እንደገና አደረጃጀቶችን ቀያይሯል። አደረጃጀቶችን እንደገና ፈጥሮ ኤርትራን፣ አሰብን፣ ትግራይንና ኦጋዴን አካባቢ ራስ ገዝ ብሎ እንደገና አደራጃቸው። ሌሎቹን ክፍለ አገሮች ከፋፍሎ ወደ 25 የአደረጃጃት አስተዳደሮች የሚል ሠራና ጠቅላላ 30 ሆኑ።

ስለዚህ በዛ የሚባል አይደለም፣ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች። በ1984 ክልሎች ሲደራጁ 14 ነበሩ፣ አዲስ አበባም ነበረች። ደቡብ ደግሞ አምስት ክልሎች ነበሩ፣ እነዚህ ክልሎች ፈቅደውና ወደው ሕዝቡ ተሳትፎ አልነበረም እንደገና የተጠቃለሉት። የኢሕአዴግ ሰዎች ለመቆጣጠር እንዲመቻቸው የፈጠሩት ነው።

ይሄን ካየህ መጀመሪያውኑ ሳይፈቅዱ ወደ አንድ የተጨፈለቁ ክልሎች ወደ ነበሩበት ቢመጡ አይገርምም። ስለዚህ በዚያ መንገድ አዳዲስ ክልሎች ቢመጡ ለኢትዮጵያ ብዙም የሚያስችግር አይደለም።

ሌላው ቀርቶ ትላልቅ የሚባሉ ክልሎች ሳይቀር ከኹለት፣ ከሦስት ተከፍለው እንደገና የሚደራጁበት ሁኔታ መታሰብ አለበት። አዲስ አበባ መልሳ ራሷን ችላ ክልል የምትሆንበት፣ ድሬድዋ በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎችን ታሳቢ አድርጎ አንድ ተመጣጣኝ የሆነ ክልል መሆን እንዳለበት፣ ሐረሬ አሁን ባለችበት መቀጠል የለባትም፣ በዙሪያዋ ያሉ ዞኖችን አካቶ ክልል ቢሆንና በአዲስ መልክ ክልሎችን ማደራጀት ተገቢ ነው።

ለፖለቲከኞች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆን አለበት። የሕዝቡ ፍላጎት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል በሚለው ነው እኔ የማምነው። እንደ ችግር አድርገን ባናየው ጥሩ ነው።

የክልልነት ጥያቄ የአስተዳደር ስርዓት ቅልጥፍናና ፍትሐዊ አስተዳደር መነሻ ያደረጉ ከመሆን አልፈው ጤነኛ ያልሆኑ የፖለቲካ ፍላጎቶች  አይንጸባረቁም ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ከሰሞኑ የሚንጸባረቀው የወሎ ክልልነት ጉዳይ?

አዎ! እውነት ነው ይንጸባረቃል። አንዳንዱ ትክክለኛ የሆነ ጥያቄ ይዞ ይመጣል። ከፍትህ አንጻር፣ ከልማትና ከአገልግሎት አንጻር፣ አጠቃላይ ከአገሪቱን ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አንጻር የሚነሳ ይኖራል። ከዚያ ሲያልፍ ግን የጥቂት ቡድኖች ጥቅም ማካበቻ ለማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ለዚህ በር የከፈተው ሕገ መንግሥቱ ነው ብዬ ነው የማምነው።

የሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት አሁን ክልሎች ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በማንኛውም ጊዜ መመሥረት ይችላሉ ይላል። የሕዝብ ብዛታቸው ግምት ውስጥ አይገባም፣ የልማት አቅማቸው፣ ሰው ኃይል አቅማቸው አይታይም። ክልል ለመመሥረት እንደ መነሻ መሠረታዊ የሆኑ መስፈርቶች መኖር አለባቸው።

ከዚያ ውጭ ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሰማንያውም ክልል የመመሥረት መብት አለው፤ በሕገ መንግሥቱ መሠረት። ከዚያም አልፎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አገር የመሆን እድል አላቸው። በማንኛውም ወቅት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አገር ነን ብለው በነጻነት የማወጅ መብት ተሰጥቷቸዋል።

ፖለቲካችን በብሔርና በዘር ከተቃኘ፣ ጤነኛ ያልሆነ ፉክክር ከታየ፣ የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ መሆን ካልቻለ እነዚህ ጥያቄዎች ይቀጥላሉ። ፖለቲካችን ታሟል። በመጀመሪያ ከችግር መውጣትና መታረም አለበት። እንደውም ብሔር ተኮር አደረጃጀት የሚከለከልበት፣ ኅብረ ብሔራዊነት ያለው እንጂ አገር ወደ ጎን የሚተዉበትና ቅድሚያ ለብሔር የሚሰጥበት አደረጃጀት በሕግም ጭምር እንዲቆም ካልተደረገ ጥያቄዎች አሁንም ይቀጥላሉ።

ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው የወሎ የክልልነት ጥያቄ፣ ከአማራ ክልል ብቻውን ተነጥሎ መታየት አለበት ብዬ አላምንም። በመርህ ደረጃ በመጽሐፌም ላይ አመላክቻለው። ለምሳሌ አማራ ክልል ቢያንስ ለኹለት ምሥራቅና ምዕራብ አማራ አለዚያ ደግሞ በአራት (ሸዋ፣ ጎጃም፣ ጎንደርና ወሎ በሚል) ቢደራጅ ፍትሕ በቅርብ ማግኘት ይቻላል።

በአንድ ክልል ከሚወከል በአራት ክልል ቢወከል የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ይኖራል። የኦሮሚያ ክልልም ቢያንስ ሦስት ከፍ ሲልም አምስት ስድስት ክልል ሊሆን የሚችልበት እድል አለ። ይሄ መታሰብ አለበት። ሌላው ቀርቶ ሶማሌ ክልል የሕዝብ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም የቆዳ ስፋቱ ትልቅ ስለሆነ በኹለት ክልል ቢከፈል ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

ነገር ግን ወሎን ብቻ ነጥሎ ክልል ላድርግ ማለት ትክክልና ጤነኛ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ከተለያየ አካልም አማራን ለማዳከም ግፊት የሚያደርጉ አካላት እንዳይኖሩ ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ። ስለዚህ አማራ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎቹም ላይ ሊሠራ በሚችል ሁሉንም ሊመልስ የሚችል ሥራ ነው መሠራት ያለበት።

ከወቅቱም አንጻር ወሎን ክልልነት ጥያቄ ለማንሳት አሁን ወቅቱ ነው ብዬ አላስብም። በርካታ ወረዳዎች ገና ነጻ ባልወጡበት ሁኔታ፣ ነጻ ያልወጡትን ነጻ ማውጣት ነው የሚቀድመው ወይስ የክልልነት ጥያቄ ማንሳት? የሚለው መታሰብ አለበት። ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች ነጻ ሳይወጡና የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ክልል ልሁን ብሎ ሌላ ተጨማሪ እዳ ማምጣት ነው።

ይሄን አጋጣሚ ደግሞ ሌሎች አካሎች አይጠቀሙበትም ብዬ አላምንም። በተለይ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወሎ ኦሮሞ ነው ብለው ያምናሉ፣ ሰሜን ኦሮሚያ ብለው መግለጫ የሰጡበት ሁኔታ አለ። እነ ጃዋር ደግሞ እስከ ራያ ድረስ የሚደርስ ካርታ ሠርተው አብዛኛው ወሎ ራያ እንደሆነ አድርገው ሲቀሰቅሱ፣ ሲጠይቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው። ለዚያም ነው በተደጋጋሚ ከሚሴ ላይ አጣዬ ላይ ግጭት እየተከሰተ ያለው። ስለዚህ ዱላ ሆኖ እንዳይመጣ በዚህ አጋጣሚ እመክራለሁ።፡

ሕገ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ችግሮች መነሻ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ እና መሻሻያ የሚፈልግ መሆኑን በጥናት ጭምር የተረጋገጠ ቢሆንም ሙከራ አለመታየቱን እንዴት ያዩታል?

እውነት ነው። እንግዲህ አንዱ ለውጥ ካስፈለገበት ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ችግር አለበት መሻሻል አለበት የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች አሉ። የለም ሕገ መንግሥቱ መነካት የለበትም ብለው የሚያምኑ በጣም በርካታ ብሔርተኞች አሉ። በተለይ የትግራይና የኦሮሞ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥቱ መነካት የለበትም ይላሉ። የተወሰኑ ወገኖች ደግሞ በጣም አክራሪ የሆኑና ለሕገ መንግሥቱ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ሕገ መንግሥቱ ተቀድዶ መጣል ነው ያለበት የሚል ሐሳብ፤ በጠቅላላ ሦስት ዓይነት ሐሳቦች ይነሳሉ።

በእኔ እምነት ተገቢ ነው ብዬ የማስበው ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት። ብዙ ችግሮች እንዳሉት፣ ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ስላሉት እነሱን አስፋፍቶ ጠቃሚ ያልሆነውን አስወግዶ አዳዲስ ሐሳቦችን አካቶ እንደገና ተከልሶ ሥራ ላይ መዋል አለበት።

በዚህ ረገድ ለውጡን እየመራ ባለው በገዥው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ሙከራዎች እንዳሉ አውቃለሁ። በፍትሕ ሚኒስቴር አነሳሽነት ውይይት እንደተደረገ እኔም አንድ ኹለት መድረኮች ላይ ተሳትፌ ታዝቢያለሁ። በአንድ በኩል ሐሳቡ አለ፣ ነገር ግን አፍራሽ የሆኑ ንግግሮች ሲነገሩ ይሰማል። ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ ለአንድ ብሔር ተብሎ አይሻሻልም የሚል በእብሪት የሚገለጽ የመታበይ መልስ ከመሪዎች አካባቢ ሲሰጥ የምንሰማበት ሁኔታ አለ። ያ ትክክል አይደለም። በጎን ለማሻሻል እንሠራለን እየተባለ፣ በጎን ደግሞ ለሚነሳው ጥያቄ ለአንድ ክልል ብለን አናሻሽልም ብሎ በእብሪት የተሞላ መልስ መስጠት እርስ በእርስ የሚቃረን ነው።

ተወደደም ተጠላም ሕገ መንግሥቱ መሻሻሉ አይቀርም። በተለይ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የመጀመሪያ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ብዬ የምጠብቀው ሕገ መንግሥቱን የመሻሻል ወይ የመቀየር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሐሳቦች ይፋጫሉ፣ በጥናት የተደገፉ ሐሳቦች ይቀርባሉ። እኔም በኢሕአዴግ ሸፍጦች መጽሐፌ አንድ ርዕስ ሰጥቼ በዝርዝር አስቀምጨዋለሁ። የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥትም ምን ያክል ችግሮች እንዳሉባቸው ለማሳየት ሞክሬአለሁ።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንደሚገባ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል። ይሄን ማድረግ ለውጥን ከሚመራ መንግሥት የሚጠበቅ ነው። ይሄን አላደርግም ካለ ለውጡ የውሸት ነው ማለት ይቻላል።

ሕገ መንግሥቱ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ሰላለ፣ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሕገ መንግሥቱን መከለስ የግድ ነው የሚሆነው። ለዚህም ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ግፊት ማድረግ እና የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች