መነሻ ገጽዜናትንታኔወደቀያቸው ለመመለስ የናፈቁ ታዳጊዎች

ወደቀያቸው ለመመለስ የናፈቁ ታዳጊዎች

ሕጻን ደጀን ኃይሉ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ሥሙ የተቀየረ) የ11 ዓመት ሕጻን ሲሆን፣ ትውልድና እድገቱ ራያ አላማጣ ነው። ሕጻን ደጀን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከትምህርቱና ተወልዶ ካደገበት አካባቢ ተፈናቅሎ በሕጻንነት እድሜው ስለጦርነት እያሰበ፣ ሰው ሁሉ በሸሸው በርሃ ላይ በ10 ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጓደኞቹ ጋር በሸራ ጎጆ ተጠልሎ እየኖረ ነው።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በተለይ ከራያ አላማጣ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወጣቶችና ሕጻናት ለመፈናቀላቸው ዋነኛው ምክንያት ከሕወሓት ታጣቂዎች አስገዳጅ የጦርነት ተሳትፎና ሥልጠና ለማምለጥ መሆኑን አዲስ ማለዳ በጃራ መጠለያ በተገኘችበት ወቅት ያነጋገረቻቸው ወጣቶችና ሕጻናት ይገልጻሉ።

“ትልቅ መስያቸው ከእነሱ ጋር ስፖርት እንድሠራና ተከትያቸው ወታደር እንድሆን ጠየቁኝ” የሚለው ሕጻን ደጀን፣ እሱ የትግራይ ተዋጊዎች የሚላቸው የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች ያቀረቡለትን ታጣቂዎችን የመቀላቀል ጥያቄ ባለመቀበሉ መትተዉት እንዳለቀሰ ይናገራል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ሕጻን ደጀን ለምን እንደተፈናቀለ ሲናገር፣ ስለ ጦርነቱ ከአንደበቱ የሚወጣው ነገር ከሕጻን የሚጠበቅና በሕጻን አእምሮ ሊታሰብ የሚገባ ሐሳብ አይደለም።

ከሕጻናቱ አንደበት የሚፈልቁ ቃላት፣ ጦርነት ምን ያህል አስከፊ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሕጻናቱ እንደሚያስቡትና ለመፈናቀላቸው ምክንያት ስለሆነው ጦርነት የሚሰጡት መልስና በአእምሯቸው የተቀረጸው ሐሳብ በዐይናቸው የተመለከቱትንና የደረሰባቸውን ነገር እያነሱ በሕጻንነት አእምሯቸው የሚያውጠነጥኑት መጥፎ ስሜትና ወደ አካባቢያቸው የመመለስ መሻት፣ አስታራቂ የሚፈልግ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ከሕጻናቱ ሐሳብና ሁኔታ መረዳት ይቻላል።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የተፈናቀሉት ከራያ አላማጣ፣ ኦፍላ፣ ዛታ፣ ኮረም እና ራያ አዘቦ ወረዳዎች ሲሆን፣ በሀብሩ ወረዳ ድሬ ሮቃ ቀበሌ ወደ 40 ሺሕ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ልዩ ሥሙ ጃራ ተብሎ በሚጠራ በርሃ ላይ ተጠልለዋል። በጃራ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በማንነታቸው ምክንያት ከሕወሓት ታጣቂዎች ጥቃትና እንግልት የሸሹ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

አብዛኛዎቹ ተፈናቃይ ሕጻናትና ወጣቶች ናቸው። በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች ያሉበት ቦታ እስካሁን ሰው ኖሮበትም ይሁን ለእርሻ ተጠቅሞት የማያውቅ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በርሃ መሆኑን ተፈናቃዮቹ ይገልጻሉ።

ተፈናቃዮች የተጠለሉበት የጃራ መጠለያ ካምፕ ከርቀት ሲታይ የደራ ከተማ እንጂ ከጦርነት የሸሹ ሰዎች መስከረም 2014 ላይ የመሠረቱት መጠለያ ጣቢያ አይመስልም። ወደ መጠለያ ጣቢያው ቀረብ ብሎ ሁኔታውን ላላየ ሰው የደራ ከተማ የሚመስለው መጠለያ ጣቢያ በነጭ ሸራ የተወጠረ በሩቅ ሲታይ አብረቅራቂ ከተማ ይምሰል እንጂ፣ በውስጡ በብዙ ነገር ነፍሳቸው የተጨነቀች ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና ሴቶችና እናቶች በየቀኑ በተመሳሳይ ውሎ እና አዳር የሚጉላሉበት ከሰው ርቆ የሚገኝ በርሃ ነው።

በሰላሙ ጊዜ ሰው ቀርቶ ከዱር አራዊት ውጪ የቤት እንስሳት እንኳን ዝር የማይሉበት በጥቅጥቅ ጫካ የተሸፈነው በርሃ፣ በተለይ ክረምት ከመግባቱ በፊት የብዙ ሕጻናትና ወጣቶች ላብ ፈሶበታል። ቦታው እጅግ ከፍተኛ ሙቀት የአየር ጸባይ ያለበት አካባቢ መሆኑን አዲስ ማለዳ በቦታው በተገኘችበት ወቅት ያነጋገረችው ወጣት ዝናቡ ካሳይ ይገልጻል። አብዛኛው ሕጻናት እየታመሙ ችግር ላይ ነው የከረምነው የሚለው ወጣቱ፣ አሁን ላይ ወቅቱ የክረምት ወቅት በመሆኑ፣ በተለይ ሕጻናትን ለሕመም የሚዳርገው ከፍተኛ ሙቀት ጋብ ማለቱን ይገልጻል።

አዲስ ማለዳ በቦታው የተገኘችበት ወቅት ክረምት ይሁን እንጂ፣ በዚህ የክረምት ወቅት እንኳን ያለው ሙቀት፣ አይደለም ለሕጻናት ለአዋቂ ሰዎችም ቀላል አይደለም። በሙቀቱ ምክንያት በተለይ ሕጻናት በፊታቸው ላይ የመቁሰል ምልክቶች ይታያሉ። በሕጻናት ፊት ቆዳ ላይ የሚታዩ የመቁሰል ምልክቶች በሙቀቱ ምክንያት የተከሰቱ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ከሕጻናት ቤተሰቦች ሰምታለች።

ተፈናቃዮች የሚገኙበት መጠለያ ካምፕ ውስጥ ጤና ጣቢያና የሕክምና ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ በሕክምና መሣሪያና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ተፈናቃዮች ሕመም ሲያጋጥማቸው የተሟላ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ ይገልጻሉ። በዚህም በተለይ ሕጻናት ከሙቀቱ ጋር በተገናኘ በብዛት ስለሚታመሙ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ወጣት ዝናቡ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ ጠቁሟል።

በጃራ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች አብዛኛዎቹ ወጣቶችና ሕጻናት የመሆናቸው ምክንያት ምን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከተፈናቃዮቹ አንደበት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሕጻናትንና ወጣቶችን አነጋግራ ያገኘችው ተመሳሳይ መልስ ነው። ይህም በማንነታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው ጥቃትና ተገዶ ወደ ጦርነት ከመግባት ሽሽት መፈናቀላቸው ነው። በዚያ በረሃ ላይ ጊዜያቸውን በትምህርት ማሳለፍ የሚገባቸው ሕጻናት እና አፍላ የሥራ ጊዜያቸውን በመጉላላት የሚያሳልፉ ወጣቶችን ሕይወት አሁን ላይ ከገጠማቸው ችግር በተጨማሪ ነገ የሚሆነው ነገር ያስፈራቸዋል።

ተፈናቃዮች ነገን እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው ምክንያት ሰላም ተፈጥሮ ወደ አካባቢያቸው የመመለስ አለመመለስ ጉዳይ አንዱ ሲሆን፣ ኹለተኛው አሁን ባለቡት ሁኔታ የተጋመሰው ክረምት ካለቀ በኋላ በዚያ በረሃ ላይ ዳግም ላለመቀጠላቸው ዋስትና የማግኘት አለማግኘታቸው ጉዳይ ነው። ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከሆነ ምኞታቸው ጦርነቱ መፍትሔ አግኝቶ ወይም መንግሥት ሕወሓትን ከአካባቢያቸው አስወጥቶላቸው ወደ አካባቢያቸው መመለስ ነው።

በጃራ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች አልፎ አልፎ የሰብዓዊ ድጋፍ መቆራረጥና መዘግየት እንደሚገጥማቸው ይገልጻሉ። በዚህም አንዳንዴ የምግብ አቅርቦት በሚዘገይበት ጊዜ ለረሃብ እንደሚጋለጡ ይገልጻሉ። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሕጻናት አልፎ አልፎ የምግብ አቅርቦት ሲዘገይ እንደሚራቡ ይናገራሉ። “አንድ ቀን እርቦኝ ያውቃል፣ ሌሎች ጓደኞቼ ብዙ ጊዜ እርቧቸው ያውቃል” የሚለው ሕጻን ደጀን፣ እናቱ አብራው ስላለች ብዙም እንደማይራብና ቤተሰቦቻቸው አብረዋቸው የሌሉ ጓደኞቹ እንደሚራቡ ይናገራል።

ተፈናቃዮች የተጠለሉበት አካባቢ በረሃማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የውሃ አቅርቦት ችግር ያለ ሲሆን፣ በቦቲ እየተመላለሰ ውሃ የሚቀርብ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የውሃ ችግር እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ። በመጠለያ ካምፕ ውስጥ በአካባቢው አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች የተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ቢሰማሩም፣ የገበያ ዋጋው ከተፈናቃዮች አቅም ጋር የሚጣጣም አይደለም። በመጠለያ ካምፕ ውስጥ በብዛት ለገበያ ከሚቀርቡ ፍጆታዎች መከካል ውሃ ዋነኛው ቢሆንም፣ የመግዛት አቅም የሌላቸው ተፈናቃዮች በቦቲ ውሃ እስኪቀርብላቸው ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

ሰላም ፈልጎ ሰላም ማጣት

- ይከተሉን -Social Media

ከተለያዩ የራያ አላማጣ አካባቢዎች ተፈናቅለው ጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት፣ ከጦርነት ሽሽትና በሰላም ውሎ ማደርን ፈልገው መሆኑን ወጣት ዝናቡ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ሰላም ፈልጎና ከጦርነት ሸሽቶ የተፈናቀለው ማኅበረሰብ የተጠለለበት አካባቢ በረሃ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከአፋር ክልል ጋር የሚያዋስን መሆኑን ተከትሎ ከአፋር በኩል በተደጋጋሚ በከባድ መሣሪያ ሳይቀር ተኩስ እንደሚከፈትባቸው ይገልጻሉ።

“የሰፈርንበት ቦታ ሰላማዊ አይደለም” የሚለው ወጣት ዝናቡ፣ በተደጋጋሚ ከአፋር ክልል በኩል የሚተኮሱ ከባድ መሣሪያዎች ለተፈናቃዮች ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻል። አሁን ያለንበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው የሚለው ወጣቱ፣ ታጣቂ የነበሩ ወጣቶችና አብረው የተፈናቀሉ የፖሊስ አባላት መጠለያ ጣቢያውን በተራ እየጠበቁ መሆኑን ይገልጻል።

የተፈናቀልነው በማንነታችን ነው የሚሉው ወጣት ዝናቡ፣ “የገጠመን ነገር ሰላም ፈልጎ ሰላም ማጣት ነው” ይላል። “በሕወሓት አገዛዝ በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል ተካለን ለ30 ዓመታት መከራ ስናይ ኖረን፣ በማንነታችን ምክንያት መፈናቀላችንን መንግሥት ተገንዝቦ የማንነት ጥያቄያችንን ተቀብሎ አማራ ስለሆንን እንደ አማራ መታየት አለብን” የሚል ጥያቄ ከተፈናቃዮች ይሰማል።

አልፎ አልፎ በጥርጣሬ እንታያለን የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ መንግሥት በማንነታችን ምክንያት መፈናቀላችንን አምኖ ያለ ጥርጣሬ እንደ አማራ ሊያየን ይገባል የሚል ጥያቄ አላቸው።

አዲስ ማለዳ ያነገገረቻቸው ተፈናቃዮች ሕጻነት ሳይቀሩ ለመፈናቀላቸው እንደ ምክንያት የሚሉት፣ አማራ ማንነት ስላለን ከሚደርሰብን ጥቃት ሽሽተን ነው የሚል ነው። ይሁን እንጂ በተጠለሉበት አካባቢ በጥርጣሬ መታየታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ።

በጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በአብዛኛው ከአላማጣና አካባቢው በጦርነቱ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጥቃትና ወደ ጦርነት ተገዶ ከመግባት የሸሹ ሕጻናትና ወጣቶች ናቸው። ወደ ጃራ መጠለያ ከገቡ ከስድስት ወር በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ሰላም ተፈጥሮ በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት ሳይደርስባቸው በነጻነት መኖር ይሻሉ።

ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበት ሰላማዊ ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ ይህ ክረምት ካለቀ በኋላ በሚመጣው ሙቀት መቃጠል እንደማይፈልጉና ጦርነቱ መፍትሔ ካላገኘ የመጠለያ ቦታ እንዲቀየርላቸው ይፈልጋሉ።

ሕጻናቱመ ካሉበት ሁኔታ የመውጣት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ምን ትፈልጋላችሁ ሲባሉ የመጀመሪያ መልሳቸው “እርዳታም ምንም ሳንል ሰላም ሆኖ ወደ አገራችን መሄድ ነው” የሚል ነው።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች