‹የአታልፉም› ትዕዛዝ

0
1151

ልጃቸው በጠና ስለታመመ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ለማሳከም መነሻቸውን ሰቆጣ ከተማ አድርገው ሲጓዙ ቆይተው ደብረ ብርሃን ሲደርሱ እንዳያልፉ በፀጥታ ኃይሎች በመከልከላቸው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተገደዋል። አሳዛኝ ገጠመኛቸውን ለአዲስ ማለዳ የሚገልጹት ባለታሪኳ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለማቅናት የተገደዱት የአልጋ ቁራኛ ልጃቸውን ለማሳከም በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት ባደረጉት ሙከራ ስር ነቀልም ሆነ ጊዜያዊ መፍትሄ ባለማግኘታቸው ነው።

የሺወርቅ መኳንንት ይባላሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ልጃቸውን ለማሳከም ከዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሰቆጣ አካባቢ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን እንዳደረጉ ይገልጻሉ። ጉዟቸው አንገብጋቢ እና ትብብርን የሚሻ እንደነበር የሚናገሩት የታማሚው እናት፤ ጉዞውን አንገብጋቢ ያስባለውም ታማሚ ልጅ በመያዛቸው እንደነበር በአጽንኦት ያወሳሉ።

ወዳጅ ዘመድ የለገሳቸውን ብር ይዘው ልጃቸውን ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ለማሳከም እየተጓዙ ደብረ ብርሃን ሲደርሱ ግን እንዳያልፉ መከልከላቸውንና ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገው መመለሳቸውን አብራርተዋል።

ከሕመሙ ትንሽ እፎይታን አገኛለሁ በሚል ተስፋ የተሞላ ልጃቸውን ‹የአታልፉም› ትዕዛዙ ይበልጥ እንዳሳዘነው የሚናገሩት የሺወርቅ፣ ግን ለምን እንደዚህ ይሆናል? ሲሉ በሐዘን የታጀበ ጥያቄን በምሬት ይጠይቃሉ።

የሺወርቅ እንደሚሉት ከሆነ፤ ልጃቸው ከታመመ ሰንበትበት ብሏል። በአንድ ቀን ጉዞ አዲስ አበባ መድረስ ቢቻልም ታማሚው ስለሚደክም በወልድያና ደሴ ከተማ አልጋ ለመያዝ ተገደው ከትራንስፖርት ተጨማሪ ወጪ ማውጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

ይብሱን ያበሳጫቸው ወጪው ሳይሆን ኹለት ቀን ተጉዘው ምንነቱን በማያውቁት ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ታግደው ያሰቡትን ሳያሳኩ መመለሳቸው ሆኗል።

‹‹ሰላም ያደፈርሳሉ እንዳንባል ምንም የያዝነው ተልዕኮና ሰላምን የሚጻረር መሣሪያ አልተገኘብንም›› ያሉት የሺወርቅ፤ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መታወቂያቸውን በማየት ብቻ ‹አታልፉም› እንዳሏቸው በመገረም ያስታውሳሉ።

ምነው የታመመ እንኳ ታክሞ ከሕመም ስቃይ ትንሽ እረፍት ቢያገኝ ሲሉ ቅሬታውን የሰነዘሩ ሲሆን፤ በክልከላው ምክንያት ልጃቸውን ሳያሳክሙ ተመልሰው በደሴ ከተማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስሞታ አቅራቢዋ በተያያዘም፤ ‹‹በጦርነቱ ምክንያት በዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን የሚገኙ በርካታ ተፈናቃዮች  ያሉበት ሁኔታ መፍትሄ ሊሰጠው ሲገባ፣ መንግሥት አለ በተባለበት አገር እንዲህ የግፍ ግፍ መሥራት ሕሊናን አልፎ አጥንትን ይሰብራል›› ሲሉ ወቅሰዋል።

አብረዋቸው የነበሩ ተጓዦች ከፊሎቹ ወደየቤታቸው እንደተመለሱ ከፊሎቹ ደግሞ በደብረ ብርሃን እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ‹‹መንግሥት ካለ መፍትሄ ይስጠን። ለሕክምናም ማለፍ አልቻልኩም››  ሲሉ አሳስበዋል።

የሺወርቅ ብቻ ሳይሆኑ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከተለያዩ ሥፍራዎች ተሳፍረው ወደ አዲስ አዲስ አበባ የሚያቀኑ በርካታ መንገደኞች ከደብረ ብርሃን ወዲህ እንዳያልፉ በፀጥታ ኃይሎች ክልከላ እየተደረገባቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ክልከላው ሰሞኑን ብቻ የተከሰተ ሳይሆን ከዚህ በፊት የነበረ መሆኑንም በማስታወስ አማርረው በመግለጽ ላይ ናቸው።

የተደጋገመው ክልከላና የሕዝቡ ሰቆቃ

ተጓዦች ደብረ ብርሃን ከተማ ሲደርሱ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የመከልከላቸው ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማ አይደለም። ይልቁንም ከዚህ በፊት በነበረውና አሁን በድርድር ሊፈታ ይችላል በሚል ሙከራ ላይ ባለው ጦርነት ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ለሕወሓት ታጣቂዎች አስረክበው ሕይወታቸውን ብቻ ለማትረፍ ከተለያዩ ሥፍራዎች ወደ አዲስ አበባ ሲተሙ የነበሩ ተፈናቃዮች ደብረ ብርሃን ሲደርሱ እንዳያልፉ መታገዳቸው ይታወሳል።

ተፈናቃዮቹ እንዳያልፉ ታግደው የነበረው በ2014 ከዘጠኝ ወራት በፊት ገደማ ነው። ይህን ተከትሎም በርካታ ተሽከርካሪዎች ሸኖ አካባቢ ቆመው ነበር። መንግሥትም በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ እንደነበር አይዘነጋም።

በወቅቱ በተለይም ሸኖ አካባቢ በነበረው ጥብቅ ቁጥጥር ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በፀጥታ ኃይሎች በመታገዳቸው በርካታ አቅመ ደካሞች፣ አራስ የሆኑ እናቶች እንዲሁም ነፍሰ ጡሮች የሚውሉበትና የሚያድሩበት አጥተው እሮሮ ሲያቀርቡም ሰሚ አጥተው ችግሩን እንዲጋፈጡ ተገደው ነበር።

ታዲያ የሚረዳ ቤተሰብ ያለው በደብረ ብርሃን ከተማ ተከራይቶ፤ ዘመድ ያለው ተጠግቶ ቀሪው መንገድ ዳር ወድቆ ከኋላው ሲመጣ የነበረውን የሕወሓትን ታጣቂ በመስጋት መቆየታቸውን ያስታወሱ በርካታ ሰዎች አሁንም በድጋሚ መታገዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም በነበረው እገዳ ኬላ ላይ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ሰዎቹን ላለማሳለፍ እንደ ምክንያት ሲያነሱት የነበረው ጦርነቱ የተፏፏመበት ወቅት ስለነበር አሸባሪዎች ተመሳስለው ይገባሉ በሚል እሳቤ መሆኑ ተገልጾ ነበር።

ባለድርሻ አካላት ይህን ይበሉ እንጂ ተሳፋሪዎቹ እንዲሁም የፖለቲካ ምሁራን ደግሞ አሸባሪዎች ተመሳስለው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡና የሰላም መደፍረስ እንዳይፈጠር ነው ከሚለው እሳቤ በስተጀርባ በርካታ ፖሊቲካዊ ይዘት ያለው ጉዳይ ሳይኖር እንዳልቀረ በወቅቱ ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ወደ አዲስ አበባ የማለፍ ክልከላ እጣፈንታ በድጋሚ የገጠማቸው ሰዎች ድርጊቱ ሌላ አሻጥር ሳይኖረው እንዳልቀረና አግባብነት የሌለው ጉዳይ ስለመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን በማንሳት ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ሻምበል አወቀ ከተለያዩ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበሩ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት በመሸሽ ደብረ ብርሃን ሲደርሱ ወደ አዲስ አበባ እንዳያልፉ ተከልክለው ከነበሩትና አሁንም ተመሳሳይ ክስተት ከገጠማቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ከዚህ በፊት ለነበረው ወደ አዲስ አበባ የማለፍ ክልከላም መታወቂያን መሠረት ያደረገ እንደነበር ገልጸው፤ ‹‹ያኔስ እሺ የጦርነት ወቅት ስለነበር ተላላኪ/ሰላይ ተመሳስሎ ሰላም ወዳለበት ስፍራ ገብቶ እንዳያውክ በሚለው ተሳበበ። የሰሞኑ አታልፉም መባልስ ምን ተብሎ ሊሳበብ ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ተሳፋሪዎቹ ከአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም በዋግኸምራ የተለያዩ ወረዳና ቀበሌዎች ነዋሪ ሲሆኑ፤ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ቢፈልጉም ካሰቡት ቦታ እንዳይደርሱ መከልከላቸው ‹‹የመንግሥት ያለህ›› አስብሏቸዋል።

ተጓዦቹን ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የከለከሏቸው የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት መሆናቸውን እና ድርጊቱን የሚፈጽሙትም የአማራ መታወቂያ የያዙትን ተሳፋሪዎች በመለየት ስለመሆኑ ከተለያዩ ሥፍራዎች መጥተው ደብረ ብርሃን ሲደርሱ ‹‹ወደ አዲስ አበባ አታልፉም›› የተባሉ ሰዎች በቅሬታቸው ተናግረዋል።

አንገብጋቢ እና አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሟቸው ‹እንደርስ ወይስ እንዘገይ ይሆን?….የመኪና ጉዞ በክረምት ወቅት ይቅርና በበጋውም እንከን አያጣውም› ከሚለው ስጋት ውጪ ሌላ እንከን ይገጥማል ብለው እንዳላሰቡ ይገልጻሉ። ቢሆንም ግን ዓላማቸውን ለማሳካት አንድ ቀን ብቻ የነበራቸው በርካታ ተጓዦች ‹አታልፉም› በመባላቸው ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ መደነቃቀፋቸው በሕይወታችን ላይ ጥቁር አሻራ አሳድሯል ነው የሚሉት።

የኦሮሚያ ፀጥታ አካላት ከደብረ ብርሃን አልፈን ወደ አዲስ አበባ እንዳንገባ ክልከላ አድርገውብናል የሚሉት ተጓዦቹ፤ የተለያዩ አፋጣኝ ጉዳዮች ለማሳካት ያቀዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እቅዳቸውን ሳያሳኩ ወደነበሩበት ለመመለስ የተገደዱና በደብረ ብርሃን የሚገኙ ቅሬታ አቅራቢዎች በገለጹት መሠረት፤ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣታቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋና ዋና የሚሏቸውን ጠቅሰዋል።

ይኸውም ታማሚ ለማሳከም፤ ሥራ አጥነት ሲያማርራቸው የኖሩና እድል ገጥሟቸው ሥራ ለመቀጠር ለፈተና የተጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፤ ቤተሰብ ሞቶባቸው ለቀብር ሥነሥርዓት መቆም የፈለጉ ሀዘንተኞች፤ በንግድ ሥራ ተሰማርተው ትዳር የሚመሩ ነጋዴዎች፤ የተለያዩ የክረምት ሥልጠናዎችን ለመውሰድ የሚሹ ተማሪዎች፤ የሥራ ቅጥር ካወጡ ተቋማት በአካል ተገኝተው ማመልከቻ ለማስገባት የሚጣደፉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፤ የሕክምና መሣሪያዎችን ሊገዙ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌላ መሰል ምክንያት ያነገቡ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ምኒልክ ፈንታው የሜካኒካል ኢንጅነሪነግ ምሩቅ መሆኑን ገልጾ፤ በአዲስ አበባ በሚገኝ ተቋም የሥራ ማመልከቻ አስገብቶ ስለነበር ከሳምንት በፊት ለፈተና በመጠራቱ መነሻውን ወልድያ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጓዘ ነበር። ይሁን እንጂ ደብረ ብርሃን ሲደርስ እንዳያልፍ መታገዱን ይናገራል።

ምኒልክ ‹‹የፀጥታ ኃይል መታወቂያዬን ዐየ። ከዛም ማለፍ እንደማልችል ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቅ እንኳ ምላሽ ሊሰጠኝ ፈቃደኛ አይደለም። እኔ ግን የትምህርት ማስረጃዬን እያሳየሁ በተደጋጋሚ ‹ኧረ! ለነገ ፈተና ተጠርቼ ነው› የሚል ሰሚ የሌለው ተማፅኖየን እያሰማሁ ነበር›› ነው ያለው።

በልብስ ንግድ ሥራ ተሰማርተው ትዳር እየመሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ሌላኛው ወዳጆ አለበል የተባሉት ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው፣ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው የንግድ እቃዎችን ለመውሰድ ያደረጉት ጉዞ ሳይሳካላቸው እንደቀረ በማዘን ገልጸዋል። የልብስ ነጋዴው ከደቡብ ወሎ የተለያዩ ስፍራዎች የመጡ በርካታ ሰዎች እንዳሉና ወደ አዲስ አበባ እንዳያልፉ መከልከላቸውን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የተነሳው ቅሬታ ተሳፋሪዎቹ ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው መጠን ከአንዱ ወደ ሌላኛው ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ አካላት መጣሱ ሳያንስ ዓላማቸውን ማሳካት አለመቻላቸው ብሎም ከታሪፍ በላይ ለሆነ ክፍያ መዳረጋቸው ነው።

ሹፌሮች የሚጠይቁት መንግሥት በየኪሎ ሜትሩ እንዲከፈል የተመነውን ታሪፍ ሳይሆን፣ ከታሪፉ ከኹለት እስከ ሦስት እጥፍ የሚደርስ ብር ነው ተብሏል። እንደ ገለጻው ከሆነ፤ ጭራሹን ትራፊክ ዝር የማይልበት ቦታም የሚገኝ ሲሆን፤ አንዳንድ መንገድ ዳር የሚገኙ ትራፊኮችም እንደወጉ ተሽከርካሪውን አስቁመው ከሹፌሩ ጋር በመጨባበጥ ብር ተቀብለው የግል ጥቅማቸውን በማሳካት የሚያልፉ እንጂ ስለታሪፍና ስለትርፍ መጫን የሚጠይቁት አልፎ አልፎ ነው ተብሏል።

ከተሳፋሪዎች መካካል ወዳጆ አለበል፣ ‹‹ሹፌሩ የትራፊክ ፖሊሱን ገና ከርቀት ሲያይ በቅድሚያ ብር አዘጋጅቶ ይጠባበቅ ነበር። ከትራፊክ ፖሊሱ ሲደርስ እንዲቆም ምልክት ተሰጠውና አቆመ። ቀጥሎም ትራፊኩ መጥቶ ለሕዝቡ ሰላምታ አቀረበ። መኪናው በሕዝብ ብዛት ታጭቆ ነበር። ይሁን እንጂ ስንት ነው የከፈላችሁት ብሎ እንኳን ሳይጠይቅ ቀጥታ ወደ ሹፌሩ ሄደና በመጨባበጥ ብሩን ተቀብሎ መልካም ጉዞን ተመኘ›› ሲሉ ጋቢና ውስጥ ሆነው ሲከታተሉት የነበረውንና በዐይናቸው ያዩትን ድርጊት ተናግረዋል።

ተሳፋሪዎቹ በጥቅሉ ይህ ዓይነት ድርጊትና ክልከላ ማኅበረሰቡን ለችግርና እንግልት እየዳረገ መሆኑን አውስተው ‹‹ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ካልሆነ ደግሞ ሕዝብ ሲያምጽ መንግሥት ማጣፊያው እንዳያጥረው›› የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በየአቅጣጫው ያለ የመንገድ መዘጋት

የመንገድ መዘጋጋት ደብረ ብርሃን ብቻ የተከሰተ ችግር አይደለም። በተለያዩ ሥፍራዎች በአንድም በሌላም ምክንያት ለዓመታት የተዘጋጉ መንገዶች መኖራቸው እሙን ነው። ይህን ተከትሎም በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህም በተለያዩ ሥፍራዎች የሚከሰትና ስር ሰዶ ዓመታትን ያስቆጠረ ክስተት ሆኗል።

በተለይም ታጣቂዎች በሚሰነዝሩት ጥቃት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ሥፍራዎች መንገዶች መዘጋጋታቸው፤ ነዋሪዎች የድረሱልኝ ጥሪያቸውን መለፈፋቸው ከመደጋገሙም አልፎ መፍትሄ ሳይሰጠው እንዲሁ እንደ ልምድ እየተቆጠረ የመጣ ይመስላል።

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የነበሩ ነዋሪዎች ታጣቂዎች ከሚሰነዝሩት ጥቃት ለማምለጥ እንዳይቻላቸው ‹‹መንገድ ተዘግቶብናል፤ ታግተናል›› በማለት ሲናገሩ ኖረዋል። አሁንም ድርጊቱ እንዳልቆመ እየተሰማ ነው።

በተጓዳኝ በታጣቂዎች ምክንያት በደቡብ ክልል በአማሮ ልዩ ወረዳ ያሉ ቀበሌዎች ሲንቀሳቀሱበት የነበረ ከሐዋሳ እስከ ዲላ፤ ከዲላ እስከ አማሮ የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ ሰባት ዓመት እንዳስቆጠረና እስከ አሁን እንዳልተከፈተም ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው አይዘነጋም።

የአካባቢው ነዋሪዎች ኦነግ ሸኔ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በአማሮ ልዩ ወረዳ ጥቃት ማድረሱን እንዳላቆመ ከለላ የሚያደርግ የመከላከያ ኃይል በብዛት እንደሌለ ብሎም የመንገድ መዘጋጋት ለሕይወታቸው አስጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ተፈጻሚነት ያጣው ሕግ

ተግባራዊነቱ የራስ ምታት ሆኖ ቢስተዋልም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ባለሙሉ መብት ስለመሆናቸው ደንግጎ ማስቀመጡን የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ አሁን ያለውን ሕገመንግሥት ጨምሮ አራት ሕገ መንግሥቶች ነበሯት። እነዚህም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የወጣው የ1923 እና 1948ቱ፤ በደርግ ስርዓት የወጣው የ1980ው እንዲሁም አሁን ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሆናቸውን የሕግ ባለሙያው ዘፋንያህ ዓለሙ ‹የሰብአዊ መብት ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ› በሚል ርዕሰ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ አውስተዋል።

ታዲያ በአፄዎቹ ጊዜ በነበረው የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ሳይቀር እስካሁን ድረስ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ሲደነገግ ቢመጣም፣ አሁን ተፈጻሚነት ማጣቱ ግን በግልጽ እየተስተዋለ ስለመሆኑ መሬት ላይ ያለው ሀቅ ሕያው ምስክር ሆኗል። የሕግ ባለሙያው እንዳሉት፣ ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት እንኳ የንጉሡ ሥልጣን ላይ ያተኩራል ሲባል የነበረው የአፄ ኃይለሥላሴ የ1923 ሕገ መንግሥትም የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ይደነግግ ነበር።

በ1923ቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22 የዜጎች የነጻነት መብት፤ አንቀጽ 23 ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ዜጎች መብታቸው መጣስ እንደሌለበት እንዲሁም በአንቀጽ 26 የዜጎች የግል ሕይወት መከበርና መጠበቅ እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል። አሁን በሥራ ላይ አለ የሚባለውን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን ጨምሮ ከዚያ በፊት የተደነገጉት ሕግጋት የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነቅፍ እንዳልነበር የሕግ ባለሙያው በጽሑፋቸው አስፍረዋል።

ይሁን እንጂ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንዲሁ ዝም ብሎ በድንጋጌ ቢሰፍርም፣ ተፈጻሚነቱ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል የሚል ቅሬታ በበርካቶች በኩል እየተነሳ ነው።

በተለይም የመብት ጥሰቱ የሚከናወነው ‹‹ሕግ አስከባሪ ነን›› በሚሉ አካላት መሆኑ ቅሬታ ሲያስነሳ ተስተውሏል። ይህን ቅሬታ የሚያነሱት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሙሉ መብት እንዳላቸው የሚያነሱትና ደብረ ብርሃን ሲደርሱ በፀጥታ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ አታልፉም የተባሉ ተሳፋሪዎች ናቸው።

ከተሳፋሪዎቹ በተጨማሪ የሕግ ባለሙያዎችም፣ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ እንደተሳነው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ደግሞ በአንቀጽ 13 ንዑስ አንቀፅ 1 ስር በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፤ ሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት አካሎች በምዕራፉ የተካተቱ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳላቸው እንደሚደነግግ የሕግ ባለሙያው ዘፋንያህ አስቀምጠዋል።

ስለዚህም ማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የመንግሥት አካል የዜጎችን ሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብት የማስጠበቅ እና የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ስለመሆኑም በጽሑፋቸው አብራርተዋል።

በመሆኑም የፀጥታ ኃይሎች የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሙሉ መብት ሲጋፉ መንግሥት ዝም ብሎ መመልከቱ፤ ሕግ አስከባሪ ነን የሚሉት አካላት በበኩላቸው ሕግ ጥሰው ሕግ አስከበርን ማለታቸው ብዙዎችን ያበሳጨ ክስተት ሆኗል።

ፖለቲካዊ አንድምታ

በፀጥታ ኃይሎች መንገድ መዘጋቱ፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚጥስና የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ መንገድ መዝጋት ፖሊቲካዊ የሆነ ይዘት አለው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ ሱራፌል አብዱ ናቸው።

‹‹ኢትዮጵያዊ ያልሆነ የውጭ አካል እንኳ በፍተሻ ወቅት ምንም ዓይነት እንከን ካልተገኘበት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ በምትፈቅድ አገር፣ ሕዝቦቿ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ክልል፤ ከተማና ቀበሌ እንዳይንቀሳቀስ በፀጥታ ኃይሎች ማገድ ተገቢነትም ተቀባይነትም የለውም።›› ብለዋል።

የአማራ ክልል ተወላጆች ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንዳይገቡ በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የሚታገዱ ከሆነ፤ የአማራ ተወላጆች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባ መኖር አይችሉም የሚል መልዕክት ነው ያለው ብለዋል የፖለቲካ ተንታኙ። በመሆኑም፣ አዲስ አበባ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሰባጥረው፤ ተጋብተው፤ ተዋልደው የሚኖሩባት በመሆኗ ይህ ከመንግሥት አይጠበቅም ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ በኩልም ቢሆን፤ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በጥልቅ ማሰብ እና ማስተካከል አለበት የተባለ ሲሆን፤  የፖለቲካ ተንታኙ በበኩላቸው ይህ ጉዳይ ከምንም በላይ መንግሥት ሊያስተካክለው የሚገባ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here