መነሻ ገጽአንደበትየማኅበራቱ ኅብረት - ከየት ወደ የት?

የማኅበራቱ ኅብረት – ከየት ወደ የት?

አዜብ ቀለመወርቅ ይባላሉ። በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በተለይም በፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከጀማሪ ባለሞያነት እስከ መምሪያ ኃላፊ ደረጃ ድረስ ሠርተዋል። ከዛ በኋላ ነው ወደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አቅንተው የኢትዮጵያ የሴቶችና ሕጻናት ማኅበራት ኅብረትን በመሪነት የተቀላቀሉት። 25 ዓመት ከተሻገረው የሥራ ልምዳቸው ውስጥም 12 የሚሆነው ዓመት ይህን ኅብረት በማስተዳደር ያሳለፉበት ነው።

ኅብረቱ ታድያ 80 የሚጠጉ ማኅበራትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ ሴቶችና ሕጻናትን በሚመለከት አያገባኝም የሚለው ጉዳይ የለም። በቅርቡም የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን በሚመለከት አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህም ከዓመት በፊት ከመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ጋር የፈጠረውን የጋራ መድረክ መነሻ በማድረግ፣ ያንን ለማስቀጠልና ለማጠናከር የሚያስችል እርምጃ ወስዷል። አዲስ ማለዳም ከአዜብ ጋር የተገናኘችው በዚሁ መድረክ ነው።

የኅብረቱን አመሠራረት፣ ወቅታዊ ሥራዎችና ወደፊት እቅዶች በሚመለከት የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ የሴቶችና ሕጻናት ማኅበራት ኅብረት ዋና ሥራ አስኪያጅ አዜብ ቀለመወርቅ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕጻናት ማኅበራት ኅብረትን ያስተዋውቁን?

ኅብረቱ በ2002 ነው የተቋቋመው። ዋና ዓላማው ለሴቶችና ሕጻናት የሚሠሩ ድርጅቶች የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል፣ ችግሮቻቸውን የሚያነሱበትና ሐሳብ የሚቀያየሩበት እንዲሁም የአቅም ግንባታ የሚፈጥሩበት መድረክ ለመፍጠር ነው። በወቅቱም 26 አባላት ናቸው የመሠረቱት። አሁን አባላቱ ወደ 80 ደርሰዋል፤ በሁሉም ክልል ላይ የሚሠሩ አባላት አሉን።

በዋናነት በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ አቅም መፍጠርና በነዛም ያሉ ችግሮች ለመቅረፍ የችግሮች መንስኤ በማየትና በዛ ላይ በማተኮር፤ የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይሠራል። እንዲሁም የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማምጣት የሰብአዊ መብቶች መከበር፤ በተለይ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ጠለፋ እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኩራል።

እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በሚመለከትም፣ በተለይ ለወጣቶችና በትምህርት ቤቶች የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማምጣት ብሎም የሥነ ተወልዶ ትምህርቶችን በመስጠት ይሠራል።

ከዛ በተጓዳኝ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ መስጠት አንዱ ሥራችን ነው። ለምሳሌ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ አማራ እና ትግራይ አካባቢ ባለፉት ዓመታት ድጋፍ እየሰጠን ነበር። በጎርፍ እና በግጭት ለተጎዱም እንደዛው ድጋፍ እየሰጠ ነበር፤ አሁንም ይሰጣል።

ሌላው ሴቶችን ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት እንዲያግዘን አንዱ የምንሠራበት ጉዳይ በምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ መጨመር ላይ ነው። በተጓዳኝ ሰላም ማስፈንና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሴቶች ሚና ምን ይመስላል፣ በምን መልኩ ይሳተፉ የሚለው አንዱ ጉዳያችን ነው።

ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ፣ ወደ ትምህርት እንዳይገቡ ወይም የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንዳይኖራቸው አስሮ ያዛቸው ክፍያ የማይከፈልባቸውን ትኩረት የማይሰጣቸው የቤት ውስጥ የሥራ ጫናዎች ናቸው። እነዚህን ለመቅረፍ ታድያ ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ግንዛቤና አቅም መፍጠርንም ትኩረት ሰጥተናል። የተለያዩ የውትወታ ሥራዎችን መሥራት ላይ በማተኮርም ነው እየሠራን ያለነው።

ሥራዎችን በሦስት መልኩ ነው የምንሠራው። አንደኛ ከአባሎቻችን ወይም በሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንሠራለን። በዚህም ፕሮጀክቶችን፣ ቅስቀሳና የአቅም ግንባታ ላይ በጋራ እናከናውናለን። ሌላው ከመንግሥት አካላት ጋር በጋራ እንሠራለን። በተለይ ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር፣ የሴቶች የከባቢ የአየር ለውጥ የሚቋቋም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አቅም መፍጠር በሚለው ዙሪያ፣ ከ12 አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን በ5 ክልሎች ለ5 ዓመታት ሠርተናል።

ከ‹ክላይሜት ጀስቲስ› ጋር በተያያዘ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ በኦሮሚያም በባለፉት ኹለትና ሦስት ወራት ሦስት ሺሕ በላይ ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የሚስችል ድጋፍ ሰጥተናል።

ስለዚህ ኅብረቱ በአጠቃላይ ለአባላት አቅም በመፍጠር፣ የሴቶችና ሕጻናትን ችግሮች ለመቅረፍ ከአባላትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የሚሠራቸው ብዙ ሥራዎች አሉ።

አስቀድሞ እንዳሉት አሁን ላይ ኅብረቱ 80 የሚጠጉ አባላት አሉት። በርከት ያሉ ዓመታትን የቆዩ ማኅበራትም አሉ። ምን ያህል እየሠሩ ነው? ለኀብረቱስ ምን ያህል አቅም ሆነዋል?

አሁን አቅም መፍጠር ወይም በጋራ ያሉትን ችግሮች አውጥቶ በጋራ የውትወታ ሥራ መሥራትና በዋናነትም ለሴቶች ድምጽ መሆን ላይ ነው የምናተኩረው። በጋራ የምንሠራው ጥናቶችን ማካሄድ ላይ ነው። ችግሩ ምንድን ነው የሚለው ላይ ጥናት አድርገናል። በአመራር፣ በከባቢ አየር ለውጥ፣ በተጠያቂነትና መሠረታዊ አገልግሎቶች በምን መልኩ ነው እየተሰጡ ያሉት፣ ሴቶችና ሕጻናትስ የእነዚህ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽና ተጠቃሚ ናቸው ወይ የሚለውን በሚመለከት ጥናቶች እንሠራለን፤ ሠርተናልም።

አሁን ደግሞ ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር ሆነን፣ በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የአመራር አቅማቸውን ለማጎልበት የሚያስችል፣ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው። ከአክሽን ኤይድ ጋር በመሆን ደግሞ ወደተለያዩ አገራት የሚፈልሱ ወጣቶችን ለማስቀረት እየሠራን ነው ያለነው።

- ይከተሉን -Social Media

እነዚህ ሁሉ ድምጽ የመሆን፣ በጋራ የመሥራት ጥረቶች ናቸው። መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ ለሴቶችም ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር ነው። ትልቁ የኢኮኖሚ አቅም፣ የትምህርት እድል አለመኖር ነው። እናም የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ የገቢ አቅማቸውን ለማጎልበት እንዲቻል በጋራ ፕሮጀክቶችን እንተገብራለን። ከመንግሥት አካላትም ጋር እንነጋገራለን። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችንም ለማስቀረት የጋራ መግለጫ ማውጣት፣ ውይይት ማካሄድና የመሳሰለው ላይ በጋራ እንሠራለን።

አሁን በኢትዮጵያ ካለው አለመረጋጋትና ሰላም ማጣት በከፍተኛ ሁኔታ ሕጻናትና ሴቶች ተጎጂ ናቸው። በሥማችሁ ውስጥ ሴቶች ብቻ ሳይሆን ሕጻናትም አሉና፤ ለሕጻናት ምን ተደረገ? በድምሩስ በጉዳዩ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

ሕጻናትን ከእናቶቻቸው ለይተን አናያቸውም። ለምሳሌ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ወላጅ አልባ ሕጻናት ከአሳዳጊ ቤተሰብ ወይም አሳድጋለሁ ብሎ ኃላፊነት የሚወስድ የቅርብ ዘመድ፣ ያም ከሌለ እንደዚሁ ሌላ የቅርብ የሚባል በአካባቢው የሚኖር ሰው ተፈልጎ ሕጻናቱን እንዲያሳድጉ ይደረጋል። ያንን ድጋፍ ለሚያደርግ ሰውም የኢኮኖሚ ድጋፍ ነው የምናደርገው።

የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ ቀጥታ ለልጆች ሊሰጣቸው ይችላል። በዋናነት ግን ወላጅ ወይም ቤተሰብ ሕጻናቱን መደገፍ እንዲችል የሥራ እድል መፍጠር ነው።

ከዚህ ባሻገር የጎዳና ተዳዳሪዎችን በምን መልክ መደገፍ አለብን የሚል፣ አልፎ አልፎም በዓላት ሲሆን የቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማቸው ገንዘብና ልብስ በማሰባሰብ ለእነሱ ድጋፍ እናደርጋለን። ይህንንም በተለይ ከወጣት ሮተሪያን ጋር በመሆን ነው የምናከናውነው።

ካለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ፣ በቂ ባይሆንም ለተፈናቀሉ ዜጎች ከማኅበራዊ ጉዳይ እና እንዲሁም ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን፣ በቀጥታም ለተለያዩ ክልሎች ድጋፍ አድርገናል።

ከዛ ባሻገር ውይይቶችን አካሂደናል። የሴቶች ድርጅቶች ይህ አሁን ያለው በአገራችን የተፈጠረው ግጭት በሴቶች ላይ እያደረሰ ያለውን መዓት በምን መልኩ ነው የምናስቀረው በሚለው ዙሪያ እንወያያለን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይህ ነገር እየተከናወነ ያለው? ኢትዮጵያዊ ነው ወይ ይህን እያደረገ ያለው? የሚለውን ለመናገር የሚከብዱ ነገሮች እየሆኑ አሉ። ስለዚህ የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ላይ የተለያዩ ውይይቶች እናደርጋለን። በየፕሮጀክቶቻችንም ከአባላት ጋር በምናካሂዳቸው ውይይቶች ይህን ሐሳብ በማንሳት፣ የማኅበረሰቡን ሐሳብ በተለይ የወጣቶችን በማካተት እየሠራን እንገኛለን።

- ይከተሉን -Social Media

በምናገኘው ድጋፍም በተለያዩ ከተሞች ወጣቶች ወደ ግጭቶች እንዳይገቡ ምን ማድረግ አለብን የሚሉ ውይይቶችን አድርገናል። ከሥራ እድል መፍጠር ጋር የሠራናቸው ሥራዎችም አሉ።

ፕሮጀክቶቻችን ውስጥ በሚካሄዱ ውይይቶች ሰላምን ለማምጣት ምን እናድርግ የሚለውን በሚመለከት ውይይት እናካሂዳለን። ከዛ ውጪ አንድ መድረክ አለን። ይህም አባሎቻችን ያቋቋሙት ነው። የሴቶች ድርጅቶች ሰላም ማምጣትና ግጭት መፍታት ዙሪያ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚመካከሩበት፣ ሐሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበትና የማኅበረሰቡን ስሜት የሚያንጸባቁበት መድረክ ነው። ከዛ ባሻገር ለወደፊቱ ማኅበረሰቡ በተለይ ሴቶች በሚካሄዱ የውይይት እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ የበለጠ እንሠራለን።

መንግሥት ላይ ጫና መፍጠር የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ይታመናል። አንደኛው በተለይ ሴቶችና ሕጻናትን በሚመለከት ሕጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡና ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በዚህ ላይ ኅብረቱ ጫና የመፍጠር ምን ያህል አቅም አለው?

አቅም ማለት በጋራ ሆነሽ የምታነሺያቸው ጉዳዮች ናቸው። ለነዛም መረጃና ማስረጃ መሠረት ያደረጉ ነገሮችን ማቅረብ ወሳኝ ነው። ስለዚህ እኛ የምናደርገው፣ ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ ጥናቶችን ነው።

ለምሳሌ የመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ፤ ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ የምስክር ወርቀት (ሰርተፍኬት) የመስጠት ሥራ በመንግሥት በኩል በሰፊው እየተሠራ ነው። ግን በዛ የምስክር ወረቀት ላይ ፎቶዋ ስለተለጠፈና ሥሟ በዛ ላይ ስለገባ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ናት ማለት አይደለም። በጣም ብዙ ችግሮች እየደረሰባቸው ያሉ ሴቶች አሉ።

በተለይ በገጠሪቱ የአገራችን ክፍሎች ጠጋ ብለን ስናይ፣ መሬታቸውን የሚነጠቁ፣ መሬት ይዘው እንኳ ከእርሻ ምርታቸው ድርሻቸው በሚገባ የማይደርሳቸው አሉ። በውርስም ይሁን በፍቺ ተመሳሳይ ችግር የሚገጥማቸው አሉ። እንደውም ከትዳሯ ሳትፋታ ከባለቤቷና ከቤተሰቧ ጋር አብራ እያለችም ጭምር ሴቷ የሚገባትን የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኘች አይደለም።

እና በዛ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመወያየትና የፖሊሲ ክለሳ በማድረግ፣ የአሠራር ችግሮችን ለይተን በማውጣት እንዳየነው፤ የአፈጻጸም ችግሮች አሉ። ያሉትን እነዚህን ችግሮች በጥናት እንለያለን።

ሌላው ለምሳሌ ባህላዊ እና ባህላዊ ያልሆኑ ሕጎች የሚጋጩበት ሁኔታ አለ። አንድ ወንድ ከአንድ ሴት በላይ ማግባት የሚችልበት ባህላዊ ሕግ ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። በዚህ ወቅት የትኛዋ ናት መሬቱን የምትቀበለው? ሲካፈሉ በምን መልኩ ነው ወዘተ የሚል ጥያቄ ይነሳል። እንዲህ ያሉ ባህላዊና ባህላዊ ያልሆኑ ሕጎችን አጣጥሞ መሄድ የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው። እና እነዚህን አጣጥሞ እንዴት መሄድ እንደሚቻል የምንወያይባቸው ብዙ መድረኮች አድርገናል።

- ይከተሉን -Social Media

ከዚህ ባሻገር የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ወይም በአጠቃላይ ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ከባብያዊ እንዲሁም ተያያዥ ችግሮች ለመቅረፍ፣ ብዙ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እና የልማት ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ የሴቶች የልማት ፓኬጅ ተብለው የመጡ ነገሮች አሉ።

ነገር ግን እነሱን ለማስፈጸም የሚቀመጡ ስልቶች ግልጽ አይሆኑም። ወይም ደግሞ በጀት አመዳደብ ላይ ችግር ይኖራል። የስርዓተ ጾታ በጀት አመዳደብ ስርዓት አለ፤ የበጀት አስተዳደር አዋጅም ሴቶች ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚደግፉ አንቀጾች አሉት። ከሕገመንግሥት ጀምሮ እነዚህ አሉ። ግን ወደ አፈጻጸም ስትመጪ፣ እነዚህን ሕጎች ወይም የልማት ፓኬጆች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በጀት ካልተመደበ፤ ትርጉሙ ምንድን ነው? ውጤታማ መሆንም አይችልም።

ስለዚህ የስርዓተ ጾታ ምላሽ ጋር የተያያዘ የበጀት ምደባ ጋር በተገናኘ ጥናት አድርገን፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት አካሂደናል። አሁን በቀጣይም የሚኖሩ መድረኮች አሉ። እናም ከአባላት ጋር አብረን በጋራ ሆነን፣ እነዚህ ችግሮች ይፈቱ ስንል ምን ጥቅም አለው? ጥቅሙስ ለሴቶች ብቻ ነው ወይ? ለልጆቻቸውና የትዳር አጋራቸው፣ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብና ለአገርስ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ምንድን ነው አስተዋጽኦው በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክርና ውይይቶችን እናካሂዳለን።

አሁን የተገናኘነው ኅብረቱ ከመገናኛ ብዙኀን ጋር በጥምረት በፈጠረው መድረክ ላይ ነው። በዚህም ክፍያ የማይፈጸምባቸውና ትኩረት ያልተሰጣቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ተነስተዋል። እስከ አሁን ምን ጥሩ ነገር ዐያችሁ? ለወደፊት ምን ታቀደ?

ይህ ከጋዜጠኞች ጋር ክፍያ የማይፈጸምባቸውና ትኩረት ያልተሰጣቸው የሴቶችን የቤት ውስጥ የሥራ ጫና ለመቅረፍ የዛሬ ዓመት የተቋቋመ መድረክ ነው።

እነዚህ ክፍያ የማይከፈልባቸውና ትኩረት ያልተሰጣቸው የሴቶች የቤት ውስጥ የሥራ ጫናዎች (Unpaid Domestic Care work) ብለን የምንጠራቸው፤ በዋናነት ማኅበረሰቡ ውስጥ የሴቶች ሥራዎች ናቸው የሚል ግንዛቤ የተያዘባቸው ናቸው። ስለዚህም ‹የእነሱ [የሴቶች] ኃላፊነት ነው፤ እነሱ ናቸው መወጣት ያለባቸው› የሚል አመለካከት ነው ያለው። እንጂ እንደማንኛውም ሰው እኩል ተካፍለን ሠርተን፣ ለቤተሰባችን የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር እንችላለን የሚል ዕይታ አይደለም።

ምክንያቱም ሴቷን በተለያየ መልኩ እየጎዳት ነው ያለው። ውሃ ለመቅዳት፣ እንጨት ለመልቀም ወይም በአጠቃላይ በተፈጥሮ ከተሰጣት ልጅ ከመውለድ ጸጋ በተጨማሪ የምትሠራቸው ሥራዎች በቀን እስከ 18 እና 20 ሰዓት ድረስ እንደሚወስዱ ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።

በእርግጥ እንደ ክልሉ ቢለያይም፤ ማንኛዋም ሴት በአማካይ እስከ ስድስት እና ሰባት ሰዓት ክፍያ የማይከፈልባቸውን ሥራዎችን ነው የምትሠራው። ውጪ ውላም የምትመጣ ትሁን ወይም ቤት ውስጥም ትሁን፣ ያው ነው። ይህም እንደ ማኅበሰረቡ የአኗኗር ሁኔታ እና ሴቷ እንዳላት የሥራ እድል የሚለያይ ሆኖ፤ በቀን እስከ 18 ሰኣት በዚህ ሥራ ተሰማርተው የሚውሉ ሴቶች አሉ።

እና ይህ ደግሞ ትምህርት እድል እንዳያገኙ፣ ጊዜ እንዳይኖራቸው፣ በጤናቸውም ላይ ጉዳት ያስከትላል፤ ድካም እንዲኖራቸውና እረፍት እንዳያገኙ፣ በቂ እንቅልፍ እንዳይወስዱ ያደርጋል፤ በማገዶ ምግብ ሲያበስሉ ወይም አጠቃላይ የቤት ሥራ ሲሠሩ ከራሳቸው ብቻ ሳይሆን የልጆች ጤና ጭምር እክል ሊጋጥመው ይችላል።

እንዲሁም ውሃ ልትቀዳ ርቃ ስትሄድ መንገድ ላይ የሚያጋጥማት ነገር አለ፡፡ መጠለፍና ተገዶ የመደፈር አለ። የሚወስደው ጊዜውም ረጅም በመሆኑ፤ ከአቅሟ በላይ መሸከም አለ። እነዚህ ነገሮች ለጤና፣ የትምህርት እድል እንዳይኖራቸው፤ የትምህርት እድል ኖሯቸው የተሻለ ገቢ እንዳይኖር ያገደ ነው። ምርታማነታቸውን አስሮ የያዘ ችግር ነው።

ስለዚህ ይህን ችግር ብንቀርፈው ለአገር እድገት አስተዋጽኦ አለው። ጥናቶች እንዳሳዩት ሴቶች በቀን በማይከፈልባቸውና ትኩረት ባልተሰጣቸው የሥራ መስኮች ከሚያጠፉት ሰዓት 2 ሰዓት ብንቀንስ፣ ለአገር የኦኮኖሚ እድገት 10 በመቶ እንደሚጨምር ነው።

እናም ይህ ከሆነ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ድህነትን ለማጥፋት በጋራ ምን ማድረግ አለብን። የማኅረሰብን ግንዛቤ ማሻሻል፣ መቀየር አለብን ከሚል፣ ለዚህ ደግሞ ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቆ ለመግባት የግድ የሚድያ ባለሞያዎች እና ድርጅቶች፣ ታች ድረስ ወርደውና ዘልቀው የሚሠሩ በመሆናቸው፤ ከእነርሱ ጋር አብረን ለመሥራት ያቋቋምነው ነው።

እስከ አሁን በጋራ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ ውይይቶች እንዲሁም በ16 ቀን የንቅናቄ (አክቲቪዝም) እና የሴቶች ዓለማቀፍ ቀን ላይ ተገናኝተናል። አሁንም ሐሳብ የምንለዋወጥበት፣ የአቅም ግንባታ የምንፈጥርበት፣ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የምንፈጥርበት መድረክ ነው። እዚህ ደረጃ ደርሰናል። ዛሬ ደግሞ በዚህ መድረክ ወይም ፎረም በምን መልክ በጋራ እንሠራለን፣ ምን ላይስ እናተኩር የሚለውን በሚመለከት አንድ መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተናል።

በዚህም መድረክ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለይተን አውጥተናል። እና ሁላችንም ያለንን ሀብት አሰባስበን አቀናጅተን በጋራ የምሠራበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ምክንያቱም በፖሊሲም፣ በሕግ ማዕቀፍም፣ በአወቃቀር፣ በግንዛቤና በአቅም ዙሪያ በጣም ብዙ መሻሻል ያሉብን ጉዳዮች አሉ። እና እነዚህ ላይ ለመሥራት የግድ መተባበር ያስፈልጋል። ይህን ትብብር ለማምጣት ታስቦ ነው ይህ መድረክም የተቋቋመው።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች