መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየድርድር ጥረቶች እና ያለመተማመን ድባብ

የድርድር ጥረቶች እና ያለመተማመን ድባብ

ኹለት ዓመቱን ሊደፍን ሦስት ወር ገደማ የቀረውና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተነሳው ጦርነት፣ ድርድር እንዲያስቆመውና ከዚህ በላይ እድሜ እንዳይኖረው ብዙዎች ከምኞት ጋር ተስፋ አድርገዋል። በአደራዳሪነትም የተለያዩ አገራትና የአገራት ኅብረቶች አለን ብለው ወዲያ ወዲህ እያሉ፤ መልዕክት እያደረሱ እና ዕይታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

በተጓዳኝ ታድያ ድርድሩ የተፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ምክንያት የሆነው ያለመተማመን መሆኑን ከአደራዳሪዎቹ መካከል ሲናገሩ ተደምጧል። ስለ ድርድር ንግግር እየተደረገ ሳለ እርስ በእርስ መጎሰሰምና ክፉ መነጋገሩም ይቆይ ሲሉ አደራዳሪዎቹ ኹለቱን አካላት እያሳሰቡ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳትና የተለያዩ ዘገባዎችን በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በሰላማዊ ድርድር እንዲቋጭ የተለያዩ አካላት ገና ከጅምሩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ነበር። በተለይ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማመቻቸት የጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎችን በተደጋጋሚ በተናጠል አነጋግረዋል። ኦባሳንጆ ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ በኹለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በኩል ተጨባጭ ለውጥ አለመታየቱን ተከትሎ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ሳይገኝለት ኹለት ዓመት ሊሞላው ሦስት ወራት ቀርተዉታል።

በፌዴራል መንግሥት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ሳይስፋፋ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ አካላት እንደነበሩ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ፣ ጦርነቱ ወደ ኹለቱ ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ትግራይን ጨምሮ በሦስቱ ክልሎች ያደረሰው ሰብዓዊ እንዲሁም ቁሳዊ ኪሳራ ክልሎቹንም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ አገር ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ከገጠማት ጦርነትና ኪሳራ እንድትወጣ የተለያዩ አካላት ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን በግልጽ ይፋ ካደረገ በኋላ ተደራዳሪ ኮሚቴ አዋቁሮ ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ያሳየውን ፍላጎት ተከትሎ ሕወሓትም ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል። ይሁን እንጂ፣ ኹለቱም ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ከመግለጽ ያለፈ ተጨባጭ አቀራራቢ እርምጃዎች ሲወስዱ አይታዩም። ኹለቱ ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች የድርድር ጥረቱን ለማገዝ የፌዴራልና የሕወሓትን ባለሥልጣናት በተናጠል አወያይተዋል።

ልዩ መልዕክተኞቹ የሕወሓትና ፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን በተናጠል ካወያዩ በኋላ ስለ ድርድሩ ያላቸውን፣ ግንዛቤ በመግለጫና ለሚዲያ በሰጡት ቃል ግልጽ አድርገዋል።

የልዩ መልዕክተኞች የድርድር ጥረት

ኢትዮጵያ በየአካባቢው የተፈጠሩ የታጠቁና የዜጎቿን ሰላም ነስተው ከሚፈትኗት ኋይሎች ጎን ለጎን፣ በሰሜኑ ክፍል ኹለተኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር ሦስት ወራት የቀሩት ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም። የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት እንዲያበቃ ከአፍሪካ ኅብረት እስከ መንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ጥሪዎች ሲደረጉ ነበር። የጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከተለያዩ አካላት ሲቀርብላቸው የነበረውን የድርድር በቅርቡ መቀበላቸውን በየፊናቸው አሳውቀዋል።

ኹለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ድርድር ለማምጣት አፍሪካ ኅብረት ጥረት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት በኅብረቱ ባይገለጽም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ይፋ ካደረገ በኋላ አውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች ስለ ድርድሩ ከኹለቱም ኃይሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመርን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የተለያዩ አገራት ተወካይ አምባሳደሮች ስለ ድርድሩ ከሕወሓት ጋር ለመምከር ወደ መቀሌ ተጉዘው ነበር።

ልዩ መልዕክተኞቹ ከመቀሌ ጉዟቸው አስቀድመው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ኢትዮጵያ ሰላም ስለምታገኝበት ሁኔታና ስለ ድርድሩ መክረዋል። የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአሜሪካን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር  ከተወያዩት መካከል ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት እያደረገ መሆኑንና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አማካይነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ለልዩ መልዕክተኛው አረጋግጠዋል።

መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ለመልዕክተኛው የገለጹት ደመቀ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ተጀራሽነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉም ለልዩ መልዕክተኛው አረጋግጠዋል።

መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ሙሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ወቅት የሕወሓት ቡድን በተቃራኒው እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለልዩ መልዕክተኛው አስረድተዋል። የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በበኩላቸው፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች እና የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ አበረታች መሆኑን በውይይታቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ከሌሎች መልዕክተኞች ጋር ሕወሓትን ለማነጋጋር ወደ መቀሌ ተጉዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክት ይዘው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። የመልዕክተኞቹ የመቀሌ ጉዞ ድርድር በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ለመምከርና በኹለቱም ወገን ያለውን ሐሳብ ለማድመጥና ለማወያየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ወደ መቀሌ የተጓዙት የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የተመድ ባለሥልጣናት የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ስለ ድርድሩ የሕወሓትን ሐሳብ አድምጠዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእከተኛ ማይክ ሐመር፣ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልእክተኛ አኔት ዌይበር፣ የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት ተወካይ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ፣ የካናዳ እና ጣልያን አምባሳደሮች እንዲሁም ተወካዮች፣ ከፍተኛ ኃላፊዎች ወደ ትግራይ በመጓዝ ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ከመከሩ በኋላ የአሜሪካና እና የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች ባወጡት መግለጫ፣ ሕወሓት በአፍሪካዊያን የሚመራ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረገግጦልናል ብለዋል።

የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፖለቲካ ድርድር እንደሚያስፈልግ ልዩ መልዕክተኞቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ የገለጹ ሲሆን፣ ኹለቱም ወገኖች ለመነጋገርና በአፍሪካዊያን ለሚመራ ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።

ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ የአሜሪካ፣ ተመድ፣ የአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላማዊ ድርድር እንዲቋጭ ጥረት እያደረጉ ነው። የፌዴራል መንግሥት እና ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ሕወሓት ሌላ ተጨማሪ እልቂት ሳይኖር ያሉ ችግሮች በሰላማዊ ድርድር እንዲፈቱ አቋም መያዛቸው ለሰላም ድርድር የተደራዳሪ አካላትን መሰየማቸው አይዘነጋም።

የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የተመድ ተወካዮች፣ የአገራት አምባሳደሮች ከትግራይ ክልል ለፌዴራል መንግሥት ደብዳቤ ይዘው ተመልሰዋል። ልዩ መልዕክተኞቹ በጋራ መግለጫቸው እንደገለጹት፣ ሕወሓት ለኢትዮጵያ መንግሥት የላከው ድብዳቤ በትግራይ ክልል የተቋረጠው መሠረታዊ አገልግሎቶችን ስልክ፣ ባንክ፣ መብራት እና የመሳሰሉትን ለመመለስ እና አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግ ወደ ክልሉ ገብተው ለሚሠሩ አካላት የደኅንነት ማረጋገጫ የሚሰጥ መሆኑን ነው።

ልዩ መልዕክተኞቹ በመግለጫቸው ሕወሓት መሠረታዊ አገልግሎት ለማስጀመር የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ለሚልካቸው ባለሙያዎች ደኅንነት ማረጋገጫ ከሰጠ፣ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ ለማስጀመር ምንም ዓይነት መሰናክል ሊኖር አይገባም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም መልዕክተኞቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የባንክ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ወደነበረበት መመለስ ለትግራይ ሕዝብ አስፈላጊ መሆኑን ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የሕወሓቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ወደ መቀሌ ከተጓዘው ልዑክ ጋር ሕወሓት ሰለነበረው ውይይት በሰጡት መግለጫ፣ ሕወሓት አምስት መሠረታዊ ነጥቦችን ማንሳቱን ጠቁመዋል። እነዚህም የሰብአዊ ድጋፍ ያለምንም መደናቀፍ የሚገባበት ስርዓት በመፍጠር መፍታት፣ የመሠረታዊ አገልግሎት በትግራይ ማስጀመር ግዴታ መሆኑን፣ ሕወሓት በምዕራብ ትግራይ ወይም ወልቃይት ጉዳይ ያለውን አቋም፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ኢትዮጵያ አንዲወጣና በትግራይ ክልል የተፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዓለም ዐቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣሩ የሚሉት ሐሳቦች ናቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌዴራል ወደ መቀሌ የተጓዙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ ወደ መቀሌ ከመጓዛቸው አስቀድሞና ከመቀሌ መልስ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተወያይተዋል።  ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይና የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ስለሚደረጉ ጥረቶች ካነጋገሯቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ የኦሮሚያ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ)፣ እናት ፓርቲ፣ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይገኙበታል።

- ይከተሉን -Social Media

ልዩ መልዕክተኛው ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ ከሲቪል ማኅበራት ጋር የመከሩ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎችና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ጋር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታና በሰብዓዊ መብት ተጠያቂነት ላይ መምከራቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ጃኮብሰን እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ኢትዮጵያ ከሚገኙት የዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን ኮሚሽን ባለሙያዎች ጋር መክረዋል። ምክክሩ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ባለሙያዎቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያደረጉትን ውይይት የተመለከተ ነበር።

አለመተማመን የፈጠረው ስጋት

የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕወሓትን ወደ ድርድር ለማምጣት ቀደም ካለው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ጥረት በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች የጀመሩት ጥረት ላይ ኹለቱ ኃይሎች ላይ የመተማመን ችግር መታዘባቸውና አለመተማመን ተቀራርቦ ለመነጋጋር ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም እየገለጹ ነው።

ሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን በየፊናቸው ቢገልጹም፣ እርስ በእርሳቸው የመተማመንና እርስ በእርስ ከመፈራረጅና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ከመወራወር የዘለለ አካሄድ እያሳዩ አለመሆናቸው በድርድር ጥረቱ ላይ ጥላ እንደሚያጠላ ለማደራደር ጥረት ከሚደርጉ አካላት እየተሰማ ነው።

በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል የሰፈነው አለመተማመን ለሰላም ድርድሩ ዋናው እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን፣ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ቬበር ከዶቼ-ቨለ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።

‹‹እኛ እንደተገነዘብነው መንግሥት እስካሁን ለድርድሩ ያስቀመጠው ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የለም። ሆኖም ከመቀሌው ጉብኝታችን እንደተረዳሁት ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በኩል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ የቀረበ ቅድመ ሁኔታ አለ።››  ሲሉ ልዩ መልዕክተኛዋ በቃለ መጠይቃቸው ገልጸዋል።

ልዩ መልዕክተኛዋ አክለውም፣ ከአዲስ አበባ መቀሌ ሲመላለሱ የከረሙት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛው ኦባሳንጆ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ያለውን አለመተማመን ለማስቀረትና ተፋላሚ ኃይሎቹ ተቀራርበው እንዲነጋገሩ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ልዩ መልዕክተኛዋ፣ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ተቀራርቦ ለመነጋገርና ድርድር ለመጀመር መተማመን አለመፈጠሩን አንስተዋል። ሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት እርስ በእርሳቸው የሚወራወሩት የጥላቻና የፕሮፖጋንዳ ሽኩቻ ካልተገታ ለድርድሩ እንቅፋት እንደሚሆን የጠቆሙት ልዩ መልዕክተኛዋ፣ ኹለቱ ኃይሎች ከጥላቻና ከፕሮፓጋንዳ ሽኩቻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት አንዱ በአንዱ ላይ የሚወራወሩት የጥላቻ ንግግር ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ እስካሁን የዘለቀ ሲሆን፣ አሁንም ለድርድር ዝግጁ ነን በሚሉበት ጊዜ እንኳን የጥላቻ ንግግርና ለፕሮፖጋንዳ መወራረፋቸውን አላቆሙም። ከጥላቻ ንግግርና ከፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ ኹለቱም ኃይሎች ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን በየጊዜው የሚገልጹ ሲሆን፣ የጦር ኃይላቸውን ዝግጁነትም እያሳዩ ነው።

አለመተማመኑ ከኹለቱ ባለጉዳይ ኃይሎች በተጨማሪ፣ በኹለቱም ኃይሎች በኩል ለማደራደር ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ እምነት የማጣት ሁኔታ እየታየ ነው። ሕወሓት ቀደም ብለው የድርድር ጥረት በጀመሩት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ አለኝ ሲል፣ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ በልዩ መልዕክተኞች ላይ እምነት እንደሌለው የሚያመላክተውን መረጃ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለተደራዳሪነት የወከላቸው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ልዩ መልዕክተኞቹ ወደ ትግራይ አቅንተው ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ከተመለሱ በኋላ፣ በቲዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ መቀሌ ደርሰው የተመለሱ ልዩ መልዕክተኞች ሁኔታ መንግሥታቸው እንዳላስደሰተው ገለጸዋል።

በአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር የተመራው የመልዕክተኞች እና የአምባሳደሮች ልዑክ የትግራይ ቆይታ፣ ከሰላም ንግግር ይልቅ በሕወሓት በተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ የወቀሱት አምባሳደሩ፣ ተጨባጭ የሰላም ንግግር እንዲጀመር ከማድረግ አንጻር ተጨባጭ ነገር አላመጡም ሲሉ ልዩ መልዕክተኞቹን ገና በመጀመሪያ ጉዟቸው ተችተዋል። የመልእክተኞቹ እና የአምባሳደሮቹ ቡድን በሕወሓት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ላይ አተኩሯል ያሉት አምባሳደሩ፣ የጎደለው ነገር የጎደሉ ሁኔታዎቹን በማመቻቸት ሰላምን በንግግር መጀመር እንደሚያስፈልግ በጽሑፋቸው ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ብቸኛው የንግግር መንገድ እንደሆነ አምባሳደሩ በመልዕክታቸው አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ፣ በሕወሓት በኩል ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ይልቅ ወደ ኬኒያው ፕሬዝዳንት ኦሁሩ ኬኒያታ የሚያመዝን መሆኑን ከሕወሓት በኩል ተሰምቷል። በዚህም ኹለቱ ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ከመግለጽ ያለፈ ተጨባጭ ጅማሮ እያሳዩ አይደለም የሚሉ ሐሳቦች በተለያዩ አካላት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ልዩ መልዕክተኛዋ ከዶቼ-ቨለ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ በኹለቱም ኃይሎች ይንጸባረቁ የነበሩ የጥላቻና በብሔሮች መካከል ውጥረትን የሚያሰፍኑ ንግግሮችና መግለጫዎችን እንዲያረግቡና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መርህና ጥላ ስር ለሚካሄደው ቀጣይ ድርድር ፍሬያማ ውጤት ሊያመጡ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ውይይት ለማካሄድ እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።

ልዩ መልዕክተኞቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አለመተማመንና ቅደመ ሁኔታዎች የማስቀመጥ ሁኔታዎችን መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ድርድር ለማድረግ የተያዘውን እቅድ አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ ኹለቱም ኃይሎች ከማናቸውም የኃይል ድርጊት እና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የሚንጸባረቅባቸው አፍራሽ እርምጃዎች እና ከጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል ብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች