ራስን ማጥፋት

0
2338

ያፈቀረችው ወጣት የፍቅር ጥያቄዋን ስላልተቀበላት ራሷን ለማጥፋት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት እንደቀረ ትናገራለች። ከሞት አፋፍ ደርሳ የተመለሰችው ወጣቷ ትላንትን አልፋ ዛሬ ታሪኳን ለማውራት የበቃችው ራሷን ልታጠፋ በነበረችበት ወቅት እናቷ ደርሰው ስላተረፏት ነው። ከሙከራዋ በኋላ አንገቷ ላይ ያለው ቁስል ለተከታታይ አራት ቀናት አብጦ ሊጎድል አልቻለም ነበር።

ዮርዳኖስ ጥላሁን (ሥሟ የተቀየረ) የ15 ዓመት ታዳጊ ናት። ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ ራሷን ለማጥፋት የወሰነቸው በወቅቱ ኹሉም ነገር መውጫ የሌለው ጨለማ ሆኖ ታይቷት ስለነበር እንደሆነ በማስታወስ ገጠመኟን በዝርዝር ገልጻለች።

ዮርዳኖስ ለጓደኛዋ የፍቅር ጥያቄ አቅርባለት፣ ‹‹አይሆንም ገና ሕፃን ልጅ ነሽ›› በሚል ለጥያቄዋ ምላሽ ሲሰጣት በውስጧ የነበረው የፍቅር ብርሃን በቅጽበት ሲጨልም ይታወሳታል። የፍቅር ጥያቄ ያቀረበችለት ወጣት ምላሹን የሰጣት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ነበር። ይሁን እንጂ ያልጠበቀችው መልስ ሲገጥማት ቀኑም ጨለማ መስሎ ታይቷት እንደነበር በመገረም ትናገራለች።

‹‹የጨለመው ግን አስተሳሰቤ እንጂ ቀኑ አልነበረም።›› የምትለው ባለታሪኳ፣ በወቅቱ ከጭንቀት ሊገላግላት የሚችል መፍትሄ የመሰለ አንድ ‹ጨለምተኛ ሐሳብ› ወደ አእምሮዋ ዘለቀ።

‹‹ያለ እርሱ መኖር አልችልም! በቃ ለምን ራሴን አላጠፋም? አጀብ! እረፍት እኮ ነው። ኧረ ግልግል ነው ሆ!…› በወቅቱ መፍትሄ የመሰላት በኋላ ላይ ሆና ስታስበው ግን ከንቱ አስተሳሰብ ስትል ያንቋሸሸችው ውሳኔዋ መሆኑ ነው።

ይህን ሐሳቧን እያወጣች እያወረደች፤ እቅዷን የምታስፈጽምበትን ቦታና ሰዓት እያመቻቸች ወደ ቤቷ ገሰገሰች። በመረጠችውና ቀድማ ባሰበችው ቦታ ራሷን ለመስቀል ብዙ ጊዜ አልፈጀችም። ከዚያ በኋላም የምታስታውሰው ነገር ባይኖራትም፣ እንዴት እንደተረፈች ግን እናቷና በቦታው የነበሩ የሰፈር ሰዎች ያወሳሉ።

መልካሙ ዜና ግን ነፍሷ ትተርፍ ዘንድ የሚፈጥን አካል አለመጥፋቱ ነው። እናቷ የቀበሌ እድር ስለነበረባቸው ከሥራ ቦታ ፈቃድ ጠይቀው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነበር። ቤት ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ነገር አስደንጋጭ ነው። ቤቱ ከወደ ውስጥ ተሸግጧል። የልጃቸውን ሥም በተደጋጋሚ ጠሩ፣ አቤት የሚል ግን አልተገኘም። ኡኡታቸውን አቀለጡት። ወዲያውኑ የሰፈር ሰው ተሰባስቦ በሩ ተሰብሮ ሲገባ ልጃቸው ራሷን ሰቅላ ነበር የተገኘቸው።

ይሁን እንጂ ራሷን የሰቀለችበትና እናቷ የደረሱበት ሰዓት ተቀራራቢ ስለነበር በተደረገላት እርዳታ ከሞት አፋፍ ደርሳ እንደተመለሰች አውስታ፣ እናቷን እና ሌሎች ሰዎችን በተደጋጋሚ ታመሰግናለች። አፍቃሪዋም ጉዳዩ ሲነገረው ወደ ቤት ጎራ ብሎ እርዳታ ያደረጉላትን ሰዎች በእጅጉ አመስግኗል። ባለታሪኳ ራስን ለማጥፋት ማሰብ የሞኝነት ጥግ መሆኑን አሁን እንደተረዳች የተናገረች ሲሆን፤ ሐሳቧን ጠቅለል አድርጋ የሚከተለውን መቋጫ ምክር መሰል ሐሳብ ሰጥታለች።

‹‹የሰው ልጅ የሚያደርገውንና የሚለምነውን በቅጡ አያውቅም። ለምሳሌ ችግር ሲገጥመው ኧረ አሁንስ በሞትኩ…አምላኬ የሞቴን ቀን አቅርበው ብሎ ይለምናል። ይህ ችኩል አስተሳሰቡ ፍጻሜው ሲርቀው ደግሞ መኖር እየቻለ አልችልም ብሎ ለራሱ በመንገር መቃብሩን ያፋጥናል። ሁኔታዎችን መሸከም ሲያቅተን ሞት እረፍት ቢመስለንም፤ ሞት ግን ለምነነው የማይመጣ፤ መምጣት ከጀመረ ደግሞ ተመለስ ብለነው የማይመለስ የራሱ የሆነ የተሰናዳ የጊዜ ሰሌዳ ስላለው የምናደርገውን እንወቅ››

መረጃዎች ምን ይላሉ?

ራስን ማጥፋት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንደ ትልቅ የሞት መንስኤ የሚታይ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም በሚገኙ ወጣቶች ዘንድም ሦስተኛው ትልቁ የሞት መንስኤ ራስን ማጥፋት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሰዎች በተለያዩ ውጣውረድ የተሞላባቸው የሕይወት ገጠመኞች በሚፈተኑበት እና መቋቋም አንችልም ብለው በሚያስቡበት ወቅት ስሜታቸው ይረበሻል። በዚህም ድብርት ውስጥ ሲገቡ፣ ተደራራቢ ሱሶች እና የአእምሮ መታወክ ተከትለው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ናቸው። እነዚህም ተደምረው ራሳቸውን ለማጥፋት የሚገፋፉበት ሁኔታ እንዳለ ሲነገር ይደመጣል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ700 ሺሕ በላይ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከሦስት አራተኛው በላይ የሚሆኑት ደግሞ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚገኙ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በድረ ገፁ ላይ አስፍሯል።

በምሥራቅ አፍሪካ አገራትም ራስን የማጥፋት አሃዝ በዓመት ከ100 ሺሕ ሰዎች ውስጥ ከ5 እስከ 15 ሰው ገደማ እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዋቢ አድርጎ ማኅበሩ ባወጣው ጽሑፍ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው ዓመታዊ ራስን የማጥፋት መጠን መካከለኛ እንደሆነ የሚጠቅሰው ማኅበሩ፣ ባወጣው ጽሑፍ በዓለም ዙሪያ በዓመት ከ100 ሺሕ ሰዎች ውስጥ በአማካኝ 9 ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ይጠቅሳል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር 30 እንደሚጠጋ ያስረዳል ይላል፤ መረጃው።

እዚህ ጋር በጉዳዩ ላይ በቂ በሚባል ደረጃ ጥናቶችና ምርምሮች አለመደረጋቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለው እውቀት ዝቅተኛ መሆኑና እንደ ችግር የሚወራ ባለመሆኑ የበርካቶች ሞት መንስኤ ሳይወራ ወይም ተደብቆ ያልፋልም ተብሏል።

አንድ የቤተሰብ አባል ራሱን ሲያጠፋ፣ ማኅበረሰቡና ቤተሰቡ ሰዎች ምን ይሉኛል በሚል ፍራቻ የሞቱን መንስኤ ይደብቃል አልያም ሌላ ምክንያት ለመስጠት ይሞክራል ነው የተባለው። ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። ስለጉዳዩ በግልጽ አለመወራቱ አንድ ሰው ራሱን ሲያጠፋ ሰዎች ለምን ብለው እንዳይጠይቁና ከሌሎች ተሞክሮዎች እንዳይማሩ ያደርጋቸዋል።

መረጃው በመላው ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝ ያሳያል። ባለፉት 30 ዓመታት ብቻ እንኳ በዓለማችን ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ራሳቸውን እንዳጠፉ ጥናቱ ያስረዳል።

‹ኢንጁሪ ፕሪቬንሽን› በተባለው የጥናት መጽሔት ላይ የወጣ ጥናት ላይ ተንተርሶ እንዳስረዳው፣ በመላው ዓለም በየዓመቱ በአማካይ 800 ሺሕ ያህል ሰዎች ራሳቸውን እያጠፉ ሲሆን፣ ለጉዳዩ የተሰጠውም ትኩረት በእጅጉ አናሳ ነው ይላል።

እ.ኤ.አ በ2019 በመላው ዓለም ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥር 759 ሺሕ እንደሚጠጋ እና ግማሽ ያህሉ ደግሞ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውን ገልጿል።

በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ያሳየው ከ70 ዓመት በላይ በሚገኘው የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆኑንም አስፍሯል።

ጃፓንን ስንመለከት ደግሞ ከየትኛውም ዓለም በፈጠነና በተገቢው መልኩ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን መረጃ በአግባቡ ትመዘግባለች። ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች መረጃ በየወሩ እየተጠናቀረ እንደሚቀመጥም መረጃዎች ያስረዳሉ።

በተለይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ ይህ መረጃ በጣም አስፈሪ ታሪኮችን ይፋ አድርጓል። 2020 ላይ ከ11 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ማለቱም ተጠቅሷል።

በሚያስገርም ሁኔታ ደግሞ የወንድ ሟቾች ቁጥር በትንሹም ቢሆን የቀነሰ ሲሆን፣ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሴቶች ቁጥር ደግሞ 15 በመቶ ጨምሯል ነው የተባለው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በተጠቀሰው መረጃ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከዛ በፊት ከነበረው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሴቶች ቁጥር 70 ከመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቶ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያም አሁን ላይ ሕይወታቸውን እያጠፉ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሁ በጦርነቱ ምክንያት በተከሰተው ርሃብና ቸግር ከመሰቃየት ሞትን በመምረጥ ቀድመው ራሳቸውን እያጠፉ መሆኑን በሥፍራው ተዘዋውረው የተመለሱ ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። በቅርቡም የአራት ልጆቻቸውን ረሃብ አላይም ብለው በአደባባይ ራሳቸውን ሰቅለው የተገኙ አባት ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ተስተውሏል።

ኹለት ዓመት ሊሞላው ወራት በቀሩት ጦርነት ሳቢያ ርሃብ በአጎራባች ክልሎችም ጭምር መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት እንደተገደዱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ከተሞች ደርሰው የመጡ ሰዎች ተናግረዋል።

መረጃ ሰጪዎቹ እንደሚሉት፤ በተለይ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ሳቢያ ነዋሪዎቹ በርሃብ እየተሰቃዩ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ግለሰቦች ራሳቸውን እያጠፉ ነው ተብሏል። ነዋሪዎቹ ራሳቸውን እያጠፉ ነው የተባለው ጎዳና ወጥተው ቢለምኑም ማግኘት እንደማይችሉ በመረዳታቸውና ከመለመን ሞትን በመምረጣቸው ነውም ተብሏል።

ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት አነስተኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ልጆቻቸው ርሃብ ሲያሰቃያቸው መመልከት የከበዳቸው ከዚህ በፊት ባለጸጋ የነበሩ ሰዎችም ጭምር ናቸው ነው የተባለው።

ትላልቅ ቤት ያላቸው ግን ልጆቻቸውን መመገብ ያልቻሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዳጠፋ መረዳታቸውን በቦታው ደርሰው የመጡት የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ክፍል ባለሙያ ዮናስ ባሕረጥበብ (ረ/ኘ) እንደሚሉት፣ በሁሉም እድሜ፣ ፆታ፣ ሀይማኖት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚገደዱበት ወቅት አለ።

ለዚህ ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚያጋልጣቸው ሁኔታዎች እንዳለ ያነሱት ባለሙያው፣ በተለይ በተለያየ ጊዜ ራስን ለማጥፋት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ሰዎች ካሉ ደግመው ራስን ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚኖር ያስረዳሉ።

እነዚህ ሰዎች ራስን ለማጥፋት ዳግመኛ ሙከራ እንዳያደርጉ ቤተሰብ የጤና ተቋማት በመውሰድ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ በአእምሮ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች፣ በድብርት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እና በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ።

ከዚህ አንፃር በእነዚህ በተለያዩ ምክንያቶች ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ወደ ማጥፋት ከመሄዳቸው በፊት የሕክምና፣ የምክር እና ሌሎች እርዳታዎችን እና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚመከር ባለሙያው ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ራስን ማጥፋት የቤተሰብ ሃረግን ተከትሎ የሚሄድበት ሁኔታ እንዳለም ባለሙያው ያሰምሩበታል። ለአብነት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ አባት ራሱን ያጠፋበት ሁኔታ ካለ ሌሎች በቤተሰቡ የሚገኙ ልጆችም ራስን ወደ ማጥፋት የሚያመሩበት ሂደት ስለሚኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪ ወጣቶች ለወሲብና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ለቃላት ጥቃት ሲጋለጡ ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲነጠቁ፣ የገንዘብ እጦት ሲገጥማቸው፣ ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ እና በተለያዩ ተደራራቢ ጫናዎች ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉበት ሁኔታ አለ ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች እንዳሉ በሚነገርበት ወቅት ሌሎች ሰዎችን በማይገፋፋ መንገድ የመገናኛ ብዙኀን ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ እና ችግሩን ለመግታት በሚረዳ መልኩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይላሉ።

መንግሥትም በተቻለው አቅም ሰዎች የአእምሮ ሕክምና የሚያገኙበትን የጤና ተቋማትን በመገንባት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንዲሁም ትምህርት በመስጠት ረገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባለሙያው ጠቁመዋል።

የጠቅላላ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጊዜው አስማማው እንደሚሉት፣ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉባቸው የተለያዩ ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል በዋነኝነት ደግሞ የድብርት ችግር በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት፣ የኑሮ ውድነት፣ በሥራ ማጣትና በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉበት እድል እንዳለ ጠቁመዋል።

በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉ ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ ግን በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ከላይ ከሰፈሩ ምክንያቶች ውስጥ ለአብነት ሥራ ማጣትን ጨምሮ በሌሎች ምክንያቶች ወጣቶች ድብርት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ጫት፣ ሲጋራና አልኮልን ወደመሳሰሉ ሱሶች ውስጥ የሚገቡበት እድል ሰፊ መሆኑን ባለሞያው ጠቅሰዋል። ችግሮች ተደራርበው ለአእምሮ ሕመም እና ለሌሎች ጭንቀቶች የሚዳረጉበት ሂደት አለም ብለዋል። በወቅቱ መፍትሄ ካላገኙ ሁኔታዎች ተደማምረው ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚገፋፉበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለሙያው ይህን ለመግታት እና ለመቀነስ መፍትሄ ያሉት፤ በተደጋጋሚ ራስን ስለማጥፋት ሲያነሱ የሚስተዋሉ፣ በድብርትና በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ያሉ እንዲሁም በአእምሮ ሕመም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላይ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰቡ እና መንግሥት የበኩላቸውን ኃላፊነት ተወጥተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።

በመጀመሪያ፣ ቤተሰብ ልጆቻቸው በተቻለ መጠን በሥነምግባር የታነፁ እና በሚያምኑባቸው ሐይማኖቶች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ አመለካከታቸው ጥሩ የሆነ እና አመዛዛኝ የሆኑ ትውልዶችን ለማፍራት መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በተጨማሪ በመንግሥት በኩል ግንዛቤ ለመፍጠር ከመሥራት ጎን ለጎን የሥነ አእምሮ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት፣ የሱስ ማገገሚያ ተቋማት እና ሌሎች የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል።

የሥነልቦና ባለሙያው ሻረው ዓለማየሁ እንደሚሉት ደግሞ፣ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉት የመኖር ትርጉም በሚያጡበት ወቅት ነው። ለዚህ ደግሞ ሰዎች የሕይወት መንገድን በሚሞክሩበት ወቅት መኖራቸው ከአቅም በላይ ሲሆንና ትርጉም አልባ ወይም ጣዕም አልባ በሚሆንባቸው ወቅት ራሳቸውን ለማጥፋት እንደሚገደዱ የሚሰማቸው ሂደት አለ ባይ ናቸው።

ከዚህ አንፃር ሰዎች ለሕይወት ያላቸው ትርጓሜ ሊስተካከል ይገባል ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በገጠራማው ክፍል ላይ ይጨምራል ይላሉ።

ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች አብዛኛዎቹ አንድን ነገር አሳካለሁ ብለው ማሳካት ሳይችሉ በሚቀሩበት ወቅት እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበራቸውን ገንዘብ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ እና በሌሎች ጉዳዮችም ጭምር መፍትሄ በሚያጡበት ወቅት የመኖር እና ያለመኖር እንዲሁም ተስፋ ቆርጠው ወደ አላስፈላጊ ውሳኔዎች ለመግባት እንደሚገደዱ ያስረዳሉ።

የሥነልቦና ባለሙያው አክለውም፣ በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በሕይወት ውስጥ ትዕግስት ማጣት ራስን ለማጥፋታቸው በምክንያነት ተጠቃሽ እንደሚሆን እና በተለያዩ የሕይወት ውጣውረድ ፈተናዎች በሚፈተኑበት ወቅት ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ ብለዋል።

አያይዘውም፣ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ከሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ቢሆንም፣ በብዛት ግን በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ኹለት ምክንያቶችን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፣ አንደኛ በቂ እውቀትና የሕይወት ልምድ ስለሌላቸው በጊዜው የሚገጥማቸውን ችግሮች ወይም ፈተናዎች እንዴት አድርገው መፍታት እንዳለባቸው ባለመገንዘባቸው ነው ይላሉ።

በኹለተኛነት በቂ በሆነ መጠን ማንነታቸው ተሠርቶ ባለማለቁ ሲሆን፣ ከልጅነት እድሜ ቢወጡም በተሻለ ደረጃ ስለተለያዩ ጉዳዮች አዋቂ ባለመሆናቸው የእድሜ መቃወስ እና ሌሎች የሕይወት መከራዎች ጋር ተደራርበው ራሳቸውን ለማጥፋት ይገደዳሉ ብለዋል።

በተጨማሪም፣ በሚገጥማቸው ውጣውረድ ውስጥ የሚያማክሩት ቤተሰብም ሆነ የቅርብ ጓደኞች ከሌሏቸው ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን ባለሙያው ጠቅሰዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ ከዚህ አኳያ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን ለመታደግ በቅድሚያ የልጆች አስተዳደግ መርህ ላይ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።

በኹለተኛ ደረጃ እንዲሁ ልጆች ጤናማ የሆኑ የሕይወት እድገት አቅጣጫዎችን በማሳወቅ እና የመዝናኛ ቦታዎች እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ በማኅበረሰቡም ሆነ በመንግሥት በኩል መሠራት እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል።

በሥነልቦና ዙሪያ የማማከር አገልግሎት በነፃ የሚሰጡ ተቋማት ቢበራከቱም ጠቃሚ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይስማሙበታል። በትምህርት ተቋማትም ሆነ በጤና ኬላዎችና በመንግሥታዊ ተቋማትም ለሰዎች ሥነልቦና ትኩረት በመስጠት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲወዱ መደረግ እንደሚኖርበትም ይነገራል። የሃይማኖት ተቋማትም ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳያጠፉ የመሥራት ቀዳሚ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ይታመናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here