መምህርነት

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ አባት ስለመሆኑ የሚከራከር የለም። ሁሉም ሙያዎች በመምህርነት ድልድይ የተሻገሩ ናቸው። ተማሪዎቻቸውን እንደ ልጆች የሚያዩ አስተማሪዎችም ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎችን በማፍራት በኩል ቀጥተኛ ሚና አላቸው። ብሎም ከአገር እድገትና ሥልጣኔ አንጻር ያለጥርጥር ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ትምህርት የሚያሳልጡ እንደመሆናቸው፤ ባለው አቅም ሁሉ ጥያቄቸው ምላሽ ሊያገኝና ጆሮ ሊሰጣቸው ይገባል።
ምንም እንኳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ለተማሪ ልጆቻቸው የሚጨነቁ አስተማሪዎች እልፍ ቢሆኑም፣ ቅሬታቸውም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በትምህርት ጥራት ላይ ሳይቀር አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር እሙን ነው። ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ባለሞያዎችን በማነጋገርና መዛግብትን በማጣቀስ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ለመግቢያ

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ ምንጭ ነው። ስለዚህም የሙያዎች አባት ብለው ይጠሩታል። በየትኛውም ዘርፍ የትኛውም ልኅቀት ላይ ቢደረስ፣ መምህርነት ያልነካው አይሆንምና፤ አንድም በዚህ የተነሳ የተለየ ክብር ይሰጠዋል።

በኢትዮጵያም በቀደመው ዘመን ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጣቸው ሙያዎች መካከል መምህርነት አንዱ ነበር። መምህር መሆንም፣ ከመምህር መዛመድም በማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ዋጋ እንደነበረውም አይዘነጋም። እንደውም የሰርግ ሙዚቃ ላይ ሳይቀር

‹‹የእኛ ሙሽራ ሹራብ ሠሪ

ወሰዳት አስተማሪ›› የሚል የስንኝ ቋጠሮ ይገኛል።

ማኅበረሰቡ ታድያ ለመምህርነት ያለውን ክብር በዚህ መንገድ ያንጻባርቃል። እንደዛው ሁሉ መምህርነትን ማክበር መምህራንና መምህራትን በማዳመጥ፣ የተሻለ ክፍያን በመክፈልና ቅድሚያ በመስጠት፣ በማበረታታት፣ ተማሪዎች እንደ እናት እና እንደ አባት ቁጣና ምክራቸውን እንዲሰሙ በማድረግ ሲገለጽም ይታይ ነበር።

በተጓዳኝ መምህራንና መምህራትም የሙያውን ክብር አውቀው የበለጠ የሚያስከብሩ ለመሆን የሚጥሩ እንደነበሩ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት የቆዩ ባለሞያዎች ይናገራሉ። መምህሮች የተማሪዎቻቸው ነገር አብዝቶ የሚጨንቃቸው፣ ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱም የሚጥሩና የሚደክሙ ናቸው። ከዛም አልፈው በአገር ጉዳይ ላይም በአንድነት ሆነው ድምጽ ያሰሙበት ጊዜ በርካታ ነው።

አሁንስ? አሁን በኢትዮጵያ ያለው አስቸጋሪና አስጨናቂ ፈተና የመምህራን ትከሻም ላይ ማረፉ አልቀረም። ትምህርት ቤቶች በጦርነትና ሰላም ማጣት ፈርሰዋል፤ ተረብሸዋል። ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ከራቁ ዓመት ዓመትን እየወለደ ጊዜው እየነጎደ ይገኛል።

የኑሮ ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑ መምህሮች የገቢያቸው ነገር እንዲያሳስባቸው አድርጓል። ብሎም በመንግሥት በኩል ስርዓተ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚደረስባቸው ውሳኔዎች በመምህርነት ሙያ ያሉ ሰዎችን እያስደሰተ አይደለም።

ይህም የትምህርት ጥራት ብሎም የተረካቢ ትውልድ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር እሙን ነው።

መምህርነትና ዙፋኑ

ሞገስ ፀጋው በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። ሙያውን በ2008 እንደተቀላቀሉ በማውሳት፣ ምን ያህል ሥራቸውን እንደሚወዱና እንደሚያከብሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል። ‹‹ወደ መምህርነት መግባት ከልጅነት ጀምሮ ሕልሜ ነበር።›› ይላሉ፤ መለስ ብለው ሲያስታውሱ።

‹‹ተማሪዎቻችን ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ማየት በእጅጉ ደስ ይላል። ጉዳት (ባለሙያው የሚገጥመው ችግር) ቢኖርም፣ ደስ እያለኝ የምሠራው ነው። ሌላ ሥራ ቢኖረኝ እንኳ መምህርነት የምተወው አይደለም።›› ሲሉም ስሜታቸውን አካፍለዋል።

ዮሐንስ በንቲ (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ለረጅም ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የመሩና እየመሩ ያሉ ሰው ናቸው። ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ የአንደበት አምድ ላይ ባደረጉት ቆይታ መምህርነት ከሁሉ አብልጠው የሚወዱት ሙያ መሆኑን ገልጸዋል። በንግግራቸውም ‹‹የመምህርነት ሙያ የሰዎችን አእምሮ ለመቅረጽ እድል የሚሰጥ፣ ከራስ በላይ ለሌሎች የማሰብን፣ ውስጣዊ ፍላጎትና መሰጠት ያለበት ሙያ ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ።

እንደውም እንዲህና እንዲያ አድርገህ አስተምር የሚል አዛዥ ናዛዥ የሌለበት፣ ለተማሪዎች ይሆናል ባሉት መንገድ እውቀትን የሚያቀብሉበት ዘርፍ ነው ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

እርግጥ ነው፤ የሰዎች የማንነት ግንባታ በሚጀምርበት የልጅነት እድሜ ላይ ነገሮችን እንዲያገናዝቡ፣ ችግር እንዲፈቱና መረጃዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ጥበብ የሚያስተምሩት መምህራንና መምህራት ናቸው።

የዓለም ባንክ የዓለም የመምህርነትን ጉዳይ በሚመለከት ባሳለፍነው ዓመት በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ማስተማር በአንድ ጉዳይ ላይ ጽንሰ ሐሳብን የማቀበል ጉዳይ ብቻ አይደለም ይላል። ይልቁንም በተማሪዎች ውስጥ ፈጠራ የታከለበት እሳቤ ማኖር፣ ተግባቦት እና ትብብርን ማለማመድ፣ ለትምህርት ፍቅር መፍጠር እና እንዴት ራሳቸውን መጠበቅና መቆጣጠር እንደሚችሉ ማሳወቅንም ይመለከታል ሲል ያትታል።

ታድያ ይህን የሚያህል የኃላፊነት ዙፋን ላይ ያለው የመምህርነት ሙያ ሊከበር እንደሚገባ ሳያሳስብ አልቀረም።  ቢቢሲ የተባለው የመገናኛ ብዙኀንም ብሔራዊ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዘርፍ ጥናት ተቋምን አጣቅሶ ባወጣው ዘገባ፣ በሁሉም አገራት ይህ ክብር ለመምህራን እንደማይሰጥ ይጠቅሳል። በእስያ አገራት ለመምህርነት የተሻለ ክብር እንደሚሰጥና ይህ መሆኑም በሂደት ውስጥ ምርጥ መምህራን እና የተሻሉ ዜጎች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

በቻይና፣ ሕንድ እና ከአፍሪካም በጋና በርካታ ቁጥር ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው አስተማሪ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፤ ያበረታታሉም። ለምን ቢባሉ፤ ‹‹ጭንቀት ያለባቸው፣ ደስተኛ ያልሆኑ እና ድጋፍ ያላገኙ አስተማሪዎች፤ ተማሪዎቻቸውን ቸል የማለትና በንቀት የመመልከታቸው ነገር ያዘነብላል። እናም ለመምህርነት ብሎም ለባለሞያዎቹ የሚሰጠው ክብር ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባም።›› ይላሉ።

ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። የትኛውም መዘመንና ለውጥ የመምህርነትን ሙያ የሚተካ እንዳይደለም ጠቅሰዋል። ‹‹ለመምህርነት ቦታ የማይሰጥና የማያከብር ሕዝብ የትም ሊደርስ አይችልም። ያደጉ አገራት ልዩነት የፈጠሩት በሳይንስና በምርምር ነው። ይህ ደግሞ በትምህርት የሚመጣ ነው። ስለዚህ ሙያው ወሳኝ ነው።›› ሲሉም አስረድተዋል።

ነገር ግን፣ ከጥቅምና ወቅታዊ ክፍያ ጋር እኩል ተደርጎ ታይቶ፣ በዚህ ምክንያት ወድቋል የሚባለው ትክክል አይደለም ባይ ናቸው። ‹‹ቁሳዊው ነገር ይምጣ ብሎ መታገል ይቻላል። የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለዚህ የሚሰስት ኢኮኖሚ መኖር የለበትም። እኛ የምንገፋውም እሱ እንዲመጣ ነው። ስለዚህ፣ በተቻለ መጠን ሙያው ሳቢና ጥሩ ተከፋይ እንዲሆን፣ የአገር ኢኮኖሚ ጉዳይ ሆኖ በሚገባ መክፈል ባይቻል እንኳ ሌሎች በርካታ የማበረታቻ ስልቶች አሉ። እና እነዚያ በጥናት ተለይተው እየተተገበሩ ሙያው ተመራጭና ተፈላጊ እንዲሆን ማድረግ የእኛ ሙያ ማኅበር፣ የመንግሥትና የማኅበረሰቡም አጠቃላይ ኃላፊነት ነው።›› ሲሉም ተናግረዋል።

ከዛ ባለፈ ግን መምህርነትን ዝቅ ማድረግ ሲጀመር፣ ያኔ የውድቀትን መንገድ መርጠናል፣ ወደ መጥፋት እየሄድን ነው ማለት ነው ሲሉ አሳስበዋል። ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ይሁን ማኅበራዊ ወይ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄው ትምህርት ስለሆነ ነው ብለዋል።

ታድያ ደመወዝ፣ ማበረታቻና የመዋቅር ጉዳይ ብቻ አይደለም። የመምህርነትን ክብር በተለያየ መንገድ ይገልጽ የነበረው ማኅበረሰብም ከዛ እንዳጎደለ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። ሞገስ ደግሞ በበኩላቸው እርሳቸው መምህር ከሆኑበት ከቅርብ ዓመት አንጻር እንኳ ለመምህርነት የሚሰጠው ክብር እንደቀነሰና ይህም በማኅበረሰብ ውስጥ በጉልህ የሚስተዋል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

- ይከተሉን -Social Media

‹‹በፊት ሙያው በጣም ክብር ነበረው። ማኅበረሰቡም የምንለውን ይሰማ ነበር። አሁን ግን ከነበረው አንጻር ተቃራኒ ሆኗል።›› ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። እርሳቸውም በትምህርት ስርዓትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ አሳላፊ ባለሥልጣናት ተገቢውን እየሠሩ አለመሆኑ አንዱ ችግር ነው ብለዋል። ከዛም ባለፈ ግን ማኅበረሰቡ ለትምህርት ያለው ዕይታ መቀየሩ አንዱ ምክንያት ነው ባይ ናቸው። እንዴት?

ትምህርት?

በተወሰነ መልኩ የትምህርትን ነገር እናንሳ። ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1874 እስከ 1983›› በሚለው መጽሐፋቸው፤ የዘመናዊ ትምህርት ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት እንደሆነ ጠቅሰዋል። በአንድ ጎን ሚስዮናውያን ሲጠቀሱ በተጓዳኝ አጼ ቴዎድሮስ በአውሮፓ ቴክኖሎጂ በተለይም በዚህ ቴክኖሎጂ ወታደራዊ ጥቅም ተማርከው ወጣት ኢትዮጵያውያን በእጅ ሙያ የሚሠለጥኑበትን ትምህርት ጋፋት ላይ ማቋቋማቸው ተነስቷል።

ይሁንና ዘመናዊ ትምህርት ለመስፋፋት የበለጠ አመቺ ሁኔታ የተፈጠረለት ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ነው። ከዚህ በኋላም መደበኛ ትምህርትን የተመለከተ ቀጣይ ወሳኝ የሚባል ድርጊት የነበረው በ1900 በንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ሥም ትምህርት ቤት መከፈቱ ነው። ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፤ በጊዜው ተፈልጎ የነበረው ባህላዊና ፈር ያልለቀቀ ሥልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ነበር።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥርዓተ ትምህርት ካሪኩለምና ኢንስትራክሽን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የሚያገለግሉት መሠረት አሰፋ (ዶክተር)፤ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲናገሩ፤ ‹‹ትምህርት ማለት ቀጣይነት ባለው የሕይወት ዘመን የሚቀሰም እውቀት ነው። ደግሞም እውቀት፣ ክህሎትና እሴትን ያካትታል። ሦስቱ ነገሮች በማንኛውም የትምህርት ሂደት ውስጥ መካተት አለባቸው።›› ሲሉ አብራርተዋል።

ምንም እንኳ ብዙ ሰው መማርን አብዝቶ የሚሻ ቢሆንም እሴትና ክህሎትን ሳይሆን ማወቅ ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ይህም ትምህርትን ከምሉዕነቱ የሚያጎድል ከመሆኑ ባሻገር ዲግሪ መጫን ወይም ዲፕሎማ ማግኘት የመማር አቻ ትርጓሜ ሆኖ እንዲቆጠር አድርጓል።

መሠረት እንደሚሉት፤ የትምህርት ዓላማ ዜጎችን በእውቀት ማበልጸግ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ማነጽ፣ በክህሎት ማዳበር እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ማንነት ጋር ማስተሳሰርን ይጨምራል። ይህ ሲሆን የትምህርት ምንነትና ጠቀሜታን መረዳት ይቻላል።

በተያያዘ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ እጓለ ገብረ ዮሐንስ በ1956 ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ ‹‹ስለትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከሆነ ማናቸውም የሕይወት ችግር ሊፈታ ይችላል። ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው።›› ሲሉ ይገልጻሉ። እነዚህን ነጥቦች ያልተረዳ ማኅበረሰብ ሆነ ስርዓተ ትምህርት፤ በትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ መቸገሩ አይቀርም።

- ይከተሉን -Social Media

የመምህሮች ነባራዊ ቅሬታዎች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመምህሮች ጉዳይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሲዘገብ ተሰምቷል። አዲስ ማለዳም በ193ኛ ዕትሟ፤ አስተማሪዎች በደመወዝ ጭማሬ አናሳ መሆንና ሌሎች መፍትሄ ባላገኙ ተደራራቢ ችግሮች መበራከት የተነሳ ሥራ እስከማቆም የሚደርስ አድማ ለማድረግ በምክክር ላይ መሆናቸውን ዘግባለች።

የዩኒቨርሲቲ መምህራንና መምህራት ሐምሌ 27 ቀን 2014 ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥት ቋሚ ተጠሪ እንዲሁም ለማኅበራዊና ሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ፣ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ለመምህራን ማኅበር ይድረስልን ብለው ደብዳቤ አስገብተዋል።

በዚህ ‹የአስተዳደር በደልን› በሚመለከተው ደብዳቤ፣ መምህራንና መምህራቱ ተልዕኮአቸውን በአግባቡ ለመፈጸም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ውስጥ ያስገቧቸውንና ከደሞዝና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር የደረሱባቸውን አስተዳደራዊ በደሎች እንዲቀረፉላቸው አቤት ማለታቸውን አውስተዋል። ይህንንም ተከትሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገንቢ የሆነ ውይይት ተደርጎ በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተነግሯቸው እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በአጭር ጊዜ መልስ ያገኛሉ ከተባሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የደረጃ ማስተካከያ ሲሆን፣ ይህንንም የሚያግዝ ጥናት መደረጉን በደብዳቤው አስፍረዋል። ነገር ግን በኋላ ላይ ‹‹የጥናቱ አካል ያልነበረና በመምህራን የኑሮ ሁኔታ እና የሥራ ተነሳሽነት ላይ ምንም ዓይነት መሠረታዊ ለውጥ የማያመጣ ውሳኔ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል መሰጠቱን› ገልጸዋል።

ይህንንም መሠረት አድርገው የሥራ ደረጃ ማሻሻያ፣ የመምህሮች የቤት አበል፣ ፍትሐዊ ደመወዝ ልዩነት፣ የረዳት ፕሮፌሰር የአካዳሚክ ማዕረግ ተፈላጊ ችሎታ፣ የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳቶች ዝቅተኛ ተፈላጊ የትምህርት ደረጃ እና የመሳሰለው ላይ ቅሬታና ጥያቄ አቅርበዋል። የሚመለከተው አካልም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባሻገር የመምህሮች የዝውውር ጉዳይም በብዛት ቅሬታ ሲነሳበት የቆየ እንደሆነ ይታወሳል። ብሔርን መሠረት ያደረገ ዝውውር እየተደረገ ነው ብለውም አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ቅሬታ ካላቸው መምህራን መካከል ሥማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ አንድ መምህር በሰጡት አስተያየት፤ ይህ ጉዳይ በፍጥነት አለመስተካከሉና ይስተካከላል ተብሎ ሲጠበቅም የተሰጠው ምላሽ ተገቢነት የሌለው መሆኑ፣ ለሙያው የሚሰጠው ክብር መቀነሱን ያሳያል ብለዋል። ለሙያው በዚህ መጠን ቸልተኛ መሆንና ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት ደግሞ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረውና የሙያ ፍልሰት ተከስቶ አቅም ያለው ባለሞያ ከዘርፉ እንዲወጣ እንደሚያደርግ አሳስበዋል።

‹‹አስተማሪዎችም ሰላም ማጣቱ ብሎም የኑሮው ውድነት ይመለከታቸዋል። ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ብንረዳም፤ ጉዳዩ የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ ግን የሚወሰኑ ውሳኔዎች በግልጽ ያሳውቃሉ። ለምሳሌ፣ በዚህ ከባድ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የ750 ብር ደሞዝ ጭማሬ ማድረግ ለይስሙላ ከሆነ እንጂ አስተማሪዎችን ምን ያህል ያግዛል ተብሎ ነው? ደስተኛ ያልሆነ፣ ከተማሪዎቹ እውቀት ሸመታ ይልቅ ኑሮውና የብሔሩ ጉዳይ የሚያስጨንቀው አስተማሪስ ምን እንዲያስተምር ነው የሚጠበቀው?›› ሲሉም ስጋታቸውን አክለው አካፍለዋል።

መምህር ሞገስም ይህን ሐሳብ ይጋራሉ። ‹‹መምህርነት ተማሪን በስርዓት ከማሳደግ ይጀምራል። ደስተኛ ያልሆነ አስተማሪ ደግሞ ለተማሪ ልጆቹ ጥሩ ነገር አይሰጥም።›› ብለዋል። ይህም የትምህርት ጥራት ላይ ችግር ስለሚፈጥር፤ ትምህርት ትልቅ ዋጋ ያለው ነውና መንግሥት ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ቢሰጥ ሲሉም አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ ከመምህራን ማኅበር በጠየቀችበት ፍጥነት ምላሽ ያገኘች ባይሆንም፤ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ከተደረጉ ቃለመጠይቆች ልታወሳ ወዳለች።

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ ማኅበሩ በመምህርነት ዘርፍ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ምን ያህል አቅምና ኃይል አለው የሚል ጥያቄ አንስታ ነበር። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ፣ ጊዜ ይፍጅ እንጂ ማኅበሩ የያዘውን ዓላማ ሳያሳካ አይቀርም ብለዋል።

ማኀበሩ ጠንካራ መሆኑን አንስተውም፤ ተጽእኖ የመፍጠር አቅሙም ጠንካራ ነው ብለዋል። ‹‹አንዱ ጥንካሬው በዘላቂነት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እየታገለ ለትምህርት ስርዓቱም፣ አቅሙ የሚችለውን ለማኀበሩና ለመምህራን አባላት ጥቅም እየሠራ የመጣ ነው። እንደተቋም የራሱ ድክመት ቢኖርበትም ግን ጠንካራ ጎንም አለው።›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

ከዚህም ባለፈ የማኅበሩ የፌስቡክ ገጽ ላይ ሰፍሮ እንደምናገኘው፣ መምህራንን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ ከግል ባንኮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቋል። ይህም በዋናነት የብድር አገልግሎትን የሚመለከት ነው። ከዛም በተጓዳኝ የመምህራን ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝ፣ የደረጃ እድገትና መሰል ጥያቄዎችን በሚመለከትም ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ምክክር ማድረጉንም በገጹ አስነብቧል።

በአንጻሩ በተለይ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ ያቀረቡ አስተማሪዎች፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር እየደረሰብን ያለውን በደል በሚመለከት ቅሬታ ማንሳት ሲገባው ዝም ብሏል ብለዋል። እንደውም ወደ መንግሥት ነው የሚያደላው የሚል ትችት ሰንዝረዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ብቁ የሆኑ መምህራንን ማፍራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።›› ብለዋል። አክለውም ‹‹የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና ብቁ ዜጋን ለማፍራት በቅድሚያ ብዙ መምህሮችን ማፍራት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህንን ለማድረግም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ጠንካራ ሥራዎች ይሠራሉ።›› ማለታቸው ይታወሳል።

ለወደፊቱ

ያም ሆነ ይህ የትምህርት ጥራት የሚያሳስበው አገርና መንግሥት የመምህራንን ጥያቄና ጉዳይ በአግባቡ፣ በተቻለ አቅምና መጠን እንዲሁም ፍጥነት ሊያስተናግድ እንደሚገባ እሙን ነው። መምህሮቹ በተለያየ መንገድ ቅሬታቸውን እያቀረቡ የማስተማር ሥራቸውንም አብረው የሚቀጥሉ እንደመሆኑ፣ ተረካቢ አገር ወዳድ አስተማሪዎችንም እንዲያፈሩ ለማስቻል ለሙያውና ለባለሞያዎቹ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ወደኋላ የሚመለሱበት ወይም በይደር የሚያቆዩት ጉዳይ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከስድስት መቶ ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉት ይናገራል። የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በዓለም ላይ ከ85 ሚሊዮን በላይ መምህራን ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል 9.4 ሚሊዮን ቅድመ መደበኛ፣ 30.3 ሚሊየን መደበኛ፣ 18.1 ሚሊዮን አንደኛ ደረጃ፣ 14 ሚሊዮን ኹለተኛ ደረጃ እንዲሁም 12.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ ናቸው።

በ2030 ተጨማሪ 68.8 ሚሊዮን መምራን ለአንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚያስፈልጉም ተመላክቷል። ከእነዚህም 20 ሚሊዮን የሚሆኑት የትምህርት መስፋፋት የሚያግዙ ሲሆኑ፣ 49 ሚሊዮን አካባቢ ደግሞ ከዘርፉ በተለያየ ምክንያት የሚወጡትን የሚተኩ እንደሚሆኑ ይታመናል።

ከዚህ ቁጥር ባሻገር፤ አንድም ለመምህራን በሚሰጥ ክብርና ቦታ የሚወሰነው የመምህራን ጥራት ጉዳይ ወሳኝ እንደሆነ ነው የዓለም ባንክ በዘገባው የጠቀሰው። ነገር ግን፣ ከሰሀራ በታች ባሉ ስድስት የአፍሪካ አገራት የተሠራ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ተፈላጊው ችሎታ/ጥራት ያላቸውን መምህራንን አያገኙም።

‹‹ደካማ ማስተማር የምን ውጤት ነው ከተባለ፤ የመምህራን ጥፋት ብቻ አይምሰላችሁ›› ይላል የዓለም ባንክ። ይልቁንም በፖሊሲ ደረጃ የተዘረጉ ስርዓቶች በአግባቡና በስርዓት መምህራንን መመልመልና ማዘጋጀት፣ መደገፍ፣ ማስተዳደር እና ማበረታታት የሚችሉ ባለመሆኑ ነው።

የዓለም ባንክ በዚሁ ዘገባው ሲያብራራ፣ በርካታ አገራት የመምህራን ፖሊሲያቸውና አሠራራቸው ውጤታማ አይደለም ወይም ዘላቂነት ይጎድለዋል። መምህራንን በማዘጋጀት ሥራ መካከል አመራረጥ ላይ ወይም የመግቢያ መመዘኛ ላይ ከሌሎች ሙያዎች አንጻር ዝቅ የማድረግ ነገርም ይስተዋላል ሲል ይጠቅሳል። እናም አገራት ይህን ባገናዘበ መልኩ አሠራራቸውን ሊቃኙ እንደሚገባም አሳስቧል።

መምህር ሞገስም በሰጡት ምክረ ሐሳብ፣ ከነባራዊ ሁኔታ አንጻር በባለሞያዎች የተደረጉ ጥናቶች እንዲከበሩ ሲሉ ጠይቀዋል። እንዲሁም ስርዓተ ትምህርትም በባለሞያዎች እንዲጠኑና አስተያየት እንዲሰጥባቸው አሳስበዋል።

በዚህ እንቋጭ፤ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ› በተሰኘ መጽሐፋቸው አፄ ኃይለሥላሴ ቤተመንግሥቱን ለትምህርት ቤትነት መስጠታቸውን በጠቀሱበት ምዕራፍ እንዲህ አሉ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታሪካዊ እድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በትምህርት እየተመራ ወደፊት ይጓዛል። ከዚህ ዓላማው ከሚያደርሱት መሣሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው። ኹለተኛው ትምህርት ነው፤ ሦስተኛውም ትምህርት ነው።››


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች