“ከመብት አንጻር ለአንዱ ሰጥተህ ለአንዱ የምትነሳበት ሁኔታ መኖር የለበትም” አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) አንትሮፖሎጂስት

0
1769

በሙያቸው አንትሮፖሎጂስት ናቸው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪ የጀመረው የትምህርት ዝግጅታቸው፣ ከጃፓኑ ቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ቅርስ ሕይወት፣ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስና ፖለቲካል ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል አንትሮፖሎጅ እንዲሁም ከዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአንትሮፖሎጂ አጥንተዋል፤ የአንትሮፖሎጂ ምሁሩ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር)።

አወቀ በሙያቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከማስተማር በተጨማሪ ወደ ፖለቲካ ሕይወት ተቀላቅለዋል። የፖለቲካ ተሳትፏቸው በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ውስጥ ሲሆን፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተወዳደሩበት አካባቢ አሸናፊ ሆነው የአማሮ ኮሬ ማኅበረሰብን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። ምሁሩ በአማሮ አካባቢ ለዓመታት በዘለቀው የጸጥታ ችግርና በደቡብ ክልል የሚታየውን የአስተዳደር ጥያቄ በሚመለከት የተነሳላቸውን ጥያቄ በመመለስ ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በተለይ ከ2011 ወዲህ የተባባሰው የአማሮ አካባቢ የጸጥታ ችግር ለዓመታት እንዲዘልቅ ምክነያት የሆነው መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው?
መሠረታዊ ችግሩ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው። በእኛ ግምገማ ችግሩ መሬት ማስለቀቅና የመሬት መስፋፋት ዓላማ ነው። አሁን ደግሞ እየበረታ የመጣ ጉዳይ ሆነ እንጂ የቆየ ችግር ነው። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ክልል ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች አንድ ላይ በማጠቃለል የኦሮሚያን ሪፐብሊክ ወይም መንግሥት እመሠርታለው ከሚለው ጋር በቀጠታ የተያያዘ ነው።

ይሄ የጀመረው በ1969 ነው። ከዚያ በኋላ የሶማሊያ ሰርጎ ገቦችን ይዘው የገቡበት እና አሁን የገላና ሸለቆን የሚባለውን ጠቅላላ ቦረናን ጨምሮ እስከ ገላና ሸለቆ እስከ አማሮ የደረሱበት ሁኔታ ነበር። በ1969 በርካታ ሰዎች በተለይም ከኦሮሚያ ጉጂ ብሔረሰብ ተመልምሎ መቋዲሾ ሄዶ ሠልጥኖ፣ ተመልሶ መጥቶ የተዋጋበት ሁኔታ ነው የነበረው። ያ ግን በወቅቱ ሶማሊያ ስትሸነፍ ቆመ እና ዓላማው ለጊዜው ቆመ።

አሁን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ያ ሁኔታ ደግሞ ከኦነግ ጋር ተያይዞ የቀጠለና በተለይ አሁን ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በተለይ ከሐምሌ 18/2008 ጀምሮ ቀጥታ ወረራ እየተካሄደ ነው ያለው። ዓላማው የግዛት ማስፋፋትና መሬት አስለቅቀን ወደ አንድ ክልል እናስገባለን ወይም አገር እንመሠርታለን የሚል ዓላማ ከኋላው ያለው ነው ብለን ነው የምናስበው። በዚህም የዘር ፍጅት ነው እየተካሄደብን ያለው ብለን በተደጋጋሚ እያሳወቅን ነው የምንገኘው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎት ያላቸው አካላት ይኖሩ ይሆን? ካሉስ እነማን ናቸው?
ያው ቅድም እንደነገርኩህ የፖለቲካ ዓላማና ፍላጎት እንዳለ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም መሬት ማስለቀቅ አንዱ ዓላማ በመሆኑ፣ የአማሮ ወረዳ አካል የሆኑ አራት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በጉልበት ወደ ኦሮሚያ እንዲገቡ ተደርጓል። በቀበሌዎቹ የኮሬ ሕዝብ እየኖረባቸው አይደለም። የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ሙሉ በሙሉ በደቡብ ክልል ውስጥ ነው ያለው ተብሎ በካርታ ይታወቃል እንጂ ተነጥቋል።

ከዚህ ውጪ 20 ቀበሌዎች ከ2008 ጀምሮ ለማስለቀቅ ቀጥታ ወረራ እየተካሄደባቸው ነው። አሁንም ጦርነት እየተካሄደ ነው። ዛሬ ከሰዓት (ረቡዕ ሐምሌ 20/2014) ጦርነት እየተካሄደ እንደሆነና ሦስት ሰዎች ሞተው የተወሰኑ ሰዎች እንደቆሰሉ መረጃው ደርሶኛል። የፖለቲካ ዓላማ በደንብ ያለውና የተሰላ ስትራቴጂ ያለው ወረራ ነው የሚካሄደው የሚል ግምገማ ነው ያለን።

በአካባቢው ጥቃት ይፈጽማል ተብሎ በተደጋጋሚ ከሚከሰሰው ሸኔ በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት እጅ አለበት ማለት ይቻላል?
የነጭ ሳርን በሚመለከት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቀጥታ እጅ አለበት። ምክንያቱም የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ይኖር የነበረው ሕዝብ እንዲነሳና ፓርኩ ጥብቅ እንዲሆን ተብሎ በማእከላዊ መንግሥትም በቱሪዝም ሚኒስቴር ሲወሰን ሕዝቡ ተነሳ። ከፓርኩ ውስጥ ወደ 1080 የሚሆን ቤተሰብ ተነሳ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ወዲያኑ በቦታው ላይ ሌላ ሕዝብ አምጥቶ አስፍሮ ሁሉንም ንብረት በነጻ ወሰደ።

ያ ብቻ ሳይሆን አሁን ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ደንበኛ መንደሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች በመንግሥት ደረጃ ተመሥርተዋል። እየመሠረተ ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ነው።

ከይርጋ ጨፌ እስከ ተመሠረተው መንደር የሚደርስ መንገድ እየተሠራ ነው ያለው። በአንድ በኩል ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እጅ አለበት። በሌላ በኩል ግን ኦነግ ሸኔም አለ። በጋራ የሚሠራ ሥራ ነው እኛ የሚመስለን፣ ምክንያቱም ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ጽሕፈት ቤትም፣ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤትም በተደጋጋሚ አመልክተናል። ሽማግሌዎች እየመጡ አመልክተዋል። ይሄን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ማስታገስ አልቻለም፤ ከራሱ ክልል እየተነሱ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎችን ማስታገስ አልቻለም።

ስለዚህ አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣው ሸኔ አለ፣ ሰሞኑን በከባድ መሣሪያዎች ውጊያ እየከፈተ ያለው ሸኔ ነው፤ በግልጽ። ግን ሌሎች የኦሮሚያ ክልል ሚሊሻዎች ይሳተፉበታል። ነገሩ እየተባበሰ የሄደው ግን አሁን የተጀመረው የከባድ መሣሪያ ውጊያ ነው። በአማሮ በኩል ያለው ገበሬ የያዘው ግፋ ቢል ክላሽ ነው። ያንን መቋቋም ስላልቻለ እየጮኸ ነው ያለው።

በዋናነት ዓላማው የኦነግ ሸኔ፣ ያው ሥሙን የዳቦ ስም ሰጥተው ምናምን ይሉታል እንጂ ያው ወራሪ ነው። ዓላማውን እያሳካ ያለው በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን ነው። ግን ተባባሪ በመንግሥት በኩልም እየተደረገ ነው። ምክንያቱም መንግሥት ሊያስቆመው አልቻለም።

በኮንሶ ዞን ከ2011 ጀምሮ አስተዳደራዊ የመዋቅር ጥያቄ በማቅረባቸው ከ80 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በምርመራ ማረጋገጡን አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር። በአካባቢው የሚነሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ለጸጥታ ችግር ምክንያት የሆኑት በመንግሥት በኩል ምላሽ ስላልተሰጣቸው ነው የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አዎ! ኹለት ነገር ነው ነጣጥለን ማየት ያለብን። አስተዳደራዊ ችግሩ አለ። የዞን መዋቅር ጥያቄ አለ፤ በፊት በኮንሶ የነበረ ችግር አለ። ከ2011 ጀምሮ ኮንሶ ላይ ከፍተኛ ችግር የደረሰበት ሁኔታ አለ። አምስት ወረዳዎችን ማለትም ኮንሶን፣ አማሮን፣ ደራሼን፣ አሌንና ቡርጂን አንድ ላይ አጠቃሎ ሰገን ዞን የሚባል ተመሥርቶ ነበር።

ያ ዞን ሰባት ዓመት ኖሮ ሊሠራ ስላልቻለ እና እንደገና ክፍፍል ተፈጥሮ አሌ፣ ደራሼና አማሮ ወደ ልዩ ወረዳ እንዲመለሱ፣ ማለትም ከሰባት ዓመት በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ውሳኔ ተወሰነ። ከዚያ በኋላ ደግሞ የሰገን ዞን ዋና ከተማና የተወሰኑ ከአማሮም፣ ከቡርጂም ቀበሌዎችን ጨምሮ እዚያ አካባቢ ጭቅጭቅ ተነሳ። ደራሼም ዞን መሆን አለብኝ ይላል፣ አማሮም ዞን መሆን አለብኝ ይላል።

ይሄንን መንግሥት ከሕዝብ ጋራ ሆኖ ሕዝብን፣ ምሁራንን እና የአገር ሸማግሌዎችን አንድ ላይ አወያይቶ መፍትሔ መስጠት ሲገባው ቸል ተባለ። ቸል በመባሉ የተነሳ ካለፈው ኹለት ወራት በፊት ሠራዊት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ፡፡ ወደ 80 የሚሆን ሠራዊት የተጨፈጨፈበት ሁኔታ አለ። መንግሥት ሕዝቡ የጠየቃቸውን ጥያቄዎች ተከታትሎ ማጥናት፣ በተገቢው ሁኔታ መመለስ ያለመቻሉና ቸልተኛ መሆኑ፤ ለሰላም እጦትና ለአካባቢው መረበሽ ምክንያት ሆኗል የሚል የራሴ ግምገማ አለኝ።

ከኦሮሚያ ክልል በኩል የሚነሱ ትንኮሳዎችንና በአስተዳደራዊ ጥያቄ በአካባቢው የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
አንደኛው አጠቀላይ ከአገሪቱ መንግሥት ባህሪና ሕገ መንግሥት ጋር የተያያዘ ነው። አንደኛው ችግር የክልሎች አከላለል ነው። ከዚህ በፊት ያለውን ለምሳሌ አማሮን ብትወስድ ከጌዴኦ ጋር ነበር። በመሀል አሁን ያለው የገላና ሸለቆ የሚባለው በአማሮና በጌዴኦ ውስጥ ነው የነበረው፣ ማለትም የጌዴኦ አውራጃ የሚባለው ማለት ነው።

የዚህ ዓይነት ግጭቶች በግጦሽና በሳር ቢኖሩም፣ የፖለቲካ ዓላማ ያለው አልነበረም። ከዚህ አንጻር አንደኛው ችግር ሊፈታ የሚችለው የአማሮም ይሁን የሌሎች አካባቢዎች፣ ክልሎችን እንደ መንግሥት አድርጎ የማካለል ሁኔታና ሕገ መንግሥቱ የፈጠረው ችግር አለ። በአንድ አገር ውስጥ ክልል መሥርቶ የአንተ ድንበር ይሄ ነው የእኔ ድንበር ይሄ ነው የሚል ከፍተኛ ችግር አለ።

የሕዝቡን አብሮ የመኖር ባህል ወደ መበጣጠስ ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ ስላለ፣ ከፍ ብሎ ሲታይ ምናልባት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ በስተቀር ወደፊትም ምናልባት የማይቆም ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ የተወሰነ ብሔረሰቦችን አካሎ ሰጥቷል፣ ይሄ የእገሌ ብሔር፣ ይሄ የእገሌ ብሔር ብሎ፣ ይሄ የመላው አገሪቱ የሚታይ የጋራ ችግር ነው። ምናልባት ወደፊት ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ የአስተዳደር ወይም አከላከል ጉዳዮች የሚሻሻሉ ከሆነ፣ እስከዚያ ድረስ ችግሩ የሚዘልቅ ይመስለኛል።

ሌላው መፍትሔ ከኃይለማርያም ደሳለኝ (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር) ጀምሮ የአማሮ ሽማግሌዎች የመፍትሔ ሐሳቦች ያቀርቡ ነበር። አንደኛው ሲሉ የነበረው በዚህ አካባቢ ተደጋጋሚ ጥቃት ስለሚደርስ አንድ የጦር ካምፕ ይመሥረትና በኦሮሚያና በደቡብ መካከል ማለትም በኮሬና በኦሮሚያ መካከል ቁጥጥር ይደረግ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው። ያ ሊመለስ አልቻለም። ምናልባትም አንዱ የአጭር ጊዜ መፍትሔ የሚሆነው እሱ ነው።

ከዚያ ውጪ መንግሥት ለሕዝቡ አይደርስም የሚል እሮሮ ነው ያለው። ሕዝቡን ከእልቂት መታደግ የሚቻለው ራሱን እንዲከላከል በማድረግ ነው። ማለትም ራሱን እንዲከላከል ማድረግ ማለት መንግሥት ለሕዝብ መድረስ ካልቻላ፣ የመንግሥት ጦር ሠራዊትና ፖሊስ ሕግ ማስከበር ካልቻለ ሕዝቡን አስታጥቆ ራሱን እንዲከላከል የሚል ጥያቄዎች ናቸው የሚቀርቡት። ስለሆነም በአጭር ጊዜ በአካባቢው የጦር ሠራዊት ካምፕ ተመሥርቶ ወዲያው እርምጃ የሚወስድና ሰላም እንዲያስከብር ማድረግ ነው። ኹለተኛው ሕዝቡ ራሱን እንዲከላከል መንግሥት አዋጭ የሆነ ሁኔታ አጥንቶ ሕዝቡን አስታጥቆ ራሱን እንዲከላከል ማድረግ ነው።

የረዥም ጊዜ መፍትሔው ግን ከሕገ መንግሥቱና ከክልሎች አከላለል ጋር የተገናኘ ስለሆነ፣ ምናልባት በሌሎችም አካባቢዎች ያለ ስለሆነ ወደፊት በጋራ ሊፈታ የሚችል ነው።

እርስዎ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው አንድ ዓመት አሳልፈዋል። በተወከሉበት አካባቢ ያለው ችግር አንገብጋቢ እንደመሆኑና እንደ ተወካይነትዎ የወከለዎትን ማኅበረሰብ ችግር በምን ያህል አቃለዋል?
ይሄን ያህል አቃልያለሁ ብዬ ደፍሬ መናገር አልችልም። ግን በትንሹ ድምጽ ለመሆን ችያለሁ የሚል ግምት አለኝ። በፊት የዚያ ሕዝብ ጉዳይ በፓርላማ ብዙም ትኩረት አግኝቶ ድምጽ የሚሰማበት ሁኔታ አልነበረም።

እንደ ተወካይ ድምጽ ሆኛለሁ። በዚህ የተነሳ የአገር ውስጥ እና የዓለም ዐቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ከሌሎች ባለደረቦቼ ጋር ማድረግ ችለናል። ይሄንን በማድረጌ ምናልባት፣ የበለጠ ጩኸቱ እንዲሰማ በማድረግ ሕዝቡ ከመጥፋት እንዲድን ያደረኩበት ሁኔታ አለ።

ግን ችግር መፍታት የአንድ ተወካይ ጉዳይ ሳይሆን፣ የመንግሥት ጉዳይ ነው። እኔ ለመንግሥት ነው ሁሌ እየጮኹክ ያለሁት፣ በተወካዮች ምክር ቤት እጮኻለሁ ወይም በሚዲያ እጮኻለሁ። ዋናው ኃላፊነቴ ደምጽ ማሰማት ነው። ይሄን ድምጽ በተቻለኝ መጠን እያሰማሁ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ የአካባቢው ችግር እውቅና እንዲያገኝ ያደረኩበት ሁኔታ አለ።

በዚህም ለምሳሌ ሰኔ 29/2014 ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርመራ እንዲደረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ አቋቁሟል። በዚህም ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ምርመራ እንዲደረግ ከተመረጡ አካባቢዎች መካከል አማሮ አካባቢ እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ነው።

እንደ አጋጣሚ እኔም የዚያ ኮሚቴ አባል ሆኜ፣ ዘጠኝ የኮሚቴው አባላት በዚያ አካባቢ ተገኝተን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ሕዝቡንም፣ የተበደሉትንም በመጠየቅ፣ ከጸጥታ አካላትም አጣርተን ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ እናቀርባለን።

አጠቃላይ በክልሉ ከሚነሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች አንዳንዶቹ ተገቢነት ያላቸው አንዳንዶቹ ደግሞ በዘፈቀደ የሚነሱ ናቸው የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። በእርስዎ አመለካከት በክልሉ የሚነሱ የአስተዳደር ጥያዌዎችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?
እንግዲህ ደቡብ ክልል ውስጥ ያለው ሁኔታ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ውስብስብ ነው። ሲመሠረት 56 ብሔረሰቦች አንድ ላይ ሆነው ከከፋና ከጋምቤላ ደንበር አንስቶ እስከ ባሌ ያለው ሕዝብ አንድ ላይ ሲሆን ሕዝቡ ምክክር ያደረገበት አይደለም። እንዴት አድርጌ ልተዳደር፣ ከማን ጋራ ልተዳደር፣ እንዴት ልሁን የሚል ምክክር ሳይደረግበት የተወሰኑ ቡድኖች ያኔ ሕወሓት አሸንፎ ሥልጣን ሲይዝ ዝም ብሎ የጨፈለቀው ነው።

ከዚያ በኋላ የተለያዩ በደሎች እየደረሱብኝ ነው፣ አስተዳደራዊ በደሎች እየደረሱብኝ ነው የሚሉ እሮሮዎች በየአካባቢው ይነሳሉ። የደቡብ ክልልም ይሁን ማእከላዊ መንግሥት ያንን ጥያቄ በሚመልስበት ሁኔታ ተመሳሳይ የሆነ አቋም ይዞ መልስ አልመለሰም። ተመሳሳይና ሚዛናዊ መሆነ መንገድ መልስ አልመለሰም። በሕገ መንግሥቱ መሠረት ቅድም ችግር አለበት ብያለሁ። ግን ችግሩ ችግር ከሆነ ለሁሉም ነው ችግር መሆን ያለበት፣ ጥሩ ነገር ከሆነም ለሁሉም ነው ጥሩ ነገር መሆን ያለበት።

አሁን ያለው ችግር ክፍፍል አለ፣ ለአንዱ ክልል ሰጥቶ ለአንዱ መንሳት። ከዚህ አንጻር መከፋት ይፈጥራል። ያ ደግሞ ክልል ተነጣጥሎ መሆኑ ጉዳት አለው። አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ችግሮች አሉት። ግን ከመብት አንጻር ለአንዱ ሰጥተህ ለአንዱ የምትነሳበት ሁኔታ መኖር የለበትም። እንደ መርህ ሕዝብ አወያይቶ ተመሳሳይ ውሳኔ መወሰን ሲገባው፣ እየቆራረጠ መንግሥት እሳት ለማጥፋት የሚሄድበት ሁኔታ ነው ችግር የሆነው። እሳት በተነሳ ቁጥር እሳት ለማጥፋት እዚህም ዛሬ አንድ ነገር ይወሰናል፣ እዚያም አንድ ነገር ይወሰናል።

ያለን ሀብት ውስን ስለሆነ፣ ያለንን ሀብት አሰባስቦ ለመጠቀም አንድ ላይ መሆን ተሰባስበን ብንኖር የተሻለ ይሆናል። ከዚህ አንጻር የደቡብ ክልል ሕዝቡ ተማክሮ የመሠረተው አይደለም። ግን በክልሉ አስተዳደራዊ በደሎችና የአስተዳደር ብልሹነት ባይኖር ኖሮ ለኢትዮጵያ ተምሳሌት ሆኖ አንድነትን ይሰብክ ነበር። ሕዝብን አንድ ላይ በምታኖርበት ጊዜ አንድ አባት ስድስት፣ ሰባት ልጆቹን እኩል እንደሚያይ እኩል ማየት መቻል አለብህ። በጣም ችግር የሆነው የአስተዳደር ብልሹነትና ፍትህ ማጣት ነው።

በአብሮነት መኖር መቻልም ማረጋገጥ የሚቻለው እኩል ተጠቃሚነትና ለሁሉም ተመሳሳይ ፍትህ ሲኖር ነው። በደቡብ ክልል ያለው ሁኔታ ሲታይ ባለፉት ዐስር ዓመታት የተወሰኑ አካባቢዎች ተጠቃሚ የሆኑበት ሁኔታ አለ። የተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በጣም ተጎጂ ሆነዋል። ስለዚህ በሕዝብ ውስጥ ተጎጂ ሆነናል የሚል ብሶት አለ። በዚህም በራሳችን በጀት ብናዝ ራሳችንን ብናስተዳድር የሚል ፍላጎት ይነሳል።

በክልሉ የሚነሱ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች የችግር ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸው የሚመለከቱ ችግሮች በየጊዜው ይታያሉ። አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ለጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይሆኑ እንዴት ቢስተናገዱ ይመክራሉ?
በነገራችን ላይ የሚነሱትን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መመካከር ነው የሚያዋጣው። አሁንም ቢሆን ለሌላ የከፋ ችግር ከመዳረጋችን በፊት መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ምክክር አድርጎ ሕዝቡ የሚፈልገውን በደንብ ማጥናትና ማወቅ መቻል አለበት።

ምናልባት ዘንድሮ እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንዱ ያደረግነው የምክክር ኮሚሽን አቋቁመን ሥራ ጀምሯል። ምናልባት የምክክር ኮሚሽኑ አንድ ነገር ይዞ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አደረጃጀቱ እንዴት ይሁን? በዚህ አገር ውስጥ ቅራኔ የፈጠሩት ምንድን ናቸው? በአገር ዐቀፍ ደረጃ፣ በክልል ደረጃ ሲወርድም በደቡብ ክልል ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ውይይቶች ያደርጋል። መፍትሔ ያመጣል አያመጣም የሚታወቅ ነገር የለም። ዞሮ ዞሮ ግን ምክክር ማድረግ፣ ከሕዝብ ጋር መወያየት፣ ሕዝቡ እርስ በራሱ ተገናኝቶ እንዲወያይ ማድረግ የግድ ይላል።

መንግሥት ሕዝብን እኔን ተከተል የሚለው መንገድ አዋጭ እንዳልሆነ ታይቷል። አሁን ደግሞ እስኪ ሕዝብ የሚለው ይሰማ። ሕዝቡ እንዴት ብተዳደር ይሻላል? እንዴት ብካለል ይሻላል? የሚለውን ራሱ እንዲወስን እድል ይሰጠው።

በክልሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን መርጣችኋል ተብለው እስር፣ እንግልትና መገለል የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተሰማ ነው። ከዚህ አንጻር በክልሉ የገጠማችሁ ችግር ምንድን ነው?
በኹለት መንገድ ነው የሚታየው። በአንድ በኩል በራዲዮ እና በቴሌቪዥን ተፎካካሪነትን ማበረታታት የሚል ፕሮፖጋንዳ ይታያል። በሌላ በኩል ግን የበቀል ደርጊት ይታያል፣ እንዴት ከእኔ ወጣህ? እኔን ሳትመርጥ እንዴት ተፎካካሪ መረጥክ? የሚል ችግር አለ። በዚህም የተነሳ በሰበብ አስባቦች እስሮችና እንግልቶች አሉ። የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የግብርና ሠራተኞች እናንተ ናችሁ ሕዝቡ ወደ ሌላ ፓርቲ እንዲሄድ ያስተባበራችሁት ተብለው ከሥራ መባረር፣ መታሰርና ከፍተኛ ምሬት አለ።

አንዳንዴ የማይገናኙ ነገሮችን አገናኝቶ የመወንጀል ሁኔታና በጸጥታ ኃይሎች የማገት ችግሮች ያጋጥማሉ። አሁን በእኛ በኩል ያለውን ብትወስድ እኔ የወከልኩት ማኅበረሰብ አስተዳደር ከእኔ ጋር ግንኙነት የለውም። አንተ የተመረጥከው ከፌዴራል ነው፣ ወረዳውን የምናስተዳድረው እኛ ነን በሚል እዚያ ካለው የኢዜማ ፓርቲ ጋርም ተመራጭ ከሆነውም ጋር ግንኙነት የለውም። ግንኙነት ለማድረግም ፍላጎት የለም። ይሄ በራዲዮና በቴሌቪዥን በሚባለው በተቃራኒ ያለ አካሄድ ነው የሚታየው።

ሰላማዊ ተፎካካሪነትን ማስተናገድ ባልተቻለበት ሁኔታ ዴሞክራሲን እንዴት ማምጣት ይቻላል?
ጥረት ማድረግ ነው፣ አንድ ነገር ያለ ልፋት የሚመጣ ነገር የለም። የታሪካችንም ችግር ነው፣ ከታሪካችንም የጭቆና እንጂ የዴሞክራሲ ያለመሆን ችግር አለ። ሥልጣን ላይ ያለው አካል ሌላ አካል አላስጠጋም የሚል አካሄድ አለው። ይሄን አካሄድ ግን በሌላ በምንም ሊለወጥ አይችልም፣ በትንሽም ቢሆን ምርጫ ስለሌለን ጥረት ማድረግ ነው።

በዚህ አገር ይህ ሁሉ ብጥብጥ ባለበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ካልሰፋ፣ ካልሰረጸና ትንሽ ትንሽም ቢሆን እየሠራ ካልሄደ አደጋ ውስጥ እንወድቃለን። ይሄ ነገር እንዲመጣ የግድ መግባባት መቻልና ጥረት ማድረግ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here