መነሻ ገጽሌሎችማኅበረሰብ አንቂ – የተከፈለበትአገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል የትውልድ ትስስር መፍጠር

አገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል የትውልድ ትስስር መፍጠር

ርዕይውን የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የበለጠ ተስማምተው እና ትርጉም ያለው ውህደት ሲኖሩ ማየት ያደረገው የብሔራዊ እና ቀጠናዊ ውኅደት ጥናት ማዕከል (Center for National and Regional Integration Studies/CeNRIS/) ሰኔ 14 ቀን 2011ዓ/ም አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሆኖ ተመሰረተ።
የጥናት ማዕከሉ በዋናነት በአገር ዐቀፍና በክፍለ አህጉር ደረጃ በሰላምና መግባባት፣ በዴሞክራሲና አካታችነት ላይ እንዲሁም ፖሊሲ አግባብነት ያላቸውን የምርምርና ፕሮጀክቶች ዙሪያ በትኩረት በመሥራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት ሐሳቦች የብሔራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ውህደት ጥናት ማዕከልን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

አገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጡ ሰዎች፣ የዩንቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የቀድሞ የተማሪዎች ንቅናቄ አባላትና የአብዮቱ ዘመን ተሳታፊዎች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት ለሦስተኛ ጊዜ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ በቀድሞው ትውልድና በአሁኑ ትውልድ መካከል ትስስር ለመፍጠር፣ የቀድሞውን ትውልድ ተሞክሮዎች ከማውሳት ጀምሮ የአሁኑን ትውልድ ጥያቄዎች በመጥቀስ ጥልቀት ያላቸው የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መሥራች፤ የቀድሞው ከፍተኛ አመራር አባልና የ“ያ ትውልድ” መጽሐፍ ደራሲ ክፍሉ ታደሰ የቀድሞውን ትውልድ ተሞክሮ አስመልክቶ ለተሳታፊዎች በሰጡት ሰፋ ያለ ማብራሪያ፣ በተለምዶ ያ ትውልድ ተብሎ የሚጠራው በሦስት ይከፈላል ነው ያሉት።

በዚህም የመጀመሪያው አውሮፓ ለትምህርት ሄዶ ጊዜውን እዚያ ያጠፋና አውሮፓ እንዴት እንደሠለጠነ ያየው ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ በዱር በገደል የጣሊያንን ወረራ ሲፋለም የነበረው አርበኛ ነው ብለዋል። ሦስተኛ ነው ያሉት፣ በውዴታም ይሁን በግዴታ ለጣሊያን ያደረው ነው።
ስለዚህም በሦስት የተከፈለው ያ ትውልድ በመካከሉ ልዩነት ያለውን ያህል አንድ የሚያደርጉት ነገሮችም እንዳሉት አንስተዋል።

ያን ትውልድ ለማስተዋወቅም በ1953 የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከኹሉም የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በርካታ ንፁሐን ሰዎች ሲገደሉ በትምህርት ላይ የነበሩ ታዳጊዎች ያዩ ነበር።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾችም ከተማሪዎች ጋር ምክክር አደረጉ። የንጉሡ ሥልጣን በመደፈሩም ንጉሡ በተማሪዎች ላይ ቂም ያዙ። በዚህም በየዓመቱ በገና በዓል ለተማሪዎች የሚሰጠው የንጉሡ ዳረጎት (የገና ዳቦ) ተቋረጠ። ንጉሡም ቤተመንግሥታቸው ደም ስለፈሰሰበት ጥለዉት ወጡ።

የጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የፍርድ ሂደት በተለይ ለወጣቱ መነቃቃት ሆነ። ተማሪዎችም በንጉሡ መማላቸውን አቆሙ። ቀስ እያለም ወጣቱ በተለይ ከስርዓቱ ጋር የነበረውን ቁርባን እየተወ ሄደ። የተማሪዎች ንቅናቄና ትግልም እየጎላ ሄደ ሲሉ አስረድተዋል።

ብዙ ተማሪዎችም ከትግሉ ላለመራቅ ከዘጠኝ እስከ ዐስር ዓመት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆን ብለው ይቆዩ ነበር ያሉት ክፍሉ ታደሰ፣ የኋላ ኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጥያቄዎቻችን ናቸው ብለው ያነገቧቸው በተማሪዎች ንቅናቄ የተነሱ ጉዳዮችን ነው በማለት ገልጸዋል።

ወደ 1960ዎቹ መጨረሻ ንጉሡ እያረጁ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ፣ የአገዛዝ ስርዓቱም እየተበላሸ ሲሄድ ብሔርተኛ ኃይሎች በተለይም በባሌና በኤርትራ መፈጠራቸውን ተከትሎ አገሪቱን የሚታደግ ብሔራዊ ኃይል መቋቋም አለበት የሚል እሳቤ ተነስቶ እንደነበርም አውስተዋል።
ይሁን እንጂ፣ በአገሪቱ ሀብት የተማረው የሕዝብ ወገን መደራጀት አለመቻሉንና በዚህ እሳቤም መከፋፈል ብሎም የእርስ በእርስ መዘላለፍ መፈጠሩን ነው የጠቀሱት።

ወዲያውም የ1966ቱ አብዮት የፈነዳ ሲሆን፣ አብዮቱ መሪ እንዳልነበረው ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም የንቅናቄው አንድ አካል የነበረውና ቀደም ብሎ መደራጀት ጀምሮ የነበረው ወታደሩ የአብዮቱ መሪ መሆኑን እንዳወጀ ገልጸዋል።

ወታደሩም በተለየ ሁኔታ ለዘጠኝ ወር ሲካሄድ የነበረውን ጠንካራ ንቅናቄ ጨፍልቆ የሽግግር ሂደቱን አጨናገፈው። እንዲሁም ከመስከረም 2/1967 በፊት በነበሩት ዘጠኝ ወራት በአንፃራዊነት ተፈጥሮ የነበረውን የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመደራጀትና የመታገል ሁኔታ በአንድ አዋጅ ማገዱን ነው የገለፁት።

ስለሆነም ክፍሉ ታደሰ የዚያን ትውልድ መሠረታዊ ክፍተቶች ሲጠቅሱ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ባህል አለመኖሩ፣ ዴሞክራሲና በኅቡዕ መደራጀት አብረው የማይሄዱ መሆናቸው እንዲሁም በከፊል ከሐይማኖት የሚቀዳ ልክ ያልሆነ አስተሳሰብ መኖሩ ነው። ያ ትውልድ የከሸፈባቸውን ነጥቦች አንስተውም፣ ሽግግሩን ማሳካት አለመቻሉ ዋናው ክሽፈቱ ነበር ብለዋል።

ጃንሆይም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቋም እንዲኖራት በእነ ሀዲስ ዓለማየሁ ሳይቀር ቢመከሩም፣ የመሬት ጥያቄን እንዲፈቱ የስርዓት ማሻሻያ እንዲያደርጉ ቢወተወቱም፣ ያን ማድረግ ባለመቻላቸው በትውልዱ የሽግግር ስርዓት መፍጠር አልተቻለም ነው ያሉት።

ክፍሉ ታደሰ በመጨረሻም፣ ከዚያ ትውልድ ጀምሮ ሕወሓት የራሱን ተለጣፊ ድርጅቶት መሥርቶ የራሱ የሽግግር ሂደት እንጂ የማንም ያልሆነ ሽግግር ያደረገበትን ጨምሮ እስከ አሁን ድረስ ከአምስት ያላነሱ የሽግግር ዕድሎች መፍጠራቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ሁሉ አንድ እንኳን የተሳካ ሽግግር ቢደረግ ኖሮ ኢትዮጵያ ለዛሬው ቀውስ ባልተዳረገች ነበር በማለት ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

ሌላኛው በመድረኩ ተገኝተው በኹለቱ ትውልዶች መካከል ስላለው ትስስር እና መግባባት ማብራሪያ የሰጡት መላኩ ተገኝ (ዶ/ር)፣ ያ ትውልድ በደንብ ከሚታወቅበት ነገር አንዱ ከዓለም ዐቀፋዊ ጉዳዮች ጋር የነበረው ትስስር ነው ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህም በወቅቱ ከነበረው ዓለም ዐቀፋዊ እሳቤና ትስስር የተነሳ አንድን ተማሪ የየትኛው ብሔር አባል ነህ ብሎ መጠየቅ ነውር ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።

በተለይ አሜሪካ በቬትናም ላይ ያደረገችው በእብሪት የተሞላው ወረራና የቬትናም ሕዝብ ያሳየው የጀግንነት ፍልሚያ በወቅቱ (1960ዎቹ) በዓለም ደረጃ በርካታ ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግሎች እንዲፋፋሙ ያደረገና በዓለም ላይም ትልቅ ተፅዕኖ ያለው እንቅስቃሴ ተደርጎ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ተማሪዎችም ከዚህ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴ ጋር የተሳሰሩ እንደነበሩ ገልፀው፣ በዚህ የተነሳም የዳበረ አመለካከት ባለቤት እንደነበሩና ከፍ ሲልም በዓለም ዐቀፍ የተማሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲሁም ሰልፎች ላይ ለመገኘት ከኢትዮጵያ የሚወጡ ተማሪዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ፣ ትውልዱ ይህን ያህል ጥንካሬ ቢኖረውም መሠረታዊ ጉድለቶችም እንደነበሩበት ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በዋናነት ያነሱትም በጥያቄው ስለገጠሩ ማኅበረሰብ ልማት የተሟላ ዕይታ አልነበረውም ብለውታል።

ለአብነትም የመሬት ጥያቄው፣ ከአምስት እስከ ኻያ በመቶ ከጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ድርሻ ያለውንና ከ61 በመቶ በላይ የአገሪቱን መሬት በእጁ የያዘውን አርብቶ አደሩን የዘነጋ ነበር ነው ያሉት።

ወጣቱ ይከተለው የነበረውን ርዕዮተ ዓለም አንስተውም፣ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ነፃነትና ከዴሞክራሲ አንፃር ሲታይ ኋላቀርነት በነበረው የማርክሲስትና ሌኒኒስት እሳቤ የተጠመቀ እንደነበር አመላክተዋል።

የቀደመውንና የአሁኑን የፖለቲካ ትውልድ ማስተሳሰር በሚል ጽሑፍ ያቀረቡት ዮናስ አሸኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ትውልድ ማለት በጊዜ መስመር የሚያልፍ ማኅበራዊ ተቋም መሆኑን በቅድሚያ አብራርተዋል።

እንዲሁም አንድ ትውልድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሕይወት ተሞክሮ (lived experience) እንዳለው ጠቅሰው፣ ታሪካዊ አውድ (historical condition) እንዳለውና መካነ ማኅበረሰብ (social location) እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አንድ ትውልድ የራሱ የሆነ ባህሪያት ያሉት ሲሆን ከእነዚህም ተከታታይነት፣ የእድሜ ልዩነት (ለአብነትም አብዮት ያየና ያላየ)፣ ባህል ፈጣሪነትና ወራሽነት እንዲሁም የራስ የሆነ ትናንትና ነገ ባለቤትነት የትውልድ ባህሪያት ከሚባሉት የተወሰኑት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ስለ አንድ ትውልድ ጥያቄ ሲነሳም ትውልዱን በመገንባት ረገድ የትኛው ጉዳይ ይበልጥ ፋይዳ አለው የሚለውን ማንሳት አስፈላጊ እንደሚሆን አንስተው፣ ምን ዓይነት የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ ገንብቷል እንዲሁም ነገውን ለመገንባት በምን መልኩ እየተጓዘ ነው የሚሉትን መዘንጋት እንደማይገባም አክለዋል።

ጽሑፍ አቅራቢው አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትውልድ (political generation) በሦስት ሊከፈል እንደሚችል በማንሳት፣ የመጀመሪያው ከድኅረ ጣሊያን ወረራ በፊት የነበረው አገሩን ለመገንባት የተሳተፈው መሆኑን ጠቅሰዋል።

እዚህ ውስጥም የተፈጠሩ ቁስሎችና ቅራኔዎች እንዳሉ በመግለፅ፣ ከዚህ ትውልድ የወረስናቸው ዛሬ ያለው ምሁሩና ፖለቲከኛው የሚተነትናቸው ትርክቶችና የጠብ ምክንያት የሆኑ ቁርሾዎች አሉ ነው ያሉት።

ኹለተኛው ትውልድ የአብዮቱ ትውልድ መሆኑን በማንሳትም፣ ከዚህ ትውልድ የወረስነው ደግሞ ፅንፍ መያዝና ተቀራርቦ በመነጋጋር ችግሮችን መፍታት አለመቻል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ፖለቲካ ማለት አለመስማማት ነው የሚል ብሂል የዚህ ትውልድ ውርስ ሳይሆን እንደማይቀርም ሳይጠቅሱ አላለፉም። በተለይ አሁን ላይ ትውስታቸውን በስፋት እየጻፉ ያሉት የተማሪዎች ንቅናቄ አባላትም ሆኑ የአብዮቱ ትውልድ አባላት፣ ይህ ትውልድ እንዲሰማቸው ከመፈለግ እንጂ ስለራሳቸው መነጋገርም ሆነ እርስ በእርስ ለመግባባት ሞክረው አያውቁም። እኛን መሠረት አድርገው ነው የሚነጋገሩት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ክፉኛ እየፈተናት ያለው የብሔር ጉዳይም በዚህ ትውልድ በተሻለ ሁኔታ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ ተንትነው ያልጨረሱትን ጥያቄ ነው ያቀበሉን ባይ ናቸው።

ስለሆነም፣ የመነጋገር ፖለቲካን አላወረሱንም። በኢሕአዴግ ተከስቶ እስከ አሁን የቀጠለው ተቋማዊ ቀውስም ከአብዮቱ ትውልድ የተወረሰ ነው የሚል እምነታቸውን አጋርተዋል።

ሦስተኛው የፖለቲካ ትውልድ ከድህረ አብዮቱ በኋላ ያለው መሆኑንም አስቀምጠዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ ትውልድ በተጨቋኝ ስርዓተ ትምህርት (oppressed pedagogy) ውስጥ ያደገ ከመሆኑም በላይ፣ ያለፈው ስርዓት ቁስሎችና የትርክት ውርሶች፣ ቴክኖሎጂ፣ ፌዴራሊዝም፣ ሊበራሊዝም እንዲሁም ሌሎች ነገሮች የተደራረቡበትና ራሱን እንደገና እየገነባ ያለ ትውልድ እንደሆነ አብራርተዋል።

እንዲሁም ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ የዚያ ትውልድ አባላት 99 በመቶ በአሁኑ ወቅት የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሉም። ይህ ለምን ሆነ?

ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይበጃል ወይ? አሁን ላይ ከምንገኝበት ተጨቁነናልና ተበድለናል የሚል የቁስለኞች ፖለቲካ ለመውጣት ምን እናድርግ? ሽግግሮች የሚከሽፉት ለምንድን ነው? የሚሉትና ሌሎች ጥያቄዎች እንዲሁም በርከት ያሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

በተለይ ከተሳታፊዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እያሱ ግዛው፣ ያ ትውልድ የሚባለውን ያህል ጥንካሬ የሌለውና በብዙ ነገሮች የተወዛገበ እንደነበር አስተያየት ሰጥተዋል። ለአብነትም ዛሬ የአማራው ሕዝብ ለሚደርስበት በደል መሠረቱን የጣለው የዚያ ትውልድ አባል የነበረው ዋለልኝ መኮንን ነው የሚል ዕይታቸውንም አጋርተዋል።

መምህሩ ስለዋለልኝ አንስተው፣ የሞተው አውሮፕላን ሊጠልፍ ሲሞክር ነበር። ይህ ደግሞ ለማኅበረሰብ እድገት እታገላለሁ ከሚል ሰው የማይጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዋለልኝ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ትኩሳት የሆነውን የብሔር ጉዳይ ያነሳው ከነ ማርክስ ኮርጆ ነው ካሉ በኋላ፣ ማርክስ ከትልቅ ብሔር የተገኘህ ከሆንክ ጥሩ ማርክሲስት አትሆንም ብሎ ያምናል። ዋለልኝም ከትልቅ ብሔር በመወለዱ የማርክስን ያህል ያሰበና ትልቅ ሰው የሆነ መስሎት፣ ከትልቅ ብሔር መወለድ ለነጻነት ከመታገል አያግድም በሚል የተሳሳተ እሳቤ ውስጥ ገብቶ ነው ያልገባውን ነገር በመኮረጅ መጥፎ ነገር ያደረገው ብለውታል።

ስለሆነም፣ ያ ትውልድ ብዙ ዕዳ ያወረሰን ሆኖ ሳለ ያን ያህል ብዙ አይተችም። በደፈናው አሰማምሮ ማለፍ (political romantics) ነው የሚታየው የሚል ተቃርኖ አንስተዋል።

አክለውም፣ የአፄ ኃይለሥላሴ አስተዳደር ለኤርትራ ፌዴሬሽን በመፍቀዱ፣ በዴሞክራሲ ረገድ በአንጻራዊነት የተሻለ ስርዓት ነበር መባሉን በመቃወም ንጉሣዊ ስርዓት (monarchy) እና ዴሞክራሲ አብረው የሚሄድ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

ለመምህሩ ግብረ መልስ የሰጡት ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) የተማሪዎች ንቅናቄ አባላት የጻፏቸው ጽሑፎች አሁንም ተጠርዘው ተቀምጠዋል። እያንዳንዱን ለምን እንዲህ አሉ የሚለውን መመርመርና ሙያዊ ትንታኔ መስጠት ያስፈልጋል የሚል ዕይታቸውን አጋርተዋል። ከተማሪዎች ንቅናቄ በፊትም የብሔር ጥያቄ ተነስቶ ነበር ያሉት ዮናስ፣ እንደምሳሌም ደራሲ አቤ ጉበኛ ከዚያ ቀደም ብሎ በጻፈው አንድ መጽሐፉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ገጸባህሪውን የሞተው በብሔር ጥያቄ ነው ብለዋል። ይህም ከተማሪዎች ጥያቄ ቀደም ብሎ የተነሳ የብሔር እርሾ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተናገሩት።

መምህሩ ንጉሣዊ አገዛዝና ዴሞክራሲ አብረው የማይሄዱ ነገሮች ናቸው ላሉትም፣ ይህን የሚያስኬዱ አገራት መኖራቸውን በማንሳት ለአብነትም ኖርዌይን ጠቅሰዋል።

መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በተለይ ዋለልኝ መኮንን የሚተቹ ሰዎች ጹሑፉን ያላነበቡና ያልተረዱ ሰዎች መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይልቅስ የተማሪዎች ንቅናቄ አባላት ትልቅ ጥንካሬና በዚያው ልክም ድክመት እንደነበራቸው በመገንዝብ ይህን ለይቶ ማወቅና ለዚያ ተገቢ እውቅና መስጠት ይገባል ባይ ናቸው።

ክፍሉ ታደሰ በተለይ ስለዋለልኝ መኮንን በሰጡት ማብራሪያ፣ በፈረንጆች 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ዋለልኝን ጨምሮ ብዙ ተማሪዎች ታሰሩ ይላሉ። በዚህ ወቅትም ከሜጫና ቱለማ ኦሮሞ እንቅስቃሴ እንዲሁም እነ ማሞ መዘምር ቦንብ አፈንድተዋል ከተባለው ጋር ተያይዞ ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች እስር ቤት ገብተው ነበር። ይህን ተከትሎም ተማሪዎች በማንነት እንቅስቃሴያቸው የታሰሩ ሰዎችን ሲያዩ ከዚህ በፊት አንስተውት ከማያውቁት ጉዳይ ጋር ተፋጠጡ። ተማሪዎችና የኦሮሞ ተወላጆችም በእስር ቤት እያሉ ስለማንነት መወያየት ጀመሩ። ዋለልኝም ስለብሔር የጻፈው ከዚህ ተነስቶ ነው፣ አሁንም ቢሆን የብሔር ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ዕልባት ማግኘት አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

እንዲሁም፣ በቀድሞውም ይሁን በአሁኑ የአንድ ትውልድ አባላት መካከል ደም መፍሰሱን በማንሳት፣ ደሙ ባይደርቅም ይህ ትውልድ ያን ተቀብሎ እንዴት መሻገር እንዳለበት ቁጭ ብሎ መነጋገር ይኖርበታል። በሕገ መንግሥቱም በዘርና በሐይማኖት መደራጀት ተከልክሎ ዜጎች በሐሳብና በሥራ ቢደራጁ መልካም ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በዘርና በሐይማኖት መደራጀት እስካልቆመ ድረስ ልዩነታችን እየሰፋ ችግራችንም እየተፈለፈለ ነው የሚሄደው ባይ ናቸው።

አሁን ስላለው ፌዴራሊዝም በማንሳትም፣ በየክልሎች ያሉ አናሳ ብሔሮች በክልሉ ነዋሪዎች ማንነት በተደራጁ ፖርቲዎች ውስጥ ገብተው የማይሳተፉበት፣ የራሳቸውን ፓርቲም ማቋቋም የማይችሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለሆነም፣ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም አሁንም የለም ማለት ይቻላል ነው ያሉት።

ስለሆነም፣ አብዛኛውን ጉዳይ ክልል ላይ አንጠልጥሎ ከማስቀረትም ዜጋ ዐቀፍ የሆኑ አካባቢያዊ ተቋማትንና የወረዳ መንግሥታት መመሥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

አሁን ላይ ቁስል ላይ የቆመው የብሔር ጉዳይም አንድነትንና መፋቀርን በሚያመጣ መልኩ መተንተን አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ሽግግርን በተመለከተ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር)፣ የተሳካ ሽግግር ለማድረግ ቅድሚያ የትውልዱን ጥያቄዎች በሚገባ ማወቅ ይጠበቃል ይላሉ።

እስከ አሁን የነበሩት የሽግግር አጋጣሚዎችም የኅብረተሰብ ተሳትፎ የተላበሱ ስላልነበሩ ሳይሳኩ ቀርተዋል ሲሉ ገልጸው፣ በመሆኑም አንድ የተሟላና ሊሳካ የሚችል ሽግግር ከተገዥነት እሳቤ ወደ ዜጋ እሳቤ የተለወጡ ግለሰቦች፣ ካለበት ሁኔታ ወደ ዜጋ ስብስብ የተሸጋገረ ማኅበረሰብ እንዲሁም የግለሰቦችንና የማኅበረሰቡን ሽግግር የሚደግፍ፣ ለውጥ የሚያስደስተው ራሱም ወደ ዴሞክራሲ የሚሸጋገር የመንግሥት መዋቅር ያስፈልጋል የሚል እሳቤ አጋርተዋል።

እነዚህ ሦስቱ የተያያዙ በመሆናቸውና የአንዱ ሽግግር ያለሌላው ውጤት አልባ በመሆኑ፣ በተመሳሳይ ሂደት ሽግግር የፈፀሙ እንደሆን እንደ አገር የተሳካ ሽግግር መፍጠርና የተሻለ ስርዓት መገንባት ይቻላል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ የዚህ ትውልድም ጥያቄ መሆን ያለበት ለምን አላደግንም? ለምን ከታሪክ መማር አቃተን? የሚል መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል።
ባለፈው ለተፈፀመው ለበጎው ውዳሴ፣ ለመጥፎው ይቅርታ በማድረግም፣ የውይይት ባህሉን ማዳበርና የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት አሁን ካለበት ቀውስ ለመውጣት ብሎም ወደፊት በመጓዝ የተሻለ ነገ ለመመሥረት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑ ታምኖበታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች