መነሻ ገጽዜናትንታኔበትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው የባንዲራ ውዝግብ

በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው የባንዲራ ውዝግብ

የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲውለበለብ፤ የኦሮሚያ ክልል መዝሙርም እንዲዘመር ማድረግ እንደተጀመረና ቀጣይነት እንደሚኖረው እየተሰማ ነው። ድርጊቱ በትምህርት ቤቶች እንደተጀመረም አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ተማሪዎችና መምህራን ይናገራሉ። ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ አንድ መምህር፣ ‹‹ድርጊቱ ቀድሞውን ታስቦበት ተቀናጅቶ የቀረበ እንጂ እንዲሁ እንደ ወፍ ዘራሽ፤ እንደ ጎርፍ ደራሽ አይደለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጉዳዩን ቅድመ ዝግጅቶች ቀድመውታል ያሉት መምህሩ፤ ‹‹ሥራው የተጀመረው የኦሮሚያ ተወላጅ መምህራንን በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በማሰባሰብ፤ የኦሮሚያ ክልል ስርዓተ ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በማካተት ነው›› ብለዋል።

በተያያዘም፤ ኦሮምኛ ተናጋሪ መምህራንን በአንድ አካባቢ ለማሰባሰብ የታለመው ሲከናወን፣ በሌላው ትምህርት ቤት ከአቅማቸው በላይ ክፍለ ጊዜ እንዲሸፍኑ የተገደዱ መምህራን በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባሳለፍነው ሳምንት በነበራቸው የምክር ቤት ውሎ፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲሰቀል፤ መዝሙሩ እንዲዘመር የማደረግ እቅዱ ከተጀመረ መቆየቱን መስክረዋል።

ከንቲባዋ በጉዳዩ ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ‹‹እንዲያው ታሪኩን ግን መለስ ብሎ ለመናገር፤ የተጀመረው ከለውጡ በፊት ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

በጉባኤው የነበሩ የምክር ቤቱ አባላትም ድርጊቱ ለአገርም፤ ለክልልም፤ ለታዳጊዎቹም የማይጠቅም መሆኑን በመግለጽ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ ያነሷቸው ጥያቄዎችም ሙሉ ለሙሉ እንዳልተመለሱላቸው እየገለጹ ይገኛሉ።

የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው፣ ይህንኑ ጉዳይ ሲተቹና አግባብነት የሌለው ሙከራ መሆኑን በአጽንኦት ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ሙከራ
የባንዲራ ነገር ሲነሳ የትምህርት ተቋማት ላይ ውዝግቡ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፤ ሰሞኑን በትምህርት ቤት ውስጥ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ አውርዶ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን የመስቀል ሙከራ ተደርጓል።

ለአብነት ብንጠቅስ እንኳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባንዲራ ዙሪያ ተስተውሎ የነበረው ግርግር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ባንዲራን መነሻ ያደረጉ እስከሞት ድረስ የተቀጣጠሉ የተለያዩ ወዝግቦች በተለያዩ ወቅቶች መከሰታቸውም አይካድም። ታዲያ ሰሞኑንም በትምህርት ቤቶች የተስተዋለው ተመሳሳይ ውዝግብ ነው።

በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በአንድ ጎን “የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ይሰቀል” በሌላ ረድፍ ደግሞ “አይሰቀልም” በሚል የተቃርኖ ሐሳብ በተማሪዎችና በመምህራን በኩል ተከስቶ ሰንብቷል። በዚህም ባንዲራን አውርዶ እስከመርገጥ የተደረሰበት አጋጣሚ እንደነበርም ነው የተሰማው።

ጉዳዩ ከቃላት ንግግር ወደ አካላዊ ጉዳት ወደሚያደርስ የድንጋይ ውርዋሮም ደርሶ ነበር። ብጥብጡ የተከሰተው የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲሰቀልና መዝሙሩ እንዲዘመር የሚፈልጉ አካላት፣ የኢትዮጵያን አውርደው የክልልን ባንዲራ ለመስቀል ሲሞክሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን የሚቃወሙ አካላት በመነሳታቸው መሆኑን በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ይናገራሉ።

ጉዳዩ በተማሪዎች፤ በተማሪ ወላጆች፤ በመምህራን፤ በምሁራን እንዲሁም በሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በኩል ትችትን አስከትሏል። ጉዳዩ ይበልጥ ትችት የገጠመው፣ ከተማዋን ያስተዳድራሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ባለሥልጣናቱ ተስማምተውበትና አቅደውበት እየተከናወነ መሆኑ በመሰማቱ ነው።

ከኹለት ሳምንት በፊት በአቃቂ ቃሊቲ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ አውርደው የኦሮሚያ ክልልን ባንዲራ ለመስቀል በሞከሩ ተማሪዎች እና መምህራን መካከል ድንጋይ እስከ መወራወር የደረሰ አምባጓሮ ተነስቶ እንደነበር በተቋሙ የሚገኙ ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከተማሪዎች መካከል አቤል ዓለሙ (ሥሙ የተቀየረ) “የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ተሰቅሎ፤ የክልሉን መዝሙር ዘምሩ እየተባልን እየተገደድን ነው። በዚህ ምክንያትም በመምህራንና በተማሪዎች እንዲሁም በተማሪዎች መካከል ድንጋይ እስከመወራወር ተደርሶ ነበር›› ሲል ተናግሯል።

የኦሮሚያ ክልልን መዝሙር መዘመር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ እንደተነገራቸው ያስታወሰው ተማሪው፤ ‹‹እስከማውቀው ድረስ ባንዲራ ኹሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክል፤ ክልልን ሳይሆን አገርን በማዜም ኹሉንም ዜጎች በአንድነት የምናስብበት ነው። ታዲያ ይህን ወደ ጎን ትቶ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ላይ አንድን ክልል ማቀንቀን ሙሉ ኢትዮጵያን ሊገልጽ ይችላልን?›› ሲል ጥያቄውን ሰንዝሯል።

ተማሪው ጥያቄውን ያቀረበው የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን ጠልቶ ሳይሆን፤ የክልል ባንዲራ በክልሉ ከመዘመር አልፎ ሁሉም ብሔር ተሰባጥሮ ባለበት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ትምህርት ቤቶች “ይዘመር” መባሉ አዲስ ስለሆነበትና አንድ ኢትዮጵያን ከማሰብ ይልቅ፣ አንዱን ክልል ከፍ ሌላኛውን ዝቅ አድርጎ የማየት ዕድል እንደሚሰፋ በመገንዘብ መሆኑን አንስቷል።

- ይከተሉን -Social Media

እንደ ተማሪው ገለጻ ከሆነ፤ ኹሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚገኙባት በአዲስ አበባ ከተማ ኹሉን ዐቀፍ የሆነው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ቢታይ ንትርክና ውዝግብ ሊነሳ እንደማይችል ነው መረዳት የተቻለው።

የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው፣ ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ በማንሳት ብጥብጡ በተፈጠረበት ትምህርት ቤት እስከማቅናት ደርሰው የተፈጠረውን ውዝግብ እያወገዙ ይገኛሉ።

ልጃቸው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን የጠቀሱ አንድ አባት (ሥማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም) ‹‹ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት የምንልከው ኢትዮጵያን ተምረው ኢትዮጵያን እንዲዘምሩ፤ ዛሬ በአንድነት የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርገው ነገም በአንድነት የኢትዮጵያን ችግር ዝቅ እንዲያደርጉ ነው። እንጂ በአገር ፈንታ አንድን ክልል እንዲያቀነቅኑ አይደለም። አንድን ክልል ያቀነቀነ ተማሪ፤ አንድን ኢትዮጵያ ሊያስብና ሊታደግ ይችል ዘንድ አይሳካለትም›› ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

መንግሥትም ይህ ተሰውሮበት ሳይሆን የለየለት አድሎ እየፈጸመ ነው ያሉት የተማሪው ወላጅ፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ውዝግብ ይበቃታልና የሰሞኑን የባንዲራ ጉዳይ የሚመለከተው አካል ሁሉ ቆም ብሎ ሊያስብበትና ማስተካከያ ሊሰጥበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ትውስታ
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከኹሉም አገራት ቀዳሚ እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና ከነገሥታቱ ጀምሮ አሁን እስካለው የኢትዮጵያ መንግሥት ድረስ፤ የባንዲራው ዓርማ ለስምንት ጊዜ እየተቀያየረ እንደመጣም አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ውዝግቡ እየተስፋፋ የመጣው በተለይም ሶሻሊዝም ከመጣ በኋላ ነው የሚል ዕይታ አለ።

ሠንደቅ ዓላማን መሠረት ያደረጉ ውዝግቦች ከተከሰቱ ዋል አደር ቢሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጉዳዩ እየከረረ የመጣ ይመስላል። ከዚህ በፊት የነበሩት ውዝግቦች በየወቅቱ የሚደረጉ የዓርማ ለውጦች ናቸው።

ውዝግብ ከሚያስነሱት ምክንያቶች አንዱ፣ የአገር መሪዎች ከመቀየር ስር በስር ተከትሎ የሚደረገው የዓርማ ለውጥ እንደነበር እሙን ነው። ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የሠንደቅ ዓላማ ታሪክ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች የታሪክ ምሁራን በአይረሴ ንግግራቸው ሲገልጹ ኖረዋል። በተለያዩ ወቅቶች የሠንደቅ ዓላማ ታሪክ ሲወሳ፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ እስከ 1890ዎቹ አጋማሽ ድረስ ወጥነት እንዳልነበረው በተደጋጋሚ ተነግሯል።

በየወቅቱ ከሚደረጉ የዓርማ ለውጦች በፊት የሠንደቅ ዓላማ የቀለም ለውጥ እንደነበርም መዛግብት ያስረዳሉ። ይህም እስከ ዘውዳዊው አገዛዝ ድረስ የነበረ ሲሆን፤ የደርግ መንግሥት ከተቀየረ በኋላ በተተካው መንግሥት ግን በሕገ መንግሥቱ እውቅና ተሰጥቶት የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእኩልነት፤ ባህል፤ ጀግንነት የሚንባጸረቅበት ይሁን ተብሏል።

- ይከተሉን -Social Media

ይልቁንም ከደርግ መንግሥት መውደቅ ወዲህ ውዝግብ እየተነሳ የመጣው በየጊዜው በሚደረጉ የዓርማ ለውጦች ላይ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ አሁን አሁን ግን ባንዲራን በመስቀል ቦታን እስከማካለል የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደተገባ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።

ከዚህ ቀደም በርካቶችን ሲያጎራብጥ የኖረው ጉዳይ በክልል ባንዲራዎች የሚስተዋለው ችግር ሳይሆን የዓርማ ለውጥ ነበር። ለአብነትም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ዓርማ የሌለው ልሙጡ እንደሆነ በማንሳት የኮከቡ ዓርማ አያስፈልግም የሚሉ ጥያቄዎች ተጠቃሽ ናቸው። ይህንኑ ተንተርሰው በመጡ ክልከላዎችም ከመታሰር እስከ ሞት ድረስ የተደረሰበት አጋጣሚም በርካታ ነው።

ከቅርቡ ብንነሳ እንኳ በ2014 የጥምቀት በዓል ዓርማ የሌለው ባንዲራ በያዙ ሰዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት እንዳደረሱባቸው ይታወቃል። ታዲያ ይኸው የዓርማ ለውጥ እስከ አሁን ድረስ ብዙዎችን የሚያሟግት የፖለቲካ አውድ የሆነ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በትምህርት ቤቶች የአንድ ክልል ባንዲራ ተሰቅሎ የአንድ ክልል መዝሙር ይዘመር የሚባልበት ጊዜ ተደርሷል።

ሕጉ ምን አለ?
ሰሞኑን እየተሰማ ያለውን የኦሮሚያ ባንዲራና መዝሙር በተመለከተ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገውን አንቀጽ በማንሳት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሕገ መንግሥቱ ሠንደቅ ዓላማ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት፤ ባህል አርበኝነት እንደሚገልጽ ይደነግጋል የሚሉት የሕግ አማካሪ ብርሃኑ ሰማው ናቸው። አዲስ ማለዳ ለሕግ ባለሙያው ታዲያ ኹሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተሰባጥረው በሚኖሩባት ከተማ ትምህርት ቤቶች የአንድ ክልል ባንዲራን ማውለብለብና መዘመር ኹሉንም ብሔር ሊገልጽ ይችላል ወይ? ስትል ላነሳችው ጥያቄ አይችልም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የሕግ አማካሪው አዲስ አበባ የኹሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤ የአንድ ክልል መዝሙር ሲዘመር ሌሎቹ ክልሎችም ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም ብለዋል። ሁልጊዜ የኹሉንም ክልል ባንዲራ አውለብልቦ የኹሉንም ክልል መዝሙር ማዜም ደግሞ የማይቻል ነው የሚሉት ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ተደርጎ የኢትዮጵያ መዝሙር ቢዘመር ግን ምንም ዓይነት ቅሬታ አይነሳም በማለት ነው የግል አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።

በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ተሰቅሎ መዝሙሩ ይዘመር የሚል ሕግ ግን በሕገ መንግሥቱ እንዳልተቀመጠ ብርሃኑ ተናግረዋል። ሲጀመርም መሪዎች የዓርማ ለውጥ፤ የባንዲራ ክፍፍል አደረጉ እንጂ የሕዝቡ ሠንደቅ ዓላማ አንድና አንድ አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም፣ ሕግ እንኳን ቢኖር ሕዝብ የማይቀበለው ከሆነና ኹሉን የማያካትት ሆኖ ቅሬታ ካሳደረ መንግሥት ሥልጣን በእጁ ስለሆነ ማስገደድ አይችልም። ይህ የሚሆነውም መንግሥት የኹሉንም ማኅበረሰብ ፍላጎት በእኩል የሚያሟላ እንጂ አንዱን ደግፎ አንዱን የሚገፋ ስላልሆነ ነው ባይ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

ፖለቲካዊ አንድምታ
የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰቀልና መዝሙሩ እንደሚዘመር የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የከተማው ትምህርት ቢሮ ተስማምተውበትና አስበውበት እየተከናወነ መሆኑ በከተማዋ ምክር ቤት ውሎ በገሀድ ተሰምቷል።

ከንቲባዋም ‹‹የተጀመረው በአራት ትምህርት ቤቶች ነው። የተጀመረበት ምክንያትም የኦሮምኛ ማስተማሪያ ከሪኩለም ስለሌላት አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከኦሮሚያ ወሰደ›› ካሉ በኋላ፤ ‹‹…በነዛ ትምህርት ቤቶችም ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የኦሮሚያ መዝሙር ይዘመራል፤ የኦሮሚያ ባንዲራ ይሰቀላል የሚል አስገዳች አንቀጽ አለ›› ማለታቸው ይታወቃል።

የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው፣ የኦሮሚያ ባንዲራና መዝሙርን በተመለከተ እየተስተዋለ ባለው ውዝግብ ላይ ሙያዊ አስተያየታውን ሲሰጡ ‹‹ድርጊቱ ብሔር ተኮር የሆነ ፖለቲካዊ ይዘት›› እንዳለው ነው ያብራሩት።

‹‹ቋንቋን ለማስተማር በሚል ንግግር ተሸፋፈነ እንጂ ድርጊቱ ብሔር ተኮረ የሆነ ፖለቲካዊ ይዘት አለው። ነገሩ አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ አይነት ነው›› የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ አያሌው ናቸው።

ተንታኙ፣ ተማሪዎች የኦሮምኛ ቋንቋ ማወቅ የሚችሉት ግዴታ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ተሰቅሎ የኦሮሚያ መዝሙር ስለዘመሩ ሳይሆን፤ ትምህርቱን ሲማሩ ነው ብለዋል። ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን ማውለብለብና መዝሙሩን መዘመር ቋንቋን ከመማር ጋር ምን አገናኘው? አንድነትን የሚሰብከውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በመስቀልና በመዘመር ኹሉንም ቋንቋ መማር አይቻልምን? የሚል ጥያቄም አንስተዋል።

ከንቲባዋ ‹ዋናው ነገር አዲስ አበባን የሚገልጽ የአዲስ አበባ መዝሙር በኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማሩ ስለሆነ፤ በኦሮምኛ ዝመራው ይቀጥላል።› ባሉት ንግግር ላይ አስተያየት የሰጡት አብዱ፤ አዲስ አበባን የግል የማድረግና የመገንጠል ሴራ የተሸረበበት ይመስላል የሚል አንድምታ ነው ያስቀመጡት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከሪኩለምን በተመለከተም፣ በርካቶች ትችት ሲሰጡ ሰንብተዋል። የፖለቲካ ተንታኙ በበኩላቸው፣ ‹‹ለኦሮምኛ መዝሙር እና ባንዲራ ገንጥሎ በማቀድ ስርዓተ ትምህርት መንደፍ በራሱ አግባብነት የሌለው፤ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል ብቻ አድርጎ ማሰብ ነው›› ብለዋል።

ባለሙያዎቹ እየሰነዘሩት ያለው አስተያየት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ጨምሮ ነው። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ‹በአጠቃላይ በትምህርት ቤቶች ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የኦሮምኛ መዝሙር ይዘመራል። የኦሮምኛ ባንዲራ ይሰቀላል› ካለ፤ ቢሮው የአዲስ አበባ ከተማ ነው ወይስ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ? የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል።

በመሆኑም፣ ይህን ዓይነት አስተሳሰብ በወቅቱ ከተጋረጡ ክስተቶች ላይ ተጨማሪ ችግር ይሆናል የሚል ስጋት ማሳደሩን ባለሙያዎች ደጋግመው እየተናገሩ ነው።

ተማሪዎች በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከኹሉም ቀድሞ መዘመርና ከፍ ማለት ያለበት የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ መሆን አለበት ባይ ናቸው። የፖለቲካ ባለሙያዎችም ሐሳቡን ይጋሩታል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ እንጂ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለም ያሉት አብዱ፤ በመሆኑም እስከ አሁን እንደነበረው በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መዘመርና መሰቀል ያለበት ብሔር ብሔረሰቦችን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ነው ብለዋል።

በተያያዘም፤ ገና ለገና አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል ይደረጋል ተብሎ ተማሪዎች የአንድን ክልል ቋንቋ እንዲያውቁ የአንድን ክልል ባንዲራ መዝሙር እንዲዘምሩ መገደድ የለባቸውም ነው ያሉት።

የሕግ ባለሙያዎች፤ የፖለቲካ ተንታኞች እንዲሁም መምህራን ሠንደቅ ዓላማንና የክልል መዝሙርን በተመለከተ የተጀመረው ጅማሮ አግባብነት የሌለው መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች