ዳግም ያገረሸው የጦርነት ድባብ

0
2052

ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ በከባድ ፈተና እየታመሰች ያለችበት ወቅት ላይ ነን። ነገሮችም እያደር በክፋት እየበረቱ ሲሄዱ፣ ይህም ያልፋል ከሚለው የተስፋ ዕይታ የወጡ ብዙዎች ‹ከዚህ በኋላ ምን ሊፈጠር ነው?› የሚል መጠራጠር ውስጥ ገብተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸም አሰቃቂ ጭፍጨፋና ጅምላ ግድያ እንዲሁም ሄድ መለስ የሚለው የእርስ በእርስ ግጭት፤ ሁሉም የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት አብዛቶ የፈተነ፣ በምድር ኑሯቸውንም በስጋት መልቶ መከራ ያበዛ ሆኗል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰው ጦርነት
በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ጥቅምት 24/2013 ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት የጦርነቱ መነሻ ነበር። ይህን ተከትሎም መንግሥት ባወጀው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” የትግራይ ክልል ሕዝብ ለስምንት ወራት በጦርነት ውስጥ ቆይቷል። በመቀጠልም የሕወሓት ቡድን ከሐምሌ 2013 ጀምሮ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት አስነስቶ፤ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቶ ነበር።

ይህን ተከትሎም በአፋር ክልል በርካታ ንጹሐን ዜጎች ከመገደላቸውም በተጨማሪ ቀያቸውን ለቀው ለመፈናቀል ተገደዋል። ከዚህም አልፎ ታጣቂ ቡድኑ በርካታ የአማራ ክልል ሥፍራዎችን ተቆጣጥሮ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ደብረ ሲና ተራራ ለመጠጋት ሞክሮ ነበር።

በዚህ ቆይታውም በርካታ ንጹሐን ተገድለዋል። ከሞት ለማምለጥ የጣሩ ሰዎች ለስድስት ወራት ለመፈናቀል ተገደው ቆይተው፤ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ በመገደዱ ወደየ ቀያቸው ለመመለስ በቅተዋል። ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ከሚያደርስባቸው የአማራ ክልል ሥፍራዎች የወጣው ታህሳስ 9/2014 እንደነበር ይታወሳል።

ሕወሓት ታኅሣሥ 09/2014 ከሰዓት የኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ሳንቃን፣ ሲሪንቃን፣ ሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን የወልዲያ ከተማን፣ ሐራን፣ ጎብዬን፣ ሮቢትን እና ቆቦን ሙሉ በሙሉ ለቆ መውጣቱን በወቅቱም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጹ አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ ቤተሰቦቻቸውን በጦርነቱ የተነጠቁ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ተፈናቃዮች እርማቸውን ሳያወጡ፤ የወደመ ቤታቸውን ሳይጠግኑ ባሉበት ሁኔታ፣ ሕወሓት የተለመደ ግብሩን ለመፈጸም ዳግም በራያ ቆቦ እና በግዳን ወረዳ የድንበር ቀበሌዎች ጦርነት መቀስቀሱን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።

ታጣቂ ቡድኑ ከሳምንታት በፊት በራያ ቆቦ ቆላማው ክፍል ማለትም ዋጃ፤ ጥሙጋ፤ ዋልካ መንደር ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መሣሪያ በማቀበል በአማራ ፋኖና ሚሊሻ ታጣቂ ቡድኑን ለመመከት ቢችልም፤ ስጋቱ አሁንም ሊቀለበስ አልቻለም።

ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ በተለይም በደጋማው የአማራ ክልል አካባቢዎች (ቆቦና ግዳን ወረዳ) ሕወሓት ስትራቴጂክ ቦታዎችን እንደያዘና ማኅበረሰቡ ላይ የቀደመ የጥቃትና ዘረፋ ግብሩን እያካሄደ እንደሆነ ነው።

በአማራ ክልል የድንበር አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት የከፈተባቸው ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። ነዋሪዎቹ ከመፈናቀል ተመልስን ወደ ቤታችን ከገባንብት ቀን ጀምሮ በስጋት ውስጥ ነው ያለነው ያሉ ሲሆን፤ ጦርነቱን የሚጀመረው በክረምቱ ነው የሚለው ወሬም ቀድሞ አስፈርቷቸው እንደነበር አልደበቁም።

የዜጎች ደም መፍሰስ፤ ተገዶ መደፈር፤ መፈናቀል፤ የንብረትና መሠረተ ልማት ውድመት ዘረፋ፤ እንዲሁም ሌሎች ጦርነት የወለዳቸውን የሰላም መሰናክሎችን ለመግታት እንዳልተቻለ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸውና ፍጻሜ የራቃቸው ውዝግቦች ምስክር ናቸው።

ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ ዜጎች “ያስተዳድሩናል” ብለው በሾሟቸው ባለሥልጣናት የአስተዳደር እንከን ቤት ንብረታቸውን ተዘርፈው ቀያቸውን እንዲለቁ ከመደረጋቸውም በላይ፣ በርካቶች ደመ ከልብ እየሆኑ አቤቱታቸውን የሚቀበል አካል ማግኘት ባለመቻላቸው ጥቃቱ እንዳላቆመ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ሳትጠቅስ ቀርታ ባታውቅም፣ ዜጎቿ በጦርነት መታመስ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ታዲያ የዜጎች ሕይወት ገሸሽ እያለ ያለው፣ ወቅቱን ጠብቀው ውጊያውን መቋጨት ሲገባቸው እድሜው ሲረዝም ወደለየለት ጦርነት በመሸጋገሩ ነው።

ራሱን የለውጥ መንግሥት ብሎ የሚጠራው የብልጽግና ፓርቲ ወደ ሥልጣን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች በሰላም መደፍረስ የጀመረው የዜጎች ሰቆቃ ወደለየለት ጭፍጨፋ ተሸጋግሮ ህልፈተ ሕይወት ቀጥሏል።

የአንድ ችግር መከሰት በርካቶች እንዲጨፈጨፉ በር እየከፈተ ቢመጣም፣ “ይህን ያህል ሕዝብ ተጨፈጨፈ” ከማለት በዘለለ በመንግሥት በኩል ስር ነቀል መፍትሄ አለመወሰዱ ችግሩን ይበልጥ እንዳናረው የፖለቲካ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

“22 የቤተሰብ አባሎቼ በአንድ ቀን ተገድለዋል”
በሰሜኑ ካለው ጦርነት ባሻገር፣ በየአቅጣጫው አሰቃቂና አሳዛኝ የሆነ የንጹሐን ዜጎች ሞትና መከራ እለታዊ ዜና ከሆነ ሰነባብቷል። በወለጋ የሆነውን እናውሳ፤ አንድ አባት የሆነውንና የደረሰባቸውን አውስተዋል። በዚህም ውስጥ ንጹሐን ዜጎች ያሳለፉትን ቅንጣቱን ለመረዳት ይቻላል።
ሙሐመድ የሱፍ በኦሮሚያ ክልል ጊምቢ ወረዳ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የእድሜ ባለጸጋው ሙሐመድ አባት ከመሆን አልፈው የልጅ ልጅ ለማቀፍ እንደታደሉ ይናገራሉ። ታዲያ አብዛኛው ቤተሰባቸው በጊንቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ነበር በኅብረት የሚኖሩት።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በማንነት ላይ መሠረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች እልባት ሳይሰጣቸው ዓመታትን ቢያስቆጥሩም፣ የሙሐመድ ቤተሰቦች የጥቃቱ ዕጣ ፈንታ አልደረሰባቸውም ነበር። ነገር ግን፣ መንግሥት አመርቂ እርምጃ ባለመውሰዱ ኦነግ ሸኔ በሚያደርሰው ጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ስጋት ከተቆራኛቸው ከራርሟል።

በወለጋ የንጹሐን መገደል፤ መታገት፤ የንብረት መዘረፍ ሁሌም የሚከሰት ድርጊት ቢሆንም ሰኔ 11/2014 ግን ለሙሐመድ ከቀኖች ሁሉ የከፋ እንደሆነባቸው ደጋግመው ይተርካሉ። ሰኔ 11 የሆነውን ሲያወሱም በውሃ የማይጠፋ፤ ልብን የሚያቃጥል በእሳት የተሸረበ ሀዘን ብለው ጠርተውታል። ለምን ቢሉ፣ የሆነውን ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውሰዋል።

ታጣቂ ቡድኑ እንደተለመደው ሰዎችን በመጨፍጨፍ ጥቃት የማብረድ ሱሱን በውስጡ አዝሎ ከላይ ሰላማዊ በመምሰል ነዋሪዎቹን ምግብ እየጠያየቀና እየተመገበ ከደንቢ ዶሎ ወደ ቶሌ ቀበሌ እየተመመ ነበር።

ሁኔታውን በቅርብ ርቀት የታዘቡት አዛውንቱ ሙሐመድ፣ ታጣቂ ቡድኑ የለመደ ግብሩን በነዋሪዎች ላይ እንዳይጎስም ስጋት ቀስሮ ይዟቸው እንደነበር አንስተዋል። “የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ፣ ሙሐመድ የፈሩት መፈጸሙ አልቀረም። ቶሌ ቀበሌ ታጣቂ ቡድኑ በሚስበው ቃታ የሚወጣውን እሳት በሚቀበለው የንጹሓን የሲቃ ጩኸት ተናጋች።

“አንተ ከዚህ ሂድ። ከቤት ካገኙህ ይገድሉሃል። መቼም ሴትና ልጅ አይገድሉም።” ሙሐመድ ከቤተሰባቸው የተለገሳቸው የነፍስ አድን መልዕክት መሆኑ ነው። የእድሜ ባለጸጋው መልዕክቱን ተቀበሉ። እግራቸው ወደ ፊት ልባቸው ወደ ኋላ እየተራመደ ከበቆሎ ማሳ ተደብቀው በታጣቂ ቡድኑ ከመገደል እንዳመለጡ ያወሳሉ። በአካል ቢለያዩም ልባቸው ከቤተሰባቸው ጋር የቀረው ባለታሪኩ፣ ከቆይታ በኋላ የቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ለማየት ሲመለሱ ግን የጠበቃቸው አስደንጋጭ ክስተት ነው።

የመጀመሪያና የሦስተኛ ልጆቻቸው ከአምስት የልጅ ልጆቻቻው ጋር፤ ኹለተኛዋ ልጃቸው ከሦስት የልጅ ልጆቻቸው ጋር፤ እመጫት ልጃቸው ከኹለት የልጅ ልጆቻቸው ጋር ሌላኛዋ ሙሽራ ልጃቸውና ወጣት ሌላ ወጣት ወንድ ልጃቸው፣ እንዲሁም ከወለደች አራት ቀን ብቻ ያስቆጠረች ልጃቸው ከአራት ቀን ጨቅላ ሕጻኗ ጋር ተገድለው ነው ያገኙት።

ስድስት ልጆቻቸውንና 16 የልጅ ልጆቻቸውን በአጠቃላይ 22 የቤተሰብ አባሎቻቸውን በአንድ ቀን የተነጠቁት አዛውንቱ፣ ከ22 ቤተሰባቸው ጋር 60 ሟቾችን ብቻቸውን መቅበራቸው ሀዘናቸውን አባብሶታል። ስድስት የቆሰሉ ልጆቻቸውን እና ሰባት እናት አባት የሞቱባቸው የልጅ ልጆቻቸውን ታቅፈው በሀዘን ሰክረው የሚዋትቱት ሙሐመድ፣ ‹‹22 የቤተሰብ አባሎቼ በአንድ ቀን ተገድለዋል።›› ሲሉ ሐዘን በሰበረው አገላለጽ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የንጹሐን ጭፍጨፋ ቢቀጥልም፣ እስከ አሁን መንግሥት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳልቻለ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ባሳለፍነው ሰኔ 11/2014 በምዕራብ ወለጋ ጊንቢ ወረዳ የሚገኙ 1 ሺሕ 600 የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ መጨፍጨፋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳና ሌሎች ሥፍራዎች በርካታ ዜጎች በታጣቂዎች እየተገደሉ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፤ መንግሥት ግን እስከ አሁን ችግሩን የሚፈታ መፍትሄ መስጠት አልቻለም።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውና ለሦስተኛ ጊዜ ዳግም ያገረሸው ጦርነት ደግም ሌላኛው ከዓመት በላይ የዘለቀና እልባት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው።

የእርስ በእርስ ጦርነት እርባና ቢስ ውጤት
ችግሩ ጦርነት እንዲሁም ብሔርን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም የንጹን ዜጎች ጅምላ ግድያ ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስም ኢትዮጵያን እንደ አጃቢ ከብበው የተቀመጡ ፈተናዎች ናቸው። ያም ሳያንስ ኢትዮጵያዊያን ላለፉት በርካታ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ሲያምሳቸው እንደኖረ ጥናቶች ያሳያሉ።

ኢትዮጵያዊያን አብዛኛውን ጊዜ የእርስ በእርስ አለማግባባት የሚገጥማቸው በመሬት ይገባኛልና በግጦሽ መሬት ምክንያት ሲሆን፤ ግጦሽን በተመለከተ በአፋርና ኢሳ (ሶማሌ) ሕዝቦች መካከል፣ እንዲሁም በሶማሌና ኦሮሚያ፣ በአፋርና ሱማሌ መካከል የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ተጠቃሽ ነው።

የሦስቱ ክልል ሕዝቦች የግጦሽ መሬት ይገባኛል ጥያቄያቸው አለመግባባት ላይ ደርሶ ወደ ጥቃት ማምራቱና በርካቶች መሞታቸው አይረሳም። ለአብነት ብናነሳ እንኳ በ1998 የሶማሊያ ታጣቂዎች መኢሶ ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካቶች መሞታቸው ይነገራል።

ኢሳዎች መኢሶ ላይ ጥቃት ፈጽመው የነበረው በኦሮሞና በደርግ ወታደሮች ደርሶብናል የሚሉትን ግፍ ለማካካስ በሚል እንደነበር ይነገራል። ታዲያ ውጤቱ እርስ በእርስ መፈረካካስ፤ በዘርና ጎሳ መከፋፈልና ጥላቻ ነው የሆነው።

የግጭት ውጤቱ መፈረካከስ መሆኑን ታሪክ ባይክድም ኢትዮጵያዊያን ግን ይህን ማስተዋል ተስኖን እርስ በእርስ መናቆሩን ተያይዘነዋል። ባለንበት ወቅት በአማራና በትግራይ ክልል፤ በአፋር ክልል፤ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የተለያዩ ዞኖች በዜጎች ላይ የሚስተዋለው መገዳደልም ካለፈው ታሪክ አለመማርን አጉልቶ ያሳያል።

በመሆኑም፣ “ቀድሞ የተነገረው በግማሽ የዳነ ነው” የሚለው አባባል በኢትዮጵያዊያን አንደበት ቢለፈፍ እንጂ፣ ከንግግር የዘለለ ተግባር የተነፈገው ይመስላል።

ምን በጀ?
አሁን አሁን እየተነገረ ያለው፣ ችግሩን የሚያባብሰው ከታች ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ሳይሆን ለሥልጣን የሚጣደፉና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚወተውቱ አካላት መሆናቸው ነው።

ችግሩ ከአስተዳዳሪው እንጂ ከማኅበረሰቡ አይደለም ይላሉ፤ የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ ይማም። አብዱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ በተለይም አርሶ አደሩ አምርቶ ከማቅረብ ውጪ ወደ ፖለቲካው ያለው ዝንባሌ የሟሸሸ ነው ይላሉ።

በመሆኑም፤ ከላይ ያሉ አስተዳዳሪዎች ኃላፊነታቸውን በመወጣት የታችኛውን የማኅበረሰብ ክፍል በማገልገል ፈንታ ለፍላጎታቸው መሳካት አማራጭ እየተጠቀሙበት ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።

አንድን ሕዝብ ከሌላኛው ጋር በማጋጨት እና እንዲፋለም ማድረግ ከአስተዳዳሪ አይጠበቅም ያሉት ተንታኙ፤ ለዚህ ደግሞ ከማንም በፊት ተጠያቂው ራሱ መንግሥት ነው ብለዋል።

አንዲት አገር በሕግ የበላይነት የምትመራ ከሆነ፤ ሕጉን በበላይነት ያስተገብራል የተባለው የበላይ አካል ሕግ የሚተላለፉትን በተደጋጋሚ ዝም ብሎ መመልከቱ፣ አንድም ፈቃደኝነትን ሌላም በሕግ የበላይነት አለመመራት ነው ከማለት ውጪ ሌላ ትንታኔ ሊሰጠው አይችልም ነው ያሉት።

ተንታኙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕውሓት ቡድንን ሆነ የሸኔ ታጣቂዎችን ጠቅልላ የያዘች ኢትዮጵያ፣ በስሯ ያሉትን አፈንጋጮች መግረዝ የምትችልበት አቅም ጠፍቶ አይመስለኝም ሲሉም የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አክለውም ሲናገሩ፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በመሬት ይገባኛል ግጭት የሚያነሱት የድንብር ቦታዎችን አካለው ከፌዴራሊዝም ጋር በማስተሳሰር ነው ብለዋል። አንዳንዶች የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለአሁኑ ማንነትን መሠረት ላደረገ የእርስ በእርስ ግጭት ቀንደኛ መንስኤ መሆኑን ያምኑበታል። የዘርፉ ምሁራንም የብሔር ፌዴራሊዝም የሚለው ስርዓት ውጤቱ አሁን ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው ከሆነ ቢቀር ይሻላል ባይ ናቸው።

በሰዎች ወይም በተወሰኑ ቡድኖች መካከል አመግባባት ሲፈጠር ወቅቱን የጠበቀ መፍትሄ አለመስጠት ጦርነት እንዲፋፋም መንገድ ከፍቷል የሚሉት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ኤፍሬም ካሳው ናቸው።

ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጣሱ ሕግ የተላለፈውን አካል በወቅቱ እርማት ከመስጠት ይልቅ፣ ጉዳዩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝብን ለአደጋ ማጋለጥ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ደረጃ እንድትደርስ አድርጓታል ነው ያሉት ኤፍሬም።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሴራ አንድ ችግር ሲፈጠር የሚመለከተው አካል ችግሩ ፈጣሪውን ተከታትሎ በመያዝ በሕግ ፊት እንዲታረም ከማድረግ ይልቅ፣ በሰበቡ በርካታ ዜጎች እንዲጨፋጨፉ በር ማሳየት ነውም ብለዋል።

እንደ ኤፍሬም ገለጻ፤ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች በጦርነትና ግጭት ውስጥ እንዲመላለሱ ያደረገው ጥቅምት 24/2013 የሰሜን ዕዝ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ብቻ ሳይሆን ጥቃቱ እንዲካሄድ የተጠነሰሱ ሴራዎችና ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ የተስተዋሉ አበረታች ሁኔታዎች ናቸው።

ከዚህ በፊት ጦርነቱ ከፈጠራቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ ከነበሩ የሥነልቦና ጉዳቶችና ከሀዘን ለማገገም ፋታ ያጡ ንጹሓን ዜጎች፣ “በደረቅ አበሳ እርጥብ ይቃጠላል” እንዲሉ የሕውሓት ቡድንና የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያካሂዱት ጦርነት አምርተው ከማስረከብ ውጪ ከፖለቲካው የተፋቱ አርሶ አደሮች፤ እናቶች፤ አዛውንቶች እንዲሁም የሕጻናት የድረሱልን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለ ይመስላል ነው ያሉት። ለሦስተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰው ጦርነትም እየታመሱ ይገኛሉ።

ወተታቸውን መግበው፤ ጀርባቸውን አጉብጠው ያሳደጉ እናቶች ሊጦሩበት በሚገባቸው ወቅት ልጆቻቸውን ዳግም ለጦርነት ለመገበር ተገደዋል። የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ፣ ለዜጎች ሕይወት ዋጋና ክብር በመስጠት ብሎም አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ፤ ንጹሐን ዜጎችን ሊታደግ የሚገባ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉና ሐሳብ ያካፈሉ ሰዎች ያነሱትና ያሳሰቡት ጉዳይ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here