መረጃ የማይሰጡ የመንግሥት ተቋማት

0
1561

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ከታሰበ የመገናኛ ብዙኀን ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን የመረጃ ነጻነት ሕግን መተግበር እና ማክበር ግድ ይላል።

መገናኛ ብዙኀን በዓለም ዐቀፍም ሆነ በአገራችን ሕገ መንግሥት ለተቀመጡ መሠረታዊ ነጻነቶች እና መብቶች መከበር እንዲሁም ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የቆሙ ናቸው። ይህንንም በማመን መረጃ የማግኘት መሻታቸውን በማሟላት ረገድ መንግሥት በቀዳሚነት ኃላፊነት እንዳለበት የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ሲያነሱ ይደመጣሉ።

በየተቋማቱ ያለው መረጃ የሕዝብ ቢሆንም፣ ለሕዝብ እና ለአገር ጥቅም በሚል የመገናኛ ብዙኀን ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚገጥማቸውን ተግዳሮት በቀላሉ ጠቅሶ ማለፍ እንደማይቻልም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የመገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ማንኛውም ሕዝብ መረጃ ማግኘት ሲፈልግ ወይም ሕዝቡ ማወቅ እፈልጋለሁ ይሰጠኝ ሲል፣ መረጃውን የያዙ ኃላፊዎች እና ተቋማት የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ይህንንም የፍትህ ሚኒስቴር ከኹለት ዓመት በፊት ማስጠንቀቁ ይታወቃል። የመንግሥት ተቋማት ቀዳሚ ተልዕኮ ሕዝብን ማገልገል፣ የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ በመሆኑ፤ ሕዝብ ለሚያቀርበው ጥያቄ እና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ለሚያነሱት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ሲል ነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያስረዳው።

የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች መረጃ ሲጠይቁ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የተቋማት ኃላፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ ከኹለት ዓመት በፊት የፍትህ ሚኒስቴር ቢያሳውቅም፣ ተግባራዊ ሲደረግ አይታይም።

ከአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት መረጃ ማግኘት ያልቻሉ የግል ሚዲያ ተቋማት በተመለከተ እንዲሁም የመረጃ ነጻነት ጉዳይን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሯል።

ተቋሙ የመረጃ ነጻነት ሕግ አፈጻጸምን አስመልክቶም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎትና ከመገናኛ ብዙኀን ተወካዮች ጋር ከኹለት ሳምንት በፊት ውይይት አድርጓል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳነሱት፤ በመንግሥት አገልግሎቶችና ፕሮግራሞች ዙሪያ ዜጎች የሚፈልጉትን መረጃ በነጻነት የማግኘት መብት አላቸው።

በወቅቱ ዓለም ዐቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አገራዊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ክስተቶች ዙሪያ የተደራጀና የተተነተነ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ- መንግሥቱ የተቀመጠ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመረጃ ነጻነት ጉዳይ በሚገባው ልክ ያልተሠራበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ለማስተካከል መንግሥት በየደረጃው ካሉ የኮምዩኒኬሽን እና የሚዲያ መዋቅሮች ጋር እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የዜጎች መረጃ የማግኘት ነጻነት መከበሩ ከለውጡ ማግስት አንስቶ ለፕሬስ ነጻነት የተከፈተውን አዲስ ምዕራፍ የማገዝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ነገር ግን፣ በመረጃ ነጻነት ሥም የሚካሄዱ ግጭት ቀስቃሽ እና አገር አፍራሽ የሆኑ የትኛውንም ዓይነት የመረጃ ስርጭት በሚያወጡት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፣ የሕዝቡ የመረጃ ነጻነት የተጠበቀ እንዲሆን የቁጥጥርና ክትትል ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እስከ አሁን የመረጃ ነጻነት ሕጉ በሚጠበቀው ልክ ያልተተገበረው በሚፈለገው ልክ በቅንጅት መሥራት ባለመቻሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ተቋሙ ችግሩን ለመቅረፍ በየጊዜው ከመገናኛ ብዙኀንና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉ ጋር ምክክር ሲያደርግ የየራሳቸውን ችግሮች ሲያነሱ እንደቆዩ እና ውይይታቸውም ችግሮችን ለመቅረፍ ጭምር የሚረዳ ይሆናል ነው ያሉት።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የግል እና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማትን በመወከል የተገኙ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ሐሳብ፣ በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት እንዲሰፍን ሁሉም የሚዲያ ተቋማት የሚሳተፉበት አሰራር ሊተገበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሬዲዮ ጋዜጠኛ የሆነው ዮሐንስ አበበ ለአዲስ ማለዳ እንዳለው፣ መረጃ የሚያጋሩ የመንግሥት ተቋማት እንዳሉ ሁሉ ፍቃደኛ የማይሆኑ ተቋማትም እንዳሉ ነው።

መረጃ ላለመስጠት የተቋሙን ስልክ እያወቁ አለማንሳት፣ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ነኝ ብለው ቀጠሮ አስይዘው ሐሳብ የመቀየር እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ለጊዜው መረጃ አንሰጥም ብለው ምላሽ የሚሰጡበት አጋጣሚ እንዳለ ጋዜጠኛ ዮሐንስ ተናግሯል።

በተለይ ከወቅታዊ የፀጥታ ችግርና የአገር ጉዳይ ጋር በተያያዘ፣ ከአገራዊ ምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ ተቋማቸው መረጃ ለማግኘት የሚፈተንበት እድል ሰፊ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ተቋማቸው መረጃ ለማግኘት ከሚፈተንባቸው ተቋማት በቀዳሚነት እንደሚሰለፉም አስረድተዋል።
ኅብረተሰቡ ላይ ያለውን ማንኛውንም ችግር መንግሥት መስማት የሚችለው ከመገናኛ ብዙኀን እንደመሆኑ፤ ጥቅሙ የራሱም እንደሆነ ተገንዝቦ መንግሥት መረጃ ከማይሰጡ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ የመገናኛ ብዙኀን የመረጃ ነጻነት መቅረፍ እንዳለበት ጋዜጠኛ ዮሐንስ አመልክቷል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እንደገለጹት፣ ለመገናኛ ብዙኀን መረጃ የሚሰጡ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ በዚያውም ልክ መረጃ ለመስጠት ሚዲያዎችን የሚመርጡ እንዲሁም የማይሰጡ ጭምር አሉ ብለዋል። ለአብነትም መገናኛ ብዙኀን ጥያቄ የሚጠይቋቸው የመንግሥት ተቋማት አብዛኛዎቹ ለመንግሥት ሚዲያዎች መስጠት የሚፈልጉ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር ለአንዳንድ የግል ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ውትወታ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ የሚሆኑ ተቋማት እንዲሁ ጋዜጠኞች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ተንተርሰው ሳይሆን በራሳቸው እና እነሱ እንዲዘገብ በሚፈልጉት መንገድ ለመናገር ነው ፈቃደኛ የሚሆኑት ብለዋል። ይህ ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ እና መገናኛ ብዙኀንም ሆነ ኅብረተሰቡ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተፈለገው አግባብ ምላሽ ላለማግኘታቸው ምክንያት በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ባይ ናቸው።

በተጨማሪም የግል የመገናኛ ብዙኀንን ተሳታፊ ያለማድረግ ሁኔታ እንዳለ እና ለዚህ ደግሞ በዘላቂነት ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት እና ሌሎች ባለድርሻ ከሆኑ የመንግሥት አካላት ጋር ተነጋግረው፣ ጉዳዩ መፍትሄ የሚያገኝበት ሂደት በዘላቂነት እንዲታሰብና ችግሩ እንዲቀረፍ ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ሌላው ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስተያየት የሰጠው የህትመት ጋዜጠኛ እንደሚለው፣ ለአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ምላሽ ለማግኘት በተቋም ደረጃ ተቸግረናል ባይ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ገንዘብ ሚኒስትር፣ ብሔራዊ ባንክ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለአብነት በዋናነት መጥቀስ እንደሚቻል ጋዜጠኛው አስረድቷል።

‹‹የመረጃ ነጻነት እንኳን ለመገናኛ ብዙኀን ይቅርና ለማንኛውም ግለሰብ የተሰጠ መብት ነው። መረጃ የማግኘት መብት ለሁሉም እንዳለ በሕግም ሰፍሮ ቢገኝም፣ ተግባራዊነቱ ግን ሊታሰብበት ይገባል›› ብሏል። በተለይ የግል መገናኛ ብዙኀን መረጃ በአግባቡ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲስተካከል መንግሥት ከተቋማት ጋር ተነጋግሮ ችግሮችን በመፍታት ረገድ እንዲሠራም ጋዜጠኛው ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ማኅበር ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ የመረጃ ነጻነት በአዋጅ ቢኖርም፣ በተግባር ግን ሲዳሰስ መረጃ የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ በተለይ ደግሞ ለግል መገናኛ ብዙኀን መረጃ የማይሰጡ የመንግሥት ተቋማት እንዳሉም የማይካድ ሀቅ ነው ብለዋል። ከዚህ አንፃር አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትን ጥያቄ ጠይቀው ምላሽ ማግኘት ያልቻሉ ጋዜጠኞች፣ በመረጃው ላይ ተደግፈን የሚመለከተው አካል ለመጠየቅ ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም ብለው የሚዘግቡበት እድል እንዳለ ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

ጋዜጠኞች ላጠናቀርነው መረጃ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ብለው ማለፍ ብቻ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ጋዜጠኞች ከዚህ በተጨማሪ መረጃ የማይሰጡ የመንግሥት ተቋማት ላይ ለምን መረጃ ሊሰጡ እንዳልቻሉ እና ሊያጋሩ ያልቻሉበትን ምክንያት በሕግ አጣቅሰው ራሱን የቻለ ኘሮግራሞችን በመሥራት ኅብረተሰቡም ሆነ ለማንኛውም ባለድርሻ አካላት በሰፊው ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኘሬዝዳንቱ አክለውም፣ በተለይ የግል የመገናኛ ብዙኀን በቀጣይም ቢሆን፣ መረጃ ሊያገኙ የሚችሉበት እድል ጠባብ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሰውን ሂደት ቢጠቀሙ እመክራለሁ ብለዋል።

በተጨማሪ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተቋማት የኮምዩኒኬሽን ቢሮዎች ጋር በመነጋገር ችግሩ እልባት የሚያገኝበትን ሁኔታ በመፍታት መገናኛ ብዙኀን የመረጃ ነጻነታቸው እንዲቀረፍላቸው መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት መረጃ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ሕጉ ቢያዝም፣ ተግባራዊ አለመሆኑ እሙን ነው ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ የማይሆኑት የመረጃውን አቅጣጫ ቀይረው ሊዘገቡ ይችላሉ ከሚል አጥጋቢ ያልሆነ ስጋት በመነሳት ነው ይላሉ።

የመገናኛ ብዙኀን የነጻነት ሕግ የዓለም ዐቀፉን ሕጎች ለመጠበቅ ብቻ የወጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን አለመተግበሩ በእውነታ ታይቷል ባይ ናቸው።

ይህ አሠራር ተገቢነት የጎደለው ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ የመገናኛ ብዙኅን ተቋሙን ጠቅሰው መረጃ ማግኘት አልቻልንም ብለው ከመዘገባቸው ባለፈ በመረጃ እጥረት ሳቢያ የተረጋገጠ መረጃ የማያስተላልፉበትም እድል እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

የሕግ ባለሙያው አክለውም መረጃ የማይሰጡ ተቋማትን የሚከታተል አካል ካለ ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ይህ ደግሞ መረጃ የማይሰጡ ተቋማት እንዳሉ እየታወቀ ከበላይ አካል የሚቆጣጠራቸው እና እርምጃ የሚወስድ አካል ላይ ቸልተኝነት እንዳለ ማሳያ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ የመገናኛ ብዙኀን መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር ካስፈለገ መገናኛ ብዙኀን ራሳቸውን የቻሉ እና ተጠያቂነትን ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮግራሞች በመሥራት ረገድ አቅማቸውን አጎልብተው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መረጃ የማይሰጡ ተቋማትን ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here