ከጥይት ከለላ አጥተው የፀሐይ ጥላ የታሰበላቸው ነፍሶች

0
1648

በተገባደደው ሳምንት መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለጥያቄዎች ማብራሪያ ዲስኩር ያሰሙበት ንግግራቸው በዋናነት ተጠቃሽ ነበር።

የቀረቡት ጥያቄዎች ዘርፈ ብዙ የሆኑ የአገሪቷን ችግሮች የዳሰሱ ቢሆንም፣ የቀረበው መልስ ላይ ግን ብዙዎች ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። ከምክር ቤቱ ሥልጣን አንስቶ ምን ማድረግ ይችላል? የሚሉ አስተያየቶች መርሓ ግብሩ ሳይጠናቀቅ ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲናፈሱ ነበር።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ ምክር ቤቱ ሥልጠና እንደሚያስፈልገው መላሽ ለጠያቂዎቹ ተናግረው ሳቅ መፈጠሩ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። እዚህ ምን ታደርጋላችሁ፣ ወለጋ አትሄዱም እያሉ እሳቸው ከዚህ ቀደም በደኅንነት ስጋት ምክንያት የቀሩበትን አካባቢ፣ ተወካዮቹ እንዲሄዱበት በአካባቢው የሞቱ የመንግሥት ባለሥልጣትን ቁጥር በተናገሩበት መድረክ መክረዋል።

በእለቱ ከተናገሩት መነጋገሪያ የሆነው ሌላው ጉዳይ፣ የኦነግ ሸኔ የዘር ጭፍጨፋን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ አሜሪካን ምሳሌ አድረገው ማነፃፀራቸው ነው። ሽብርተኛ የተባለ ቡድን የሚፈፅመውን ድርጊት፣ ግለሰቦች ዘርን መሠረት ሳያደርጉ ከሚያካሂደት ተግባር ጋር (የሽብር ሊባል ቢችልም) ቁጥርን መሠረት አድርገው ማስቀመጣቸው የእኛ አነሰ ለማለትና እንደነሱ ሲበዛ ነው የሚያሳስበው ለማለት አስበው ይሆን በሚል አግራሞታቸውን ያሰሙ ነበሩ።

አንድ ዓይነት ዓላማና አቅም ያላቸው የተደራጁ ቡድኖች ቢሆኑ እንኳን ዘርና ሐይማኖትን እያነፃጸሩ አልሻባብና ቦኮሃራምን ማንሳታቸው ሳያንስ፣ ራሳቸውን ስለሚያጠፉ ሰዎች ማንሳታቸው የተጨፈጨፉት ጋር በምን ለማገናኘት አስበው ነው ሲሉ የተናገሩት ትችት አሰንዝሮባቸዋል።

ከሁሉም ንግግራቸው የብዙዎችን ትኩረት የሳበው፣ ጭፍጨፋው ተስፋፍቶ እየተካሄደ ችግኝ መትከል ላይ መንግሥት አተኮረ ስለመባሉ የመለሱት ላይ ነው። “ሰው እየሞተ የሞተበት ቦታ ችግኝ እንተክላለን፣ ቢያንስ አስከሬኑ ጥላ እንዲኖረው” ብለው ቃል በቃል የመለሱትና በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጭምር ተቀንጭቦ የቀረበው ንግግራቸው ላይ በርካቶች አስተያየታቸውን በሀዘኔታ አሰምተዋል።

ሰው ከሞተ በኋላ ጥላ ምን ሊሠራለት ነው ከሚል አስተያየት ጀምሮ በርካታ ምሬት አዘል አስተያየቶች እንደሚያሳዩት፣ ምላሹ በሟቾችና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንደማሾፍ እንደተቆጠረ የሚያመላክት ነው። የአገር መከላከያ እንደሥሙ የዜጎችን ሕይወት ከጥቃት መከላከል ሥራው ቢሆንም፣ መንግሥት ከጥይትም ሆነ ከካራ ሊከላከልለት ያልቻለውን ሰውነት፣ ተገድሎ አስከሬን ከሆነ በኋላ ፀሐይ እንዳይመታው ችግኞቹ አድገው ጥላ ይሆኑታል መባሉ በሌላም ተተርጉሟል።

አድገው ዛፍ እስኪሆኑ ግድያው እንደሚቀጥል መጠቆማቸው ነው ወይስ ሳይቋረጥ በሚቀጥለው ጭፍጨፋ አስከሬኖቹ ሳይነሱና ሳይቀበሩ ዓመታት ይነጉዳሉ ለማለት አስበው ነው በሚል ንግግራቸውን የተነተኑም ነበሩ። እንስሳትም ሆኑ ተክሎች ለሰው ልጆች በሕይወት መኖር እንዲጠቅሙ እንጂ፣ ሰው በጅምላ ተጨፍጭፎ ማዳበሪያ እንዲሆንላቸው መታሰብም አልነበረበትም በሚል አገላለጻቸውን ክፉኛ የተቹ በርካቶች ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here