መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና የመንግሥት ፍጥጫ

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና የመንግሥት ፍጥጫ

በኢትዮጵያ በተለያየ ዘመን የታዩ የሰብአዊና ተያያዥ መብት ጥሰቶች ምክንያት የተሰሙ የተማሪዎች የተቃውሞ ድምጾች ጥቂት አይደሉም። ያንን የተቃውሞ ድምጽ ተከትሎም አመጽና ትግል ተወልዶ በታሪክ የማይረሱ የፖለቲካ ለውጦች ታይተዋል። ስለዚህም ይመስላል፤ በተለያየ ጊዜ ወደ ሥልጣን ብቅ የሚሉ አመራሮች በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚኖሩ የተቃውሞ ድምጾችን ይፈራሉ፤ በፍጥነት እርምጃ ከመውሰድም ወደኋላ አይሉም።

ሰኔ 11/2014 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመውን የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋን በማስመልከት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል። ሆኖም ግን ሰልፎቹ በፀጥታ ኃይሎች ተበትነዋል፣ ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎቹም ጥቂት እንዳልሆኑ ታውቋል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ፣ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በመንግሥት መካከል የሚታየውን ፍጥጫ እና የነበሩ ክስተቶችን በማውሳት የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ነገር አድርጎታል።

በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚፈጠሩ ችግሮች ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተቃውሞ በር ሲከፍቱ ይስተዋላል። እስከ አሁን የተሰሙ የተማሪ ተቋውሞዎች በብዛት የተሰሙት በመንግሥት ላይ ሲሆን፣ በየጊዜው ችግሮች ሲፈጠሩ ተማሪዎች መንግሥትንና የድርጊቱን ፈጻሚ የሚያወግዙበትና የሚቃወሙበት ድምጽ ያሰማሉ።

ሰኔ 11/2014 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ በመቃወም የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ተቃውሞ እንደ ማንኛውም ሰላማዊ ተቃውሞ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ መሞከራቸው፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለኃይል እርምጃና እስር ተዳርገዋል።

ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲያቸው ድርጊቱን በመቃወም ባሰሙት የተቃውሞ ሰልፍ፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ድብደባና እስር ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተማሪዎችን ሰላማዊ ሰልፍና የተቃውሞ ደምጽ ለማፈን በሚመስል መልኩ ተማሪዎችን በኃይል ለመበተን ሲሞክሩም ታይተዋል።

የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በምዕራብ ወለጋ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ ለማውገዝ ድምጻቸውን ለማሰማት ሰኔ 18/2014 ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የደረሰባቸውን የኃይል እርምጃና እስር አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ተመልክታለች። በእለቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ስድስት ኪሎ ከሚገኘው ከዋናው ግቢና አምስት ኪሎ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩሊቲ ተማሪዎች ዶርም ተሰባስበው በጠዋት ነበር በሰላማዊ ሰልፍ ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩት።

በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙ ተማሪዎች የንጹሐኑን ግድያ የሚያወግዙና መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮችን እያሰሙ፣ ወደ አራት ኪሎ እያመሩ አምስት ኪሎ እስከሚደርሱ ድረስ በፌዴራል ፖሊስ ተከበው ነበር። ተማሪዎችን የከበበው ፌዴራል ፖሊስ ተማሪዎች አምስት ኪሎ ሲደርሱ በኃይል ለመበተን ባደረገው ሙከራ በተማሪዎች ላይ ደብደባ ተፈጽሟል። በሰዓቱ አምስት ኪሎ የነበረው የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ፣ ፖሊስ ተማሪዎችን ከቦ በፈጸመው ድብደባ የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸውና ደም የፈሰሳቸው ተማሪዎችን ተመልክቷል።

ፌዴራል ፖሊስ የተማሪዎችን ሰላማዊ ሰልፍ ለመበተን በተጠቀመው የኃይል እርምጃ፣ ከፖሊስ ድብደባ ለማምለጥ የሞከሩ ተማሪዎች በሰልፉ ውስጥ ሲሯሯጡ የመውደቅና የመረጋገጥ ሁኔታ እንደነበርም የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ ተመልክቷል። ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን በተጠቀመው የኃይል እርምጃ ትርምስ፣ አምስት ኪሎ የሚገኘው የሳይንስ ፋክልቲ ተማሪዎች መኖሪያ ሕንጻ በር ላይ በሰልፉ የተሳተፉ ተማሪዎች ጫማ፣ አልባሳትና አልፎ አልፎ የሚታይ ደም ፖሊስ ሰልፉን በኃይል ከበተነ በኋላ የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ ተመልክቷል።

የተማሪዎችን ሰልፍ በኃይል የበተነው ፖሊስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎችን ማሰሩም ተሰምቷል። የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ፖሊስ በተማሪዎች ላይ ከፈጸመው ደብደባ በተጨማሪ ኹለት ተማሪዎችን በፖሊስ ተከበው ሲወሰዱ ተመልክቷል።

በኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ ለማውገዝ አደባባይ የወጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከደረሰባቸው ደብደባ በተጨማሪ፣ ከሰልፉ በኋላ ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸውና ሰላማዊ ሰልፉ ከተበነ በኋላ የታሰሩ ተማሪዎች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ግድያውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማውገዝ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች በተሳተፉበት ሰልፍ “ሞት በቃ”፣ “አማራ እየሞተ የምትበለጽግ ኢትዮጵያ የለችም” የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተጨማሪ በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ግድያ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የደብረ ማቀርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት ሙከራ አድርገዋል።

በወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የንጹሐን ዜጎች ጅምላ ግድያ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፖሊስ ተከበው የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል። በባህር ዳር ከተማሪዎች በተጨማሪ የከተማ ወጣቶች የተሳተፉበት የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋ የሚያወግዙ ሰልፎችና ተቃውሞዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ተማሪዎቹና የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ገዢውን ፓርቲና ሸኔን የሚያወግዙ ተቃውሟቸውን፤ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በግራና በቀኝ ተከበው አሰምተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባሰሙት የተቋውሞ ድምጽም፣ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ ሁኔታ በፖሊስ ሳይከበቡ ድምጻቸውን አሰምተዋል። ይሁን እንጂ ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ ተማሪዎች መታሰራቸውን የአማራ ተማሪዎች ማኅበር (አተማ) አስታውቋል።

አተማ እንደገለጸው ከሆነ፣ ሰኔ 20/2014 በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የማኅበሩ አመራሮችን ጨምሮ አምስት ተማሪዎች “ዐመጽ ቀስቅሳችኋል” በሚል ለእስር ተዳርገዋል ብሏል። ከታሰሩት የማኅበሩ አመራሮችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ የማኅበሩ አመራሮች መሆናቸውን ማኅበሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ሥማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ ከጠየቁ የማኅበሩ አመራር ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት የሞከሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ድብደባ፣ ወከባና እስር እየደረሰባቸው ነው ብለዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ግቢ ተማሪዎች እና የሕክምና ባለሙያዎች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት ቢሞክሩም በጭስ ቦንብ መታፈን፣ ተኩስ እና ድብደባ ደርሶባቸዋል ተብሏል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ ማንኛውም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የመግለጽ መብት እንዳላቸው የጠቆሙት የማኅበሩ አመራር፣ “መንግሥት የተማሪዎችን ድምጽ ለማፈን ሰልፍ በወጡ ተማሪዎች ላይ የፈጸመው እርምጃ ተገቢነት የለውም” ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግሥት ሰልፎችን በኃይል ለመበተን ከወሰደው እርምጃ በተጨማሪ፣ በጸጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይሉ በኩል ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። የኢትዮጵያ የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት መጀመራቸውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተከሰተን ችግር ምክንያት በማድረግ ሆን ብለው ግጭት ለማነሳሳት እየተንቀሳቀሱ ካሉ የሕወሓት ተላላኪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ሲል አሳስቧል።

ሕወሓት “አገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን በጦርነት ማሳካት ስላልቻለ በየቦታው ባደራጃቸውና ባስታጠቃቸው ተላላኪ ቡድኖች የጅምላ ግድያ በተልዕኮ እየፈጸመና እያስፈጸመ ይገኛል” ያለው የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ፣ የድርጊቱ ዋና ዓላማ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ተስፋ ቆርጦ እንዲነሳና ሰላም እንዲደፈርስ ለማድረግ ነው ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ተማሪዎች ማኅበር አመራር የግብረ ኃይሉን መግለጫ፣ “መንግሥት የራሱን ችግር ለመደበቅ የተማሪዎችን ሰላማዊ ተቋውሞ ጥላሸት ቀብቶ ለማስቆም የተወጠነ ነው” ይላሉ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት፣ ግብረ ኃይሉ የተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍና ተቋውሞ ለመወንጀል የተጠቀመው ስልት የተማሪዎችን ተቃውሞ ከሕወሓት ጋር ማያያዙን ነው።

“በአሸባሪው ሕወሓት ፋይናንስ የተደረጉ ሚዲያዎችን በመጠቀምና እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማደናቀፍ፣ ተማሪዎችን በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል ግጭት እንዲፈጠር ለማነሳሳት ሌት ተቀን አሸባሪዎች እየሠሩ መሆኑን ደርሼበታለሁ” ያለው የጋራ ግብረ ኃይሉ፣ ሥማቸውን ባይጠቅሳቸውም፣ “እነዚህ ሚዲያዎች ሰሞኑን ግጭት ለመቀስቀስ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያነጣጠረ ግጭት ለማስነሳት፣ አማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የኦሮሞ እና የሌሎች ብሔር ተማሪዎችን ለማጥቃት የተደራጀ የደኅንነት ቡድን ወደ አማራ ክልል ተልኳል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።” ሲል ገልጿል።

“የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከራሱ በፊት ለሕዝብ እና ለሀገር ሕይወቱን እየሰዋ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚጠብቅ ኃይል መሆኑ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ፣ የተፈጠረውን ክስተት ምክንያት በማድረግ የዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችና ማኅበረሰብ የተከሰተውን ችግር ምክንያት በማድረግ ሆን ብለው ግጭት ለማነሳሳት እየተንቀሳቀሱ ያሉ የአሸባሪው ሕዋሓት ተላላኪዎችና ቅጥረኞች መኖራቸውን በመገንዘብ፤ ከእነዚህ አሸባሪዎች ራሳችሁን በመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ” ሲል አሳስቧል።

ግብረ ኃይሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሰጠው ማሳሰቢያ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰጠሁትን ማሳሰቢያ ተላልፈው ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ አካላትን እንደማይታገስና ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃም ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን እወቁልኝ ብሏል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚያሰሟቸው ተቃውሞዎች በመንግሥት በኩል ስጋት የሚፈጥሩ ሲሆኑ፣ የለውጥ መነሻ የሚሆኑበት አጋጣሚም ይፈጠራል። ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚያነሷቸው ተቃውሞዎች ወደ ግጭት ሲያመሩም ነበር።

ምንም እንኳን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግጭት መነሻ የሚሆኑበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ ግብረ ኃይሉ ያወጣው ማስፈራሪያ አዘል መግለጫ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማስቆም ያለመ መሆኑን የአተማ አመራሩ ይገልጻሉ። እስከ አሁን በሰላማዊ ሰልፍ ድምጻቸውን ለማሰማት የሞከሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ሐሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ከመጠቀም ውጭ የጣሱት ሕግ አለመኖሩን የሚገልጹት አመራሩ፣ መንግሥት የተማሪዎችን ድምጽ ለማፈን የሚያደርገው ጥረት ሌላ ችግር እንዳይወልድ በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን መፍታት እንዳለበት ጠቁመዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ተማሪዎች በመንግሥት ላይ ተቃውሞ በሚያነሱበት ወቅት፣ በመንግሥት ላይ ጫና እንደሚፈጠር የሚገልጹት የአተማ አመራሩ፣ ተማሪዎች በመንግሥት ላይ የሚያሳድሩት ጫና የሚበረታው ድምጻቸውን ለማፈን በሚያደርገው ጥረት ነው ብለዋል። ተማሪዎች እንደ ማንኛውም ዜጋ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ሐሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውን እንዲጠቀሙ መንግሥት አለመፍቀዱ ተማሪዎችን ይበልጥ ያበሳጨ መሆኑንም አመራሩ ጠቁመዋል።

መንግሥት በተማሪዎች ተቃውሞ ሲገጥመው ቀድሞ የሚነሳው 1967ቱ የተማሪዎች አመፅ ነው። ከሰሞኑ በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች ላይ ተማሪዎች ያሰሙትን ተቃውሞ፣ ከ1967ቱ አብዮት ጋር ያያዙት አልጠፉም። መንግሥት የሚነሱበትን ችግሮች ካላስተካከለ የ67ቱ አብዮት አይቀርለትም የሚሉ ድምጾችም የሰሞኑን የተማሪዎች ተቃውሞ ተንተርሰው ተሰምተዋል።

በ1997ቱ የተማሪዎች አብዮት ከተሰሙ የተቃውሞ ድምጾች መካከል “የመንግሥት ተግባር ጭቆናና ጭቆና እስከሆነ ድረስ፣ ግድያ እስከሆነ ድረስ፣ ደም ማፍሰስ እስከሆነ ድረስ፣ የሕዝብ ብሶት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየደረጀ የሚሄድ አብዮታዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ልትጠራጠሩት አይገባም። ጭቆና እስካለ ድረስ የሕዝብ ትግል አይቀርም” የሚሉ ነበሩ።

የተማሪዎችንና የመንግሥትን ሰልፍ እናደርጋለን አታደርጉም ፍጥጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰኔ 22/2014 ባወጣው መግለጫ፣ “መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በአግባቡ ያክብር” ሲል ጠይቋል።

ኢሰመጉ በመግለጫው በምዕራብ ወለጋ ሰኔ 11/2014 በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ በማውገዝ፣ ሰኔ 18/2014 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሰኔ 20/2014 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምናና ጤና ሳይንስ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፎችን ያደረጉ ቢሆንም፣ ሰልፎቹን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስንና ኃይልን በመጠቀም እንደበተኑት እና በኹለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በነበሩ ሰልፎች ላይ የተደበደቡ እና የታሰሩ ተማሪዎች እንደሚገኙ ካሰባሰብኩት መረጃ ተረድቻለሁ ብሏል።

ኢሰመጉ በመግለጫው መንግሥት የዜጎችን የመሰብሰብ መብት ማለትም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ድብደባ እና እንግልት የፈጸሙ አካላትን ለሕግ በማቅረብ ተጠያቂ እንዲያደርግ እና በጸጥታ አካላት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባሮችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣ በዚህ ሰልፍ ምክንያት ታስረው የሚገኙ ሰዎችን የአካል ነጻነታቸውን እንዲያከብር እንዲሁም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ማንኛውም ሰው ሐሳብን የመግለጽና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳለው ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም ዐቀፍ የሕግ ድንጋጌዎችና፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በግልጽ ያስቀምጡታል።

ሰኔ 11/2014 በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ መንደሮች ውስጥ ንጹሐን ጨቅላዎች፣ ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋዊያን የአማራ ብሔር ተወላጆች ማንነታቸው ተለይቶ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ውግዘት እና ተቃውሞ ያስከተለው እና እያስከተለ ያለውን የጅምላ ግድያ የፈፀሙት፣ መከላከል ሲገባቸው ያላደረጉት እና አካባቢውን የሚያስተዳድሩት ለሕግ ቀርበው ፍትሕ እንዲገኝ በብዙዎች ዘንድ እየተጠየቀ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ወለጋ ውስጥ በተመሳሳይ ማንነት ተለይቶ የጅምላ ግድያ እና ጭፍጨፋ ሲፈጸም ያለፈው ሳምንት የመጀመሪያ አለመሆኑ፣ መንግሥት አንድም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና መፍትሔ እንዲገኝ አልፈለገም አልያም በቸልታ ነገሮችን ከማለፍ ባሻገር አካባቢውን ከታጣቂዎች ጥቃት መጠበቅ አልቻለም በሚል ከብዙ አካላት ትችት እንዲቀርብበት አድርጓል።

ዓለም ዐቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች ቃል ኪዳን ሠነድ አንቀጽ 21 ላይ እንደደነገገው፣ ሰዎች ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳላቸው እና ለብሔራዊ ጸጥታና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጥቅም ወይም የሕዝብን ጤናና ሥነ ምግባር ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብቶችና ነጻነቶች ለማስከበር ከሚያስፈልገውና በሕግ ከተደነገገው በቀር በዚህ መብት ላይ ምንም ገደብ እንደማይደረግ አስቀምጧል።

በሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ላይ የወጣው የአፍሪካ ቻርተር በአንቀጽ 11 ላይ ሁሉም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን የመሰብሰብ መብት እንዳለው እና ይህ መብት ሊገደብ የሚችለው በሕግ አግባብ በተደነገገው መሠረት ብቻ ለብሔራዊ ጸጥታ፣ ደኅንነት፣ ጤና፣ ሥነ ምግባር እና ለሌሎች ነጻነቶች እና መብቶች ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 30 ላይ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትንና አቤቱታ የማቅረብ መብት በማለት ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳለው ይደነግጋል። እነዚህ ዓለም ዐቀፍ የሕግ ድንጋጌዎችና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በግልጽ ያስቀመጠው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የሚያመላክቱ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘት፣ ሰልፍን በኃይል የመበተን ሁኔታዎች ያመላክታሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች