ጥቂት ስለ ዐጀሚ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል በወር ኹለት ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያያ መድረክ ያዘጋጃል። ባሳለፍነው  ሰኔ 18/ 2014 ታድያ በዚሁ መድረክ ላይ ‹ዐጀሚ ሥነጽሑፍ በኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ ነበር። በመድረኩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዐረብኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ሐሰን ሙሐመድ (የPhd ዕጩ) ገለጻ አድርገዋል።

ዐጀሚ ከሚለው ቃል በኋላ ‹ሥነጽሑፍ› የሚለው ቃል ባይኖር፣ ዐጀሚ ምንድን ነው ቢባል ብዙ ሰው እርግጠኛ ሆኖ ለመገመት እንኳ ሊቸገር ይችላል። በእርግጥስ ዐጀሚ ምንድን ነው? አዲስ ማለዳም ይህን ለማወቅ በእለቱ ከጳውሎስ ሆስፒታል አልፎ ካለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ጉለሌ ቅርንጫፍ) ገባ ብሎ ወደሚገኘው፣ የቀድሞ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መኖሪያ ቤትና አሁን የሳይንስ አካዳሚ ግቢ አቀናች። ከመድረኩ የሰማችውን ልታካፍላችሁ እነሆ፤

ዐጀሚ?
ዐጀሚ ቃሉ አረብኛ ነው በማለት ጀመሩ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዐረብኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ሐሰን ሙሐመድ።

ዐጀሚ የሚለው ቃል አሁን ላይ በአረብኛ ቋንቋ የተጻፉ ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጥራት የሚያገለግል ነው። በቀደመው ዘመን ግን ዐጀሚ ሲባል የነበረው መረዳት፣ ግልጽ ያልሆነ ንግግር ወይም ለመረዳት የማይቻል አረብኛ ወይም ደግሞ አረብ የሆኑ ሰዎች አረብ ያልሆኑ ሰዎችን የሚገልጹበት ቃል ነበር።

ነገሩ የተለወጠው ፐርሺያኖች ወደ እስልምና ከገቡ በኋላ ነው። ፐርሽያኖቹ ሀይማኖቱን ለመረዳትና ለማስተማር እንዲያግዛቸው የራሳቸውን ቋንቋ በአረብኛ ወይም አረብኛ ፊደልን በመጠቀም መጻፍ ጀመሩ። ይሄኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ዐጀሚ የሚለው ቃል አሁን ያለውን ትርጉም ያገኘው። ታድያ ፐርሽያኖች ብቻ ሳይሆን በእነርሱ አቅራቢያና ዙሪያ ያሉ ማኅበረሰቦችም ዐጀሚ መጠቀም ጀመሩ።

የዐጀሚ እድገት ከዛ በኋላ ቀጠለ። ስፔን በእስልምና ስር በነበረች ጊዜም፣ የራሷ ቋንቋ ስለነበራት፣ ዐጀሚ ተጠቅማለች። ታድያ ዐጀሚ ሳይሆን ‹ዐልጃማይዶ› ብለው ይጠሩት እንደነበር ሐሰን ጠቅሰዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በስፔን አካባቢ ያሉ ቋንቋዎች በአረብኛ ፊደል ተጽፈው የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም 800 ዓመት አካባቢ ወደኋላ ስንሄድ የምናገኘው ታሪክ ነው።

በተመሳሳይ የእስያ አገሮች ለምሳሌ ፐርሺያ፣ ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን፣ ሕንድና ሌሎችም የተለያዩ አገራት አረብኛ ፊደል ተጠቅመው የራሳቸውን ቋንቋ ጽፈዋል። ከ1924 በፊትም ኦቶማን ቱርክ የአረብኛ ፊደል ተጠቅመው የራሳቸውን ቋንቋ ይጽፉ እንደነበር ሐሰን ታሪክ አጣቅሰው አስረድተዋል።

ዐጀሚ በአፍሪካም ተሰራጭቷል። ከሰሀራ በታች ባሉ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ብዙ ቋንቋዎች ዐጀሚን ሲጠቀሙት ነበር።
ይህን መሠረት አድርጎ ነው ዐጀሚ የሚለው ቃል አረብኛ ፊደልን ተጠቅመው ሌሎች ቋንቋዎችን የመጻፍ ወይም የመዘገብ ልምድ የሚሰየምበት ቃል የሆነው።

የዐጀሚ እድገት
የዐረብኛ ቋንቋ መምህሩ ሐሰን በጉዳዩ ላይ በጥናት የደረሱበትንና የሚያውቁትን ሲያስረዱ፤ የዐጀሚ እድገትን በሚመለከት የነበሩ ሂደቶችን አውስተዋል። በዛም እንዳሉት፣ አረብኛ ፊደልን ተጠቅሞ ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጻፍ ወይም ዐጀሚን ለመጠቀም በፊደሎቹ ላይ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ማለቱ አልቀረም።ምክንያቱም የተወሰኑ የአረብኛ ድምጾች የተለያዩ ቋንቋዎች ውስጥ የሉም፤ የተለያዩ ቋንቋዎች ውስጥ ያሉ ድምጾችም አረብኛ ውስጥ የሉም። እነሱን ለማካካስ የአረብኛ ፊደላት ላይ የተለየ ጭማሪ ወይም ማሻሻያ ተደርጎ ጥቅም ላይ ውሏል።

የዐጀሚን እድገት በሦስት ከፍለው አስቀምጠዉታል። አንደኛው ‹ኮንታክት› የሚባለው የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ይህም መጀመሪያ ከቃሉ ጋር የተደረገ ግንኙነት ነው። ይህ እንደውም አረብኛ ራሱ በደንብ መጻፍ ሳይጀመር በፊት የነበረ ነው ብለዋል። እነዚህም በአረብኛ የሚጻፉ የቦታ ሥሞች፣ የግለሰብ ሥሞችና የመሳሰሉት ናቸው። በዚህም መሠረት በአረብኛ ጽሕፈት ውስጥ የሌሎች ቋንቋዎች ቃላት ይገኛሉ።

ይህ በቃላት የሚገለጽ ደረጃ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ሰነድ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ነው። በኹለተኛው ደረጃ ከዚህ ከፍ ያለ ሆኗል። ይህም በ16ኛውና 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ የሚታመን መሆኑን ያነሱት ሐሰን፣ ይህም በምሥረታ ላይ ያለ ወይም ‹ፎርማቲቭ› እንደሚባል ጠቅሰዋል። በዚህ ደረጃ ከቃላት በዘለለ ዐጀሚ ራሱን ችሎ ይጻፍበት እንደነበር አንስተዋል።

ከዚህ በኋላ ሦስተኛው የተባለውና የዐጀሚ ጽሑፍ በጣም የተሰራጨበት የ19/20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጣ። በዚህ ጊዜም እንደልብ የሚጻፍበት፣ ይሰራጭ የነበረበትም ደረጃ መሆኑን ነው ሐሰን ያስረዱት።

ዐጀሚ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ውስጥ በዐጀሚ የተጻፉ፣ እስከ አሁን የተገኙና የታወቁ 11 ቋንቋዎች ናቸው። ከእነዚህም አብዛኞቹ ህትመት ያላያቸው ሲሆኑ፣ የሐረሪ ዐጀሚ ብቻ ግን ታትሞ ይገኛል። እንደ ሐሰን ገለጻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዐጀሚ የተጻፉ ሰነዶች በቤታቸው ያሏቸው ወይም ከቤተሰብ የወረሱ ሰዎች እያሳተሙ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ታድያ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አርጎብኛ፣ ሐረሪኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ቀቤነኛ፣ ወለንኛ፣ ጉራጊኛ እና አላቢኛ በዐጀሚ ተጽፈው የተገኙ ሰነዶች መካከል ይገኙበታል።

ዐጀሚ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ መች ነው መዘውተር የተጀመረው ለሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ እንደሌለ ሐሰን አስረድተዋል። ነገር ግን አንዳንዶች ከ300 ዓመት በፊት ነው ሲሉ፣ ‹የለም! ከ500 ዓመት በፊት የተጻፈ ሰነድ እኛ ጋር አለ› ብለው እድሜው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

በኢትዮጵያም ጊዜው በትክክል ባይታወቅም፣ በዐጀሚ የተጻፈና ረጅም እድሜ እንዳለው የሚታወቀው ሐረር የተገኘው የሐረሪ ዐጀሚ ነው። ቀደምት ተብሎ የሚጠቀሰውም በሼኽ አብዱልመሊክ የተገጠመ 542 ስንኞች የያዘ (ከአሊፍ እስከ ያ የተደራጁ ስንኞች ያሉት) መጽሐፍ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ታድያ በዐጀሚ ተጽፈው የሚገኙ ሰነዶች ይዘታቸው ሀይማኖታዊ ብቻ እንዳልሆነ ሐሰን ገልጸዋል። ከእስልምና ሀይማኖት አስተምህሮ ከሆኑ ምክርና ተግሳጽ፣ ከቅዱስ ቁርዓንና ሐዲስ ትንታኔዎች ባሻገር፣ ዐጀሚ በተስፋፋበትና በተሰራጨበት ዘመን የተጻፉ ዓለማዊ ሰነዶችም ይገኛሉ።

እነዚህም የግለሰቦች የሕይወት ታሪክ ጨምሮ የሕግ ትምህርት፣ የንግድና አስተዳደር መዝገብ፣ አካባቢ ክስተቶችና የመሳሰሉት በዐጀሚ ተጽፈዋል። ፖለቲካና ማኅበራዊ ይዘት ያላቸው ብሶትን መግለጫ ግጥሞችም ይገኛሉ። የበሽታ መድኃኒት የሚገኝባቸው ባህላዊ ሕክምናዎች፣ የአካባቢ ወጎች እና ታሪክ ነክ ጽሑፎችም በይዘት ይካተታሉ።

ጥናቶች አሉ ወይ?
በኢትዮጵያ በቂ ጥናቶች ስላልተደረጉ ትክክለኛው መረጃ አይታወቅም እንጂ፣ ብዙ ሕዝብ ዐጀሚ ማንበብና መጻፍ እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ሐሰን ተናግረዋል። የጽሑፍ ቅርሶች የሚገኙ ቢሆንም፣ ወደ ጥናት ማዕከላት ግን በበቂ ያልተሰበሰቡና ያልተተረጎሙ ብሎም ያልተጠኑ ናቸው ብለዋል። ሙከራዎች መኖራቸውን ግን ሳያነሱ አላለፉም።

‹‹በአካዳሚው ዓለም የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች ይገኛሉ። በበቂ ሁኔታ ተጠንቷል ወይ ስንል፣ አልተዳሰሰም። ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው።›› ያሉት ሐሰን፤ አንደኛው ጥናት ያልተደረገበት ምክንያት አፍሪካ ያለው ማንበብና መጻፍ የማይችል፣ በሥነቃል ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ሕዝብ እንደሆነ መታሰቡ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያንም በተመለከተ አጥኚዎች ብዙ መዛግብት ተጽፈው በተገኙበት ግዕዝ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን በማድረጋቸው ዐጀሚን ትኩረት እንዳልሰጡት ጠቅሰው፣ በግዕዝ ጽሕፈት በሚገኙ መዛግብት ላይ የተደረጉ ጥናቶች ለኢትዮጵያ ያስገኘላትን ጥቅም ሳያወሱ አልቀሩም።

ከዚህ ባሻገር በዐጀሚ የተጻፉ መዛግብት በስርዓት አለመሰብሰብ እና በቤተ መጻሕፍት አካባቢ በብዛት አለመገኘታቸው ነው ብለዋል። ከዛም አለፍ ሲል በዐጀሚ የተጻፉትን የማንበብ ችሎታ አለመኖር እና ፍላጎትም የሌለ መሆኑ ተደማምሮ፣ በጉዳይ ላይ ብዙ ጥናት ሳይደረግ እንዲቀር አድርጓል።

በኢትዮጵያ የሐረሪ ዐጀሚ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጥሩ ተስፋ እንዳለ ነው ሐሰን የገለጹት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍልም በተለያዩ የዐጀሚ ጽሕፈቶች ላይ የተወሰኑ የተሠሩ ጥናቶች አሉ። እነዚህም ብዙ የሚባሉ ባይሆንም እንኳ እንደ ጅማሬ ግን አለ ብለዋል።

ሐሰን ዐጀሚ ወደፊት በስፋትና በምልዐት ሲታወቅ አፍሪካን የምንረዳበት ይሆናል እንዲሁም ሥልጣኔዋን ልናውቅ ያስችለናል ተብሎ እንደሚታመን ጠቅሰዋል። በዐጀሚ የተጻፉ መዛግብት የእውቀት ምንጭ የያዙ ናቸው፤ ሀይማኖታዊና ዓለማዊ ጽሑፍን የያዙ በመሆናቸውም ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች