መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናየመዝናኛ ጨዋታና የአእምሮ ብሩህነት

የመዝናኛ ጨዋታና የአእምሮ ብሩህነት

ልጅነት የመማሪያና እያወቁ የማደጊያ ወቅት ብቻ ሳይሆን የመጫወቻም እንደሆነ ይታመናል። ‹ልጆች ይጫወቱ በጊዜያቸው!› የሚለው አባባል ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ብቻ ሳይሆን፣ መጫወትም ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ሕፃናት በጨዋታ መልክ የቀለም ትምህርትን ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበራዊ ኑሮን እና አብሮ የመኖር ፀጋንም እንዲላመዱ ያስችላቸዋል።

ልጅ ሲስቅና ሲቦርቅ ደስ የማይለው ባይኖርም ለሁሉም ነገር ለከት አለው እየተባለ፣ ‹በኋላ እንዳታለቅስ ተው!› የምንባልበትን አስተዳደግ ብዙዎቻችን አልፈነዋል። ወላጆቻችንም ሆነ ማኅበረሰቡ ለመጫወቻም ሆነ ለቁምነገር ወቅትና ተገቢው ቦታ እንዳለው በደንብ አስተምረውናል። ታላላቆች ራሳቸው ጊዜ ሰጥተው እያጫወቱ የጨዋታንም ሆነ የመዝናኛን ጣዕምና ጥቅም ገና ከትንሽነታችን እንድናውቀው አስችለውናል።

ሕፃናት የሚጫወቱት ጨዋታ እንደዘመኑ ለውጥ ከትውልድ ትውልድ የሚለያይ ቢሆንም መሠረታዊ የማይለወጡ ባሕሪያትም አሉት። በዋናነት የሰውነት እስፖርታዊ እንቅስቃሴን ግድ የሚሉና እድገታችን ብቁ እንዲሆን የሚያደርጉ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል። በብዛት በትልልቆች ከሚዘወተረው ገበጣን ከመሳሰሉ ተቀምጠው ከሚጫወቷቸው መዝናኛዎች በስተቀር፣ አብዛኞቹ መሯሯጥንና ጉልበትን የሚጠይቁ መሆናቸውን ከቀደሙት ትውልዶች ትዝታ ማረጋገጥ ይቻላል።

ሥልጣኔ እየመጣ ዘመናዊ መጫወቻም እየተመረተ ሲመጣ ብዙ ለውጦች ታይተዋል። በእንጨትና በኮባ ይሠራ የነበረ የመጫወቻ ‹ጦር መሣሪያ› በፕላስቲክ በተመረተ ውሃን ወይም ሌላ ተተኳሽን የሚያስወነጭፍ ሽጉጥና ጠመንጃ ሆኖ በብዛት ለወንድ ልጅ መጫወቻ ተደርጎ ይሰጣል። የፆታ ልዩነት መደረጉ ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን እንተወውና፣ ለሴቶች ደግሞ በብዛት አሻንጉሊት ይሰጣል። ጭቃ አቡክቶ መጫወትን ያስቀረው ይህ የዘመናዊ መጫወቻ ምርት፣ ‹እቃ እቃ› በሚል ስያሜም ከውድቅዳቂዎች ይሞላ የነበረን የምናብ ቤት በፋብሪካ ምርቶች እንዲተካ አድርጓል።

ሌለው ኳስን በተመለከተ ከተፈጥሮ ፍሬና ቅጠል ይዘጋጅ የነበረ ቀስ በቀስ በጨርቅ፣ ቀጥሎም ከካልሲ በሚሰፋ ተተክቶ አሁን አሁን ከተማ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ካፖርተኒ እያልን በምንጠራው ትልቅ ኳስ ተተክቷል። እስከ አሁን የጠቀስናቸው መጫወቻዎች ከሞላ ጎደል ጥንቱንም ነበሩ ማለት ቢቻልም፣ በዘመናዊ መልክ መጫወቻዎቹም ሆኑ ጨዋታዎቹ እየተሻሻሉና እየተቀየሩ የመጡ ናቸው። በጅራፍ ድብድብ፣ ትግል፣ አባሮሽና ድብብቆሽን የመሳሰሉ አድካሚ ጨዋታዎች ቀስ በቀስ እየከሰሙ እንደመጡ ማየት ይቻላል።

በፊት የነበሩ ጨዋታዎች የመቅረታቸውን ያህል ዘመናዊ የሚባሉ ዓለም ዐቀፍ ይዘት ያላቸው መጫወቻዎችም በየትምህርት ቤቱ እየገቡ የልጆችን ተቀባይነት በሰፊው አግኝተዋል። ዥዋዥዌ፤ ሸርታቴ፤ መኪና ወይም እሽክርክሮሽ፤ ሚዛን፤ መንጠላጠያ፤ ስእል መገጣጠም፤ እግር፣ መረብና ቅርጫት ኳስ፣ እንዲሁም ቴኒስ፣ ዳማና ቼዝን የመሳሰሉ መጫወቻዎችን ትምህርት ቤቶች ጭምር ያዘጋጃሉ።

በሌላ በኩል፣ ልጆች እንዳያዘወትሯቸው የሚመከሩ የመጫወቻ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቪዲዮ ጌም እየተባለ የሚታወቀው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምንጫወታቸው መዝናኛዎችን ነው።
ቅርፆችን መሰካካት ከሚዘወተርባቸው የድሮ የእጅ ጌሞች አንስቶ በቀደሙ ኮምፕዩተሮች ያሉ ማሪዮንና የካርታ ጨዋታዎችን የመሳሰሉ፣ እንዲሁም ‹ስኔክ›ን በመሳሰሉ የቀደሙ ስልኮች ላይ በነበሩ ጌሞች የጀመረ እድገታቸው አሁን ከእውነታው ለመለየት የሚያስቸግሩ ረቀቅ ያሉ ጨዋታዎችን በኮምፕዩተርም ሆነ ለዚሁ ተብለው በተፈበረኩ ፕሌይ-ስቴሽኖች ማጣጣም ይቻላል።

ወላጆች ልጆቻችን ተጣብቀው አልለያይ አሉን ከሚል ስሞታ ጀምሮ ትምህርታቸውን እያስተዋቸው ነው የሚሉ ቅሬታዎችን አካተው በርካታ መጥፎ የሚሉትን ችግራቸውን ሲያነሱ ይሰማል። የሚጫወቱበትን ሰዓት ከመቆጣጠር ጀምሮ መጫወቻውን አለመግዛትም እንደአማራጭ ቢወስዱም፣ በቀላሉ ሊያገኙ የሚችሉትን ስልክ ላይ ያለን ለመከልከል ግን ሲቸገሩ ይስተዋላል። ዘመድ በመጣ ቁጥር ከሠላምታ አስቀድመው ስልክ የሚጠይቁና ስለተለያዩ ስልኮች ከወላጆቻቸው በብዙ እጥፍ በማወቅ በልጠው የሚገኙ ሕፃናትንም ማግኘት አይከብድም።
የታዳጊዎችንና የቪዲዮ ጌምን ቁርኝት ለመግለፅ አጠር ያለ ፅሑፍ በቂ ባይሆንም፣ ልጅ የሌለው ቢያንስ ዘመድ ይኖረዋል ተብሎ ስለሚገመት ሁሉም ሁኔታውን ይረዳል ለማለት ያስደፍራል። ቤት ይቁጠረው ተብሎ የሚተው ባለመሆኑም፣ በታዳጊዎች ዘንድ ከፊልም በላይ መዝናኛ እየሆነ ስለመምጣቱ ራሳቸውን መጠየቁ በቂ ነው።

በተለይ ታዳጊዎች በተለያየ ምክንያት በሚገናኙበት ወቅት በተራ በተራ የሚጫወቷቸው ጌሞች ላይ ረጅም ጊዜን ማሳለፍ የተዘወተረ ድርጊታቸው ነው። በየድግሱና ማኅበራዊ ግንኙነት ወቅት ትልልቆች በወሬ ሲጠመዱ ልጆች እንደቀደመው ዘመን ውጭ ወጥቶ ከመጫወት ይልቅ አንድ ክፍል ውስጥ ታሽገው ምናባዊ ጨዋታን ማድራቱን ይመርጣሉ።

ይህ የሚሆነው መጫወቻ ቦታ በሌላቸው መኖሪያ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገር በተሟላላቸው ግቢዎች ጭምር መሆኑን የታዘቡት ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በሕፃናትና ታዳጊዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ትልልቅ ወላጆች ላይ ጭምር የሚስተዋል ነው።
ልጆች ሲማሩም ሆነ ሲዝናኑ ቁጭ ብለው በመዋላቸው ለአካል ብቃታቸው ዝቅተኛ መሆን እንደምክንያት ይጠቀሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማዳበር ረገድ እንደቀደሙት ዘመናት ትውልዶች መሆን ይሳናቸዋል በሚል ልማዱ ሲተች ይሰማል።

ከዘመኑ መጫወቻዎች መካከል በብዛት ለልጆች ጎጂ እንደሆነ ሲነገር የምንሰማው ቪዲዮ ጌም ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ምርምር ሳይደረግ በዘልማድ ብቻ ጎጂ ነው ተብሎ ይተች እንደነበር ከሠሞኑ ይፋ የተደረገ ጥናት ጠቁሟል። ቪዲዮ ጌም በተለምዶ እንደሚባለው የታዳጊዎችን የማሰብ ብቃት ዝቅተኛ እንደማያደርግ ነው። እንደውም በተቃራኒው ከማይጫወቱት በላይ አእምሯቸው ብሩህ እንዲሆን በማድረግ ልጆቹ ብልህ እንዲሆኑ ያደርጋል መባሉን ኒው አትላስ አዲሱን የጥናት ውጤት ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።

በአውሮፓውያን ተመራማሪዎች ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው ይህ የጥናት ውጤት እንዳመላከተው፣ ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ አነሰም በዛ ቪዲዮ ጌም የመጫወት ልምድ ያላቸው ታዳጊዎች ምንም ከማይጫወቱት ጋር ሲነፃፀሩ በአዕምሮ እድገትም ሆነ ብስለት የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል።

ቴሌቪዥንና ቪዲዮ ጌሞች በሕፃናት ላይ ያላቸውን ተፅእኖ ለማወቅ ጥናት ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ባለፉት ዐስር ዓመታት የመጣውን የቴክኖሎጂ መራቀቅ ተከትሎ ግን ለውጡም ሆነ ትስስሩ ከፍተኛ ሆኖ ዘልቋል።
ጥናቶቹ በአብዛኛው ሰዎች ስክሪን ላይ የሚያፈጡበትን ጊዜ የዳሰሱ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ጌም በሚጫወቱበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከጓደኞቻቸው ጋር ቻት የሚያደርጉበት፣ ፊልም የሚያዩበት፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙበትን እንዲሁም ላፕቶፕን በመሳሰለ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ጥናት የሚያጠኑበትንና የቤት ሥራ የሚሠሩበትን ጊዜ የሚያካትት ነው።

ታዳጊዎቹ እንደሚጠቀሙበት መንገድ ስክሪን ላይ መቆየታቸው ሙሉ በሙሉ ጎጂ ወይም ጠቃሚ ነው ማለት ሳይቻል ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የተወሰነ ዓይነት ተግባርን በመለየት ጥናት ማካሄድ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ቪዲዮ ጌምን ለይቶ ለማጥናት ተመርጧል። በዚህ መንገድ ከአእምሮ ብስለት ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሚሆን ለማወቅ የተለያዩ መንገዶችን በማነፃፀር ግኝታቸውን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።

የአእምሮ ብስለትን የሚጠቁሙ የማንበብና የማስታወስ ብቃትን የሚያሳውቁ የእውቀት መለኪያ ያሏቸውን መንገዶችን በጥያቄ መልክ ለናሙና በተመረጡ ቪዲዮ ጌም በሚጫወቱና በማይጫወቱ መካከል በማቅረብ ያለውን ልዩነት ለማወቅ ጥረዋል። አምስት ሺሕ ገደማ ሕፃናትን ለኹለት ዓመት ገደማ በመከታተል በኹለቱ ጎራ መካከል ያለውን የብልህነት መጠን ልዩነት ለማወቅ ችለናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ይገመት ከነበረው በተቃራኒ ቪዲዮ ጌም የሚጫወቱት ሕፃናት ከማይጫወቱት በበለጠ የተሻለ አእምሮ ብቃት እንዳላቸው ማየት ችለናል ማለታቸውም ተመዝግቧል።
ዘጠኝ ዓመት የሞላቸው ሕፃናትን ታሳቢ አድርጎ የተካሄደው ጥናት ገና ሲጀምሩ ጀምሮ ያላቸውን ብቃት ከኹለት ዓመት በኋላ ከነበረው ጋር በማስተያየት የተካሄደ ነው። ታዳጊዎቹ በሚሰጡት መረጃ ላይ ተመስርቶ የመዝናኛ ጊዜያቸው ቆይታ እውነታነት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነው ባይባልም፣ በሦስት ተከፍሎ ጌም ተጫዋች፣ ፊልም ተመልካችና ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ብለው ከፋፍለዋቸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በምርምሩ መጀመሪያ ሦስቱም ዓይነት ቡድኖች ላይ ምንም አይነት ለውጥ ባይታይም ከኹለቱ ዓመት ቆይታ በኋላ ግን ለውጡ በገሐድ ታይቷል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ ያን ያህል የሰፋ ልዩነት ባይታይም፣ ፊልም የሚያዘወትሩት አእምሮ ላይ ግን መጠነኛ የብስለት ለውጥ መታየቱን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል። ቪዲዮ ጌምን የሚጫወቱት ግን ከተጠበቀው በላይ አእምሯቸውን ማዳበር የቻሉ ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ የጨዋታንና የብልሀትን ግንኙነት ሳይንሳዊ ነው ባሉት መንገድ ማረጋገጥ መቻላቸውን አሳውቀዋል።
የጥናቱ ውጤት ሙሉ በሙሉ ቪዲዮ ጌም ብልህ ያደርጋል ብሎ የሚያረጋግጥ ሳይሆን፣ ሰነፍ ያደርጋል ተብሎ የሚታመነውን የተሳሳተ አመለካከት ያስቀራል ሲሉ ተመራማሪዎቹ የግኝታቸውን ውጤት ይፋ አድርገዋል።

የምርምሩን ወጪ የመንግሥት አካል ይደግፈው አልያም ጌምና ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያዎች በገንዘብ ድጋፍ ያስጠኑት ባይታወቅም፣ እስከዛሬ በግምት የነበረውን አመለካከት የሚያጠራ ነው ተብሎለታል። በተቃራኒው የሚሞግት የአሁኑን ውጤት አፍራሽ የሆነ ግኝት ለወደፊት ይፋ እስካልተደረገ ድረስም፣ ታዳጊዎች አእምሯቸውንም ሆነ የአካል ብቃታቸውን የሚያጎለብቱ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉ ሊበረታታ ይገባዋል። መዝናኛዎችም ሆኑ መጫወቻዎችም በአግባቡ ሲሆኑ ብቻ እንደሚጠቅሙም መረዳት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች