መነሻ ገጽዜናትንታኔበበጦርነት ጠባሳ የቆዘሙ ከተሞች

በበጦርነት ጠባሳ የቆዘሙ ከተሞች

ደብረ ሲና ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚጓዝ ሰው ሁሉ “ቆሎ፣ ቆሎ” የሚሉ ልጆቿ ፍቅርና ሳቅ የማይጠገብ ሰላምታና ምርቃት የሚቋደስባት፣ ከግራም ከቀኝም የሚመጣው ተጓዥ የሚያርፍባትና አክብሮትና ሽር ጉል በበዛበት መስተንግዶዋ የምትታወቅ ከተማ ናት።

ለሥራ ጉዳይ ወደ አፋር ክልል ለመጓዝ የመረጥኩት መሥመር ደብረ ሲናን፣ ሽዋሮቢትን፣ አጣዮንና ኬሚሴን አቆራርጦ በኮምቦልቻ ባቲ አድርጎ ወደ ሰመራ የሚወስደውን ነው። በሰሜኑ ጦርነት ከላይ የጠቀስኳቸው ከተሞች ያስተናገዱትን ጉዳት በዜናና በምስል ከመመልከት የዘለለ ወደ አካባቢው አቅንቼ የሆነውን ሁሉ ለማየት አድል አላገኘሁም። ነገር ግን፣ ወደ ቦታው አቅንተው የሆነውን ሁሉ በዐይናቸው የተመለከቱ ጋዜጠኞች በጥቂቱም ቢሆን፣ ጥሩውንም ክፉውንም አጫውተውኛል።

የሥራ ባልደረቦቼ በጥቂቱ ስለ ሁኔታው ሲተርኩልኝ የሆነውን ሁሉ በቦታው ተገኝቼ የመመልከት ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ። ይሄው ቀኑ ደርሶ ወደ አፋር የማደርገውን ጉዞ ረዥሙን መሥመር መርጬ የሆነውን ሁሉ እያየሁ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ በማለዳ ጉዞዬን ጀምሬያለሁ።
ከአዲስ አበባ 12 ሰዓት አካባቢ ማልጄ በመነሳቴ፣ ጉዞው በማለዳ ፀሐይ እንደታጀበ ነበር ደብር ብርሃን ከተማ አቋርጨ ደብረ ሲና ከተማ የደረስኩት። ደብረ ሲና አስክደርስ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የማየውን የጦርነት ፍርስራሽ ወይም ሰለባ እያሰብኩ ስለነበር፣ ምን አይ ይሆን? በሚል የስሜት መረበሽና ጉጉት ውስጥ ከራሴ ጋር በውስጤ እየታገልኩ ነበር ደብረ ሲና ከተማ የደረስኩት።

ከአዲስ አበባ በ190 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ሲና ከተማ ከወራት በፊት የጦር አውድማ ሆና ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት የነበረውን ግስጋሴ የተገታባት ከተማ ነበረች።
እኔም ይሄን እያሰብኩ ዐይኔን በግራና በቀኝ በትኩረት ለቅኝት አሰማርቼ ነበር ደብረሲና ከተማ የገባሁት። ከአዲስ አበባ መግቢያ ከተማዋን በግራ በቀኝ ስቃኛት በአንዳንድ ቤቶች ላይ ከሚታየው ሰላባ ውጭ ደህና ትመስላለች።

ወደ ማኅል ስንገባ “ቆሎ፣ ቆሎ” እያሉ ተሯሩጠው ከግራም ከቀኝ የሚገባውን ተጓዥ በፍቅር የሚያባብሉ ሴቶች እንደወትሮው እየተሯሯጡ መጥተው “ቆሎ፣ ቆሎ” ማለታቸውን ቀጠሉ። ይሁን እንጅ ደብረ ሲና የጦርነት አውድማ ከመሆኗ በፊት የነበረው ድባቧና ድምቀቷ አይታይም።

ደብረ ሲናን ከጦርነቱ በፊት ከአንድ ኹለት ጊዜ ተመላልሸባት አውቃለሁ። ሁሌ ደብረሲናን የሚነካ ጉዞ ሲኖረኝ ደብረ ሲናን አስባታለሁ። ደስ የሚል ድባብ አላት ብዙ ሰዎችም ደብረ ሲናን በጉዟቸው ከሚያስታውሷት ከተማ መካከል አንዷ ናት።
ደብረ ሲና በደጇ የሚያልፈውን ሁሉ ለወትሮው በፍቅር ተቀብላ መለያዋ የሆነው ጣፋጭ ቆሎ ሰንቃ የምትሸኝ አይነ ግቡ ከተማ ናት። ታዲይ ይች የፍቅር ከተማ ከግራም ከቀኝም አላፊ አግዳሚውን ከጦርነት ማግስት እንደወትሮው ፍቅር ለመለገስ የወትሮው ጥረቷ አልተለያትም።

ይሁን እንጂ ደብረ ሲና እንደ ቀድሞ ድምቀቷ አይደለችም። ከወራት በፊት የጦርነት አውድማ ሆና ለማንሰራራት የምታጣጥር ከተማ መሆኗን በቆሙበት የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች፣ እነዚያ ፍቅር የደራባቸው ቤቶች ወደ አመድነት ተቀይረው ከነ ሙሉ ሰለባቸው ይታያሉ። የደብረ ሲና ሴቶች እንደወትሮው ባይሆንም ታዋቂ ቆሏቸውን ሰንቀው በግራ በቀኝ የተጓዦችን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁበት ሁኔታና በቁማቸው የተቃጠሉ ተሸከርካሪዎችና ቤቶች በአደባባይ የመንገደኛን ትኩረት መሳባቸው፣ ከተማዋ በማንሰራራትና በቁዘማ ውስጥ መሆኗን ያሳብቃሉ።

ደብረ ሲና ከተማ ጦርነቱ የተገታባት ከተማ በመሆኗ በበጎም፣ በመጥፎን የሚነሳ ትዝታ በራሷ ላይ ጽፋለች። በጎው ነገር ጦርነቱ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ደብረ ብርሃን የሚያደርገው ግስጋሴ የተገታባት መሆኗ፣ መቼ የማትረሳውና መጥፎው ትዝታዋ ደግሞ በጦርነቱ ያጣቻቸው ልጆቿ፣ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትለው የንብረት ውድመት ናቸው።

ደብረ ሲና የአደባባይ ጠባሳዋን መደበቅ ባትችልም የሆዷን በሆዷ ይዛ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ መቀበሏንና ጣፋጭ ቆሎዋን ሰንቃ መሸኘቷን ቀጥላለች። ደብረ ሲና ስደርስ ወደ ወትሮው ድምቀቷ ለመመለስ የምታደርገው ሽር ጉድ ቀድሞ የነበረውን ምን አይ ይሆን የሚለውን የመረበሽ ስሜቴን በመጠኑ ቢያስታግስልኝም፣ ደብረ ሲና ረግጦ የሚያልፈውን ተጓዥ ኹሉ ከንፈር የሚያስመጥጡ የጦርነት ሰለባዎች ከአደባባይ አለመጥፋታቸው እንኳን በየቀኑ ሲወጡ ሲገቡ አይናቸው ላይ ተደቅኖ ያን መጥፎ ትውስታ የሚፈጥርባቸው ነዋሪዎቹ እኔ አልፎ ሄያጁም የህሊና ሰላም አልተሰማኝም።

ደብረ ሲና ላይ የነበረኝ ቆይታ ተጠናቆ፣ የጦርነት ቀጠና ወደ ነበሩ ከተሞች ጉዞ እንደጀመርኩ በየመስመሩ የምመለከታቸው የተቃጠሉ ተሸከርካሪዎች በእውነት በእጅጉ ስሜት የሚረብሹ ናቸው። ገና ከደብረ ሲና እንደወጣሁ በየአስፋቱ መሀልና ዳር ከቤት መኪና አስክ ገልባጭ መኪና በቆሙበት ተቃጥለውና ስፔር ፓርታቸው ተወስዶ ቧዷቸውን ቆመው ማየቴ የፈራሁትን የመረበሽ ስሜት ቢፈጥርብኝም፣ ጉዞዮን ቀጥያለሁ።

በየመስመሩ የተቃጠሉ ተሸከርካሪዎች መመለክት እየለመድኩ ከደብረ ሲና 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሽዋሮቢት ከተማ የደረስኩት አምስት ስዓት አካባቢ ነበር። ሞቃታማዋና የንግድ ከተማዋ ሽዋሮቢት የወትሮ ድምቀቷ በእጅጉ ርቋታል። ደረብረ ሲና ላይ ያለ የማንሰራራት ተስፋ ሽዋሮቢት ላይ ገና እየተጀመረ ነው ማለት ይቻላል።

ሽዋሮቢት መሀል አስፋልት ላይ ቆመው የተቃጠሉ ተስካርካሪዎች ባሉበት ቆመው ማየት፣ ከደብረ ሲና ጀምሮ ያለ ቢሆንም፣ ሽዋሮቢት ላይ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆች፣ መኖሪያ ቤቶች ህንጻዎች በጦርነቱ ወቅት ያስተናገዱትን ጉዳት ገጽታ እንደተላበሱ ናቸው።
በከተማዋ የፈረሱ መኖሪያና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና ንግድ ቤቶች አልፎ አልፎ ተዘግተው ይታዩ እንጅ፣ በእድሳት ላይ የሚገኙ ጉዳት ያስተናገዱ ቤቶችም አሉ። በመሀል ከተማ የጦርነት ሰለባዎችን በየቀኑ ማየት በነዋሪዎች ስነ ልቦና ላይ ጫና መፍጠሩን መታዘብ ይቻላል። የነዋሪዎችን ስሜት ለመጋራት ፍላጎት ስለነበረኝ፣ አብረውን ከነበሩ ኹለት ጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ ምግብ ቤት አቀናን።

ምግብ ቤት የምትሰራውን ወጣት ሴት ምግብ አዘን ምግቡ እስከሚቀርብልንና በልተን እስከምንወጣ ምንም አይነት ሰው ወደ ምግብ ቤቱ አልገባም። አሁን ስላሉበት ሁኔታ ወጣቷን ሴት ስጠይቃት በትህትና በታጀበ ደምጽ “አይ ያው እንደምታዩት ነው” አለችኝ። የልጅቷ መልስ አሰጣጥ ሁኔታ፣ ከጦርነት በኋላ ብዙ ነገሮች እንደወትሮው እንዳልሆኑና ተጽዕኖው የከተማዋን ነዋሪዎች እንደተጫናቸው ያሳብቃል።

የመረጥኩት የጉዞ መስመር አሁንም የጦርነት ሰለባዎችን በግራ በቀኝ መመልከት አሁንም የሚያበቃ አይደለም። ከሽዋሮቢት ወደ አጣዬ ጉዞ እንደቀጠለ ሲሆን፣ አሁንም በየመሀል አስፋልቱ የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች ሰለባ ማየት አስካሁን በተጓዝኳቸው ጉዞዎች ስለለመድኩት የተለየ ስሜት አልፈጠረብኝም።

ይሁን አንጅ አጣዬ ከተማ ስገባ የሶርያና የሊቢያ ጦርነት ላይ በምስል ካየሁት ምስል ጋር የሚቀራረብና በእጅጉ ስሜትን የሚረብሽ ነው። በመደዳ የተሰደሩ ከተሞች ጣራቸው ተቃጥሎና ፈራርሰው የትኩስ ጦርነት ስሜት ይፈጥራሉ። አብዛኛዎቹ የንግድ ቤቶች እስካሁን አልተከፈቱም፣ ተደራራቢ ችግር የቀመሰችው አጣዬ አሁንም በእጅጉ እንደቆዘመች ትገኛለች። በመሀል አስፋልት ፊት ለፊት የተሰደሩ ቤቶች ተቃጥለውና ተዘግተው መመልከት የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም።

የአጣዬን የጦርነት ጠባሳ ከደብረ ሲናና ሽዋሮቢት ለየት የሚያደርገው በተደጋጋሚ ከተለያዩ ኃይሎች ጥቃትን ያስተናገደ ከተማ መሆኑ ነው። መንግሥት “ሸኔ” የሚለውና እራሱን “የኦሮሚያ ነጻ አውጭ ጦር” ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል ከተማ ላይ ከፉኛ ጉዳት አድርሶባት ነበር። ታዲያ ከደረሰባት ክፉ በትር በቅጡ ሳታገገም የሰሜኑ ጦርነት ተስፋፍቶ አጣዬን አልፎ ደብረ ሲና ሲደርስ አጣዬን በጉዳት ላይ ሌላ ጉዳት ደርቦቧት ነው ያለፈው።
በብዙዎችቻችን የሶሪያንና የሊቢያን ጦርነት በዜና ስንመለከት ፍርስራሽ ከተሞችን ሳናይ አንቀርም፣ የአጣዬም ጉዳት ያንን የሚስተካከል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

- ይከተሉን -Social Media

ምክንያቱም ከተማዋ ከሌሎች ከተሞች ላይ ካለው ሁኔታ አንጻር የፈረሰች ከተማ መሆኗ ጎልቶ ይታያል። አጣዬ በተደጋጋሚ ያረፈባትን በትር መቋቋም የቻለች አይመስልም። ይሁን አንጂ ነዋሪዎቿን በዚህ የፍርስራሽ ከተማ ስሜት አቅፏ ለማንሰራራት ዳዴ የምትል ከተማ ሆናለች።
ከደብረ ሲና እስከ አጣዬ በመሀል አስፋልት ላይ ተቃጥለው የጦርነቱ ሰለባዎች የሆኑ የቆሙ ተሸካርካሪዎችን፣ ነገሬ ብሎ ያያቸው ያለ አይመስልም። መሀል አስፋልት ላይ የተቃጠሉና የውስጥ እቃቸው ተወስዶ የቆሙ ከትንሽ እስከ ትልቅ ተሽከርካሪዎች አላፊ አግዳሚውን ከንፈር ያስመጥጣሉ።

ተጓዞችን በውልብታ ከንፈር የሚያስመጥጡና የሚረብሹ የጦርነት አስታዋሽ ሰለባዎች፣ ነዋሪዎች ሌት ተቀን በወጡ በገቡ ቁጥር ከፊታቸው የሚደቀንባቸው የከተማው ነዋሪዎች ምን ይሰማቸው ይሆን።
በጦርነት ወቅት ጦርነት ያስተናገደ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙ የድህረ ጦርነት ችግሮች መካከል በጦርነት ጠባሳዎች ሁኔታዎችን መጥፎ ክስተቶችን በማስታወስ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች “ሳይኮሎችካል ትራውማ” የሚሉት ስሜት ወይም የመንፈስ መረበሽ የሚፈጥሩ፣ ጦርነት አስታዋሽ ነገሮች አንደነበሩ መቀመጣቸው በነዋሪዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ማሰብ ባለሙያ መሆንን የሚጠይቅ አይደለም።

የጦርነት ሰላባ የሆኑ አካባቢዎችንና ከተሞችን በአካል ለማየት ጉጉት አንጻር የመረጥኩት እረዥም ጉዞ፣ ገና ተጀመረ እንጅ አላለቀም። የቀጣይ ጉዞዬ ከሚሴንና የኢንዱስተሪ መንደሯን ኮምቦልቻን አቆራርጦ ሌላ የጦርነት ጠባሳ ወዳስተናገዱ አፋር አካባቢዎች ይቀጥላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች