መነሻ ገጽአንደበት“አገዛዙ የአገር ጉዳይ ከሥልጣን ሊበልጥበት አልቻለም”

“አገዛዙ የአገር ጉዳይ ከሥልጣን ሊበልጥበት አልቻለም”

‹‹በፖለቲካ ዓለም አንጋፋ ከሆኑና በለጋ እድሜ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን ከጀመሩ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፤ አንዱዓለም አራጌ። በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተለያየ ደረጃ አገልግለዋል። ታድያ እንዲሁ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆኑ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉም ስለነበሩ፣ በቀደመው ኢሕአዴግ አገዛዝ በተለያየ ጊዜ ለእስር ተዳርገው ነበር።

የጽናት ተምሳሌት እንደሆኑ ብዙዎች የመሰክሩላቸው አንዱዓለም፤ ‹ያልተሄደበት መንገድ› ‹የአገር ፍቅር ዕዳ› እና ‹3000 ሌሊቶች› የተሰኙ መጻሕፍትንም ለአንባብያን አድርሰዋል። የአንድነት ለፍትህ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሥራች እና ሊቀ መንበር ሆነው ያገለገሉም ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የተመሠረተው ኢዜማንም በምክትልነት ሲመሩ ቆይተዋል።

በቅርቡ ደግሞ የፓርቲውን አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ተከትሎ (ሰኔ 25/26 2014 ይካሄዳል) ፓርቲው መሪውን ይመርጣል። በዚህም ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመወዳደር አንዱዓለም አራጌ በእጩነት ቀርበዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታና የፓርቲውን እንቅስቃሴ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ለኢዜማ መሪ በሚደረገው ምርጫ ካሸነፉ ኢዜማ አሁን ባለበት አካሄዱ ይቀጥላል ወይስ የተለየ ነገር ይኖራል?
የተለየ ነገር ይኖራል። አንደኛ ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት አሁን ባለው ደረጃ፣ መርህ አልባ የሆነ ግንኙነት አይሆንም። መርህ ላይ የተመሠረተ፣ መንግሥት በጎ ሲሠራ በስነስርዓት እንደግፋለን፤ መንግሥት የሕዝብን መብት ካላከበረና የገባውን ቃል ካልፈጸመ ደግሞ በስነስርዓት የሰላ ትችት ከመሰንዘር አልፈን በሰላማዊ ትግል ለሕግ እንዲገዛ፣ የሕዝብን መብት እንዲያከብር እንታገለዋለን።

ከውጪ ግንኙነት አንጻር ካየኸው፣ እስከ አሁን ያለን የውጭ ግንኙነት በጣም ደካማ ነው፤ ያለንም ግንኙነት ከመንግሥት ጋር ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ግን ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ተቃዋሚዎች ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል ከሚሉት ሁሉ፣ ምንም ያህል የተለየ ነገር ቢኖረንም ካልተዋያየን መፍትሄ እናመጣለን ብለን አናምንም። ስለዚህ ከእነሱ ጋር የውጭ ግንኙነታችን አብረን እንደ አንድ አገር ልጆች፣ ልባችንንም በራችንንም ከፍተን የምንወያይበት ሁኔታ ይኖራል።

ከውጭ አገር ፓርቲዎች ጋርም ቢሆን እንዲሁ፣ ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብም ጋር ቢሆን ጠንካራ ዓይነት ግንኙነት ይኖረናል። ሌላው ደግሞ ተተኪ መሪዎችን ዓላማ አድርገን፤ እንደዚህ ሳይሆን ወደ ፊት በሚቀጥለው ጉባኤያችን ላይ ብዙ ዐይነ ግቡ ወጣት መሪዎችን አፍርተን፤ ለፓርቲያችን ብቻ ሳይሆን ለአገርም የሚተርፉ መሪዎችን የምናፈራበትን ሁኔታ አቅደን ሥራችን ብለን ይዘን እንቀጥላለን።

በድርጅቱ አሁን ባለው ሁኔታ የተሠሩ በጎ ነገሮች አሉ። እነሱን አጠናክረን እንቀጥላለን። ሻዶ ካቢኔው (ትይዩ ካቢኔው) እንደገና ይዋቀራል። በጣም ዝርዝር የሆኑ የፖሊሲ ሐሳቦች አሉ። ግን እነሱን በዋና ዋና ለምሳሌ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳይ ስር የሚወድቁትን፣ አንድ ላይ በማድረግ ሰፋ ያሉ ሥራዎች እንዲሠሩ ብዙ እቅዶች አሉን።

በአጠቃላይ ኢዜማ የሕዝብ ቅቡልነት ያለው፣ ተመራጭ፣ ተደማጭ፣ የሚከበር፣ በሕዝበ የሚታመን እና ሲያስፈልግም ደግሞ ለቃሉ የሚቆም፣ የተናገረውን የሚያደርግ ፓርቲ አድርገን እንሠራለን።

ኢዜማ ገና ከምሥረታው ጀምሮ የመንግሥት ተለጣፊ ነው የሚል ትችል ይነሳበት ነበር። መሪው ብርሃኑ ነጋ የመንግሥት ሥልጣን ከተቀበሉ በኋላ ደግሞ ትችቱ በርትቷል። እውነት ኢዜማ አሁን ላይ ከመንግሥት የራቀ ነው?
አንደኛው እኔን ለመሪነት እንድወዳደር ከገፉኝ ውስጥ፣ እንዳልኩት ምርጫውን የያዝንበት ጉዳይ ብዙ የለየን ጉዳይ ነበር። ኹለታችን ደግሞ ጦርነቱን በሚመለከት የነበረን አቋም ነው። ሦስተኛ ብዙ ያወያየን፣ ከመንግሥት ጋር ያለው ነገር ነው።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአመክንዮና በሞራላዊ አስተሳሰብ የሚታማ ሰው አይደለም። ግን ከብልጽግና ወይም ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚመለከት ያለው ዕይታ፣ በፍጹም እንዳይነካበት የመከላከል ነው። አንዳንዴ ፓርቲውን ነው የሚያስቀድመው ወይስ ብልጽግናን ብለን እስክንጨነቅ ድረስ በፍጹም የብልጽግናን ክፉ በፓርቲው ውስጥ ለመስማት የሚቸገር፣ (እርሱ የሚያውቀው ነገር ካለ አናውቅም እውነት ለመናገር) ግን ከምክንያት ባለፈ ለእኛ በማይገባን ሁኔታና ደረጃ (ብንረዳው ቢገባን ደስ ይለን ነበር)፣ ድርቅ ብሎ የብልጽግናን፣ (ኢዜማ እንኳ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ፣ እጃችን ላይ እንደ ሳሙና እያለቀ) አሁንም ትክክል ነው፤ ብልጽግናን መደገፍ አለብን የሚል፣ ምንም ቅር ሳይለው የሚናገረው አቋም አለው።

ይህ ለእኔ ምክንያታዊ ሆኖ አላገኘሁትም። በዚህ አካሄድ ከቀጠልን ፓርቲው እንደ ሳሙና እጃችን ላይ ያልቃል። የሚቀጥለው ጉባኤያችን ላይ ስንደርስ፣ ፓርቲው ስሙ ብቻ ካልሆነ በቀር የሚከበር፣ የሚታመን እና የሚፈራ ፓርቲ ቀርቶ በመካከለኛ ደረጃ ያለ ፓርቲ እንኳ ይኖረናል ብለን አናምንም።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ኢዜማ የሚያደርገው አይነት የመሪ ምርጫ አልተለመደም። ምንአልባት የመሪነት ምርጫ ፉክክሩ በፓርቲያችሁ ውስጥ ልዩነት እንደተፈጠረ ያሳብቃል የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ ምን ይላሉ?
ኢዜማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ የሚባል ቁመና የተላበሰ እና ብዙ ሥራዎችን የሠራ ፓርቲ እንደሆነ አንዘነጋም። ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ይንቀሳቀሳል። ሲንቀሳቀስ የተለያየ መገፋፋት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን የእኛ ግን የሐሳብ ፍጭት ነው። ያ የሐሳብ ፍጭት ደግሞ ከአንድ ጤነኛ ፓርቲ የሚጠበቅ ነው።

በአንድ ግለሰብ ተረግጦ የተያዘ ፓርቲ ነው ዝም ብሎ እኛ አገር እንደለመድነውና በገዢው ፓርቲ ውስጥ እንደምናየው፤ 500 ሰው ተሰብስቦ 500ውም እጅ የሚያወጣበትና አንድ ዓይነት የሚሆንበት ፓርቲ፣ ያ የሞተ ፓርቲ ነው።

በእኛ ፓርቲ ውስጥ ግን ጤነኛ የሆነ ውይይት አለ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ክርክሮች አድርገናል። ግን አንዳችን በሌላችን ጀርባ የሠራነው ነገር የለም። ቢያንስ እኔ ስለራሴ በእርግጠኝነት የምናገረው፣ ሐሳቤን በቀጥታ እናገራለሁ። ከዛ ውጪ ግን ስንወጣ ወንድማማች ነን።

‹ብሬ› ‹አንዱ› ተባብለን ነው የኖርነው። አሁንም ቢሆን የሐሳብ ፍጭት አለ። የሐሳብ ፍጭት ወደ ጋዜጣ ይዘን መውጣት፣ ሚድያ ላይ ሕዝቡን ማሰላቸት አልፈለግንም። በሕግ እና በሕግ ብቻ የሚሠራ ፓርቲ እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዛ ደግሞ ጉባኤያችን ደርሷል። በጉባኤያችን ላይ የሐሳብ ልዩነታችንን አቅርበን፣ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው መራጩ ራሱ የፈለገውን ይመርጣል ማለት ነው።

ከዛ በኋላ የሚሸነፈው አክብሮ ይቀጥላል፤ የሚያሸንፈውም የተሰጠውን ኃላፊነት ተሸክሞ ይቀጥላል። ይህ ጤነኛ የሆነ ሂደት ነው። እኛ አገር የተለመደ ስላልሆነ እንጂ፣ አንድ ፓርቲ ውስጥ ብንሆንም መቶ በመቶ አንድ ጉዳይ ላይ እንስማማለን ማለት አይደለም። የምንግባባባቸው በጣም ምሰሶ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ለዛ ነው አብረን የቆምነው። ግን ስትራቴጂክ ሳይሆን ታክቲካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች አሉን።

- ይከተሉን -Social Media

እንዴት ለአንድ ዓላማ ግን በየትኛው መንገድ ሄደን እንዴት እናድርሰው የሚሉ ነገሮች ብዙ ጊዜ ይለዩናል። እና እሱ ጤነኛ ነው። ለምሳሌ የምርጫ ፕሮግራሙ የተጀመረበት ሁኔታ፣ ለአገራችንም ለፓርቲዎችም ለሁላችንም የሚያስደስት ትልቅ ፋና ወጊ የሆነ ሂደት ነው ያደረግነው። ይህን በአባሎቻችን እንዲሁም በፈጣሪ እርዳታ ወደ ተሻለ ደረጃ እናደርሰዋለን፤ በጥሩ ሁኔታ እንጨርሰዋለን ብዬ አምናለሁ።

ኢዜማ በመጀመሪያ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በሚያደርገው የመሪ ምርጫ፣ ለመሪነት በሚወዳደሩበት ሰነድ ላይ ኢዜማ ስትራቴጂክ ግቦቹን ማሳካት እንዳልቻለ ገልጻችኋል። ለምን ስትራቴጂክ ግቦቹን ማሳካት አልቻለም?
ዋናው ነገር ይመስለኛል፤ ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ነው። ለምሳሌ ከመንግሥት ጋር ሆነን እንሠራቸዋለን ብለን የያዝናቸው ነገሮች፤ መንግሥት ከይስሙላ ባለፈ እኛ በጠበቅነው ደረጃ አላገኘነውም።

ሁለተኛ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታው በጣም ከግምታችን ባለፈ፣ (በሁሉም ዜጎች ጋር ያለ ድምዳሜ ይመስለኛል) ከእቅድ፣ ከፍላጎትና ሕልም ውጪ የሚመጡ በየቀኑ ከእኛ ወጪ በሆኑ ኃይሎች የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። ስለዚህ ያንን ስትራቴጂክ ግባችንን ለማሳከት ለምሳሌ በአገራችን የተሳካ ምርጫ ለማድረግ የነበረን ፍላጎት፣ እኛ ምንም ያህል በንጽህና ለመጫወት ብንሞክርም፤ አገዛዙ የአገር ጉዳይ ከሥልጣን ሊበልጥበት አልቻለም። ስለዚህ በዛ ሁኔታ ተበላሽቷል።

ሌሎችም ከመንግሥት ጋር አብረን የምንሠራቸው ሥራዎች፤ ለይስሙላ አብረን እንድንሠራ የሆነ ሂደት ያስጀምሩልናል። ለምሳሌ ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራትን እየተወያየን እንፈታዋለን/እንገባበታለን ካሉ በኋላ አንድ ወረቀት ላኩልን። እኛም አስተያየታችንን ከላክን በኋላ፣ ሂደቱን አቋርጠው በራሳቸው መንገድ ‹ዩኒላተራል› የሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ ገቡ።

እና እንዲህ ዓይነት ሥራዎች በአንድ በኩል የድርጅታችን አባላት በሂደቱ እንዲበሳጩ እንዲያዝኑ፣ በሕዝብ ዘንድም የነበረን ተቀባይነት እንዲጎዳ ያደረገ ተግባር ነው።

ለምሳሌ እንደ አንድ ስትራቴጂክ ግብ የወሰድነው፤ አገር ማረጋጋት፣ በእኛ ፍላጎት ብቻ የሚሆን አልነበረም። በሌሎች ተጻራሪ ኃይሎችና መንግሥት ጉዳዩን በያዘበት ሁኔታ እየተባባሰ ሊሄድ ቸሏል። እና ብዙ ምክንያቶን ማንሳት ይቻላል።

በፓርቲያችሁ ውስጥ የሐሳብ ልዩነቱን መሰረት በማድረግ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድም አንዱ ሌላኛውን ለማፈን ሙከራ መደረጉ ሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። የተፈጠረው ልዩነት ምንድን ነው?
እኛንም በጣም ያስደነገጠን ነገር ነው፤ በፍጹም ያልጠበቅነው ነገር ነው፤ አዝነናልም። የሆነውን ነገር ለመግለጽ፤ (በእርግጥ ጉዳዩ በሕግና ዲሲፕሊን ኮሚቴ በኩል ተይዟል፤ ውጤቱንም እንጠብቃለን። ለዛ ውጤትም እንገዛለን) ፕሮፌሰር ብርሃኑን ለማስመረጥ የሚሠራ ቡድን አለ። ይህ ቡድን ሰነድ አዘጋጅቶ ነበር፤ የራሳቸው የመገናኛ ማሰራጫ አላቸው። ወደዛ ላክን ብለው የሥራ አስፈጻሚው ‹ዋትስአፕ› ቡድን ላይ ጫኑት።

መጀመሪያ ነገሬ አላልነውም ነበር። ነገር ግን በኋላ ወረቀቱን ገብተን ስናይ ለምሳሌ የጉባኤውን አዘጋጆች የፈለጓቸውን ሰዎች ማድረግ፣ ጉባኤ ውስጥ የሚናገሩ ሰዎችን ራሳቸው መመደብ፣ የሚቀመጡበትን ቦታ መመደብ፣ ከዛ ከጉባኤ አዘጋጆቹ ጋር ደግሞ ከሚመሩት ጋር እንዴት እንደሚገናኙ መሥራት፣ ከክፍለ አገር የሚመጡ መራጮች የሚቀመጡበትን ቦታ መወሰን፣ ሌሎች ተወዳዳሪዎች እንዳያገኟቸው መከላከል የሚልና በጣም ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ፣ ከእኛ ሰዎች ውስጥ እንዲሀ ያለ ሥራ ፈጽሞ የሚጠበቅ አልነበረም። ያ ሁኔታ አጋጠመን። በጊዜው ትንሽ ተነጋገርንበት። ሥራ አስፈጻሚው ይህ ነገር ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ኢ-ሞራልና ኢ-ሕጋዊ ነው የሚል ውሳኔ ወስኖ፤ ዞሮ ዞሮ በፓርቲያችን አሠራር መሠረት የሕግና ዲሲፕሊን ኮሚቴ አለ፤ ወደዛ ተመርቷል። እንግዲህ ውሳኔውን እንጠብቃለን።

- ይከተሉን -Social Media

ለማፈን ሙከራ ያደረገው የብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አስመራጭ ቡድን ነው ማለት ይቻላል?
አዎ! እንደዛ ብዬ አምናለሁ።

በተለይ በመንግሥት በኩል ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመከፋፈል ሴራ ይኖራል ተብሎ ይጠረጠራል። በውስጣችሁ ያለውን ልዩነት እንደ ተፈጥሮአዊ ፈተና ነው የምታዩት ወይስ ፓርቲውን ያሰጋዋል?
ብዙ ጊዜ ችግር የገጠመው ሰው ቢደነግጥ፣ ቢፈራ፣ ቢሰጋ አይፈረድበትም። እኛ አገር በተደጋጋሚ ከመንግሥት የሚነሱ ተቃዋሚ ፓርቲን ለማጥቃት የተደረጉ ሥራዎችን ለብዙ ዓመታት ዐይተናል፤ ሰለባም ሆነን እናውቃለን። ይህ ነገር አእምሯችን ውስጥ አለ። ግን በዛው መጠን በፓርቲም ደረጃ መጠንቀቅ አለብን ብዬ የማምነው፤ እኔ እንደ ግለሰብ የማራምደው፤ አንድ ሰው በጎ ነገር ከሠራ ያ በጎ ነገሩ መመስገን አለበት። በጎ ነገር ካልሠራ ደግሞ ዋጋ ቢያስከፍልም በችግሩ መጠንና ልክ መነገር አለበት፤ ሊያርምም ይገባል ብዬ አምናለሁ።
አሁን ባለው ሁኔታ ከመንግሥት በተጨባጭ ይህ ነው የሚባለው፤ የደኅንነቶች ክትትልና ሌላ ሌላ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ግን ያም ቢሆን እኛ ከግምት ባለፈ መንግሥት በፓርቲያችን ላይ ይህን እያደረገ ነው ብዬ መናገር የሚያስችለኝ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለኝም።

ግን ግምት ስጥ ካልከኝ፤ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ጠንካራ፣ አቋማቸውን በትክክለኛ መሠረት እና በሀቀኛ ሰጥቶ መቀበል ላይ መሥራት አለባችሁ የሚላቸው እንዲመረጥ ይፈልጋሉ ብዬ አልገምትም። እነሱ እሽሽ የሚላቸውን እና እንደፈለጉ ምኞታቸውን የሚያሳካ ሰው ስለሚፈልጉ፤ ተጽእኖ የማሳደር ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። ግን እንዳልኩህ በተጨባጭ እስከ አሁን ይህ ነው የሚባል ነገር ስላላየን፣ ያለማስረጃ እነሱን መክሰስ ተገቢ አይሆንም።

ብሔር ተኮር የፖለቲካ ኃይሎች በበዙባት ኢትዮጵያ፣ የኢዜማ ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አሰላለፍ እንዳሰበው እየሄደለት ነው ማለት ይቻላል?
ችግር ባለበት ነው መፍትሄ የሚያስፈልገው። ችግር ከሌለ መፍትሄ የሚያሳስብ ነገር አይደለም። የብሔር ችግር፣ (ዘርም ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን) ዘርን መሠረት ያደረገ ሰውን በብሔሩ፣ በቋንቋው አቧድኖ ለፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ የሚሠራን ሥራ፣ ልክ የዛን ብሔር መብቱ እንደሚከበር፣ የዜጋውን መብት ሳያከብር የብሔሩን በድምር መብት አከብራለሁ የሚል የተፋለሰ አስተሰሰብ በዚህ አገር ላይ ሰፍኖ፣ ምን ያህል ከደረጃ የወረደ ነገር ውስጥ እንደምንገኝ፤ እንደ አገር ምን ያህል እንደተዋረድን፣ ምን ያህል ኢ ሰብአዊነት እንደነገሠ መቼም ሁሉም ሰው ያውቃል።

እንዲህ ባለ ሁኔታ ሰው በሰውነትና በዜግነት ክብር ላይ ቆሞ፣ የትም ቦታ በሕግ የበላይነት ሰዎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት ስርዓት ማምጣት ፍቱን መድኃኒት ነው ብለን እናምናለን። ከዛ አንጻር በጎ ጅምሮች አድርገናል፤ ግን እንዳልከው የዘር ጎርፍ አገሪቷን እያጥለቀለቃት ያለበት ሰዓት ነው። በ60ዎቹ ምንአልባት ከዛ ቀደም ብሎ የተጀመረ ብሔርን መሠረት ያደረገ አሠራር፣ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰበት ዘመን ካለ፤ እስከ አሁን ካለው ይህኛው የከፋው ነው።

በዛ ሂደት ሂደቱን ለማስቆም የምንችልበት ሁኔታ ላይ አልነበርንም። ግን መኖራችን፣ የአገራዊ ፖለቲካውን አርማ አንግበን መቆየታችን ትልቅ ዋጋ አለው ብዬ አምናለሁ። በአገር ዐቀፍ ደረጃም ነገሮች ቢከፈቱ፣ መንግሥትም ከብሔር አስተሳስብ የወጣ አለመሆኑ እንጂ፣ እንደ 97 ዓይነት መንግሥት ወኔ ኖሮት ነገሮች የሚከፈቱበት ሁኔታ ቢመጣ፤ አሁንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዜግነትና በሰውነቱ ላይ ቆሞ የሚያስብ ሕዝብ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ አሁንም አርማውን ይዘን እንቀጥላለን።

አንደኛው የእኛ ግብ ይህን በከፍተኛ ሁኔታ የተመታውን የዜግነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ምድር እንዲያንሰራፋና አሁን ለምንገኝበት ዙሪያ መለስ ችግር መፍትሄ እንዲሆን አድርገን እንንቀሳቀሳለን። እሰከ አሁን ግን ብዙም ውጤታማ አልነበርንም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።

የብሔር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ዋጋ አስከፍሏል፤ አሁንም እያስከፈለ ነው። እንዴት ከብሔር ፖለቲካ መውጣት ይቻላል?
ጥያቄው ከባድ ነው፣ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም። እንደሚመስለኝ ግን ትልቁ ነገር የሚጀምረው መንግሥት ከጊዜያዊ ጥቅም ባለፈ ሩቅ የሚያልም መንግሥት ከሆነ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እስካልፈጠርን ድረስ፣ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ዓይነት ያሉ ትንንሽ አገራት ነገ ከምናየው በላይ ሌላ መከራ እንደሚጋርጡብን እና ወደ ከፍተኛ ውድቀት እንደሚገፉን ጥያቄ የለውም።

- ይከተሉን -Social Media

ለምሳሌ በፊት ኢሕአዴግ ሲያራምድ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንዳይሸራረፍ አስከብራለሁ በሚል ተረት፣ ኢትዮጵያዊያን እንዲለያዩ ያደረገበትን ሂደት አሁንም ብልጽግና በማኒፌስቶ ቃል ገብቶ እያስፈጸመ ያለበት ሁኔታ አለ። የሚናገሩት በአንደበት ደረጃ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ይላሉ፤ በተግባር ግን ብልጽግና ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች እንኳ እንዲሁ በብሔር ተከፋፍለው፤ በውጥረትና በመገፋፋት ነው ያሉት።

አገር እየመራ ያለው ፓርቲ ውስጥ ያለው እንደ እኛ የአስተሳሰብ ሳይሆን የብሔር ቡድንተኝነትና መገፋፋት ነው። እርሱ ትልቅ ሳንካ ነው። ስለዚህ እነሱ ትክክለኛ አገራዊ አስተሳሰብ ይዘው አገራዊ ፓርቲ ቢኖራቸው ጥሩ ጅምር ይኖራል። ፋይናንሱም ሠራዊቱም በእጃቸው ስላለ ነው እነሱን ቅድሚያ የሰጠሁት።

ኹለተኛ ግን ቁርጠኝነቱ ካላቸው ብዙ ፓርቲዎች የልሂቃን ምክክር ያስፈልጋል ይላሉ። የልሂቃን ምክክር ወሳኝ ነው። ሁሉን ችግር በአንዴ ባንፈታም፤ ተከባብረን ተቀራርበን በር ዘግተን የምንወያይበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ በየአካባቢ የሚቀጣጠለው ቋያ እየጠፋ ይሄዳል። ይህ ሁሉ በአገሪቱ የሚታየው ቀውስ በአገሪቱ ልሂቃን ተከባብሮና ተቀራርቦ መወያየት ባለመቻሉ የመጣ ነው።

ስለዚህ እንደዛ ዓይነት መድረኮች መንግሥት ለይስሙላ ሳይሆን በሀቅ፣ ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መንገድ ኃላፊነት ወስዶ ማመቻቸት አለበት። ሁላችንም እናልፋለን፤ የተወሰነ ዘመን ነው ምድር ላይ የምንኖረው። ከምድር ገጽ ከተወገድን በኋላ ግን የማይወገድ ታሪክ ለልጆቻችን የሚያኮራ ነገር ጥለን ነው ማለፍ ያለብን። እንደ አንድ ትውልድ የዛሬ መቶ ዓመት የት እናድርሰው ብለን፣ የተለያዩ ልዩነቶች ቢኖሩን እንኳ በመሠረታዊ ሐሳቦች ተግባብተን ይህን አገር ወደፊት ይዘን መሄድ እንችላለን። እንደዚህች አገር መሥራች አባቶች ሆነንም ልንቆጠርና እንደ ትውልድ ሞገስ ልናገኝ አንችላለን።

የማይፈቱ ልዩነቶች ካሉን ደግሞ፣ እነዛን ወደ ሕዝብ ውሳኔ የምንወስድበት መድረክ ማዘጋጀት ይጠበቃል። በአፈሙዝ ሰውን እንጂ ሐሳብን መግደል አይቻልም። የሞኝ ሥራ ነው። በዚህ በሠለጠነ ዘመን በዚህ መንገድ በአፈ ሙዝ ለመሸናነፍ የምናደርገው ትግል የትም አያደርሰንም። ሁላችንም እንደ አገር እንደ ሕዝብ የምንሸነፍበት ሁኔታ ነው ያለው።

እና እዚህ ሁለት ነገሮች ላይ ብናተኩር። መንግሥት በችግሩ መጠን ራሱን ቢያዘጋጅ፤ መድረኮችን ቢያመቻች። ልሂቃን ደግሞ ለመወያየት ቢቀመጡ። ጀግንነት ያ ነው። በዚህ ዘመን የጀግንነት ጥግ ሐሳብን በግልጽ አቅርቦ መወያየትና የሌላውንም ለመስማት መድፈር ነው ብዬ አስባለሁ።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል? መፍትሄውስ ምን ይመስልዎታል?
አንዳንዱን የሚሰማህን ነገር በቃላት አትገልጸውም፤ ስሜት ነው። ይሰማህል። በምናብ ታየዋለህ ግን ያ በምናብ የምታየውንና በስሜት የሚሰማህን ነገር በቃላት አቀናጅተህ ማቅረብ ከባድ ነው።
አሁን ያለው ነገር፤ አንደኛ የገባንበት የልጆቻችን ደም በግራና በቀኝ የፈሰሰበት አውዳሚ ጦርነት አለ። መለስ ብለን ብናወራው ብዙ ነውና አልገባበትም።

ኹለተኛ ጦርነት የማይሸከም ኢኮኖሚ ነበር የነበረው፤ በግድ አሸከምነው። አሁን ያ ኢኮኖሚ ትቢያ ላይ እንደወደቀ፣ እየተፍገመገመ ነው የሚታየኝ። የዋጋ ግሽበትና ያንን ለማተካከል የሄድንበት መንገድ ሁሉ በጣም የተበላሸ ነው።

ከዛ ደግሞ መጥኖ መጉረስ የማይችል መንግሥት ነው ያለው። ቅድሚያ ለምን መስጠት አለብኝ ብሎ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየት የተሳውና እንደው ዝም ብሎ ስሜታዊነት የበዛው ነገር አለው። ለምሳሌ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን እንደማሳያ ብንጠቅስ፤ የወጣበትና ምን እያገኘንበት ነው ብለን መጠየቅ ነው። ዘይትና ስኳር፣ ዳቦ እንኳ ለሕዝቡ በቅጡ ማቅረብ የማይችል መንግሥት፤ ያ ነገር (ፕሮጀክቱ) ምን ገንዘብ አስገኘ፣ የቱ ነበር የሚቀድመው። በሂደት ደግሞ ካፒታልህን እየወሰድክ፤ ማኅበረሰብ ልማት ላይ፣ ሥራ አጡን ሥራ የሚያሲዙ ሂደቶች ውስጥ ባልገባህበት ወቅት፣ እንዲህ ትልልቅ ለታይታ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን ማድረግ፤ ኢኮኖሚውን ያነቃቃዋል ወይ፣ ያነሳሳዋል ወይ ካልከው አይመስለኝም። እየወደቀ ነው ያለው።

እና የተወሳሰበ አገራዊ ችግር ነው ያለው። ልዩነታችንን በውይይት የመፍታት ጅማሮ ቢኖርም፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች ተገፍተዋል። በኢትዮጵያ ትልቅ ልዩነት አለን የሚሉት በውይይቱ ቀርበው የመወያየት እድሉ አልተጀመረም። አሁንም ከአፈሙዝ ውጤት ይገኛል ተብሎ በግራ በቀኝ ፉከራ እና የጦርነት ድግስ እየተደረገ ነው ያለው።

የቀጠናውን ሁኔታ ስታይ በጣም አሳሳቢ ነው። ከግብጽና ሱዳን ጋር ያለው ውጥረት፣ ከኤርትራ ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ስታይ ጥሩ ሁኔታ አይታይም። በሶማሌም እንደዛው። ብቻ ዙሪያ ገባውን ስታይ፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ እንደ መልኅቅ አገር የምትታይ አገር ነበረች፤ በዲፕሎማሲም ደረጃ ቢሆን ኢትዮጵያ በፊት የነበራት ክብርና ስም ተጠብቋል ወይ ብለህ ራስህ ጠይቀህ ራስህ መመለስ ትችላለህ። በብዙ ውጥረት ውስጥ ያለች አገር እንደሆነች ይሰማኛል።

የሚሰማኝን በሚገባ አልገለጽኩትም። ግን ችግሮች አሉብን። ለዚህ ሁሉ የመጀመሪያው መፍትሄ ብዬ የማስበው የፖለቲካ መረጋጋት ነው። የፖለቲካ መረጋጋት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ መረጋጋትን ያመጣል። እሱን ተከትሎ መጠናከር ሲመጣ አገራት ያከብሩሃል፤ ዲፕሎማሲ ያድጋል። ማንም ተነስቶ ድንበርህን ወርሮ አገሬ ነው አይልህም። በክብር መደራደር ትችላለህ።

የፖለቲካ መረጋጋት የሌላውንም መረጋጋት ይዞ ይመጣል። እና መፍትሄው እሱ ነው ብዬ አምናለሁ። ለዛም በሁሉም ወገን ተወያይቶ፣ እንደ አንድ ትውልድ ይህን አገር ለሚመጡት መቶ ዓመታት የት እናድርሰው ብሎ ቆሞ የሚያስብ፣ ከምንም በላይ ትውልድና አገርን የሚያስቀድም የፖለቲካ ልሂቃን ስብስብ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች