የፌዴራል መንግሥት ሕወሓት “ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሐሰት ትርክቱ ነው” ቢልም፣ ከተለቀቁት ሰዎች ውስጥ በሕወሓት ተማርከን ነበር የሚሉ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ከተለቀቁ የመከላከያ አባላት ቤተሰብ ሠምታለች።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሓት ለአራት ሺሕ ምርኮኞችን ምኅረት አደረኩ ብሎ የለቀቃቸውን ሰዎች ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢ መሸኘቱ የሚታወስ ነው። ሕወሓት በሰቆጣ በኩል ወደ አማራ ክልል የሸኛቸው አራት ሺሕ ሰዎች ግንቦት አጋማሽ ሰቆጣ መግባታቸውንና ሕወሓት ከለቀቃቸው ሰዎች መካከል፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩና የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ከመውጣቱ በፊት በሕወሓት የተማረኩ የሠራዊት አባላት አሉበት።
በሕወሓት ተሸኝተው አማራ ክልል የገቡ የመከላከያ አባላት ሰቆጣ እንደገቡ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ደውለው መለቀቃቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ የመከላከያ አባል የነበሩ ቤተሰቦቻቸውን ያገኙትን ሰዎች አነጋግራለች።
የመከላከያ አባል የነበሩና ሕወሓት ከለቀቃቸው ሰዎች መካከል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአክስታቸውን ልጅ ያገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደገለጹት፣ መከላከያ ሠራዊት አባል የነበረ የአክስታቸውን ልጅ ከ10 ወራት በኋላ ከተለቀቁት ወታደሮች መካከል አንዱ መሆኑንና ሰቆጣ መግባቱን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
መከላከያ ከሕወሓት ጋር እየተዋጋ ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል በቆየበት ወቅት ተንቤን አካባቢ በግዳጅ ላይ እንደነበርም የአዲስ ማለዳ ምንጭ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ፣ መንግሥት ሰኔ 21/2013 ለትግራይ ሕዝብ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጃለሁ ብሎ መከላከያን ከትግራይ ሲያስወጣ፣ የአስክስታቸው ልጅ አለመመለሱንና ለ10 ወራት ይኑር ይሙት ቤተሰቡ የሚያውቀው ነገር እንዳልነበር አስታውሰዋል።
ሕወሓት ከለቀቃቸው ሰዎች መካከል ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ በአፋርና በአማራ ክልል ጦርነት ባካሄደበት ወቅት አፍኖ የወሰዳቸው የሚሊሻ አባላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሲቪል ሰዎች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ከተለቀቁት የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል ከሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ በሕወሓት ታፍነው ወደ መቀሌ ተወስደው የነበሩ ግለሰብ ከተለቀቁት ሰዎች መካከል ተገኝተዋል። ከተለቀቁት ግለሰብ ጋር በሕወሓት ታፍነው የነበሩ ተጨማሪ አራት ሰዎች ይኑሩ ይሙት እስከ አሁን የታወቀ ነገር የለም።
ሕወሓት በሰቆጣ በኩል የሸኛቸው ምርኮኛ የነበሩ የሠራዊት አባላትና ሲቪል ሰዎች፣ ሰቆጣ እንደደረሱ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ደውለው መለቀቃቸውንና ሰቆጣ መግባታቸውን ከገለጹ በኋላ የት እንደሚገኙ እንደማያውቁ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ያነጋገሩ ሰዎች ጠቁመዋል።
ሰቆጣ የገቡ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሰዎች፣ ከሳምንት በፊት ሌሊት በመኪና ተጭነው ወደ ላሊበላ መስመር እንደተጓዙ አዲስ ማለዳ ከሰቆጣ ከተማ የዐይን እማኞች ሰምታለች።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሳምንት “በሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም” በሚል ርዕስ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ “ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሐሰት ትርክቱ” ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው ማጭበርበር ነው ማለቱ የሚታወስ ነው።
መንግሥት በበኩሉ አደረኩት ባለው ማጣራት፣ “በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሠራዊቱ ቤተሰብ አባላት ናቸው” ብሏል።
አገልግሎቱ አክሎም “ከልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሥራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ኃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ሥም አሰልፏቸዋል” ነው ያለው።
ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014