መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅሕግን በሕገወጥ መንገድ ማስከበር አይቻልም!

ሕግን በሕገወጥ መንገድ ማስከበር አይቻልም!

ሕግ የሚወጣውና መተዳደሪያ እንዲሆን የሚደነገገው ኅብረተሰቡ ፍትኃዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀምበት ነው። ለማኅበረሰቡ ሕይወት ሲባል ይጠቅማል ተብሎ ሕዝቡ ተስማምቶ እንዲፀድቅ መደረግ የሚኖርበት ሕግ፣ ማገልገያ እንጂ መገልገያ መሆን እንደማይገባው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ሕግ ወጥቶ በጽሑፍ ብቻ እንዳይቀር ተፈጻሚ የሚያደርገው የመንግሥት አካል እንዲኖር ቢደረግም፣ ይኸው አካል ፍትኅ እንዲኖር በማድረግ ፋንታ ሚዛን መሆን የነበረበትን ሕግን እንደጦር መሣሪያ ማጥቂያ ሲያደርገው ይታያል። ሕግን “አስከብራለሁ” እያለም መሠረታዊ የሕግ ፅንሰ ሐሳቦችንም ሆነ ድንጋጌዎችን በሚጥስ መልኩ “ሕግን አክብሩ” ብሎ የሚያስንቅበት እርምጃው፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለ የሕግ ተቀባይነት እንዲቀንስና ስርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ ሆን ብሎ የሚገፋፋበት መሆኑ በተግባር እየታየ ይገኛል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል እንደትግራይ ክልሉ ጦርነት “የሕግ ማስከበር እርምጃ ነው” በተባለው ዘመቻ፣ በርካታ ከመንግሥት የማይጠበቁ ተግባሮች መፈፀማቸው ሲነገር ቆይቷል። ከዚህ መካከል የአንድ ዓመት ጨቅላ ሕፃንን አፍኖ የመውሰድና ለ6 ቀናት እስር ቤት የማቆየት ተግባር በዋናነት ይጠቀሳል። ሕፃኑ ሕግን አላከብር አለ ተብሎ ሳይሆን የተያዘው፣ ከተማ የሌለ አባቱ መጥቶ እጁን እንዲሰጥ ለማስገደድ ነው። በሚሳሱለት እየመጡ የሚወዱትን ማጥመጃ ማድረግ ለማንም ቢሆን አሳፋሪ ነው።

ምንም የማያውቅ ሕፃን የሚንከባከበው ቤተሰብ እያለው፣ የማያውቃቸው ታጣቂዎችም ሆኑ ታሳሪዎች ጋር እንዲሰነብት ማድረጉ በምንም መለኪያ ለእሱ ታስቦ ነው ማለት ሕዝብን ከመናቅ ምንም አይተናነስም። እንዲህ ዓይነት እንቦቀቅላን ለፖለቲካ መጠቀሚያ አልያም እንደተባለው ለ‹ሕግ ማስከበሪያ› ማዋል፣ በዓለም ዐቀፍ ሕግም የሚያስጠይቅ ሕሊና ቢስ ተግባር መሆኑ ግልፅ ነው።

ቤተሰብ የሌለው ባለሥልጣንም ሆነ ተራ ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር እየታወቀ፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል ያሉ ግለሰቦች ችግሮቻቸው ከራሳቸው አልፎ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊተላለፍ አይገባም።

ወላጅ ባጠፋው ልጅ የማይጠየቅበት የበለፀገ የጥንቱን አስተሳሰባችንን ጥለን ዘመናዊ ለመባል በምንጥርበት በዚህ ወቅት፣ የስብዕናችንን መቆሸሽ የሚያሳይ የአስተሳሰብ ድህነታችንን ለዓለም እያንፀባረቅን እንደምንገኝ የአዲስ ማለዳ እምነት ነው። ጨቅላ ልጅ በጠላትነት ተፈርጆ ወህኒ የሚወርድበት ዘመን ላይ ከደረስን ጠላት የምንላቸውን ሰብዓዊ መብት ለማክበር ምን ያህል እንደማንችልም አመላካች ነው።

ይህ ዓይነት የማፈኛ እገታ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ለመረጃ ቅርብ የሆነ ሁሉ ያውቀዋል። ሰሞኑን ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌለበት በዚህ ወቅት ከቤቱ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ለመያዝ የተገኙ የፀጥታ አካላት ናቸው የተባሉ አሳሪዎች፣ እሱን ቢያጡ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻቸው ምንም የማትፈለግ እህቱን አግተው እሱን ማሰሪያ መሣሪያ እንዳደረጓት ተነግሯል።

ይህ ዓይነቱ እርምጃ የመጀመሪያ አለመሆኑን የሚያመላክቱ የኢሕአዴግ ዘመን በርካታ ተግባራት መኖራቸው ይታወቃል። ሥም በመቀየር ብቻ አሁንም ድረስ በኃላፊነት ላይ ያሉ ሹሞችን ባህሪ መቀየር ባይቻልም ቢያንስ ትንሽ ማሻሻል በተገባ ነበር።

አንድ ሰው ባጠፋ ቤተሰብ ላይ በደል መፈፀም እኛ አገር ብቻ ሳይሆን በእስራኤልም ተፈፃሚ እንደሚሆን ይሰማል። የሽብር ተግባርን የፈፀመ ሰው የቤተሰቡ ቤት ጭምር እንዲወድምበት በማድረግ ከሽብሩ ተግባር በተገኘ ሀብት ቤተሰቡ እንዳይጠቀም ለማድረግ በሚል ሽፋን ሌላውም በምሬት ወደጥፋት እንዲገባ በሚደረገው በእንዲህ አይነቱ ትግበሯ፣ አገሪቱ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ስትኮነን ይሰማል። እሷ ላቷን ውጭ የምታሳድርበት የተማመነችበት ኃይል ቢኖራትም፣ እኛ አገር ግን ከደም መቃባት ባሕላችን አኳያ እንዲህ ለትውልድ ቂምን የሚያተርፍ ተግባር ላይ ባንገባ ይመረጣል።

ምንም ጥፋት ባላጠፋ ቤተሰብ ላይ የሚፈፀም ግፍ እነሱን እንደመያዣነት በማሰር ብቻ አይደለም የሚከናወነው። የሚፈለግን ግለሰብ ሰዋራ ቦታ ጠብቆ አፍኖ በመውሰድ ቤተሰብ እንዳያገኝና ያለበትን አለማሳወቅ የሚጎዳውም ታሳሪውን ብቻ አይደለም። ይልቁኑ የቤተሰባቸው አባል የት እንደቀረ የማያውቁት ቤተሰቦችን ጭምር በሐሳብ ማሰቃየት በመሆኑ፣ በአስቸኳይ መቆም ያለበት በሕግ የተከለከለ ተግባር መሆኑን አዲስ ማለዳ አፅንኦት ሰጥታ ትናገራለች።

ጦርነት በዋናዋ ከተማ ያለ ይመስል ያለምንም ሕጋዊ መንገድ ድንገት በጎዳና ላይ በመንግሥት ታጣቂዎች የሚደረግ የእስርም ሆነ የአፈና ተግባር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን ሪፖርት እንደግብዓት በመውሰድ መሻሻል የነበረበት የመንግሥት አካል፣ እየባሰበት ሲሄድ ማየቱ መጨረሻው ምን ይሆን? እኛንስ ምን ላይ ይጥለን ይሆን ብሎ ኅብረተሰቡ እንዲሰጋ ማድረጉም ከግምት ሊገባ ይገባል።

በማናለብኝነት የሚካሄዱ የማስፈራራትም ሆነ ተቀናቃኝን የማስወገድ ተግባር አርቆ ሊታሰብበት በተገባ ነበር። ጫካ የገቡ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ምንም ያህል ጊዜ ይፍጅባቸው ያሰቡትን ከማሳካት የሚያግዳቸው እንደማይኖር ከትህነግ ታሪክ መማር ከባድ ሊሆን አይገባም።

“ሕግ ለማስከበር” በሚል ኃላፊነቴን አሁን ካልተወጣሁ ብሎ ውጥረት ውስጥ አገሪቷን የከተተው መንግሥት፣ ከአራት ሺሕ በላይ ዜጎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ቢናገርም፣ ስለአያያዛቸውም ሆነ ስለሚደረግላቸው አስፈላጊ እንክብካቤ ያለው የለም። የተያዙት ሰዎች ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ግን ድንገት ታፍነው ለእስር የበቁት ወዳጅ ዘመዶቻቸው የት እንዳሉ አያውቁም፣ አልያም እንዳይጠይቋቸው ለማድረግ ሩቅ ቦታ እየወሰዱ እንደሚያስሯቸው ነው።

ይህ የማሰሪያ ቦታ ጉዳይም በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ማቅረብ ይገባል እንደሚለው ድንጋጌ ተፈፃሚ መሆን ያለበት የሕግ ፅንሰ ሐሳብ ነው። ይህን የመሳሰሉ ሕገወጥ ተግባሮችም ሕግን ለማስከበር እንደማያገለግሉ ሕሊና ያለው ሁሉ ይረዳል። በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ማስረጃ ፍርድ ቤት መቅረብ አይችልም የሚለው የሕግ ፅንሰ ሐሳብ ባለሙያዎችን ቢያከራክርም አብዛኞቹ ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባውም በሚለው ይስማማሉ።

የፀጥታ አካላት ሕግ ማስከበር በሚል የዳቦ ስም ሕገወጥ ተግባርን ፈፅመው ያገኙትን ሰውም ሆነ ማስረጃ ፍርድ ቤት አቅርበው ተቀባይነት ቢያገኙ፣ ነገ ምንም ቢያደርጉ አልታዘዝ ያላቸውን ዳኛ ጭምር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከወዲሁ ማሰብ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች