መነሻ ገጽዜናወቅታዊግንቦት 20ን በምልሰት

ግንቦት 20ን በምልሰት

‹ግንቦት 20፤ 1983 ማለዳ ላይ የኢሕአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። መንግሥት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ስርዓት ከውሉ ሲለወጥ፣ የተሰማው ተኩስ ጥቂት ያንገራገሩ የመንግሥት ጠባቂዎች ከድል አድራጊው ጦር ጋር ያደረጉት የተኩስ ልውውጥ ብቻ ነበር።›
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት የታሪክ መጽሐፍ የመጨረሻው ምዕራፍ የመጨረሻው ገጽ ላይ የሚገኝ አንቀጽ ነው።

ግንቦት 20/1983 ኢትዮጵያ በፖለቲካው የተነሳ አዲስ ምዕራፍ የገለጠችበት እለት ሆነ። አዲሱ ምዕራፍ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውን ለማየት ከግምት ባለፈ 30 የሚሻገሩ ዓመታትን ገልጦ ማየት አስፈላጊ ሆኖ ነበር። ግንቦት 20ም በ1983 ከፈጠረው ስሜት ይልቅ፣ ከዓመታት በኋላ ‹ፍሬው ምንድን ነው? ምን አስገኘ?› በሚለው ጥያቄ መሠረት እየተመዘነ አከራካሪና አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

እንደሚታወቅው እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ ግንቦት 20 በመንግሥትና በመንግሥት ተቋማት በድምቀት የሚከበር በዓል ነበር። ያም ሆኖ ተቃዋሚና ብዙ ምክንያት ደርድረው ‹የለም! እንደ ድል ቀን መከበር የለበትም› የሚሉ ጥቂት አልነበሩም። በሌላ በኩል ለሕዝብ ብዙ ዋጋ የተከፈለበትን ታሪክ የሚያስታውስ ነው የሚሉ አሉ። እነዛም ቢሆኑ ግን በአንድ ቡድን የሥልጣን ጥመኝነት የተነሳ የመከነ ነው በሚል መከበሩ ትርጉም እንደሌለው ይናገራሉ።

ይከበር አይከበር የሚለው ሙግት ይቆየንና፣ እንደው ነገሩስ በጠቅላላው የግንቦት 20/1983 የመንግሥት ለውጥ እንዴት ይታያል? ለኢትዮጵያስ ምኗ ነው? የሚለውን እንቃኝ። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችና ፖለቲከኞች፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ቀርበው ስለ ግንቦት 20 የተናገሩትንና ያሉትን ለማስታወስ ሞክራለች። ይልቁንም ከኹለት ዓመት በፊት በጉዳዩ ላይ ብዙ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ተሰምቷልና ከዛ በማጣቀስ እናውሳ።

ሰዎቹ ምን ይላሉ?
በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ከሰጡት መካከል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኦባንግ ሜቶ ይገኙበታል። በእርሳቸው ዕይታ ግንቦት 20 የድንጋይና የሲሚንቶ ድልድዮችና መንገዶች ይሠሩ እንጂ የሰላምና የአንድነት መንገዶች የፈረሱበት ነው።

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ በኋላ፣ ‹በሱ አትምጡብኝ፣ ዐይኔ ነው› የሚለው የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ጉዳይ ነው። ይህም ብዙዎች እንዲቀበሉት፣ እንዲያመሰግኑት ከዛም አልፎ ትግሉን እንዲቀላቀሉለት የገፋፋቸው መንስኤ ሆኖም ነበር። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ፍሬው ሲታይ፣ የተወራለትን ያህል አልሆነም። ኦባንግም ይህን ነጥብ ነው ያነሱት። በተለይ ኢሕአዴግ ከመነሻው ጀምሮ ለሥልጣንና ለውስን ሰዎች ጥቅም የቆመ መሆኑ መታየቱና ክልሎችም ቢሆን በነጻነት ራሳቸውን ያስተዳድሩ እንዳልነበር ነው የተናገሩት።

ከሁሉም በላይ ኦባንግ በዋናነት ደጋግመው ያነሱ የነበረው፣ ፎቅና መሬት ላይ ጥሩ ተሠርቶ በማኅበራዊ እሴቶችና ሕዝብን ባስተሳሰሩ ታሪኮች ላይ የደረሰውን ጥፋት ነው። ስለዚህም የተከፈለለትን ዋጋ ያህል ያልተሠራበት ምዕራፍ ነው ሲሉ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረው ነበር።
አንዳርጋቸው ጽጌም ይህን ሐሳብ በብዛት ይጋራሉ። አንዳርጋቸው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነበር፣ ‹የግንቦት 20 በዓል ከመንግሥት ለውጥ ባሻገር በሕዝብ የሚፈጸመውን ግፍና ጭቆና አላስቀረም› ሲሉ የተናገሩት። አልፎም እለቱ በአደባባይ የምንደሰኩርበት ሳይሆን አንገታችንን ሊያስደፋን የሚገባ ነው ሲሉ ነው ዕይታቸውን የገለጹት።

እንደውም ኢሕአዴግ በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት በአገሪቱ ተገኘ የሚባለው ልማትም ኢሕአዴግ በሥልጣን ከቆየበት ጊዜ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል። እናም ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲጋጭ የተደረገበት፣ በስደት ያለው የተገለለበትና በከፍተኛ ደረጃ አገርና ሕዝብ የተዘረፈበት በመሆኑ ‹ጥቁር ነጥብ የጣለ› እለት/በዓል ነው ብለዉታል።

የሶማሌ ከልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው፣ ግንቦት 20 ለክልሉ ካስገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል። <<ግንቦት 20 ለሶማሌ ክልል ሕዝብ በቋንቋው ከመማርና ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፀጥታ ችግር በመፍጠር መጥፎ አሻራ ያሳረፈ ነው።>> ሲሉ ነው የገለጹት።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ የታዩ ለውጦች እንዳሉ ቢያምኑም፣ የስነልቦና እና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ይበረታል ባይ ናቸው። ሥርዓቱም በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሲያራምድ የነበረው ሕዝብን ከሕዝብ የማናከስና የጥላቻ ፖለቲካ እንደነበር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለመጠይቅ አመልክተዋል።
ከዚህ በተለየ ለግንቦት 20 የተከፈለው መስዋዕትነት በሥልጣን ወዳዶች የተነሳ መክኗል ያሉት ደግሞ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት የተነሳ በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ባለመቻሉ ለግንቦት 20 ድል የተከፈለው መስዋትነት መባከኑን ነው የተናገሩት።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ወጣቶች ጫካ ገብተው መራራ ትግል በማድረግ የደርግን አገዛዝ ቢጥሉም፤ በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት የተነሳ የተከፈለው መስዋዕትነት ሊመክን ችሏል ነው ያሉት።

<<ከዘውዳዊው አገዛዝ ማብቂያ ማግስት ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት የመጡ አገራዊ ለውጦች በዋናነት የከሸፉት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱና የአንድ ቡድን የበላይነት በአገሪቱ በመንገሡ ነው።>> በማለት የተናገሩት መረራ፣ ወደቀደመው ጊዜ መለስ ብለው እንደሚከተለው አስረድተዋል፣

<<በንጉሡ ዘመነ መንግሥት በዋናነት የወጣቱ ጥያቄ የእኩልነትና መሬት ለአራሹ የሚል ነበር። የዚያ ዘመን ወጣቶችም ዋጋ ከፍለው የንጉሣዊ ሥርወ መንግሥትን ከጫንቃቸው አሽቀንጥረው ቢጥሉም የመጣውን ለውጥ ደርግ ነጥቆ የራሱን አብዮት ለ17 ዓመት አካሂዶበታል። ደርግም ወደ ሥልጣን ሲመጣ መሬት ለአራሹ የሚለውን ጥያቄ በገደምዳሜው ቢመልስም፤ በ17 ዓመቱ አብዮት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱና የአንድ ቡድንን የበላይነት በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመጣል ሲደረግ በነበረው ግብ ግብ፣ የአገሪቱ ብርቅዬ ልጆች ተሰውተዋል፤ ብሔር ብሔረሰቦች ተጨፍልቀዋል፤ የእምነትና የፖለቲካ ነፃነት ተገፏል።

ወጣቶች ጫካ ገብተው መራራ ትግል በማድረግ የደርግን የጭቆና አገዛዝ ገርስሰው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሰፊው ሕዝብ አጨብጭቦ ቢቀበላቸውም፤ ተጨቁነናል ብለው ጫካ ገብተው የታገሉ ሰዎች ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከትላንት ታሪክ ሳይማሩ የጠባብ ቡድንን ስሜትና ፍላጎት በሰፊው ሕዝብ ላይ ለመጫን ባደረጉት ጥረት ወደ ጨቋኝነት ተሸጋግረዋል።>> ሲሉ ነው የተናገሩት።

ከንጉሡ አገዛዝ መጨረሻ ጀምሮ ኢትዮጵያ በችግር ላይ ችግር የሚደራረብባት የፖለቲካ ጥያቄ ባለመፈታቱ እንደሆነ ነው ፕሮፌሰር መረራ የሚያምኑት። ከታሪክም በአገሪቱ የአንድ ቡድንን የበላይነት ለማስፈን የሚደረግ ጥረት አገርን ያፈርስ እንደሆን እንጂ ማንንም አትራፊ እንደማያደርግ ማወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
<<አገር በአንድ ቡድን ፈቃድ ብቻ አገር አትሆንም። አገር እንድትሆን ሁሉም የሚሳተፉበት እና አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትንም ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። ለዚህ ደግሞ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።>> ሲሉ አመልክተዋል።
በአንጻሩ ከሁለት ዓመት በፊት በ2012 ግንቦት 20ን በሚመለከት መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፣ እለቱ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ እለታት አንዱ ነው ሲሉ ነበር የገለጹት።

‹‹ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትኃዊ እና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ሰውተዋል። የግንቦት 20 ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትኀዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው። ግንቦት 20ን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት።›› ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አያይዘውም ግንቦት 20 ሲታሰብ፣ ‹‹በተባበረ ክንድ ከግንቦት 20 የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደርግ ምጡቅ ስርዓት ለመገንባት ቃላችን የምናድስበት እና ወደ ላቅ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል>> ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ ወደ ግንቦት 19 የተመለሰች ይመስላል። አንዳንዴ ለውጥ ነውጥ አያጣውም በሚል ብዙ ችግሮች የለውጥ ሂደት አካል ናቸው ቢባልም፣ አሁን ላይ በዛ መልክ ለማሰብ በማያስችል ሁኔታ ኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተገኝታለች።

በድምሩ ግንቦት 20 ያስገኘው ውጤት እንዳለ ሁሉ የሚኮነንበትም ችግር ብዙ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ለኢትዮጵያ ጥቅም አምጥቷል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከአገር ፍቅር አንጻር የለም እንደውም ደርግ ሳይሻለን አይቀርም ነበር የሚሉም ብዙ ናቸው። ያም ሆነ ይህ ግን የሰው ሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት እንደሆነ ሁሉም ይስማማል።

የግንቦት 20 ለውጥ በመጋቢት 24 ለውጥ ተተክቷል። ከእነዚህ ለውጦች መረዳት የሚቻለው አንድ ነገር፣ ለውጥን ከማምጣት ባለፈ እና በላይ ማስቀጠልና በተነሱበት ዓላማ ዘልቆ መቆየት ነው ከባዱም ወሳኙም ጉዳይ። በተለያየ ጊዜ የለውጥና የአዲስ ምዕራፍ ወጋገን ለማየት የቻለችው ኢትዮጵያ፣ ያቆይልሽ ይርሳብሽ ተብላ የተመረቀችበት ለውጥ ያለ አይመስልም። ኢትዮጵያ በተስፋ አሁንም ጉዞ ቀጥላለች፣ ለውጥ ደግሞ የጉዞ አንዱ አካል ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች