መነሻ ገጽአምዶችዓውደ-ሐሳብቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት ሙስና እና የዋጋ ግሽበት

ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት ሙስና እና የዋጋ ግሽበት

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተብሎ በድፍረት ሊጠቀስ በሚችል ውስብስብና በርካታ ችግር ውስጥ ትገኛለች። ሰላም ማጣትን ተከትለው የሚመጡ ጦሶች ሁሉ ደርሰዉባታል፤ አሁንም እነዛኑ እየታገለች ትገኛለች። መምህር እውነቱ ይታይ ከአዲስ አበባ ባሰፈሩት አጠር ያለ ጦማር ደግሞ፣ በተለይ ለዋጋ ግሽበትና አሁን በኑሮ ላይ ለተፈጠረው ጫና ከምክንያቶች ሁሉ ልቆ ያለው ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት ነው ሲሉ እንደሚከተለው አስፍረዋል።


የዋጋ ግሽበት በአጭሩ የገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስና የሸቀጦች ዋጋ ንረት ነው። የዋጋ ግሽበት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የገቢና ወጪ ንግድ ሚዛን መዛባት፣ የምርትና ምርታማነት መቀነስና፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የብር ኖት መታተምና በገበያ ውስጥ መሰራጨት፣ ከፍተኛ የሸመታ እቃዎች ፍላጎት እንዲሁም ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነትና ሙስና ናቸው።

ሌሎቹን ምክንያቶች ለጊዜው ትተን በአምስተኛው ላይ ብቻ እናተኩር፣ ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነትና ሙስና።

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅጥ ያጣ አባክኝነቱን በግልፅ እያሳየ ይገኛል። ለዚህም ከተለያዩ ምሁራንና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚሰጡትን ቅን አስተያየቶችን ሁሉ ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ‹የስርዓቱ ተቃዋሚዎች› በሚል ሲፈርጅ እንጂ አስተያየቶችን በቅንነት ተቀብሎ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ፍቃደኛ ሲሆን አልታየም።

ይህ በመሠረቱ አንድ መንግሥት ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ያለውን ንቀት “ምን ያመጣሉ” ባይነትን በግልፅ ከማሳየቱ በተጨማሪ፤ ለአንድ መንግሥት የውድቀቱ መንስዔዎች መካከል ነው ብንል እንደ ሟርት ሊቆጠርብን ይችላል፤ ግን እውነታው እርሱ ነው።

ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት ምንድነው?
ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት ማለት፣ መንግሥት ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሕዝብን ገንዘብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለሌላቸው ጉዳዮች ማፍሰስ ነው። መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ገንዘብ ማባከን ላይ ተጠምዷል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነውም ሃይ ባይ የለውም ወይም ሃይ ባዮቹን ለመስማት ፍቃደኛ አይደለም።

አባካኝነቱን ግልፅ ከሚያደርጉ ተግባራት መካከል አንደኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕንፃ ዕድሳት ተጠቃሽ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ለሕንፃው ዕድሳት 2.2 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጌያለሁ ሲል ይሉኝታም ሆነ ሃፍረት አልተሰማውም። እጅግ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው! እደግመዋለሁ የከተማ አስተዳደሩ ተግባር እጅግ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው!

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ‹ለሕዝባችን ያለንን ክብር ለማሳየት ነው በዚህን ያህል ወጪ ያደስነው› ብለዋል። እኛ ግን እንላለን ‹ለሕዝቡ ያላችሁን ንቀት ለማሳየት ነው! በቀን አንዴና ኹለቴ መብላት ብርቅ ለሆነበት ሕዝብ በዚህን ያህል ወጪ ሕንፃ ማደስ ለዚህ ምስኪን ሕዝብ ያላችሁን ንቀት፣ ‹ምን አባታችሁ ታመጣላችሁ፣ ሁሉ በእጃችን ነው እንደፈለግን ለማድረግ ሥልጣኑ አለን!› ማለታችሁን ነው የሚያሳው።›

ለመሆኑ 2.2 ቢሊዮን ብር ምን ያህል ነው፣ ምን ትርጉምስ ይኖረዋል? 2.2 ቢሊዮን ብር ቢያንስ ኹለት ደረጃቸውን የጠበቁ አጠቃላይ ሆስፒታሎችን ይገነባል፣ ኹለት ሆስፒታሎች ለአዲስ አበባ ሕዝብ ምን ጠቀሜታ ይኖራቸዋል? እንደሚታወቀው የጤና አገልግሎት ሽፋናችን እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉ አገራት አንዱ ነው።

በመሆኑም በከተማዋ ኹለት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች ቢገነቡ፤ ሥራ አጥተው የሚንከራተቱ 200 ዶክተሮችን እና 400 ነርሶችን ይቀጥራሉ፣ በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ 400 የድጋፍ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ በዓመት በአማካኝ ከ20 ሺሕ በላይ ሕሙማንን ያገለግላሉ። እነዚህ የተዘረዘሩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው 1000 ሰዎች ቢያንስ 5000 ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉ መሆናቸውን ልብ በሉ።

ተመልከቱ! ከዚህ የላቀ ኢኮኖሚያዊ፣ የጤና እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው ገንዘብ ነው ለአንድ ሕንፃ ዕድሳት የፈሰሰው። እድሳቱ ለሕዝብ ማለትም ለተገልጋዩ ጠቀሜታ በሚያመጡ ስርዓት (System) ላይ ኢንቨስት አለመደረጉ ደግሞ እጅግ በጣም ከማሳዘኑም በላይ የመንግሥትን ዓላማ ከጥያቄ ያስገባል።
በከተማዋ ዛሬም የተሻሻለ የአገልግሎት ዘርፍ የለም። መታወቂያ ካርድ በበጀት ዕጥረት ምክንያት በየወረዳዎቹ ለማግኘት የወራት ወረፋ ይጠብቃል። ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት መሰለፍና እጅ መንሻ መጠየቅ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ይህን ለማረጋገጥ አንድ ቀላል አገልግሎት ለመጠየቅ ወደ ወረዳው የሄደ ሁሉም ተገልጋይ እማኝ መሆን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ ሌሎች በርካታ የቢሮ ኃላፊና ምክትል የቢሮ ኃላፊዎችን ቢሮዎች ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ እያደሰ ይገኛል (ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል)።

እንግዲህ ተመለከቱ! ይሄ ሁሉ ወጪ ከዚሁ “ምን አባታችሁ ታመጣላችሁ ሁሉ በእጃችን ነው እንደፈለግን ለማድረግ ስልጣኑ አለን!” ከተባለው ምስኪን ሕዝብ በተለያየ መልኩ የተሰበሰበና አገልግሎትን ማሻሻል፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የጤና ተደራሽነትን ማሳደግ የመሳሰሉት ተግባራት ላይ መዋል የሚገባው ገንዘብ ነው። ያ ገንዘብ በእንዲህ ያለ መልኩ እየባከነና ለተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች አለአግባብ መጠቃቀም እየዋለ ይገኛል። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መልኩ ለዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ አስዋፅዖ ያበረክታል።

2.2 ቢሊዮን ብር በርካታ በእንጥልጥል የቀሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚረዳ ከፍተኛ ገንዘብ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን። በሌላው ዓለም እንዲህ ያለ በሕዝብ ገንዘብ (Tax payers money) ‘መባለግ’ (ለቃሉ ይቅርታ ግን ይሄ በሕዝብ ገንዘብ መባለግ መሆኑ ይታወቅ) በፍፁም የማይታሰብና የማይደረግ መሆኑንም እንዲታወቅ እንፈልጋለን። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ከዚህ ስህተቱ መማርና እራሱን ማረም ካልቻለ፣ ነገም በተመሳሳይ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው የሕዝብ ገንዘብ እንደሚያባክን መረዳት ይኖርብናል።

በሌላ መልኩ መንግሥት በርካታ ብልጭልጭ ፕሮጀክቶችን አቁሞ ለካፒታል ኢንቨስትመንት ማለትም ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉና ግብርናን የሚያዘምኑ እንዲሁም ትራንስፖርትና ሎጂስቲክሱን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ካደረገ የዋጋ ግሽበቱን በተወሰነ መልኩ እንኳን ለመግታት ይረዳል።
ሆኖም መንግሥት አሁንም ከፍተኛ በጀት የሚያፈሰው በብልጭልጭ ፕሮጀክቶች ላይ እና ለካድሬዎቹ ፈንጠዚያ በመሆኑ የዋጋ መረጋጋት ይመጣል የሚለው ተስፋችን ተሟጧል።

ቅጥ ያጣ የመንግሥት አባካኝነት በፌዴራልና ክልል ተቋማትም እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ተንሰራፍቷል። እጅግ በጣም ጥቂቶቹን እንመልከት። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየሳምንቱ (ድግግሞሹን ለማመልከት ነው) በሆነ ባልሆነው ምክንያት በአፄ ሚኒልክ የግብር አዳራሽ ይደግሳሉ፣ ይጋብዛሉ።
ለብልፅግና ፓርቲ አንደኛ መደበኛ ጉባኤ የታተሙ ባነሮች፣ ፖስተሮች፣ የነበረው ድግስ ፌሽታና ከበርቻቻ ፓርቲውንና መንግሥትን ከፍተኛ ትዝብት ላይ ከመጣሉ በተጨማሪ ፓርቲው ለሕዝብ ውግናና የሌለው፣ ኃላፊነት የማይሰማውና የይሉኝታ ቢሶች ስብስብ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል። በጦርነት ላይ የምትገኝ፣ በረካታ ዜጎቿ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉባት፣ ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ያለባትን አገራችንን ችግር ከድጥ ወደ ማጥ አድርጎባታል።

- ይከተሉን -Social Media

በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለሕንፃ ኪራይና ለቢሮዎች ዕድሳት ካወጡት ከፍተኛ ወጪ በተጨማሪ እጅግ በጣም ውድ ውድ ሬስቶራንቶችን በቅጠር ግቢያቸው ቦታ ሰጥተው ከሕዝብ በጀት ለራሳቸውና ለሠራተኞቻቸው ምግብ እንዲያቀርቡ አድርገዋል፣ የቢል ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ይታወቃል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ባለፈው ከሚያዚያ 25-30/2014 ለስድስት ተከታታይ ቀናት የተለያዩ የሀይማኖት ተወካዮችን፣ ባለሀብቶችን፣ አርቲስቶችንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ክፍለ ከተማ አመራሮችን በሸራተን አዲስ አንደኛ ደረጃ ብፌ ምሳ ጋብዟል። ወጪው በ100 ሚሊዮኖች እንደሚሆን ይታወቃል (በጀት ለመጨረስ በሚመስል መልኩ)።

በሚያሳዝን ሁኔታ በዚህ ወቅት ሆስታሎች ማደንዘዣ አጥተው ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማከናወን በጣም ተቸግረዋል። እንግዲህ ምን እንላለን ፈጣሪ የሆነብንን ይመልከት እንጂ።

በተጓዳኝ የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የክልል አመራሮች፣ የዞን አመራሮች የወረዳ አመራሮች የአበል፣ የነዳጅ፣ የተሽከርካሪ፣ የምሳና ሌሎች ወጪዎች፣ ከአገሪቱ የካፒታል በጀት እጅግ በጣም ይበልጣል። ይህ ማለት የዋጋ ግሽበቱ እጅግ በሚያስፈራ መልኩ ሊጨምር ይችላል ማለት ነው። ምክንያቱም እንደምንሰማው 442 በላይ አምራች ኩባንያዎች ተዘግተዋል። ጦርነቱ መቋጫ አላገኘም፣ በየአካባቢው ግጭትና ዘረፋ አለ። ምርታማነት በሚያስደነግጥ መልኩ ቀንሷል፣ የመንግሥት ካድሬዎች ወጪያቸው አገራችን ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ሆኗል።

በነገራችን ላይ እንደው ለምሣሌ ያህል እነዚህን ጠቀስን እንጂ መንግሥት ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ አመራሩ እጅግ በሚያሳፍርና ይሉኝታ የለሽ በሆነ መልኩ የሕዝብ ገንዘብ በማባከን ላይ እንደተጠመዱ የአደባባይ ሚስጥር ስለመሆኑ ማንም ሰው ማረጋገጥ ይችላል። በተለይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉ ወራት እነዚህ ማባከኖች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፣ ምክንያቱም በጀት ለመጨረስ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሙስናና የአሰራር ብልሹነት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ለማመን በሚያዳግት መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቷል። በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ያለ እጅ መንሻ (ጉቦ) አንድ ኢንች አይንቀሳቀሱም (በቅንነት ሕዝባቸውን የሚያገለግሉ አመራርና ሠራተኞችን ሳንዘነጋ፥ ለእነርሱ ፈጣሪ ብድራቱን አብዝቶ ይከፈላቸው)።

ለምሳሌ ከሦስት ዓመታት በፊት ዕጣ የወጣባቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች በርካቶች እስካሁን ባለመጠናቀቃቸው ለባለ ዕድለኞች አልተላለፉም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይ በኮዬ ፈጬ ሳይት የቤቶች ልማት አመራሮችና ሠራተኞች ለሥራ ማስፈፀሚያ ለኮንትራክተሮች ከሚለቀቀው በጀት እስከ 10% ለእነርሱ እጅ መንሻነት ካልተሰጠ ገንዘቡን እንደማይለቁላቸው በግልፅ እንደጠየቁ ማስረጃዎች አሉ። ይሄ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት የተለመደ ተግባር መሆኑን ልብ በሉ። ሆድ ይፍጀው ነው!

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚወጡ ጨረታዎች፣ በትውውቅ፣ በኮሚሽንና በዝምድና ለሆነ አካል የተሸጡ ናቸው። የፕሮጀክቶች ውጤታማ አፈፃፀም የሚታየው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ነው። የአቃቂ-ቃሊቲ ማሠልጠኛ አስፋልት ሥራ ፕሮጀክት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም ይኸው ከተጀመረ ከ5 ዓመታት በኋላ እንኳን አፈፃፀሙ ከ50% አልበለጠም።

በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍና ለማበረታታት የተዘጋጁ ፈንዶች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለሚፈልጓቸው ቡድኖች ይከፋፈላሉ፣ አንዳንዴም በሌለ ኢንተርፕራይዝ ሥም ገንዘቡ ይበላል።
ስለዚህ መንግሥት ሆይ! እባክህ ስማ! ከዚህ ምስኪን ሕዝብ ላይ በተለያዩ መልኩ የተሰበሰበውን ገንዘብ እንዲህ ባለ ይሉኝታ በጎደለው መልክ ማባከን አደጋው ለራስህ መሆኑን እወቅ። ሕዝብህን አትናቅ። እንዲህ ቅጥ-ላጣው አባካኝነትህ ልጓም አበጅለት!


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች