መነሻ ገጽሌሎችማኅበረሰብ አንቂ – የተከፈለበትአገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል

አገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል

ርዕይውን የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የበለጠ ተስማምተው እና ትርጉም ያለው ውህደት ሲኖሩ ማየት ያደረገው የብሔራዊ እና ቀጠናዊ ውኅደት ጥናት ማዕከል (Center for National and Regional Integration Studies/CeNRIS/) ሰኔ 14 ቀን 2011ዓ/ም አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሆኖ ተመሰረተ።

የጥናት ማዕከሉ በዋናነት በአገር ዐቀፍና በክፍለ አህጉር ደረጃ በሰላምና መግባባት፣ በዴሞክራሲና አካታችነት ላይ እንዲሁም ፖሊሲ አግባብነት ያላቸውን የምርምርና ፕሮጀክቶች ዙሪያ በትኩረት በመሥራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት ሐሳቦች የብሔራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ውህደት ጥናት ማዕከልን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።


የትውልድ ቅራኔን መፍታት

የበለጸጉ አገራት የኋላ ታሪክ እንደሚያሳየው በትውልድ መካከል ለተፈጠረ ክፍተት በዋናነት እንደመነሻ የሚወሰዱት የሀብት ክፍፍል፣ የማንነት ጥያቄዎች እንዲሁም የሥልጣን ክፍፍሎች ናቸው። በእነዚህ የተነሳ ባለፈው ትውልድና በቀጣዩ መካከል አለመስማማት ሊፈጠር እንደሚችል ይነሳል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ያለፈው ትውልድ ለቀጣዩ ያወረሰው ዕዳ ሲኖር ወይም የገባው ቃል ያልተፈጸመ እንደሆነ፣ የሚፈጠር የእሴት ለውጥ (value shift) አልያም የፍላጎት ልዩነት (conflict of interest) እንዲሁ በቀደመውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ለሚፈጠር ክፍተት እንደመንስኤ ይወሰዳል።

ሆኖም ይህን (clash of generation) ለማስተካከል ይረዳሉ ከሚባሉ የመፍትሄ እርምጃዎች አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ዘመን ድርጊት እውቅና መስጠት ነው። ምን ነበር የተደረገው ብሎ ከመጠየቅም ለምን ተፈጠረ ብሎ ማጤን ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን፣ በጎ የሆኑትን በማንሳት መደናነቅም እንደመልካም እርምጃ ይቆጠራል ነው የሚሉት በዚህ ጉዳይ የተሰነዘሩ የምሁራን ሐሳቦች።

በቅርቡ የፖለቲካ ምሁራን፣ አስተማሪዎችና ተማሪዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም አሰላሳዮች በተገኙበት በአገራዊ እና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል (Center for National and Regional Integration Studies/CeNRIS) አማካኝነት የትውልድ ግጭትን መፍታት በሚል መሪ ቃል የምክክር መድረክ ተካሂዶ ነበር።
በዚህ መድረክ ስለጉዳዩ በርካታ ነጥቦች የተነሱ ሲሆን፣ ጅማሮውን “ትውልድ ሲባል ምን ማለት ነው?” በሚለው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) አጭር ማብራሪያ ጀምሯል።

ይህን ተከትሎም ትውልድ ማለት ከ-እስከ ተብሎ በጊዜ የሚገለጽ፣ ማኅበራዊ ተቋም (social institute) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እዚህ ላይ የአብዮቱ ትውልድ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። እንዲሁም የታሪክ፣ የኑሮ፣ የዘመን ጥያቄና መልስ የሚፈለግበት ሙዳይ (location or problem space) ሊሆን ይችላል ሲሉ መምህሩ በማብራሪያቸው አሳይተዋል።

በተጨማሪም ትውልድ ሲባል በሆነ ዘመን የተደረገ ታሪክ፣ የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ገድል በአጠቃላይም የተኖረ የሕይወት ልምድ (lived experience) ወይም የኑሮ ስንክሳር የሚታይበት ገጽ ሊሆንም ይችላል ነው ያሉት መምህሩ፡፡ ለአብነትም ከ17 እስከ 25 ዓመት እድሜውን በጦርነት ያሳለፈ ትውልድ (Cohort group) አንድ ራሱን የቻለ የትውልድ ቦታ ሊሰጠው ይችላል ብለዋል፡፡

ስለሆነም፣ አገርን የተሻለች አድርጎ ለመገንባት በእኛ የትውልድ ጥያቄ (problem space) ውስጥ ሆነን ያለፈውን ትውልድ ልንረግም አይገባም ባይ ናቸው። ይህም እነሱ ከኖሩበት ዘመን አንጻር አሁን ያለንበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አውድ ተቀይሯልና ነው።

በእርግጥ መምህሩ እንዳብራሩት ስለኢትዮጵያ ሲነሳ ማን የየትኛው ትውልድ ተወካይ እንደሆነ ማወቅ ያስቸግራል የሚል ክርክር አለ፡፡ ማን የትኛው ትውልድ ውስጥ ይካተታል የሚለው ጉዳይም እንዲሁ አከራካሪ ሲሆን፣ በትውልድ መካከል ግጭት አለ ለማለትም አስቸጋሪ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ባለፈው ትውልድ እና አሁን ባለው መካከል ግጭት አለ ከሚለው ሐሳብ ይልቅ አሁን ባለው ትውልድ መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ሊኖር ይችላል የሚለው ሐሳብ ሚዛን እንደሚደፋም ነው የተመላከተው፡፡

ሆኖም የትውልዱን በጎ አመለካከት ለመገንባትና መልካም እሴት እንዲወራረስ ለማስቻል በየጊዜው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ልብ ማለት እንደሚገባ በመደረኩ ተነስቷል። ጥያቄዎችን ማፈን ወይም በደንብ ባልተጠና ሁኔታ መልስ መስጠት ምናልባትም ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ቀውስ የበኩሉን ሚና ሳይጫወት እንዳልቀረ ነው የተገለጸው።

ለአብነትም በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው ትውልድ፣ የመሬት፣ የማንነት፣ የመደብ እንዲሁም የዴሞክራሲ ጥያቄ የነበረው ቢሆንም፣ የንጉሡ አስተዳደር መልስ መስጠት ባለመቻሉ የአብዩቱን ትውልድ ፈጥሯል። ይህ ትውልድም በዋናነት የመሬት ጥያቄውን ለመፍታት የሞከረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የወሰደው ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ አገሪቱን ቀደሞ ከነበራት የተሻለ ብልጽግና ላይ ያሰቀመጠ አልነበረም።

በኋላም ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውም የማንነት ጥያቄ የኢሕአዴግ ስርዓት የመለሰበት መንገድ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት አስከፊ የእርስ በእርስ መጠላለፍ እንደ ትልቅ መንስኤ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ነው በመድረኩ የተንጸባረቀው። ይህም ትውልድ በየኖረበት ዘመን የሚያነሳቸውን ጥያቄ አንክሮ መስጠት ለአንድ አገር የነገ መዳረሻ ያለው ሚና የገዘፈ መሆኑን ልብ ይላል።

ዛሬ ላይ ያለው ትውልድም ከትናንቱ ትውልድ የተቀበለው እርሾ እንዳለ ሆኖ፣ እርስ በእርስ በመከፋፈል በተፈጠሩ ግጭቶች የጋራ ሕልም መፍጠር ያቃተው መስሎ ይስተዋላል። ለዚህም ብሔራዊ መግባባት በእጅጉ አስፈለጊ ሲሆን፣ ለዚህስ እስከ የት ድረስ ነው የምንሄደው የሚለው እና ከትላንት ለዚህ ጉዳይ የምንጠቀማቸው የትኞቹን ነው የሚለው ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ተብሏል።

በተለይም ይደረጋል የተባለው ብሔራዊ የምክክር መድረክ የተጣለበትን ተስፋ መወጣት ባይችል እንኳን ቢያንስ ለሰላም ንቅናቄ መንገድ ጠርጎ ማለፍ እንዳለበት ነው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ የተናገሩት።

አክለውም፣ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ቀድሞም ቢሆን ከሰላም ይልቅ ኃይልን ያስቀደመ እንደነበር አውስተው፣ አገረ መንግሥቱን ለማስቀጠልም ኃይል ብቸኛ አማራጭ መስሎ መቀጠሉን ጠቁመዋል። ይህም ጉዳይ (violence) በአገራችን ውስጥ እንደ መልካም እሴት ተቆጥሮ መቀጠሉ ቀርቶ ከዚህ ተቃራኒ (non violence) የሆነ መንገድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል በበኩላቸው፣ እስከ አሁን ያለው የፖለቲካ ስርዓት ወጣቶችን ብቁ ለማድረግ የማያስችል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ብዙ የሚባልለትና አብዮት ያፈነዳው የ1960ዎቹ ትውልድ ስኬታማ አልሆነም የሚል እምነታቸውን አጋርተዋል።
በየትኛውም ዘመን ያለው ትውልድ ያለፉ የታሪክ ሕመሞችንና መልካም ጎኖችን ሊጋራ ይገባል የሚሉት አምባሳደሯ፣ ከዚህ በላቀ ሁኔታ ግን እንደ አገር ሐሳብ ላይ ሊሠራ ይገባል ባይ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

ለአብነትም አንድ እስራኤላዊ ወደፊት መሆን ስለሚፈልገውና ሌላም ያለው ሐሳብ ተቀርጾ የሚቀመጥበት የሐሳብ ባንክ በአገረ እስራኤል እንዳለ ገልጸው፣ የበለጸገች አገር ለመገንባት ኢትዮጵያ ውስጥም ሐሳብ ቦታ ሊኖረው ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

ለመድረኩ ተሳታፊዎች የተወሰኑ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያ ለሆነው “አሁን ላለንበት አገራዊ ሁኔታ የዳረገን በትውልድ መካከል (inter-generation conflict) ያለ ቁርሾ ሊሆን ይችላል ወይ?” ለሚለው ጥያቄ በርካታ ነጥቦች ተነስተዋል፡፡ የሁሉም ጭብጥ ግን ቁርሾ አለ ብሎ ከመውሰድ ይልቅ፣ በዚያ ትውልድ እና በዚህኛው መካከል እየተወራረሰ የመጣ መልካም ያልሆነ አስተሳሰብ ስለመኖሩ የሚገልጽ ነበር።

አሁን ያለው ትውልድም ከዚያኛው የተቀበለውን መርምሮ አዎንታዊ በሆነ መንገድ እልባት ከመስጠት ይልቅ የወረሰውን ችግር ይበልጥ እየለጠጠ ዘመኑን ለማበላሸት ተጠቅሞበታል የሚል አንድምታ ተነስቷል። የዘመኑ ትውልድ ካለበት ያለፈውን የመውቀስ አባዜ ተላቆ፣ ከትናንት ድርጊት ትምህርት ወስዶ፣ ዛሬ ላይ በመሥራት፣ ነገውን ለመገንባት የሚያደርገው ተግባር እምብዛም እንዳልሆነ ነው የተገለጸው፡፡

ለረዥም ጊዜ ያለፍንበት የፖለቲካ ስርዓትም በንግግርና በመደማጥ ላይ የተመሠረተ መሆን ሲገባው፣ በአመጽና በጉልበት ላይ የተመሠረተ መሆኑ የትውልዱን ቅራኔ ይበልጥ እያሰፋ ስለመሄዱ ተመላክቷል፡፡

ኹለተኛው ጥያቄ “አሁን ላይ በጋራ እየኖሩ ያሉት የተለያየ ዘመን ትውልዶች (በንጉሡ ዘመን የነበሩ፣ በአብዮቱ ዘመን የኖሩና የድኅረ አብዮቱ ትውልድ) አሁን ያለውን ሁኔታ አልፈው የተሻለ አገራዊ መገባባት ላይ ይደርሳሉ ወይ?” የሚል ነው። ለዚህም ወጣቶችና ምሁራን የየራሳቸውን ዕይታ አስቀምጠዋል።
በዋናነት ሊከብድ ይችል ይሆናል እንጂ የማይቻል አይደለም ያሉት ተሳታፊዎች፣ ተቋማት እንዲሁም ስርዓት ላይ ከሠራን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በጎውንም መጥፎውንም መጋራት ከቻልን የተሻለ አገራዊ መግባባት አምጥተን የበለጸገች ኢትዮጵያን የማንፈጥርበት መንገድ አይኖርም ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም ደግሞ አቋም ስለያዝንበት ትላንታችን ሐሳብ ለመቀየር ዝግጁ ነን ወይ የሚለው እንዳለ ሆኖ የተሸነፍንበትንም ያሸነፍንበትንም ታሪካችንን ተቀብለን ለአገር ግንባታ ልንጠቀምበት ግድ ይላል የሚል ሐሳብ ተሰጥቷል።

“በትውልዶች መካከል የሚደረግ ውይይት (inter-generation dialogue) ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደ አንድ አጀንዳ መቅረብ አለበት ወይ?” ተብሎ የተነሳው ሦሰተኛው የመወያያ ጥያቄም አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል።
ያለፉ ችግሮቻችንን አውድ በግልጽ ተንትኖ ለማስቀመጥ፣ የትውልድ የሕይወት ልምድን ለመጋራት፣ ለአሁኑ ትውልድ ቦታ ለመስጠት በጥቅሉም ለዜጋ ግንባታ ይህ ጉዳይ የምክክር ኮሚሽኑ እንደ አንድ አጀንዳ ተደርጎ ቢያዝ መልካም ነው ተብሏል።

በማጠቃለያ ላይ በተነሱ ሐሳቦችም፣ የአሁኑ ትውልድ ያለፈውን ከመውቀስ፣ የቀደመውም የአሁኑን ከመናቅ ኢትዮጵያ ወደፊት ጠንካራ አገር ሆና እንድትቆም በሚያደርጋት ጉዳይ ላይ ኹሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተመላክቷል።

መሰል ለብሔራዊ መግባባት ፋይዳ ያላቸው መድረኮችን በማዘጋጀትም የማኅበረሰቡን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ ተፈላጊ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በትውልዶች መካከል እና በትውልዱ ውስጥ (inter-generation and intra-generation dialogueምክክሮችን በማደረግ ሁለንተናዊ መግባባት ላይ መድረስ መቻል አስፈላጊነቱ ሳይጠቀስ አላለፈም።

- ይከተሉን -Social Media

ለብሔራዊ ምክክሩ ጥግ ይዞ ለመግባት የሚፈልገውን አካል የጋራ ወደሆነው ወደ መሃሉ ለማምጣትም መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባም ነው የተነሳው።
ትውልዱ የመዋቅራዊ ቅራኔዎች እስረኛ እንዲሁም ባተሌ ሆኖ እንዳይቀርም፣ መንግስት፣ ምሁራንና ወጣቶች፣ ተቋማት በትጋት ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት ነው ተብሏል።

በመድረኩ እንደተገለጸው፣ በአገራችን በትውልድ መካከል የተፈጠረ ቅራኔ አለ ብሎ ለመወሰን አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ትውልዱ ግን በርካታ ትርክቶችን ተሸክሞ የሚጓዝ፣ ብዙ መግለጽና እንዲፈቱለት የሚፈልገው ጉዳዮች ያሉት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡
በመሆኑም፣ መነጋገርን እንደ አንድ የፖለቲካ ሥነዘዴ በመውሰድ ክፍተቶችን በሠለጠነ መንገድ መሙላትና የትውልድን ጥያቄ ምሁራዊ በሆነ መንገድ መፍታት መቻል ራስን፣ ትውልድ እና አገርን ማዳን እንደሆነ ይታመናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች